Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልወለቃ- የወርቅ ዕቃው መንደር

ወለቃ- የወርቅ ዕቃው መንደር

ቀን:

በአፄ ፋሲል በ1628 ዓ.ም. የተቆረቆረችው ጎንደር ለ250 ዓመታት የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አገልግላለች፡፡ ከአክሱምና ከላሊበላ በመቀጠል በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ምዕራፍ ያላት ጎንደር በኪነ ሕንጻ ጥበብ፣ በቤተ ክህነት ትምህርትና በዕደ ጥበብ ውጤቶች መፍለቂያነቷ ስሟ ይጠራል፡፡ በግንባር ቀደምትነት ከተማዋን ውበት በማላበስ የሚጠቀሱት አፄ ፋሲል እንዲሁም ተከትለዋቸው ሥልጣን የያዙ ነገሥታት የገነቧቸው አፄ ፋሲል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ አብያተ መንግሥት ናቸው፡፡ በኪነ ሕንፃ ጥበብ ተጠቃሽ ከሆኑት ቅርሶች በተጨማሪ የዕደ ጥበብ ሥራዎችም በስፋት ይገኛሉ፡፡

በጎንደር ከተማ ባደረግነው ቆይታ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለገበያ የሚያቀርቡ መደብሮች ተመልክተናል፡፡ በእንጨት፣ በብረት፣ በሸክላና ሌሎችም ግብዓቶች የተዘጋጁ የቤት ውስጥ መገበያያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በትልቅና በመጠነኛ መደብሮች የቀረቡትን የዕደ ጥበብ ውጤቶች ከተማዋን ተዘዋውረን ከተመለከትን በኋላ ከአፄ ፋሲል ግንብ በስተሰሜን አቅጣጫ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወለቃ መንደር አመራን፡፡

‹‹ዌል ካም ቱ ፈላሻ ቪሌጅ›› የሚሉ በርካታ ሰሌዳዎች ተቀበሉን፡፡ አካባቢው በጭቃ በተሠሩ ቤቶች የተሞላ ሲሆን፣ በቤቶች ጣሪያና ግድግዳ የዳዊት ኮከብ በትልቁ ይስተዋላል፡፡ ወደ መንደሩ እንደዘለቅን ከሸክላ የተሠሩ የአዕዋፋት ቅርፅ የያዙ ሕፃናት ቅርጾቹን ለመሸጥ ይረባረቡ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ ቤት መግቢያ ሰፊ መደብ ይገኛል፡፡ መደቡ የሽክላ ቅርጻ ቅርጾች፣ በሰበዝ የተሠሩ መሶቦችና ሌሎችም የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለገበያ የሚቀርቡበት ነው፡፡

- Advertisement -

ወለቃ መንደር ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች የሚሠሯቸው የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለገበያ ከሚያቀርቡበት መደብ አቅራቢያ በከፊል የተጠናቀቁ ጅምር ሥራዎች ይገኛሉ፡፡ ማምረቻቸውና መሸጫቸው እዛው አካባቢ በመሆኑ ሁለቱንም ሒደት መከታተል ይቻላል፡፡ ወ/ሮ መሠረት ሙሌ፣ ያገኘናት ቅርጻ ቅርጾችን እየሠራች ነበር፡፡ የተወለደችው ወልቃይት ሲሆን፣ ከባለቤቷ ጋር ወለቃ መንደር መኖር ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት የዕደ ጥበብ ሙያን ከባለቤቷ እንደተማረች ትገልጻለች፡፡ የምትኖርበት መንደር ቀድሞ በዕደ ጥበብ ሙያ የተካኑ ቤተ እስራኤላውያን ይኖሩበት ስለነበር ታዋቂ መሆኑን ትናገራለች፡፡ የቤተ እሥራኤላውያኑን መንደር ለመጎብኘት ወደ አካባቢው የሚያቀኑ ግለሰቦች በርካታ በመሆናቸው ቦታው ጥሩ የገበያ አማራጭ እንደሆናትም ታስረዳለች፡፡ እሷና ባለቤቷ የዳዊት ኮከብ የተቀረፀባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲሁም ዋልያ፣ ዝሆን፣ ጅግራና ሌሎችም እንስሳትን በሸክላ ይሠራሉ፡፡ ከሃያ እስከ መቶ ብርም ይሸጧቸዋል፡፡ ያን ያህል የተጋነነ ገቢ ባያገኙም ኑሯቸውን ይገፉበታል፡፡

‹‹ቀድሞ ቤተ እሥራኤላውያን ወደሚኖሩበት እዚህ አካባቢ ቤት ገዝተው ወይም በመንግሥት ተመርተውም የመጡ ይኖራሉ፡፡ ብዙዎቻችን የዕደ ጥበብ ውጤቶች እያመረትን በመሸጥ ቤተሰቦቻችንን እናስተዳድራለን፤›› ትላለች፡፡ ወደ አካባቢው የሚሄዱ ጎብኚዎች ቁጥር በሚቀንስበት ወቅት ገበያቸውም ዝቅ ይላል፡፡ እሷ እንደምትለው፣ በአካባቢው ያሉ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ለቤተሰቦቻቸው ሙያውን ስለሚያወርሱ በዕድሜ አነስ ያሉትም የሸክላ ሥራ እንግዳ አይሆንባቸውም፡፡

የንግሥተ ሳባና ንጉሥ ሰሎሞን ምስል የሚታይባቸው ቀንዲሎች (ሻማ ማብሪያዎች) በአካባቢው በብዛት ከሚሠሩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ወ/ሮ መሠረት እንደምትናገረው፣ ለሸክላ ሥራ የሚሆን አፈር አዘጋጅተውና ቀቅለው ከደረቀ በኋላ ይወቅጡታል፡፡ አፈሩን በመንፋት ጠጠሩን ለይተው፣ ከሳምንታት በኋላ የሚፈልጉትን ቅርፅ ያወጡበታል፡፡ ቅርጹ እንዳይበላሽ ጠብሰው አስጊጠው ይሸጡታል፡፡ ሒደቱ የሚወስደው ጊዜና የሚያገኙት ገቢ ተመጣጣኝ ነው ማለት ባይቻልም የተካኑበት ሙያ በመሆኑ ዕድሜያቸውን በሥራው ያሳልፋሉ፡፡

ወለቃ መንደር (ወለቃ ፈላሻ መንደር በሚል የሚታወቀው) ስያሜው ወርቅና ዕቃ የሚሉትን ሁለት ቃላት በማጣመር እንደተገኘ ይነገራል፡፡ በመንደሩ የሚመረተውን ምርት ለማድነቅ የተመረጠ አጠራር መሆኑን ተያይዞ ይነሳል፡፡ በግላቸው ባህላዊ የሸክላ ሥራዎችን በማምረት ከሚተዳደሩ ባለሙያዎች በተጨማሪ ተደራጅተው የሚሠሩ ሴቶችም አሉ፡፡ በመንደሩ አቅራቢያ ፕላውሸር የተሰኘ የሴቶች የዕደ ጥበብ ማዕከል ይገኛል፡፡ በ1985 ዓ.ም. የተቋቋመው ማዕከል በእንግሊዝና ጃፓን የተራድኦ ድርጅቶች የሚደገፍ ሲሆን፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች በዘመናዊ መልክ የሚሠሩባቸው መሣሪያዎችም ይገኛሉ፡፡

ወለቃ መንደርና ፕላውሽር ማዕከል ባህላዊና ዘመናዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶች የማይታዩባቸው ሥፍራዎች ናቸወ፡፡ በማዕከሉ የሸክላ ሥራና ሽመናን የሚያቀላጥፉ ዘመናዊ መሣሪያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹ በሥራ ላይ እያሉ የሚጎበኙበትና ካጠናቀቁ በኋላ ሥራዎቻቸው ለገበያ የሚቀርብበት ክፍል አለ፡፡ ስለአካባቢው ታሪካዊ ዳራና ነባራዊ ሁኔታ የገለጸልን የአርያም ቱር ማርኬቲንግ ማናጀር አሰግድ ተስፋዬ እንደሚናገረው፣ ቤተ እሥራኤላውያን ከስሜን ተራራ እስከ ደንቢያ ባለው አካባቢ ይኖሩ ነበር፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በ332 ዓ.ም. ከአክሱም ከተማ ተገልለው ነበር፡፡ ወንድማማቾች ኢዛናና ሳይዛና አክሱምን ሲያስፋፉ ስሜን ተራራ አካባቢን ሲያስገብሩ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በጎንደር ይኖሩ ጀመር፡፡

ቤተ እስራኤላውያኑ እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ጌዲዮን የተባለ መሪያቸውን ጨምሮ በተለያየ ዘመን ከክርስቲያን ነገሥታት ጋር ይዋጉ ነበር፡፡ አፄ ሱስንዮስ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የካቶሊክ ሃይማኖትን ሲያውጅ ከእነሱ እምነት ጋር በሚጻረር መልኩ የሳምንቱ መጨረሻ ቀን (ቅዳሜ) የሥራ እንዲሆን መደረጉም ግጭቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ አሁን ባለው የወልቃ መንደር እንዲኖሩ የተደረገው በ1662 ዓ.ም. በዳግማዊ አፄ ዮሐንስ ንግሥና ዘመን ነበር፡፡

