Sunday, May 26, 2024

ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ሥራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር አቅምን ያዳክማል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓት በምርጫ ውድድር በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያሸነፈ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥት የሚመሠርቱበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለመሆኑ፣ የተለያዩ ጥናታዊ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህም በቀጥተኛ የሕዝብ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የፓርላማውን አብላጫ ወንበር በማግኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩን (የአገሪቱን መሪ) የመምረጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ካቢኔ በማቋቋም መንግሥት የሚመሠርትበት አሠራር ነው፡፡

ይህንን ፓርላሜንታዊ ሥርዓት በርካታ አገሮች (ከ130 በላይ) የሚጠቀሙበት ሲሆን እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና በርካታ የአውሮፓ አገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ አውስትራሊያ ጠንካራ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የገነባችና ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን የምትከተል አገር በመሆኗ፣ ተመሳሳይ ሥርዓትን በምትከተለው ኢትዮጵያ እንደ ሞዴል ትቆጠራለች፡፡ አውስትራሊያ ጠንካራ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የመሠረተች በመሆኑ በፓርላማ ሥነ ሥርዓት ውስጥ ለተቃዋሚ ፓርቲ እኩል ድምፅ ይሰጣል፡፡

በፓርላማ ውስጥ ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ትልቅ መቀመጫ የያዘ ተቃዋሚ ፓርቲ በመንግሥት የሚቀርቡ ረቂቅ ሕጎችን፣ ፖሊሲዎችን፣ የአፈጻጸም ሪፖርቶችንና አማራጭ ሐሳቦችን በነፃነት እንዲያቀርብና እንዲከራከር የተለየ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማም ሥራ አስፈጻሚው የአውስትራሊያ መንግሥት የበጀት ጥያቄ ሙሉ ተቀባይነትን የሚያገኘው በላይኛው ምክር ቤት በመሆኑ፣ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በሆነባቸው ዘርፎች የበጀት ጥያቄው ያለተፅዕኖ ሊቀነስበት ይችላል፡፡

በአጠቃላይ ግን በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ውስጥ መንግሥት የሚመረጠው ከሕግ አውጪው ፓርላማ ውስጥ በመሆኑ፣ በመንግሥትና በሕግ አውጪው መካከል ግንኙነት በመኖሩ የቁጥጥርና የክትትል ተግባሩ ደካማ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በአብዛኞቹ ፓርላሜንታዊ ሥርዓቶች መንግሥት የሚመሠርተው ፓርቲ ሊቀመንበር የሥራ አስፈጻሚው የበላይ (ጠቅላይ ሚኒስትር) የመሆን ዕድል ያለው በመሆኑ፣ በፓርቲ ዲሲፕሊን ሥርዓቱ የይስሙላ እንዲሆን እንደሚገደድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 45 ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው፤›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት 22 ዓመታት ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ በሕዝብ ውክልና ከሚመጡ ተመራጮች መካከል አብዛኛውን መቀመጫ የሚወክል ፓርቲ መንግሥት እንዲመሠርት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ላለፉት አምስት የምርጫ ዘመኖችም የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የመንግሥት ሥልጣንን መያዙ ይታወቃል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት ከተደረጉት ምርጫዎች በሦስቱ የተቃዋሚዎች ውክልና ይብዛም ይነስም የነበረ በመሆኑና ፓርላማውም ለተቃዋሚ ተወካዮች ዕድል ይሰጥ ስለነበር፣ መንግሥትን በመቆጣጠርና በመከታተል እንዲሁም የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች እንዳይታፈኑ በማድረግ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡

ይሁን እንጂ በመጨረሻዎቹ ሁለት የምርጫ ዘመኖች ገዥው ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ ከአጋሮቹ ጋር መቀመጫዎችን በመቆጣጠር መንግሥት የመሠረተ በመሆኑ፣ ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት በመከታተልና በመቆጣጠር፣ እንዲሁም አማራጭ ሐሳቦች እንዳይሸፈኑ ማድረግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡

የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጎምቱ ፖለቲከኛ እንዲሁም የቀድሞ ሚኒስትር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የፓርላማ አባልና የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ፓርላማው አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን መንግሥትን የመቆጣጠር ሥራውን ያለ ተፅዕኖ ማከናወን ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሕዝብ ምክር ቤቶች መንግሥትን በመቆጣጠር ረገድ ያላቸውን ሚና ለመፈተሽ ዓርብ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት፣ ‹‹አስፈጻሚው ለዚህ ምክር ቤት ተጠያቂ መሆኑ በተግባር መታየት አለበት፡፡ ተጨማሪ ርቀቶችን መሄድ መቻል አለብን፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዓባይ ይህንን ሐሳብ ያቀረቡት ፓርላማው መንግሥትን በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት አቅቶታል ከሚል ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡

‹‹አገር ያናወጠ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሲፈጠር የክልል ምክር ቤቶችም፣ የፌዴራል ምክር ቤቶችም ፀጥ ነበር ያሉት፡፡ ገዥው ፓርቲ በራሱ መንገድ ይሂድ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎች የመንግሥት አካላትም የራሳቸውን መንገድ ይሂዱ፡፡ ፓርላማው ግን ዝም ማለት አልነበረበትም፡፡ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ጠርቶ መጠየቅ፣ በራሱም ማጣራትና ቁጥጥሩን ማድረግ ነበረበት፤›› በማለት ኃላፊቱን በመወጣት ረገድ ቸልተኝነት መኖሩን በመግለጽ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሌሎች በውይይቱ የተሳተፉ ባለሙያዎችም ሥራ አስፈጻሚው የሥልጣን ምንጭ የሆነውን ፓርላማና የምክር ቤቱን አባላት እንደሚንቁ በመግለጽ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በተነሱት ጉዳዮች ላይ ምላሽ የሰጡት በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ናቸው፡፡ አቶ አስመላሽ ለተነሱት ጥያቄዎች በተለይም የሥልጣን ክፍፍልን አስመልክቶ ለቀረቡት መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ተኮር መሆኑን በማውሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት መሆኑንና በዚህም አብላጫ ወንበር በፓርላማ ውስጥ ያገኘ ፓርቲ መንግሥት የሚመሠርት በመሆኑ፣ በመንግሥትና በፓርላማው መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሁለቱ የመንግሥት አካላት መካከል የፖሊሲ ልዩነት የለም፡፡ ሰለዚህ የፖሊሲ ክርክር አይኖርም፡፡ በሥራ አፈጻጸም ላይ ግን ያለ ገደብ ውይይት ማድረግ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

የገዥው ፓርቲ የፓርላማ አባል የፓርቲዎችን ፖሊሲ በመቃረን አስተያየት መስጠት እንደማይችል፣ ይህንን ማድረግ የሚችለው ፓርቲውን በመልቀቅ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ፓርላማው የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት አበጅቶ እንደሚንቀሳቀስ የተናገሩት አቶ አስመላሽ፣ ክትትልና ቁጥጥሩ በዋናነት መሠረት የሚያደርገው በመደጋገፍ ላይ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሁለተኛ ደረጃ የምንጠቀመው ማሳጣትና ማጋለጥ ነው፤›› የሚሉት አቶ አስመላሽ፣ የመጨረሻው አማራጭ ዕርምጃ መውሰድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት አፈጻጸም ላይ መሠረት ያደረገ እንጂ አማራጭ ሐሳቦችና ፖሊሲዎች የሚደመጡበት መሆን አልቻለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የጠነከረ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለመኖርና የምርጫ ሕጉም በአብላጫ ድምፅ ሕግ የሚመራ በመሆኑ ነው የሚሉ ተቺዎች፣ ይህ ሁኔታ እንዲቀየርና በተሻለ ሁኔታ የሕዝቦች ድምፅና አማራጮች በእኩል እንዲደመጡ ቢያንስ የምርጫ ሕጉ መቀየር ይኖርበታል ይላሉ፡፡

የምርጫ ሕጉ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና መምጣት እንዳለበት፣ በዚህም የተቃዋሚዎች ውክልናን ማግኘት የሚቻል በመሆኑ አማራጭ ሐሳቦችንና ሙግቶችን ፓርላማ ውስጥ ማድመጥ ይቻላል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ይለግሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የፓርላሜንታዊ ሥርዓተ መንግሥት በሥራ አስፈጻሚውና በሕግ አውጭው መካከል በማፈጥረው ቅርርብና ትስስር የእርስ በርስ ቁጥጥርና ክትትልን ደካማ የማድረግ ዕድል እንዳለው የሚታመን ቢሆንም፣ የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበርና የዴሞክራሲ ተቋማትን በተለይ የሚዲያና የሲቪል ማኅበራት ሚናን በማጠናከር የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚቻል የሚከራከሩ አካላት አሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -