Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪሚየር ሊግ ቀሪ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሊካሄዱ ነው

የፕሪሚየር ሊግ ቀሪ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሊካሄዱ ነው

ቀን:

  • የጨዋታ ውጤትን ለማጭበርበር የፋይናንስ ምንጩ ከየት ነው? የሚሉ አሉ

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሪሚየር ሊጉን ቀሪ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ፡፡ የመውረድ ሥጋት ያለባቸው ክለቦች በገንዘብ ውጤት ለማስቀየር እየሠሩ መሆኑን ጥቆማ እንደደረሱም ተናግሯል፡፡ የጨዋታን ውጤት ለማጭበርበር የሚውለው ፋይናንስ ምንጩ ከየትና እንዴት (ማች ፊክሲንግ) እንደሆነ መታወቅ ካልቻለ ለእግር ኳሱ ህልውና አደጋ እንዳለው ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

የዘንድሮው ውድድር ሊጠናቀቅ የሦስት ሳምንት ዕድሜ በቀረበት በዚህ ወቅት ቡድኖች የሥራቸውን ውጤት ከመጠበቅ ይልቅ የመንግሥትና የሕዝብ ቋት በማራቆት የፕሪሚየር ሊግ ቆይታቸውን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያለው ሩጫ ሰሞነኛ መነጋገሪያም ሆኗል፡፡

ጉዳዩ ያሳሰበው ብሔራዊ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ለማካሄድ መወሰኑን ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በወጣው ፕሮግራም መሠረት በዚህ ሳምንት ሊደረግ ታቅዶ የነበረው 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ወደ ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲተላለፉ መደረጉንም አስታውቋል፡፡ ለፕሮግራሙ መራዘም ምክንያት ያለው ደግሞ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ድልድል የበቃው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውስ ጋር ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ስለሚያደርግ በዚህ መሀል  ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ ከሚጫወተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሌሎች ክለቦች ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በማሰብ ጭምር እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ሊግ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ ተቋሙ ውድድሮችን በበላይነት የሚያስተዳድር አካል እንደመሆኑ መጠን፣ ቀሪ ጨዋታዎችን በተመሳሳይ ለማስኬድ ውሳኔ ላይ ከመድረሱም በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጨዋታዎች በሚደረጉባቸው ሜዳዎች በመገኘት የጨዋታውን ሒደት የሚከታተሉበት አግባብ ሊኖር እንደሚችል ነው ያስረዱት፡፡ እንደ ሊግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከሆነ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ ግንቦት 20 ቀን እንዲጫወቱ ይደረጋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውሳኔ ያበቃውን አቶ አበበ እንደገለጹት፣ በውጤታቸው ቅደም ተከተል ሦስት ቡድኖች ወደ ከፍተኛው ሊግ ወርደው፣ ሦስት ደግሞ ከከፍተኛው ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ ‹‹በዚህ መነሻነት ከፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ባለው ጨዋታ ወራጁ ቡድን ማነው? የሚለው በውል ስላልታወቀ በዚህ ሥጋት ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ደግሞ የጨዋታ ውጤቶችን ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ በገንዘብ ኃይል ለማስለወጥ የሚደረጉ ምልከቶችን እያሳዩ እንደሚገኙ በጥቆማ መልክ ለፌዴሬሽኑ ደርሷል፡፡ ተቋሙም ኃላፊነት ስላለበት መፍትሔ ነው ብሎ ስላመነበት ነው ለዚህ ውሳኔ የበቃው፤›› ብለዋል፡፡

የጨዋታ ውጤት ማስቀየር (ማች ፊክሲንግ) ጋር በተያያዘ የአንዳንድ ክለቦች እንቅስቃሴና ጅምር ለእግር ኳሱ ውድቀት ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ 99 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ ክለቦች በጀታቸው ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ቋት በሆነበት አግባብ ለዚህ የሚውለው ፋይናንስ ምንጩ ሊጤን እንደሚገባውም ይመክራሉ፡፡

እንደ ፌዴሬሽን፣ በአሁኑ ወቅት ለፕሪሚግ ሊጉ ቀሪ የጨዋታ መርሐ ግብሮች መቃወስ በዋናነት የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች፣ ዳኞችና ራሳቸው ተጨዋቾቹ ጭምር ዋና ተዋንያን ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