አሰግድ እንደሚለው፣ ቤተ እሥራኤላውያን ከወለቃ መንደር በተጨማሪ ካይላ ሌማ (በጣልያን ኦቶፓርኰ ተብሎ የተሰየመው) ሰፈርና በአበራ ጊዮርጊስ አካባቢም ይኖሩ ነበር፡፡ በጎንደር ኪነ ሕንፃ ጥበብና የዕደ ጥበብ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በመንደሩ ብረት ቀጥቃጭ፣ ሸክላ ሠሪ፣ ባህላዊ ቁሳቁስና አልባሳት ሠሪዎች ለዓመታት ከኖሩ በኋላ ቤተ እሥራኤላውያኑ እንደ ‹‹ኦፕሬሽን ሰሎሞን›› (ዘመቻ ሰሎሞን) ባሉ እንቅስቃሴዎች ከኢትዮጵያ ወጥተዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ግን የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በመንደሩ መስፈር ጀምረዋል፡፡

በአካባቢው በዕደ ጥበብ ውጤቶች በተጨማሪ ቤተ እሥራኤላውያኑ ምግብ ለማብሰልና ለፀሎት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶችም ይጎበኛሉ፡፡ መንደሩን ቤተ እሥራኤላውያን ጎብኚዎች እንዲሁም ሌሎች ጎብኚዎችም ሲመለከቱ ስለ ቤቶቹ ታሪክም በተያያዥ ይነገራቸዋል፡፡ ከጎንደር ከተማ አስጎብኚዎች በተጨማሪ የወለቃ መንደር ነዋሪዎችም ለጎብኚዎች መረጃ ለመስጠት ሲሞክሩ አስተውለናል፡፡

በአስጎብኚያችን ገለጻ፣ ቤተ እሥራኤላውያን ከመንደሩ ጋር ትስስር ስላላቸው ሥፍራውን ይጎበኛሉ፡፡ ሆኖም አምቦ በር በመባል ለሚጠራውና ከጎንደር ከተማ ወጣ ባለ ቦታ ለሚገኘው መኖሪያ መንደር ያላቸው ተቆርቋሪነት የበለጠ ነው፡፡ በአካባቢው ማዕከል ያቋቋሙ ሲሆን፣ ችግኝ በመትከልና በሌላም ከቦታው ጋር ያላቸውን ቁርኝት አሳይተዋል፡፡ ወለቃ መንደርን በጎበኘንበት ወቅት ቀድሞ የቤተ እሥራኤላውያን ምኩራብ (የፀሎት ቤት) በነበረው ክፍል፣ ምጣድና ሌሎችም የዕደ ጥበብ ውጤቶች ተመልክተናል፡፡ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ፎቶግራፎችም በቤቱ ግድግዳ ተለጥፈዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አያልነሽ አራጋው የፀሎትና የመመገቢያ ቤቱን አጭር ቁልፍ በመያዝ ጎብኚዎች ሲሄዱ ያስተናግዳሉ፡፡ በተለይም አይሁዳውያን ጎብኚዎች ወደ አካባቢው እያመሩ ቦታውን በደስታ እንደሚመለከቱት ይገልጻሉ፡፡ የመንደሩ ነዋሪ የሆኑ ሕፃናት ሳይቀሩ በመጠኑም ቢሆን ስለ አካባቢው ታሪክ ማወቃቸውም ደስ እንደሚያሰኛቸው ያክላሉ፡፡ ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ወለቃ መንደር ውስጥ ያሉ ቤቶች በነዋሪዎቻቸው ከሚደረግላቸው ጥበቃ ባሻገር ብዙም አልተሠራባቸውም፡፡

ስለአካባቢው ታሪክ የሚያስረዱ ሰነዶችና የዕደ ጥበብ ውጤቶቹም በተደራጀ መንገድ ለዕይታ የሚበቃበት ሁኔታ ቢፈጠር መንደሩን የበለጠ ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በአካባቢው ሙዝየም የመገንባት ዕቅድ እንዳለ ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወ/ሮ መሠረት፣ ወ/ሮ አያልነሽና ሌሎችም የመንደሩ ነዋሪዎች አካባቢው የጎብኚዎች መዳረሻ እንደመሆኑ ከዕደ ጥበብ ውጤቶች ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ይኖራሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...