Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት

አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት

ቀን:

ለአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን 100 ቀናት መፈተኛ፣ መወቀሻ ወይም መወደሻ፣ ዕቅዳቸውን ማሳወቂያና መጀመሪያ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል መተግበሪያም ናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተለያዩ ፖሊሲዎችንና መመርያዎችን ለማሻሻል ብሎም ሙሉ ለሙሉ ለመቀየርና በአዲስ ለመተካት ስምምነታቸውን በፊርማ የሚያረጋግጡበት ወቅትም ነው፡፡ ሕዝባቸውም ሆነ የተለያዩ አገሮች ተመራጩ ፕሬዚዳንት በእነዚህ ጊዜያት የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች ነቅተው የሚጠብቁበት፣ የፖለቲካ ተንታኞችም የሰላ ትችታቸውን የሚሰነዝሩበት  ጊዜም ነው፡፡ ፕሬዚዳንቶች በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቧቸውን ነገሮች ዕውን እንደሚያደርጉ ፍንጭ የሚያሳዩበት ብሎም ተግባራዊ የሚያደርጉበትም ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውጭ መሪዎችን ጋብዘው ይወያያሉ፣ እነሱም ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ይመክራሉ፡፡

45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚናገሯቸው ንግግሮችና በሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ትችት የበዛባቸው፣ በአገራቸው ሚዲያም ከአዎንታዊ ጎናቸው ይልቅ በአሉታዊው የተቃኙ ናቸው፡፡

በመጀመሪያዎቹ የሥልጣናቸው 100 ቀናትም ከአሜሪካ ጋር መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወዳላቸውም ሆነ ወደሌላቸው አገሮች አላቀኑም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዲዮ፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፣ የቻይና ፕሬዚዳንት ጂን ፒንግ፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከልን ጨምሮ የ13 አገር መሪዎችን ጋብዘው በዋይት ሐውስ አነጋግረዋል፡፡

ከመሪዎቹ የተመካከሩባቸውን፣ በስደተኞችና አሜሪካ በሚገቡ ሕገወጥ ዜጎችና ከሜክሲኮ ጋር ስለሚኖራቸው የድንበር አጥርና ከንግድ ልውውጥ ጋር ተያይዞ ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች ‹‹የመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናት አስደማሚ ጉዞ›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

የመጀመሪያዎቹን 100 የሥራ ቀናት አስመልክቶ ለደጋፊዎቻቸው በፔንሲልቫኒያ ግዛት ባደረጉት ንግግር ውጤታማ መሆናቸውን፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በእሳቸው ላይ የተሳሳተ አቋም እንደሚያራምዱና ውሸታሞች እንደሆኑም ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡

በሚዲያዎች ላይ አዲስ ነቀፋ የሰነዘሩት ትራምፕ፣ ‹‹በዋይት ሐውስ ኮሮስፖንደንትስ የእራት ግብዣ ላይ የሆሊውድ አክተሮችና ሚዲያዎች ተሰባስበዋል፡፡ ሲኤንኤንና የኤምኤስኤንቢ የውሸት መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡ ከእኛ ጋር ቢሆኑ ይወዱ ነበር፡፡ ሆኖም በአሰልቺው የእራት ግብዣ ላይ መገኘትን መርጠዋል፤›› ሲሉም ዋይት ሐውስ ያደረገውን የእራት ግብዣ አጣጥለዋል፡፡

ከምርጫ ቅስቀሳቸው አንስቶ ከሚዲያው ጋር መግባባት ያልቻሉት ትራምፕ፣ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ከሆሊውድ ዝነኞችና ከሚዲያው ጋር በዓመት አንዴ በሚገናኙበት የእራት ግብዣ፣ ካለፉት 36 ዓመታት ወዲህ ያልተገኙ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የእራት ግብዣው ከሚካሄድበት ዋሽንግተን 100 ማይልስ ርቀው በ100ዎቹ የሥራ ቀናቸው ስላሳለፉት ታላቅ የሥራ ጉዞ ከደጋፊዎቻቸው ጋር መምከርን መምረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ባሳለፏቸው የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ቀናትም መልካም ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ያነሱት ለአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ኔል ጐርሳችን አቅርበው ከሴኔቱ ይሁንታ ማግኘታቸውንና ከትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ ስምምነት አሜሪካን ለመነጠል ያሳለፉትን ውሳኔ ነበር፡፡ ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናት ያስመዘገቧቸውን ውጤቶችና ስህተቶች ቴሌግራፍ ተንትኖታል፡፡

