Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ብድር እንደሚያሳድግ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት የግሉ ዘርፍ የባንኩን ብድር እንደሚገባው አላገኘም አሉ

በአፍሪካ ልማት ባንክ የግሉ ዘርፍ፣ የመሠረተ ልማትና የኢንዲስትሪ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የብድር መጠን ማሳደግ እንደሚፈልግ አስታወቁ፡፡ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፒዬር ጉስሌን ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከግሉ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡

      በኢትዮጵያ ለተለያዩ 26 ያህል የመንግሥት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸውን የፋይናንስ አቅርቦቶች የሰጠው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በግሉ ዘርፍ በኩል ተበዳሪዎች ብዙም እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ ሚስተር ጉስሌን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብቸኛው የግል ተበዳሪ ኩባንያ ደርባ ሲሚንቶ እንደሆነ ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይህ እንዲሻሻል ባንኩ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ የግሉ ዘርፍም ባንኩ ስለሚሰጣቸው ድጋፎች ብዙም ግንዛቤ ካለመኖሩም እንደሚመነጭ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍላጎት በአብዛኛው የወጪ ንግድ ተኮር በሆኑ መስኮች ለተሰማሩ ኩባንያዎች ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑና ዝቅተኛው የመበደር ጣሪያም እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንዲሆኑ የሚጠይቅ መሆኑም ሌላኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ደርባ ሲሚንቶ እ.ኤ.አ. በ2009 ከአፍሪካ ልማት ባንክ 55 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱን ያስታወሱት ሚስተር ጉስሌን፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ባንኩ የተከፈለውን ጨምሮ ቃል የተገባለት ካፒታል በጠቅላላው 100 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የአክሲዮን ድርሻ 1.5 በመቶ መሆኑን ያስታወሱት ሚስተር ጉሌን፣ ባንኩ ካለበት የካፒታል እጥረት አኳያ ኢትዮጵያን ጨምሮ የባንኩ ባለድርሻዎች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ካፒታል የማሳደግ ውሳኔው የባለአክሲዮኖች በመሆኑ በባንኩ የቦርድ አባላት ወደፊት ውሳኔ እንደሚሰጥበት አስታውቀዋል፡፡ 

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በግብርና ውጤቶች ማቀነባበርና በሌሎችም መስኮች የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች የባንኩን የብድር አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡ በአገሪቱ በመንግሥት የሚካሄዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ ልማት ሥራዎችንም ባንኩ የመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1975 ጀምሮ ባንኩ በኢትዮጵያ ሲካሄዱ ለቆዩና እስካሁንም ለሚካሄዱ 130 ፕሮጀክቶች በድምሩ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ ማቅረቡ ይነገራል፡፡ በተለይም የትራንስፖርት፣ የኢነርጂ፣ የውኃና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች አብላጫውን የባንኩን ፋይናንስ እንዳገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የማኅበራዊ ዘርፎችም የባንኩን ብድር ካገኙት ውስጥ ተካተዋል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ የትራንስፖርት ምህንድስና ዘርፍ ቺፍ መሐንዲስ ሚስተር ሙሚያ ዋኬንዶ በበኩላቸው፣ በኢትጵያና በጂቡቲ መካከል ለተዘረጋው የኃይል መስመርና ከኢትዮጵያ ኬንያ እየተዘረጋ ለሚገኘው የኃይል መስመር ማሠራጫ ግንባታ፣ ለገጠር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም ለመቐለ-ዳሎል የኃይል ማሰራጫ ግንባታዎች 900 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በትራንስፖርት ዘርፍም የአገሪቱን ትራንስፖርት ኔትወርክ ለማሻሻልና የቀጣናውን የትራንስፖርት ኮሪዶሮችን ለማስተሳሰር አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር መስጠቱን ሚስተር ዋኬንዶ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ – ኬንያ ትራንስፖርት ኮሪዶር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንዲሁም የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ፕሮጀክቶች ከብድሩ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል እንደሚጠቀሱ ባንኩ አስታውሷል፡፡ በግብርና መስክ 7,000 ሔክታር መሬት የሚያለማውንና 77 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የማከማቸት አቅም ያለውን የቆጋ ግድብ ፕሮጀክት ለመደገፍ የ630 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍም ባንኩ ከተሳተፈባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በኢንዱስትሪው መስክ ለደርባ የሰጠውን 55 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጨምሮ 130 ሚሊዮን ዶላር ብድር የሰጠው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ለውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች 340 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ እንዲሁም በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ዘርፍ የበጀት ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡

ይሁንና ባንኩ በኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት ምክትል ፕሬዚዳንት ጉስሌን፣ በቴሌኮም ኢንዱስትሪው መስክ በኢትዮጵያ መንግሥት የተያዘው የሞኖፖል አሠራር ወደፊት ለአገር ውስጥና ለውጭ ባሀብቶች ክፍት ሊደረግ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክን በግሉ ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማትና በኢንዱስትሪ መስክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለመምራት ሚስተር ጉስሌን የተሾሙት እ.ኤ.አ. በ2016 ነው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ በዓለም ባንክና በሌሎች ተቋማት የብዙ ዓመታት ልምድ ያካበቱት አዲሱ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በተለይ በቴሌኮም መስክ በአፍሪካ መንግሥታት የሚዘወተረውን የመንግሥት የሞኖፖል ድርሻ ለመለወጥ እንደሚሠሩ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች