Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውኃ በወንፊት እየቀዳን ነው!

ሰላም! ሰላም! ያው እንደ ወትሮዬ ለጎጆዬ መሞቅ ላይ ታች እላለሁ። ታዲያ ሚዛን ካልጠበቃችሁ ላይ ታች ማለቱም እንደ ሎተሪ ዕጣ ብርቅ ነው። ማለቴ በ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅዱ ውጤት፣ በራሳችን ስንፍና አልያም በአስፈጻሚዎች ቸልታ ተቋዳሽ መሆን ካልቻልን ለማለት ነው። መቼም በአደባባይ ሚስጥራችን ልንቆዝም መሰለኝ ሳምንት ቆጥረን የምንገናኘው። አይደል እንዴ? ምን ይታወቃል? ሁሉን እያወቅነው ጓሮ ለጓሮ መንሾካሾክ እንጂ በግልጽ መወያየት እንፈራለን ብዬ ነው። ታዲያ ለዚህ ለዚህም ሳይውል ሳያድር  ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ ያስፈልገዋል በሉልኝ። ምነው ብቻዬን የምታስለፈልፉኝ? “ሼሪንግ ኢዝ ሃፒነስ” አላሉም ፈረጆች? ሐበሻ ቢለው ኖሮ የሰው ለመብላትና ሰውን ተገን አሐፈርጎ ለመጠቀም ነው ብለን አጣጥለን እናልፈው ነበር። ደግሞ ራሳችንን ለማጣጣል? ፈረንጆች ጠቅሰውት ግን ስንት ያልጠቀሱትን ጠቀሱ፣ ያልተስማማቸው አጠበደላቸው ብለን እየቀዳን እዚህች ላይ ለምን ኪሳችንም፣ አፋችንም እንደተቆለፈ አልገባኝም። አቤት! ስንቱን የተቆለፈ በር የመክፈት የቤት ሥራ እንዳለብን አስባችሁታል? ራስ አያምም?

 

ለነገሩ ራሳችን የሚያዞረው ነገር በዛ መሰለኝ ራስ ምታት እንዴት እንደነበር የሚያስታውሰን ሳያስፈልገን አይቀርም። እያደር የምንሰማውና የምናየው፣ ውርደት እንደ ክብር፣ ሽንፈት እንደ ጀብድ የሚቆጠረው ነገር የአዕምሮን ሚዛን አቃውሶታል። የቱ ትክክል የቱ ስህተት እንደሆነ መለየት እየተቸገርን ነው። እናም ከዚህ በላይ ጨርቃችንን ጥለን መሮጥ አለብን ትላላችሁ? አንድ ወዳጄ እንደውም “‘ፒፕሉ’ እኮ ‘ኖርማል’ አይደለም። አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የአዕምሮው ባትሪ ስለደከመ በ‘ጃንፐር’ ነው ከተቀመጠበት ተነስቶ የሚጓዘው፤” ሲለኝ ነበር። ኋላ ለባሻዬ ልጅ ስነግረው፣ “ተመስገን በል። ባትሪው እንደ ሞተ መኪና በ‘ጃንፐር’ ተነስተን ከተጓዝንም እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ‘ማሽን’ ለሚዘውረን የ‘ትራንስፎርሜሽን’ና የልማት ዕቅድ ክፍተት ማሳያ ሆነናል ማለት ነው። ብቻ እንዲሁ ከቀጠልንና ልማቱን ካሳካን እውነትም ታሪክ ሠሪ ትውልድ ነን፤” ብሎ አሾፈ። ወይ ታሪክና እኛ ብዬ እኔም ዝም! ካበዛሁት ማን ያስጥለኛል ብዬ ነዋ!