የትራምፕ እመርታዎች

ትራምፕ ውጤታማ ሆነውባቸዋል ከተባሉት ሥራዎቻቸው አንዱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ያቀረቧቸው ኔል ጐርሳች ከሴኔቱ ዕውቅና ማግኘታቸው ነው፡፡ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አሜሪካና 11 የፓስፊክ ተጋሪ አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የደረሱበትን ስምምነት እንደማይቀበሉ የተናገሩት ትራምፕ፣ ከተመረጡ በኋላም ይህንን አፅንተዋል፡፡ አገሮቹ ከስምምነት ቢደርሱም በየአገራቸው ፓርላማ ማፀደቅ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱን የፈረሙ ቢሆንም፣ ትራምፕ ይህንን በኮንግረሱ አፀድቀው ዕውን እንደማያደርጉ ማሳወቃቸው እንደ እመርታ ተይዞላቸዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው አሜሪካ በሚገቡ የሌሎች አገር ዜጎች ላይ ጠንካራ ገደብ መጣላቸውም ተደንቆላቸዋል፡፡ ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላም ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር በጉልህ ቀንሷል፡፡ በሕገወጥ ስደተኞች ላይ ያሰመሩት ቀይ መስመር የስደተኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ36 በመቶ እንዲቀንስ አስችሏል፡፡  

የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በተመለከተ ትራምፕ ቀጥታ ጣልቃ መግባታቸውም መልካም ተብሎላቸዋል፡፡ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ተጠቅመዋል መባልን ተከትሎ፣ አሜሪካ በሶሪያ ላይ የክሩዝ ሚሳይል ድብደባ እንድትፈጽም መፍቀዳቸው፣ ሰሜን ኮሪያ ላይ ያላቸው አቋምና ከቻይና ጋር የፈጠሩት ወዳጅነት ከበጎ ሥራዎቻቸው ተቆጥረዋል፡፡

የትራምፕ ስህተት

ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናት ካከናወኗቸው እንደ ስህተት ተቆጥሮ የሰላ ትችት የተሰነዘረባቸው በኢራን፣ በኢራቅ (በኋላ እንዲቀር ቢደረግም)፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በሊቢያ፣ በሶሪያና በየመን ዜጎች ላይ ያሳለፉት የጉዞ ዕገዳ ነው፡፡ የየአገሮቹ ዜጎች ለተወሰነ ጊዜ አሜሪካ እንዳይገቡ ያሳለፉት የመጀመሪያ ውሳኔ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ቢደረግም፣ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያንም ውሳኔውን ተቃውመው ሠልፍ ወጥተዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የተጣለው ገደብም ቢሆን የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የጣሰና ሙስሊሞችን ያገለለ ተብሏል፡፡

ኦባማኬር የሚባለውን የጤና ዋስትና በሌላ መተካት የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ አጀንዳ ነበር፡፡ 14 ሚሊዮን ያህል አሜሪካውያንን የጤና ዋስትና ያሳጣል የተባለው የትራምፕ ኦባማኬርን የመተካት ፍላጎት አሁን ድረስ ውሳኔ አላገኘም፡፡ ውሳኔ ማግኘት ካልቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ አማራጭ የጤና ዋስትና ሥርዓት ማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፖለቲካዊ ድርድር ልምድ ማጣታቸው ኦባማኬርን ለመተካት ላቀረቡት ሐሳብ ድጋፍ አሳጥቷቸዋል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ይዘው ወር ሳያስቆጥሩ የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ፍሊን ከሥራ መልቀቃቸው የትራምፕ ስህተት ተብለው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ፍሊን በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር ስለነበራቸው ቆይታ የተሳሳተ መረጃ ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ሰጥተዋል ተብለው ሥራ በያዙ በሁለት ሳምንታቸው ትችት የተሰነዘረባቸው ሲሆን፣ ሥራ በያዙ በ24ኛ ቀናቸው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡

‹‹በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ግንብ እገነባለሁ›› ያሉት ትራምፕ፣ በአቋማቸው ተተችተዋል፣ ስህተት ሠርተዋልም ተብለዋል፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ ግንባታው ለሚጀመረው ግንብ ‹‹ገንዘቡን ሜክሲኮ እንድትከፍል አደርጋለሁ›› ቢሉም፣ ግንባታውን ማን በገንዘብ እንደሚደግፈው አልታወቀም፡፡

ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናት ለመሥራት ካቀዷቸው ሥራዎች አንዱ የአገሪቱን መሠረተ ልማት ማጠናከር ነበር፡፡ ለዚህም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ይህንን በጀት ለማግኘት ከኮንግረሱ የታየ ፍንጭ የለም፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ንግግሮችን አለማድረጋቸውም እንደ ስህተት ተቆጥሯል፡፡ በተለይ የተሰማቸውን ሁሉ ትዊት ማድረጋቸውና መደበኛ መረጃ የማሠራጫ ዘዴ ወይም የዋይት ሐውስ ፕሬስን አለመጠቀማቸው አስተችቷቸዋል፡፡

በዋይት ሐውስ አስተዳደር ውስጥ አለመግባባት አለ ከመባሉም ባለፈ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዘርፎች ክፍት መሆናቸው ትራምፕ በ100ዎቹ ቀናት መሥራት ካልቻሏቸው ተመድቧል፡፡ 553 ቁልፍ ሹመቶችም የሴኔቱን ይሁንታ ማግኘት አልቻሉም፡፡

ትራምፕ በሕዝባቸው ተቀባይነት ያገኙና ያላገኙ 43 ከፍተኛ ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዞችን ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለመራጮቻቸው ቃል የገቧቸው አጀንዳዎች ይገኙባቸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...