Saturday, June 15, 2024

የመደራጀትም ሆነ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አሁንም ቀንበሩ እንደከበደ ነው!

የዓለም የሠራተኞች ቀንም ሆነ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበሩ፣ የመሠረታዊ መብቶች አካላት የሆኑት መደራጀትና ሐሳብን በነፃነት መግለጽ በፈተና ውስጥ መሆናቸውን ፍጹም መካድ አይቻልም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች መንግሥት አገሪቱ ታዳጊ በመሆኗ ምክንያት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመከበራቸውን ቢያምንም፣ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ሸክማቸው እየከበደ ነው፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ እንዲሁም የመደራጀት መብት በግልጽ ቢደነገግም በንድፈ ሐሳብና በተግባር መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀንበሩ የከበዳቸው ዜጎች ሁሌም አቤት እንዳሉ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን አቤቱታ በአንድ ጆሮ ሰምቶ በሌላው እያፈሰሰ ስለሆነ ችግሩ ከመጠን በላይ እየሆነ ነው፡፡ መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡

የመደራጀት መብትን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 31 ላይ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው ይላል፡፡ በማስከተልም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ መሆኑን ደንግጓል፡፡ ይሁንና በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ በመደራጀት የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም በሕጉ ይደገፋል፡፡ ነገር ግን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነትም ሆነ በደጋፊነት መሳተፍ ያስፈራል፡፡ ለዓመታት የሚታወቀው ልምድም አሸማቃቂ በመሆኑ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተደራጅቶ ሰላማዊ ትግል ማካሄድ ለብዙዎች የማይሞከር ነው፡፡ ይህ ችግር የአገሪቱን የፖለቲካ ዓውድ ከማበላሸቱም በላይ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የመንግሥት ጫና የበረታባቸው ፖለቲካን እርም ብለው ጥግ ሲይዙ፣ ሌሎች ደግሞ የማይፈለግ ተግባር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰላማዊውን ትግል የማያዋጣ እንዲሆን የተዛባ ምሥል ይፈጥራል፡፡ በጥልቅ ተሃድሶው ይህ የተገመገመ ስለሆነ አጣዳፊ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል በሙያና በጥቅም ማኅበራት፣ እንዲሁም በሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ተደራጅተቶ ዓላማን ማሳካት ዳገት ሆኗል፡፡ ማኅበራት ለአገር የሚኖራቸው ጥቅምና አዎንታዊ ጎን እየታለፈ ገና ለገና የፖለቲካ መሣሪያ ይሆናሉ ተብሎ እንዲኮላሹ ሲደረግ የሚጎዳው አገር ነው፡፡ በተለይ ለወጣቶች አርዓያነት ያላቸው ተግባራትን ማከናወን የሚችሉ፣ በጥናትና በምርምር የታገዙ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን የሚያመነጩ፣ ወጣቶች በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መሠረታዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡና በርካታ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሲቪክ ማኅበራትን መደገፍና ማበረታታት ሲገባ ተሽመድምደው ተጠቅመዋል፡፡ ይህ እንደ አገር ሊያሳስብ ይገባል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት የዓለም የሠራተኞችን ቀን ሲያከብሩ በምሬትና በሰቆቃ ውስጥ መሆናቸው አሁንም ሊፈታ ያልቻለ የአገር ችግር ነው፡፡ ከሥራ ቦታ ደኅንነት፣ ጤንነት፣ ክፍያ፣ ጥቅማ ጥቅምና ሌሎች በደሎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች በስፋት ይነገራሉ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሠሪዎች ድብደባ የሚፈጸምባቸው፣ ያለምንም ክፍያ ከሥራቸው የሚባረሩ፣ ለጤና ጠንቅ በሆነ ቦታ ላይ ተመድበው በሰቆቃ ዕድሜያቸውን የሚገፉ፣ ለአካል ጉዳትና ለሕልፈት የሚዳረጉ ሠራተኞች ጉዳይ በስፋት ይሰማል፡፡ በሕጉ መሠረት ተደራጅተው ከአሠሪዎች ጋር መደራደር ያለባቸው ሠራተኞች ማኅበራቸው ሲፈርስ ወይም እንዳይቋቋም ሲከለከል የሚከላከልላቸው በመጥፋቱ ብቻ በርካታ ሰቆቃዎች ይሰማሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ሰላምን የሚያናጉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በቸልታ የሚታለፈው ለምን ይሆን? ይህም ብርቱ የሆነ ክትትልና ፈጣን ውሳኔ ያስፈልገዋል፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በተመለከተ ያሉ ችግሮች የዘወትር እሮሮ ናቸው፡፡ በተለይ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር በዚህች አገር ውስጥ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 እንዳለ ተወስዶ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የሆነው መብት በተግባር ቢከበር ኖሮ ብዙ መነጋገርና መወዛገብ አይኖርም ነበር፡፡ ይህ አንቀጽ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለው አረጋግጧል፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡ የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል ይላል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተለይ የተለያዩ መብቶች ተዘርዝረውለታል፡፡ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ የተገኘም በሕግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ የሰብዓዊ መብት ሁለንተናዊ ድንጋጌዎች፣ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መርሆዎች ድንጋጌ፣ የዊንድሆክ ድንጋጌ፣ የአፍሪካ ብሮድካስቲንግ ቻርተርና የአፍሪካና የኔፓድ ኮሚሽን የተጠቃለሉ መርሆዎች ፈራሚ ናት፡፡ እነዚህ በራሳቸው የትና የት ለማድረስ የሚረዱ ነበሩ፡፡ ግና ፈተናው ብዙ ነው፡፡

የአገሪቱ ፕሬስ 120 ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ በተሟላ ሁኔታ የግሉ ፕሬስ በዚህች አገር ውስጥ በይፋ መሥራት ከጀመረ 24 ዓመታትን አገባዷል፡፡ ይህ ጮርቃ የግል ፕሬስ ለሙያው አዲስ ከመሆኑም በላይ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባርና የልምድ ጉድለቶች አሉበት፡፡ የሙያ ችግሮችን በተመለከተ በአገሪቱ ገበያው በሚፈልገው መጠን ጋዜጠኞችን የሚያፈሩ የትምህርት ተቋማት በሚገባ አለመኖራቸው፣ የጋዜጠኞችን ክህሎት ለማሳደግ የግሉ ፕሬስ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ በዚህ ምክንያትም የሙያ ሥነ ምግባር ዝቅተኛ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡ ብዙዎቹ የግል ፕሬሶች የሙያ ሥነ ምግባር መመርያም ሆነ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የላቸውም፡፡ ብዙዎችም መሠረታዊ የሆነ የመዋቅር ችግር አለባቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ ገለልተኝነት እየጠፋ ጽንፈኝነት፣ ከዚያም ባለፈ ወደ ፖለቲካ አቀንቃኝነት (Activism) ውስጥ ተገብቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ራስን በራስ ለመቆጣጠር የሚረዳ የፕሬስ ካውንስል ለማቋቋም የፈጃቸው 20 ዓመታት የሁኔታውን አስቸጋሪነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በዚህ ላይ አሉ የሚባሉት የጋዜጠኛ ማኅበራት ደካማነት፣ በቅጡ አለመደራጀትና ወገንተኝነት የችግሩ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ መጠነ ሰፊ ችግር ላይ መንግሥት ለግሉ ፕሬስ ያለው ዕይታ ጥሩ ካለመሆኑም በላይ ማበረታቻን ማሰብ የሰማይ ያህል ይርቃል፡፡ መንግሥት ድጋፍ ካለማድረጉ በተጨማሪ ማግለሉና ተጋፊ መሆኑ ሁኔታዎችን አክብዶአቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ከአምስቱ ግንባር ቀደም አገሮች ተርታ በመሆን ጋዜጠኞችን አሳሪ መሆኗ ለሙያው አደጋ ነው፡፡ ሙያውን ለማካሄድ የማይመቹ ጨካኝ ሕጎች መኖራቸው ደግሞ ሌላው ፈተና ነው፡፡ እስከ መቼ በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል?

የአገሪቱን ሚዲያ ካውንስል ለማቋቋም የታዩ ፈተናዎች በፕሬሱ የመደራጀት መብት ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥለዋል፡፡ በወርኃ መስከረም 2009 ዓ.ም. ከበርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ የተመሠረተው የሚዲያ ካውንስል በ19 የሚዲያ ድርጅቶችና የጋዜጠኛ ማኅበራት ቢቋቋምም፣ ላለፉት ስምንት ወራት በተደረገው ጥረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት ባለማግኘቱ መፃኢ ዕድሉ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የተደረገው ጥረት ከንቱ እየሆነ ያለው በአገሪቱ ይህንን ተግባር ማከናወን የሚችል መንግሥታዊ ተቋም ባለመኖሩ ነው ተብሏል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚዲያ ካውንስል እንደ ሚዲያ ድርጅት መቋቋምና ሥራውን መቀጠል የተለመደ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ይህ መሆን አልቻለም፡፡ ለበርካታ የመንግሥት አካላት ይህ ችግር በተደጋጋሚ ቢነገርም መፍትሔ አልተገኘም፡፡ በመሆኑም ተመዝግቦ ዕውቅና ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት በተለይ የግሉ ፕሬስ ጠላት እንደሆነ ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ ሚዲያ ደካማ፣ ጽንፈኛና ስሜታዊ፣ ከሙያውም ከሥነ ምግባሩም የሌለበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ደካማ፣ በሙያውም እዚህ ግባ የማይባል፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትና ሙያተኞችን መሳብ የማይችል ሆኗል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ጠንካራ የግል ፕሬስ ያስፈልጋታል፡፡ ዴሞክራሲያዊት አገር የምትገነባው የግሉን ፕሬስ ሚና መንግሥት ማመን ሲኖርበት ነው፡፡ የመንግሥት ባህሪና ፖሊሲ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ መንግሥት ባለሥልጣናቱም ሆኑ ተቋማቱ ለግሉ ሚዲያ እኩል ዕድል እንዲሰጡ ማዘዝ አለበት፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሁለንተናዊ ችግሮች የሚቀረፉት በገዥው ፓርቲ ወይም በሚመራው መንግሥትና አደረጃጀቶች ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለሕግ የበላይነት ትኩረት በመስጠት በሕገ መንግሥቱም ሆነ አገሪቱ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፋዊ ሰነዶች ዋስትና ያገኙ መብቶችን ማክበር ለአገር ዘለቄታዊ ሰላምና ደኅንነት ይበጃል፡፡ በፊትም ሆነ አሁን እየታየ ያለው ግን ሌላው ቀርቶ የፕሬስ ነፃነት በሚከበርበት ዕለት እንኳ የሚደረጉ የፓናል ውይይቶች አጀንዳዎች ላይ መግባባት ብርቅ ነው፡፡ ጠንከር ያሉ ሐሳቦች ሲቀርቡ በጠላትነት መፈራረጅ የተለመደ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን እየተዘከረ የሐሳብ ብዝኃነት አለመፈለጉ በራሱ የሚናገረው አለው፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር ተከቦ መፍትሔ ለመፈለግ አለመሞከር ለአገር አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም የመደራጀትም ሆነ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቀንበሩ አይክበድ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...