Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐበሻ ቢራ ካፒታሉን ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያሳድግ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ አስመዘገበ

የአገሪቱን የቢራ ገበያ ከተቀላቀለ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ካፒታሉን ለማሳደግ በተጠራው ስብሰባ ወቅት፣ ባለአክሲዮኖች የድርጅቱ ካፒታል ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል መወሰናቸው ተገለጸ፡፡ የመጀመሪያውን የሥራ ዘመኑን በኪሳራ ያሳለፈው ሐበሻ በሁለተኛው ዓመት የተጣራ 32 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይፋ አድርጓል፡፡

የአክሲዮን ኩባንያው እሑድ፣ ሚያዝያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. 5ኛ እና 6ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሁም 11ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአንድ አጣምሮ ባካሄደበት ወቅት፣ በተለይ በ11ኛው ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳው የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ ሐሳብ አቅርቦ በዚያው መሠረት በአሁኑ ወቅት ያስመዘገበው የ1.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ አስወስኗል፡፡ ዓምና ያስመዘገበው 32.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍም ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል ተወስኗል፡፡ 

ከካፒታል ማሳደጉ ጎን ለጎን አዲስ የአክሲዮን ሽያጭ እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን፣ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድም የአክሲዮን ሽያጭ የማካሄድ፣ ሽያጩን የማስመዝገብና አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን የመቀበል ሥልጣን የሚሰጥ ውሳኔም ተላልፏል፡፡

ኩባንያው የአክሲዮን መጠኑን ለማሳደግ የወሰነው የምርት አቅሙን ለመጨመር የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ሐበሻ ቢራ ሥራ የጀመረው 300 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ይዞ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ይህንን አቅሙን ወደ አራት መቶ ሺሕ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ቀስ በቀስ 700 ሺሕ ሔክቶ ሌትር ማምረት የሚችልበት አቅም ላይ በመድረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የገበያ ድርሻውን ከፍ ለማድረግ እንደቻለ አሳይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት የ700 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የምርት አቅም በመጪው ዓመት ደግሞ ወደ 1.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ለማድረስ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚገልጸው የኩባንያው ሪፖርት፣ ይህንን ለማሳካት ካፒታል ማሳደጉ አንዱ ዕርምጃ በመሆኑ ይህንኑ ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት በባለአክሲዮኖች ዘንድ ተደርሷል፡፡

የሁለተኛውን የማስፋፊያ ምዕራፍ በመተግበር፣ በዚህ ዓመት እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2017 ሁለተኛው ሩብ ዓመት፣ ከያዘው የ950 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ፋይናንስ በተጨማሪ የባንክ ብድር ለማግኘት ስለመታቀዱ የኩባንያው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የሒሳብ ሪፖርቱና ዓመታዊ የሥራ ክንውኑ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መሠረት ተሠርቶ የቀረበ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. የ2015 እና የ2016 የሥራ ክንውን ሪፖርቶች በተናጠል በቀረቡበት ከእሑዱ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ መገንዘብ እንደተቻለው፣ በ2015 ኩባንያው የ20.3 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቦ ነበር፡፡ በተናጠል በቀረበው የ2015 ሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰውም ሥራ በጀመረበት በዚያው ዓመት (ካቻምና) የ73 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጦ እንደነበረ አመልክቷል፡፡ ሆኖም የተገመተውን ኪሳራ ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ በመሥራቱና ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር በተወሰዱ ዕርምጃዎች ምክንያት ዓምና፣ በ2016 32.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ሊያስዘግብ ችሏል፡፡

‹‹የሐበሻ ቢራ ምርትና ብራንድ በገበያው ዘንድ ያገኘው ከፍተኛ ተቀባይነት፣ እነሆ በድጋሚ ከታቀደው በላይ ሽያጭ በማስመዝገብና የትርፍ ህዳጋችንን በማሻሻል ወደ ተጨባጭ የፋይናንስ አፈጻጸምና ውጤት ለመተርጎም ተችሏል፤›› በማለት ኩባንያው ያገኘውን ውጤት ገልጾታል፡፡