        ያለ ነገር ስለወሬና ወሬኞች ጎነታትዬ እንዳልጀመርኳችሁ ይገባችኋል። አጉል በአሉባልታ አጥብቀን ያላሰርነው ዘቅዝቀን እየተሸከምን የምንደፋው እህል፣ የምንዘጋው ዕድል እያደር ብሷል። እኔም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። እናም ሰሞኑን ስሜ በሚያውቀኝ ሁሉ በሐሰት ሲብጠለጠል፣ ሲነሳና ሲጣል ሰነበተ። ካለእናንተ ለማን ይነገራል ብዬ እኮ ነው? ምን ተባልኩላችሁ መሰላችሁ? አንድ ‘ሲኖትራክ’ እዚህ ጫንጮ ተበላሽቶ በቆመበት በተገመተው ይሸጥልኝ የሚል ደንበኛ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝና ወጣ ወጣ አበዛሁ። እንደ ወትሮው ፊቴ  የሚመታባቸው ሥፍራዎች ‘አንበርብር የት ደረሰ?’ በሚሉ ጥያቂዎች ደመቁ። ኋላ አንዱ የወሬ ፈላስፋ፣ “አልሰማችሁም እስካሁን? አንበርብር እኮ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ በሌለበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በማላይበት አገር መኖር በቃኝ ብሎ ወደ ጎረቤት አገር ተሰደደ፤” ብሎ ነዛው። ዘር እንደ ወሬ ብንዘራ ይህቺ ድንግል መሬት ለሰባት ትውልድ የሚበቃ እህል አታስወቃንም ነበር ግን? ይገርማል እኮ።

        ወዲያው ትናንሽና ጥቃቅን ወሬኞች (አንዴ ለኳሽ ያግኙ እንጂ አይቻሉም) “እውነት ነው ካንደበቱ ሰምተናል። ‘ከዕለት ወደ ዕለት ቅሬታዬ እየበረታ ሄዷል። ልማት ያለ ዴሞክራሲ በአፍንጫዬ ይውጣ ሲል በጆሬዬ ሰምቻለሁ፣ እኔም ሰምቻለሁ፣ እኔም የሰማሁ መስሎኛል…” እየተባባሉ ጫንጮ ተቀምጬ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈቃድ በወሬ አስጠይቀው በወሬ አሰጡኝ። ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ደንበኛና የሰማ ሁሉ ጉድ አለ። ‘አምኖ ያበደረ ክስ መሠረተ፣ የተበደረ ውስኪ አወረደ’፡፡ እውነትም ‘ጦር ከፈታው ወሬ . . . !’

     “አኖርሽ ነበረ በሬዬንም ሸጬ፣ አበላሽ ነበረ ወይፈኔን አርጄ፤ በምኔ ልቻልሽ ባንገቴ ተይዤ፤” አልኩ የተባለውን ስሰማ። ማንጠግቦሽ፣ “እንኳን አንተ ዝም ያለው ፈጣሪም ዝም አለ ተብሎ ይወነጀላል። በአሉባልታ ይወገራል። ያለ ነው ብላ…” ልታፅናናኝ ጣረች። ላያስችል አይሰጥ ሆነና ደግሞ ስመለስ ቀንቶኝ ኮሚሽኔን ተቀብያለሁ። እንዳልኳችሁ አስችሎኝ ጭራሽ የሥራ ሞራሌ ተነሳስቶ አንዳንድ ቦታ ልደውል ትኩረቴን ሰበሰብኩ። ማስታወሻዬን ገላለጥኩ። በእንጥልጥል የያዝኩትን ድለላ ካቆምኩበት ልቀጥል ስልኬን አንስቼ ልክ ልደውል ስል ይደወላል። “ሃሎ!” ስል ዕምነት የጎደለው ድምፅ፣ “አንበርብር!” ብሎ ይጮሃል። “አዎ ነኝ!” ከማለቴ፣ “ምንድነው የምሰማው?” ብሎ አንድ የሚያውቀኝ ያናዝዘኛል። አስተባብዬና አስረድቼ ወሬኛውን በትብብር የእርግማን ናዳ አሸክሜ ስዘጋ ሌላ ስልክ መጣ። “ሃሎ!” ስል አገላብጬ እመልሳለሁ ብዬ የተበደርኩት ሰው እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ይጮህብኛል። “አሁን ከዚህ ወዲያ ለእኛ ገንዘብ እንጂ ፖለቲካ ምናችን ነው? ሰው መቼስ ጫፍ ሳይዝ አይቀጥልም?” ሲል መዓት ወረደብኝ። እሱንም እንዲሁ አባብዬ ወሬውን ሳስተባብል ሰዓቴ ነጎደ።

በልቤ ግልጽነትና ተጠያቂነት ፍፁም ይንገስ ቢባል መንግሥታት በጀታቸውን በሚቀጥሯቸው ቃል አቀባዩችና ማስተባባያ መድረኮች ሊጨርሱት ይችላሉ ማለት ነው እላለሁ። በትዝብት በመገረም እተክዛለሁ። ከሁሉ ከሁሉ ‘የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀ’ መባሌ ትዝ ሲለኝ የቂመኛዬን ቀለም ዕወቅ፣ ማንነት ድረስበት እያለኝ እረበሻለሁ። እንዲያረጋጋኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ስደውል ደግሞ እሱ ያው የምታውቁት ነው ቀለል አድርጎ፣ “እንኳን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጠየቀ አላሉህ። እንዲያ ቢሉህ ኖሮ ሠርተህ እየኖርክ የምትበላው ሳታጣ ምን ልትሆን ነበር? ይልቅ የስም ኪራይ ጀምር። ሰው በእጅ አዙር በሰው መታወቂያ የልቡን መዘክዘክ የሚፈልግበት ጊዜ ሆኗል፤” ይለኛል። እስኪ አሁን ካልጠፋ ‘ቢዝነስ’ ስሜን አጥፉ ብዬ ለብሶት መተንፈሻ ላከራይ? ይህ ነበር የቀረኝ!

እጄ ላይ ምን የመሰለ የሚሸጥ ቪላ ስለነበረ የማስተባበል ሥራዬንና ቀጣናዬን የማረጋጋት ተግባሬን ለጊዜው አቆይቼ፣ ለመጨረሻ ውሳኔ ቤቱን አሳየን ወደ አሉኝ ገዢ ደንበኞቼ ከነፍኩ። ቤቱን አይተው ጥቂት እርስ በርሳቸው ከተነጋገሩ በኋላ (በዕድሜ ጠና ጠና ያሉ ወይዘሮዎች ናቸው) ትንሽ ተደራድረው እንደሚገዙት አበሰሩን። ገዢውም እኔም ፈንድቀን፣ “እንኳን ለውሳኔ አበቃችሁ!” ብለን ሳናበቃ በማናውቀው ምክንያት፣ “ምን መሆንሽ ነው? ምን መሆንሽ ነው?” እየተባባሉ ፊታችን ቡጢ ቀረሽ ንትርክ ጀመሩ። የማላየው ነገር የለም መቼም! ቆየት ብዬ እንደተረዳሁት በአንድ ዓመት የሚበላለጡ እህትማማቾች ኖረዋል። የንትርኩ መንስዔ ታዲያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‘እኔ ነኝ መነጋገር ያለብኝ አንቺ አርፈሽ አዳምጪ! የለም አንቺ ምን ስለሆንሽ ነው እኔ ነኝ መናገር ያለብኝ’ በሚል ግብግብ የተፀነሰ መሆኑ ነው።

ለታዛቢ ቀላል ይምሰል እንጂ ለባለቤቶቹ ግን የልጅነት ትውስታን እያስመዘዘ ስንት መስማት የማይገባንን ገመና ያዘካዘከ ግጭት ነበር። ሁለቱንም አረጋግተን ጥቂት በሊቀመንበርነት ቦታው ማን ይቀመጥ የሚለውን እንዲነጋገሩ ፈቀቅ አልንላቸው። “ትልቅ ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም’ የሚባለው ለካ እውነት ነው?” ለቤቱ ባለቤት ስል እንደ ቀልድ፣ “ድሮስ የዚህች አገር የዘመናት ጥያቄ ይባስ ሲተበተብና ሲከር የኖረው በአዋቂው አይደል እንዴ?” በማኖ አስነካኝ። ቀይ ወይ ቢጫ በማላይበት ማኖ ብነካ ‘ኮሚሽኔን’ ሳልቀበል ንቅንቅ እላለሁ እንዴ?  እሺ ብለን የምንጎትተው ነገር ብሷል ስላችሁ! እንዲያው ምንድነው ግን አንተ ቅደም እኔ ልከተል መባባልን የነሳን? በታላቅና በታናሽ ባሰ እኮ ጎበዝ!

