ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚ ልዩ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ነዋይ ገብረ አብ፣ የቀጣዮቹ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ዋነኛ ፈተና የሚሆነው የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር መሆኑን ጠቆሙ፡፡ አቶ ነዋይ ይኼንን የተናገሩት በቅርቡ ከኤቲ ኪራኔ ጋር በአገሪቱ የአሥር ዓመታት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አወቃቀር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲቀየር ለማድረግ መሠረት የሚጣል መሆኑን የገለጹት ልዩ አማካሪው፣ በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የመዋቅራዊ ለውጡ ዕውን እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያን ቢያንስ የመጀመርያው የመካከለኛ ገቢ ደረጃን እንደምትቀላቀል፣ እንዲሁም የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1,200 ዶላር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ሁለት ስትራቴጂካዊ የዕቅድ ዘመኖች ከተሜነት እንደሚስፋፋ፣ በርካታ በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ወደ ከተማ እንደሚፈልሱና በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች እንደሚቀጠሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢንዱስትሪውን ዘርፍ የምርት መጠን መጨመር ችግር አይሆንም፡፡ ዋናው ችግር የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚቀጥረውን የሰው ኃይል መጠን መጨመር ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ነዋይ ይኼንን ያሉት በአገሪቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር መኖር የኢንዱስትራላይዜሽን ዕቅድ ትግበራው ላይ ፈተና እንደሚሆን ለመግለጽ ነው፡፡ ‹‹ስኬታማ መዋቅራዊ ለውጥ ማለት የአገሪቱን የቅጥር ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ነዋይ፣ በኢትዮጵያ በርካታ የሰው ኃይል በኢንዱስትሪው ዘርፍ መቀጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በተለይ የሠለጠነ የሰው ኃይል በቴክኒክም ሆነ በማኔጅመንት በፍጥነት ሊፈጠር ይገባል ብለዋል፡፡ ይኼንን ትልቅ ፈተና መንግሥት በመረዳት ከ35 እስከ 40 ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝና ከእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ተመራቂዎች ገበያውን እንደሚቀላቀሉ ገልጸዋል፡፡ ይኼ ማለት ግን ችግሩ ተቃልሏል ማለት እንዳልሆነ አቶ ነዋይ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች አጠቃላይ ሥልጠና ነው የሚሰጡት፤ በአንድ ዘርፍ ላይ ጥልቅ ዕውቀት የሚገኘው በሥራ ቦታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ኩባንያዎች ይኼንን ችግር ተገንዝበው ሊሰማሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይኼንን የሚገነዘቡ ኩባንዎችን ማግኘት በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፣ ማግኘቱ ግን ቀላል አይደለም፡፡ ይኼም የኢትዮጵያ የቀጣይ ዓመታት ፈተና ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አርከበ ዕቁባይ ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት ግን አቶ ነዋይ ገብረ አብ ያነሱት ፈተና የሚያሳስባቸው አይመስልም፡፡ አቶ አርከበ ዕቁባይም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ርካሽ የሰው ኃይል መኖሩን በመግለጽ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ይሞክራሉ እንጂ፣ ያለው የሰው ኃይል ከኢንዱስትሪው ጋር ምን ያህል ፈጥኖ ሊግባባ እንደሚችል ሲገልጹ አይስተዋልም፡፡ በአጠቃላይ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪ ዞኖች ልማት እንደምታወጣና በእነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች አማካይነት በየዓመቱ 200,000 አዲስ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ አቶ አርከበ ይገልጻሉ፡፡