የኩባንያው የ2016 የተጣራ የሽያጭ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንዳስመዘገበ የሚያመላክተው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ የሽያጭ ወጪውም በአንፃሩ 546 ሚሊዮን ብር እንደነበር አመላክቷል፡፡ የሽያጭ ወጪው ከተጣራ የሽያጭ ገቢው አንፃር ያለው ድርሻ 53 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአፈጻጸሙም ካቻምና ከነበረው የ62.4 በመቶ የወጪ ድርሻ ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ የተሻለ ነው ተብሏል፡፡

ከሽያጭ፣ ከምርት ሥርጭትና ከግብይት ወጪዎች ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ ከተጣራ ሽያጭ ላይ 10.5 በመቶውን፣ ቢራው ወደ ገበያው እንዲሰርጽ ለማድረግ በሚያስችሉ የብራንድ ማስተዋወቂያ ሥራዎች ላይ ወጪ አድርጓል፡፡ ለሽያጭና ለምርት ሥርጭትም 166 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የኩባንያው የጠቅላላ አገልግሎትና አስተዳደር ወጪዎች 128 ሚሊዮን ብር ማስመዝገባቸውን የሚገልጸው የፋይናንስ ሪፖርቱ፣ በ2016 ከወለድና ከታክስ በፊት የተገኘው ገቢ 85.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ መመዝገቡን አስፍሯል፡፡ ከካቻምናው የ20.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አንፃር ሲታይ ኩባንያው በትርፋማነቱ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል እንዳስመዘገበ አመላካች መሆኑም ተነግሯል፡፡

ሐበሻ ቢራ ለሚጠቅሳቸው መሻሻሎች ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱት መካከል የሽያጭና የምርት ሥርጭት ሰንሰለቶችን ውጤታማ ማድረግ መቻሉ አንዱ ሆኗል፡፡ የኩባንያው የተጣራ ቋሚ ንብረትም ከ933.3 ሚሊዮን ብር ወደ 1.35 ቢሊዮን ብር ማደጉን የሚያመላክተው የኩባያው ሪፖርት፣ ለዚህ ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ ካበረከቱት ውስጥ የመጀመሪያው በምዕራፍ አንድ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራዎች ላይ የታየው የተፋጠነ ዕድገት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ባለአክሲዮን ከሆነው ከባቫሪያ ኦቨርሲስ ኩባንያ መበደሩንም ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ ‹‹ኩባንያችን በ2015 እና በ2016 ከባቫሪያ ኦቨርሲስ የቢራ አምራች ኩባንያ ጋር ባደረገው የብድር ስምምነት ሦስት ብድሮችን አግኝቷል፡፡ ሁለቱ ብድሮች እያንዳንዳቸው 2.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሦስተኛው ደግሞ 9.8 ሚሊዮን ዶላር) በድምሩ 14.80 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፤›› በማለት ከኩባንያው የተገኘውን ጠቅላላ የብድር መጠን አስታውቋል፡፡ ሁሉም ብድሮች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ተሰጥቶባቸው እንደተገኙ ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

የወደፊቱን የመጠጥ ኢንዱስትሪውን አቅጣጫና ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ የሚገመቱ ሥጋቶችም በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡ ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተጋረጡበት በመሆኑ፣ ለምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ተጠቅሶ ይኸው ችግር ሊቀጥል እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የቢራ ገብስ ምርጥ ዘር በዓይነትና በጥራት እንደሚፈለገው መጠን አገር ውስጥ አለመኖሩ፣ ጥራት ላይ የተመሠረተ የቢራ ገብስ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር የሚከናወነው ሥራ ደካማ መሆኑ፣ የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ የማበረታቻ ስልቶችን የመንደፍና የመተግበር ጥረት አለመኖሩና ሌሎችም ችግሮች በኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ንግድ ሥራ ውስጥ የሚታዩ ተጠቃሽ እክሎች ስለመሆናቸው አትቷል፡፡

