Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ቀን:

በአማራ ክልል በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣  ቅዳሜ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት አቅራቢያ አንድ ቦምብ ፈንድቶ በሁለት የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

ካለፈው ዓመት የክረምት ወራት ጀምሮ በሁለቱ ከተሞች እየደረሰ ያለው የቦምብ ፍንዳታ የከፋ ጉዳት ባያደርስም፣ በጎንደር ከተማ ከዚህ በፊት በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

 ከዚህ በፊት በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች የተለያዩ ክብረ በዓላትና ዝግጅቶች በሚደረጉበት ጊዜ የተለያዩ የቦምብ ፍንዳታዎች መድረሳቸውን አቶ ንጉሡ ጠቁመዋል፡፡

ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ ጨምሮ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ባለችበት ጊዜም ቢሆን፣ አልፎ አልፎ በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች ሁከትና ረብሻ ለመፍጠርና የኅብረተሰቡን ሰላማዊ ኑሮ ለማወክ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳ በተለያዩ ጊዜያት በባህር ዳርና በጎንደር ከተሞች የቦምብ ፍንዳታዎች የደረሱ ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡም ሰላማዊ ኑሮውን እየገፋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ባህር ዳር ከሳምንት በፊት የጣና ፎረምን ማስተናገዷን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ጎንደር የከተሞች ፎረምን ያለ ምንም ችግር እያካሄደች መሆኑን አቶ ንጉሡ ገልጸው፣ አሁን በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሥጊ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

በቦምብ ጥቃት የሚፈጽሙ ግለሰቦች በከተሞቹ ነዋሪዎችና በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ጥረት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡

‹‹መረጃችን እንደሚጠቁመው የተለያየ ተልዕኮ ይዘውና በገንዘብ በመደለል የኅብረተሰቡን ሰላማዊ ሕይወት ለማናጋት፣ አሁን በክልሉ ያለው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ፍላጎት የሌላቸው አካላት ክልሉ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አይደለም የሚል ድምዳሜ እንዲያዝ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የሚያርጉት ጥረት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ይህን አደጋ የሚያደርሱ ግለሰቦች ፍርኃት የተቀላቀለባቸው በመሆኑ ፍንዳታዎችን የሚያደርሱት በባዶ ሜዳ ላይ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ግን በአሳቻ ቦታ አሳቻ ሰዓት በመጠቀም የከፋ ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩ ፀረ ሰላም  ኃይሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ የባህር ዳርም ሆነ የጎንደር ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዳልተገታ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ አካባቢ ሰላም የሌለ እንዲመስልና ኅብረተሰቡ ሥጋት ላይ ወድቆ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እንዲስተጓጎል በመፈለግ፣ የተለየ ተልዕኮ ያላቸው ወገኖች ከውጭ በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ በመደለል ይህን ድርጊት እንደሚፈጽሙ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በዳሽን ቢራ ስፖንሰርነት ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ሊካሄድ የነበረው ኮንሰርት በቦምብ ፍንዳታ ምክንያት ሙሉ ዝግጅቱ ሳይቀርብ መቅረቱን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የዚህ ኮንሰርት መዘጋጀት ሲገለጽና ታዋቂ ድምፃዊያን ዝግጅቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህልም ታዋቂዎቹ ድምፃውያን መሀሙድ አህመድ፣ አረጋኸኝ ወራሽና ኩኩ ሰብስቤ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ሙዚቃቸውን እንደሚያቀርቡ ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም፣ ድምፃዊ መሀሙድና አረጋኸኝ ዝግጅታቸውን አለማቅረባቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ዜጎቹ ወደ ጎንደር ከተማ እንዳይሄዱ የጉዞ ማሳሰቢያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...