Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየርቀት ትምህርት ሲመዘን

የርቀት ትምህርት ሲመዘን

ቀን:

ከዓመታት በፊት በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የላይብረሪ ሠራተኛ ሆነው ሲቀጠሩ የትምህርት ደረጃቸው ብዙም አልነበረም፡፡ ዲግሪም ሆነ ዲፕሎማ አልነበራቸውም፡፡ ጥቂት ከሠሩ በኋላ ግን የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሰኑ፡፡ አንድ የርቀት ትምህርት በሚሰጥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅም በዲፕሎማ ፕሮግራም ላይብረሪ ሳይንስ መማር ጀመሩ፡፡ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ከሦስት ዓመታት በላይ የፈጀባቸው አቶ አፈወርቅ ግዛው፣ በቆይታቸው ጥቂት የማይባሉ ነገሮች ታዝበዋል፡፡

‹‹የሚሰጡን ሙጁሎች በጣም አሪፍ ነበሩ፡፡ ቱቶሪያልም በሴሚስተር ሁለት ጊዜ  ይሰጠን ነበር፤›› የሚሉት አቶ አፈወርቅ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሙጁሎች ወቅታቸውን ጠብቀው ሳይደርሱ የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በሌላ በኩልም ከተማሪዎች በኩል የሚፈጠሩ ችግሮች በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

አብዛኞቹ ተማሪዎች ዲፕሎማ ለመያዝ እንጂ ለትምህርቱ ብዙም ግድ እንዳልነበራቸው፣ በሴሚስተር ሁለት ጊዜ የሚሰጠው የቱቶሪያል ፕሮግራም ላይ እንደማይገኙ፣ ተከታትለው ሙጁል የማይወስዱም እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በክፍል ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች መቅረት የተለመደ ነበር የሚሉት አቶ አፈወርቅ፣ ለዚህም የትራንስፖርት ችግር የሥራ መደራረብና ጊዜ ማጣትን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ አቶ አፈወርቅ በአንድ የቱቶሪያል ፕሮግራም ላይ ያጋጠማቸው አይረሳቸውም፡፡

ማኔጂንግ ላይብረሪ የተሰኘውን የትምህርት ዓይነት ለመማር ክፍል ገብተው እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ትምህርቱ ሳይጀመር ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ይሁንና ሌላ የመጣ ተማሪ አልነበረም፡፡ ነገሩ ግራ ገብቷቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ይጠባበቁ ጀመረ፡፡ ብቅ ያለ ግን አልነበረም፡፡ በመሆኑም መምህሩ አቶ አፈወርቅን ብቻ ለማስተማር ተገደዱ፡፡

ቱቶሪያል ላይ ካለመገኘት ባለፈ ሌላም ችግርም ነበረ፡፡ የተሰጧቸውን ሙጁሎች በሚገባ አጥንተው ለፈተና የሚዘጋጁት ጥቂት ናቸው፡፡ ‹‹የርቀት ትምህርት ተማሪዎች እርስ በርስ አይተዋወቁም፡፡ ማን ጎበዝ፣ ማን ሰነፍ እንደሆነ ስለማይታወቅ ፈተና ቢከብዳቸውም ተኮራርጀው ለመሥራት አይደፍሩም፣ ነገር ግን መልሶችን በወረቀት ይዞ በመግባት (አጤሬራ) አልያም ከሙጁል ለመሥራት ይሞክሩ ነበር›› ሲሉ፣ ሳያጠኑ ቀርተው ፈተና ለመሥራት የነበረውን ትንቅንቅ አቶ አፈወርቅ ያስታውሳሉ፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በተለይም ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መሰጠት የተጀመረው በ1940ዎቹ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የመጀመሪያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋምም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲት ኮሌጅ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ የተማሩ ሰዎችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በቄስ ትምህርት ቤት የተገደቡ ነበሩ፡፡ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስጀመር ጥረት የተጀመረው ዘግይቶ ቢሆንም፣ ጅማሮውን ተቀብሎ ለማስፋፋት የተደረገ እንቅስቃሴ ብዙ አልነበረም፡፡

 እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ በአገሪቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርሲቲዎችና 17 ኮሌጆች ብቻ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በዩኒቨርሲቲዎቹና በኮሌጆቹ የመማር ዕድል የሚያገኙት ተማሪዎች ቁጥር ከአሁኑ ጋር ሲተያይ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ለምሳሌ በ1992 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲዎችና በኮሌጆች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ31,000 አይበልጡም ነበር፡፡ ይህ አገሪቱ በሚያስፈልጋት መጠን የተማረ የሰው ኃይል እንዳታገኝ ማነቆ ሆኖባት ቆይቷል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የቀድሞ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ተሾመ፣ ከማርች 2008 እስከ ዲሴምበር 2015 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ እመርታዎች ፈተናዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተው ባቀረቡ ኤግዚት ሪፖርት፣ ውስን የነበረው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 33 መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በዲግሪ ፕሮግራም የሚያስተምሩ ከ90 የሚበልጡ የግል የትምህርት ተቋማትንም ማፍራት ተችሏል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከልም ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የርቀት ትምህርት ፕሮግራሞች ይሰጣሉ፡፡

በ1840ዎቹ እንደተጀመረ የሚነገርለት የርቀት ትምህርት፣ በሥራና በአኗኗር ሁኔታቸውና በሌላም ምክንያት ትምህርት ቤት በአካል ተገኝተው መማር የማይችሉ ባሉበት ሆነው እንዲማሩ አስችሏል፡፡ ካለው ጠቀሜታ አንጻርም በአሁኑ ወቅት ብዙዎች ይመርጡታል፡፡ በመላው ዓለም በስፋት ሥራ ላይ የዋለው ፕሮግራሙ፣ በአገር ውስጥም ሥራ ላይ ከዋለ አሥርት ዓመታት አልፈዋል፡፡ እንደ አቶ አፈወርቅ ያሉ የትምህርት ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ እያሰቡ ነገር ግን በጊዜ እጦት ሳይሳካላቸው የቆዩ ብዙዎች በዚህ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አገሪቱ ያላትን የተማረ የሰው ኃይል ሀብትም ከፍ እንዲል የማይናቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

የርቀት ትምህርት ፕሮግራም ከሚሰጡ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት መካከል ጂማ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የርቀት ትምህርት መስጠት ከጀመሩ ቀዳሚ ተቋማት ተርታ ይመደባል፡፡ በዲግሪ ደረጃ 15 ዓይነት የርቀት ትምህርት ፕሮግራሞች ይሰጣል፡፡ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ሶሻል ሳይንስ ኤንድ ሂውማኒቲስ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሒስትሪ ከሚሰጣቸው የትምህርት መስኮች ይጠቀሳሉ፡፡ በየዓመቱ በአንድ ፕሮግራም በአንድ ማዕከል ከ40 እስከ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል፡፡

በእነዚህ ዓመታት በርካቶችን በሙያቸው ብቁ እንዲሆኑ ቢያደርግም፣ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ ለፕሮግራሙ የተመደበ ራሱን የቻለ በጀት የለም፡፡ የሚንቀሳቀሰውም ከተማሪዎች በሚያገኘው የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡ ይህም የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ የሚቀረው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ለማቅረብ እንዲቸገር፣ ለመምህራን በቂ ደመወዝ ለመክፈል አቅም እንዲያንሰው አድርጓል፡፡

‹‹በኪሳራ የምንንሳቀስባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ የሚስብ ደመወዝ ስለማይከፈልና አቅም ባለመኖሩ በቂ የሰው ኃይል ለማግኘት ችግር ነው፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ሙጁሎችም በጊዜ አይደርሱልንም፣ ትራንስፖርትም ሌላው ፈተና ነው›› ያሉት በጂማ ዩኒቨርሲቲ ተከታታይና የርቀት ትምህርት ዳይሬክተር ዶክተር የማነብርሃን ቀለመወርቅ ናቸው፡፡

በጋምቤላ፣ በአሶሳ፣ በአዲስ አበባ፣ በወልቂጤና በሌሎችም 13 ከተሞች ቅርንጫፎች ከፍቶ የርቀት ትምህርት በመስጠት ላይ የሚገኘው ጂማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሌሎችም ችግሮች እያጋጠሙት ይገኛሉ፡፡ እንደ ዶ/ር የማነ ገለጻ፣ ብዙ ጊዜ ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል በአንደኛው ቅርንጫፍ ተመዝግቦ መማር የጀመረ፣ ለተቋሙ ሳያሳውቅ ተቋሙ ቅርንጫፍ በከፈተበት ሌላ አካባቢ በድንገት በመዘዋወር ትምህርት ይጀምራል፡፡ ይህም የተማሪውን መረጃ ለማስተላለፍ እንቅፋት ከመፍጠሩ ባሻገር ተቋሙን ለሌላ ልፋት ይዳርጋል፡፡ ተመሳሳይ ገጠመኞች በተቋሙ የተለመዱ ናቸው፡፡

ሌላው ማኅበረሰቡ ስለ ርቀት ትምህርት ባለው የተዛባ አመለካከት የሚፈጠረው ክፍተት ነው፡፡ ‹‹ተማሪዎች ስለ ርቀት ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው፡፡ በቀላሉ ወረቀት የሚያገኙበት ይመስላቸዋል፤›› የሚሉት ዶ/ር የማነ ብርሃን፣ የርቀት ትምህርት ለመማር የሚመዘገቡ ብዙዎቹ በትምህርት ደካማ የሆኑ፣ ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እስከከፈሉ ድረስ መመረቅ እንደሚችሉ የሚያምኑ መሆናቸውን፣ ተቋሙ የሚያዘጋጀው ቱቶሪያል ላይ ብዙዎቹ እንደማይገኙ፣ እንደማያጠኑና በብዛት ማለፊያ ውጤት እንኳ እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በኤግዚት ኤግዛም (የብቃት መመዘኛ ፈተና) ላይ ያስመዘገቡትን አነስተኛ ውጤት በማሳያነት ያነሳሉ፡፡ በተቋሙ ኤግዚት ኤግዛም ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ውሰጥ 140 የሚሆኑ የሕግ የርቀት ተማሪዎች ተቀብሎ አስተምሯል፡፡ በማስተማር ላይም ይገኛል፡፡ ነገር ግን ኤግዚት ኤግዛም ከተፈተኑት 140 ተማሪዎች መካከል ማለፍ የቻሉት አሥሩ ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ለርቀት ትምህርት ባለው የተሳሳተ ግንዛቤ ‹‹ባናጠናም ችግር የለውም፤›› በሚል እምነት ለፈተና ስለማይዘጋጁ የተፈጠረ ችግር ሲሆን፣ ከዓመት ዓመት መሻሻሎችን ባለማሳየቱ ‹‹የሕግ ትምህርት ፕሮግራሙን ለመዝጋት አስበናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከዚህ በተቃራኒ መደበኛ ትምህርት በሚማሩና የርቀት ትምህርት በሚማሩ ተማሪዎች መካከል ምንም ዓይነት የአቅም ልዩነት የለም፡፡ ልዩነቱን የፈጠረው ማኅበረሰቡ ለርቀት ትምህርት ያለው የተዛባ አመለካከት ነው፤›› ሲሉ የሚከራከሩት የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋዬ ናቸው፡፡

ከተቋቋመ 18 ዓመታትን ያስቆጠረው አድማስ ዩኒቨርሲቲ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልና በአዲስ አበባ 11 ዋና ማዕከላትና ንዑስ ማዕከላት ከፍቶ በአካውንቲንግ፣ በማርኬቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በሶሻል ወርክና በሌሎችም ሰባት የትምህርት መስኮች የርቀት ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡

እንደ ዶ/ር ሞላ ገለጻ፣ በአቋራጭ መረጃ ለማግኘት የሚመጡ ተማሪዎች የሉም፡፡ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮችም በመደበኛው የትምህርት ዘርፍ ከሚያጋጥሙት የተለዩ አይደሉም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በሚሠራባቸው አካባቢዎች በተፈለገው ሙያ የሠለጠኑ መምህራን ለማግኘት ይቸገራል፡፡ ይሁንና ይህ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ለመምህራን ከፍተኛ ደመወዝ ከፍሎ በየአካባቢው ይመድባቸዋል፡፡ ልዩ ልዩ የትምህርት መረጃ ግብዓቶችን ለማቅረብ በሚደረገው ጥረትም አልፎ አልፎ የትራንስፖርት ችግር ይከሰታል፡፡ ይህንንም ተቋሙ በራሱ መንገድ ይወጣዋል፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም፣ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ  የተገኘው መረጃ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በማንኛውም ተቋም የሚሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠናዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና ከአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ሌሎች አግባብነት ካላቸው ፖሊሲዎች ጋር መገናዘባቸውን የማረጋግጥ ሥልጣን ተሰቶታል፡፡ ኤጀንሲው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የተቋማትን ደረጃና ብቃት በመገምገም ያሉበትን ደረጃ በየጊዜው ያሳውቃል፡፡

በዚህም የርቀት ትምህርት ፕሮግራም የሚሰጡ ተቋማት አሠራር ላይ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ታዝቧል፡፡ የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ገረሱ እንደሚሉት፣ የርቀት ትምህርት ለመጀመር ፈቃድ የጠየቀ አንድ ተቋም የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ ከመስፈርቶቹ መካከልም በአንድ በተዘጋጀ የትምህርት ዓይነት ውስጥ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች፣ በተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ያሰበው ቱቶሪያል፣ የማስተባበሪያ ማዕከል፣ የተሟላ ኦዲዮቪዥዋል፣ ሲዲዎች፣ ሙጅሎች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

ነገር ግን ይህንን መስፈርት አሟልተው ፈቃድ ካገኙ በኋላ ነገሮች እንዳልነበሩ ይሆናሉ፡፡ የዕውቅና ፈቃድ ባልተሰጣቸው አካባቢዎች ቅርንጫፍ ከፍተው የሚሠሩ የመንግሥትና የግል ተቋማትም ያጋጥማሉ፡፡ አስፈላጊውን ግብዓት ሳያሟሉ የሚያስተምሩም ብዙ ናቸው፡፡ የቅበላ መስፈርት የማያሟሉ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ ተቋማትም አሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተቋሙ የተለያዩ ኬዞች አጋጥመውታል፡፡

አንዲት የጤና ተማሪ በአንድ የርቀት ትምህርት በሚሰጥ የግል ተቋም ተምራለች፡፡ የተማረችው ግን አስፈላጊውን የቅበላ መስፈርት አሟልታ አልነበረም፡፡ ተቋሙን ለመቀላቀል የሚጠበቅባትን የብቃት መመዘኛ (ሲኦሲ) ፈተና አልተፈተነችም፡፡ የርቀት ትምህርቱን ለመማር የተመዘገበችውም ‹‹ዲግሪዬን የምወስደው ሲኦሲ ተፈትኜ ካለፍኩኝ በኋላ ነው›› የሚል ውል ከተቋሙ ጋር በመፈጸም ነው፡፡

ተመሳሳይ ውሎች ከመስፈርቱ ጋር ስለሚቃረኑ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ተቋሙ ፈቅዶ ልጅቷ መማር ችላለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ሌላ ስህተት ነበረ፡፡ ልጅቷ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ ተቋሙ ዲግሪዋን የሰጣት በውላቸው መሠረት ሲኦሲ ተፈትና ሳይሆን እንዲሁ ነበር፡፡ ጉዳዩ የተጋለጠውም ልጅቷ ሥራ ለመቀጠር በአንድ ተቋም መረጃዎቿን አስገብታ ቀጣሪው ድርጅት መረጃዋን ተጠራጥሮ ጉዳዩን ኤጀንሲው እንዲመረምርለት በማድረጉ ነው፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ገጠመኞች ብዙ ናቸው፡፡ መሰል ተግባር የሚፈጽሙ ተቋማትን ብንዘጋ የሚጎዳው ተማሪው ነው፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ መስፈርቱን ተከትለው ባልሠሩ ሰባት ተቋማት ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፤›› ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

ከተቋማት የአሠራር ክፍተት ባሻገርም ተማሪዎች ጋር ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ተማሪ በአቋራጭ ወረቀት ለማግኘት ሲል  በርቀት ትምህርት ይመዘገባል›› ሲሉ፣ ብዙዎቹ የርቀት ተማሪዎች በሚዘጋጅላቸው የቱቶሪያል ፕሮግራም ላይ እንደማይገኙ ገልጸዋል፡፡

ይህ በተቋማቱ የአሠራር ችግርና በተማሪዎች የአመለካከት ችግር እየተፈጠረ ያለው ክፍተት፣ በርቀት ትምህርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ለብዙ ተቋማት መዘጋትም ምክንያት ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ የተቀሩት ሌሎች ተቋማት አሠራራቸውን አስተካክለው ሥራቸውን ለመቀጠል ቁርጠኝነቱ ቢኖራቸውም የተማሪዎቹ የራስ ተነሳሽነት ወሳኝ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...