የአገር ውስጥ ገበያው በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 በመቶ እያደገ፣ የቢራ ፍጆታም በመጪዎቹ ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ ወደ 20 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር እንደሚያድግ ተገልጿል፡፡ ከቢራ ፍላጎትና ፍጆታ ጎን ለጎን በርካታ የቢራ ፋብሪካዎች በሚያካሂዱት የማስፋፊያ ሥራዎች አማካይነት የምርት መጠንም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ ከዓምና አሐዞች በመነሳት፣ የአገሪቱ ጠቅላላ የቢራ ፋብሪካዎች አጠቃላይ አቅርቦት ከ11 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ እንደደረሰ ግምቶች መኖራቸውን ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

የቢራ ገብስ አቅርቦት ዕጥረት የቢራ ፋብሪካዎችን የሚገዳደራቸው ፈታኙ ችግር ሲሆን፣ በዚሁ ዘርፍ አዲስ አቅም መፍጠር፣ ያለውንም ማሳደግ ግድ እንደሚል የሚጠቅሰው ሐበሻ ቢራ፣ አዳዲስ አምራቾችና የምርት ዓይነቶች ወደ ገበያው መጉረፍ የሚችሉበት ዕድል በርካታ መሆኑንም ይገልጻል፡፡  

ኩባንያው የውጭ ገበያ በትኩረት ከተሠራበት ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበለጠ ዕድል ይከፍታል የሚል እምነት አለው፡፡ በዚህ መስክ እስካሁን ዓይነ ግቡዕ እንቅስቃሴ ባይታይም ወደፊት፣ ብዙ ርብርብ የሚደረግበት ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ሁነኛ ምልክቶች መታየት እንደጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ ሐበሻ ቢራም ለውጭ ገበያ ትኩረት ከሚሰጥቸው ምክንያቶች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርን ለማስተንፈስ የሚረዳና ለዘለቄታውም አጋዥ መላ እንደሆነ ይገልጻል፡፡  

ሐበሻ ቢራ በመጪው ዓመት ስለሚኖረው ክውንውን በሰጠው ማብራሪያ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ዓምና ካስመዘገበው ይልቅ በ54 በመቶ ብልጫ ያለው የሽያጭ መጠን ይጠብቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዓምና ካስመዘገበው ትርፍ በ200 በመቶ ብልጫ የሚኖረው የትርፍ ዕድገት እንደሚያስዘግብም አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ከአገሪቱ ቀዳሚ የቢራ አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን የሚገልጸው ሐበሻ ቢራ፣ ዓምና የነበረው የገበያ ድርሻ 13 በመቶ እንደነበርም አስታውቋል፡፡     

ከ8,800 በላይ ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበው ሐበሻ ቢራ፣ 70 በመቶ የአክሲዮን ድርሻው የባቫሪያ ኩባንያ ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት በተደረገ ውይይትም የሐበሻ ቢራን አብላጫ ድርሻ ባቫሪያ መውሰዱ አከራክሮ ነበር፡፡ 70 በመቶው የባቫሪያ ድርሻ መሆኑ ከፍተኛ ድምፅ እንዲኖረው አስችሎታል፡፡ ወደፊት ሊካሄድ በታሰበው የአክሲዮን ሽያጭም ይኸው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ከያዘው የበለጠ ድርሻ መቆናጠጥ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል በማለት ሥጋታቸውን የገለጹ ባለአክሲዮኖች ድምጻቸውን ቢያሰሙም የባቫሪያ ኃላፊዎች ግን ካላቸው የ70 በመቶ በላይ የአክሲዮን ድርሻቸውን እንደማያሳድጉ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች