- ኢትዮጵያ በምርጫው አትሳተፍም
የአፍሪካ ብሔራዋ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) 17ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከግንቦት 1 እስከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በጂቡቲ ያካሂዳል፡፡ ጉባኤው ለቀጣዩ አራት ዓመት አኖካን የሚያስተዳድሩ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት ምርጫም ያከናውናል፡፡ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ካሜሩንና አይቮሪኮስት ተፋጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምርጫው አትሳተፍም ተብሏል፡፡
ለጂቡቲው የአኖካ ምርጫ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ትኩረት ባይሰጡትም አይቮሪኮስት፣ ካሜሩን፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሳኦ ቶሜ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ስዋዚላንድ፣ ጂቡቲ፣ ማዳካስካር፣ ሞሪሸስ፣ ሌሴቶ፣ ኬፕቨርዴ፣ ሱዳን፣ ዜምባቡዌ፣ ጋምቢያ፣ ናይጄሪያና ሌሎችም ብሔራዊ ኦሊምፒኮች ተቋሙን ለማስተዳደር ተወካዮቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተ ከብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እንደሚነገረው ከሆነ፣ ቀደም ሲል የነበሩት የኦሊምፒክ ኮሚቴው አመራሮች የአገልግሎት ዘመን በያዝነው የውድድር ዓመት የሚያበቃበትና በምትካቸው አዳዲስ አመራሮች ምርጫ የሚደረግበት ዓመት በመሆኑ ምክንያት የዕጩ ማቅረቢያው ጊዜ ገደብ በማብቃቱ ዕጩ ተወካይ መላክ አልቻለችም፡፡
አኖካ ለዕጩ ማቅረቢያ በሰጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ አንድ አገር ለምርጫ የሚያቀርበውን ዕጩ ሙሉ ስምና ማንነቱን ጭምር ማሳወቅ እንዳለበት፣ በቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡም ተነግሯል፡፡ የተቀመጠው የአኖካ ደንብ ኢትዮጵያ በወቅቱ የሚወክላትን ለማሳወቅ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤና ምርጫም በመዘግየቱ ምክንያት ዕጩዋን ለማቅረብ እንደማትችል ዋና ፀሐፊው አቶ ታምራት በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
መፍትሔውን በተመለከተ አቶ ታምራት፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን የሚያዋቅሩት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ዓመታዊ ጉባኤያቸውን የአገሪቱን የበጀት ዓመት ጠብቆ በማከናወን የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውንም ዓመታዊ ጉባኤና ምርጫ ቶሎ ብሎ በማካሄድ ተወካዮችን ለአኖካና ለሌሎችም ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት በጊዜውና በሰዓቱ በማቅረብ ተሳታፊ መሆን እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡
በጂቡቲ በሚካሄደው የአኖካ ዓመታዊ ጉባኤና ምርጫ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩ ካሜሩናዊው ሀማድ ካልካባ እና በሥልጣን የቆዩት አይቮሪኮስታዊ ፓሌንፎ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደላከው መግለጫ ከሆነ፣ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ጨምሮ ሰባት ለውድድር ክፍት የሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተገለጸው ችግር ምክንያት የጉባኤው ታዳሚ ከመሆን ባለፈ ለተጠቀሱት የኃላፊነት ቦታዎች አትቀርብም፡፡
ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ከጨዋታ ውጪ እየሆነችባቸው ከሚገኙት አህጉርና ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል አኖካ ይጠቀሳል፡፡ ባለፈው ወር በካይሮ (ግብፅ) በተካሄደው ኢትዮጵያ ያለችበት የዞን አምስት አኖካ ባካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ ያልተካፈለች ሲሆን፣ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዑጋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዊልያም ብሊክ መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
በአጭሩ አኖካ የሚባለው የአህጉሪቱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር በ1970ዎቹ መጀመሪያ እንዲመሠረት በነፍስ ኄር ይድነቃቸው ተሰማ አማካይነት ቁልፍ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ፣ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ በ1979 ዓ.ም. ስታስተናግድ በተደረገው ምርጫ በወቅቱ የስፖርት ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፀጋው አየለ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው፣ አቶ ይድነቃቸውም የክብር ፕሬዚዳንት መደረጋቸው ይታወሳል፡፡ ባሁኑ ወቅት የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባሏ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይም ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የአኖካ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እንዲሁም የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን እና የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ጨምሮ በሌሎችም አኅጉራዊ ተቋማት ውስጥ ቀደም ባሉት ዓመታት ጉልህ ተሳትፎ እንደነበራት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ ተቋማት የበይ ተመልካች እየሆነች መምጣቷ ይታያል፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ቀደምት ባለሙያዎች አገሪቱ ለዚህ ችግር መንስኤው በዋናነት ከአገር ውስጥ እንደሚጀምር ያምናሉ፡፡ በማሳያነትም በአገሪቱ የተለያዩ ስፖርቶች በአንድም ሆነ በሌላ የመመረጥ ዕድል የገጠማቸው ሰዎች የቱንም ያህል ጠንካራ አፈጻጸም ቢኖራቸውም በያዙት ኃላፊነት የመቀጠል ዕድል አይገጥማቸውም፡፡ አኖካን የመሳሰሉት አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ተቋማት አንድ ሰው በያዘው ኃላፊነት በቆየ መጠን በዘርፉ ለሚኖረው የሙያ ብቃት ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ የተለመደ እንዳልሆነና በቀጣይ ግን እርምት ሊደረግበት እንደሚገባ ያምናሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ከአፍሪካው ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምና ዝና ያላት አገር እንደሆነች፣ ይሁንና በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን እንኳ ምንም ዓይነት የኃላፊነት ድርሻ የሌላት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