 

በሉ እንሰነባበት። ያሻሻጥኩትን ቪላ ቤት ‘ኮሚሽን’ በተቀበልኩ አመሻሽ ባሻዬ ደወሉልኝ። የማርያም አራስ ሊጠይቁ ያለ እኔ አልሆንላቸው ብሎ ነበር የደወሉልኝ። ተያይዘን አራስ ጥየቃ። ሳያት የት እንደማውቃት ጠፋኝ እንጂ መልኳ አዲስ አልሆነብኝም። ባሻዬን ጠጋ ብዬ፣ “መቼ አገባች? አልሰማሁም ማግባቷን?” አልኳቸው። ባሻዬ ደንግጠው፣ “ኧረ ባክህ ስለፈጠረህ ዝም በል። እኔ የወለደ እንጠይቅ አልኩህ እንጂ ላገባና ላላገባ እንመስክር ብዬ አመጣውህ?” ብለው ሲቆጡኝ ነገሩ ገባኝ። የገባኝ መስዬ ባሻዬን ለመካስ፣ “እንዴት ነበር ታዲያ ምጡ? ጠናብሽ?” ብዬ መጠየቅ። አፌ አያርፍም እኮ አንዳንዴ። “ማማጥ ድሮ ቀረ። ዕድሜ ለቀዶ ጥገና” አለችኛ። ባሻዬን ቀና ብዬ አላየሁም። ግድ ካልሆነ ባሻዬ በምንም ተዓምር በቀዶ ጥገና፤ መገላገልን አይደግፉም። ስንቀለቀል መስማት የማይፈልጉትን ስላሰማኋቸው እንደሚቆጡኝ ገብቶኛል። ምኔ ሞኝ ነው ታዲያ? አውቄ ስልክ ተደወለልኝ አልኩና ‘ማርያም ጭንሽን ታሙቀው’ ብዬ ላጥ።

ወዲያው ለልጃቸው ደወልኩለት። የተለመደችዋ ግሮሰሪ እንድንገናኝ ተነጋገርን። ስንገናኝ የሆነውን ለልጃቸው ነገርኩት። እንደ ወትሮው በአባቱ ወግ አጥባቂነት ዘና እያለ ያጫውተኛል ስል ኮስተር ብሎ “በቃ፣ አምጦ መውለድ ተረት ሊሆን ተቃረበ ማለት ነው?” አለኝ። “አቤት?” ስለው ባሻዬ የመጡ መስሎኝ ክው ብዬ፣ “አሳሳቢ የሆነ እክል ሊገጥም እስካልቻለ ድረስ ሰው ለምን አምጦ መውለድ እንደሚፈራ አልገባኝም። በምጥ የሚወለድ ልጅ፣ የሚገኝ ፍሬ እኮ ጤናማነቱና ጥንካሬው ሌላ ነው። እህ በአቋራጭ የመክበር፣ በአቋራጭ የመደለብ፣ በአቋራጭ የመንገሥ የዘመኑ አካሄድ ስንቱን ጤናማ ተፈጥሯዊ በረከት አበላሸው መሰለህ? ሕመም ፈርተን፣ ላብ ተፀይፈን፣ ሥራ ንቀን፣ ጎንበስ ማለት ጠልተን፣ በአጠቃላይ ምጥ ገሸሽ ብለን ያዋጣናል? ማቆራረጥና ዝላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፍራ…” እያለ ሲያስፈራራኝ አመሸሁ። ከአሁን አሁን አምጥ አለኝ ብዬ ነዋ። ይኼ ዘመን እኮ ውኃ በወንፊት ላስቀዳ እያለን እኮ ነው፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት