Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትመቐለ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሻምፒዮናን ጨምሮ ሦስት ስፖርታዊ ክንውኖችን ታስተናገዳለች

መቐለ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሻምፒዮናን ጨምሮ ሦስት ስፖርታዊ ክንውኖችን ታስተናገዳለች

ቀን:

ሰሜናዊቷ መቐለ ከተማ በመጪው ዓመት ለሦስት አገራዊና አህጉራዊ ስፖርታዊ ክንውኖች ከወዲሁ መሰናዶዋን ጀምራለች፡፡ በከተማዋ እንደሚካሄዱ ይፋ የተደረጉት ውድድሮች የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሻምፒዮና፣ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድሮች ናቸው፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የትግራይ ክልል ለስፖርታዊ ክንውኖቹ እያደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በመቐለ ከተማ በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዓመታዊ ሻምፒዮና እና ስድስተኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በተከታታይ በየካቲትና በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ሲካሄዱ፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ደግሞ በሐምሌ ወር ይስተናገዳል፡፡

ለስፖርታዊ ክንውኖቹ ክልሉ እያዘጋጃቸው ከሚገኙት የስፖርት መሠረተ ልማቶች መካከል የግንባታው ሒደት መዘግየቱ የሚነገርለት የትግራይ ሁለገብ ዘመናዊ ስታዲየም አንዱ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይኼው  ስታዲየም የግንባታው ጥንንስ የተጀመረው በክልሉ ተወላጆች መልካም ፈቃደኝነት በ1999 ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  ኃላፊ አቶ ጎይተኦም ይብራህ እንደሚናገሩት፣ ዓመታትን ያስቆጠረው የትግራይ ዘመናዊ ስታዲየም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የሙሌት ሥራው ተጠናቋል፡፡ እስካሁን ላለው የግንባታ ሒደት የክልሉ መንግሥት 539 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ግንባታው በተጀመረበት በ2003 ዓ.ም. ተይዞለት የነበረው በጀት 22 ሚሊዮን ዶላር (በአሁኑ ምንዛሪ 560 ሚሊዮን) ቢሆንም፣ እስካሁን ወጪ ከተደረገለበት 600 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅ አቶ ጎይተኦም ያስረዳሉ፡፡

የስታዲየሙ ግንባታ መዘግየትና የኅብረተሰቡ አስተያየት

የስታዲየሙ ጥንስስ የተጀመረው በ1999 ዓ.ም. ቢሆንም የሐሳቡ አመንጪዎች ለግንባታው ያቀዱት በጀትና ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው የገንዘብ መጠን ሊጣጣም ባለመቻሉ ምክንያት የፕሮጀክቱ ግንባታ ሳይጀመር እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ መጓተቱ ይነገራል፡፡ እንደ አቶ ጎይተኦም ይብራህ ከሆነ፣ የክልሉ መንግሥት ፕሮጀክቱን በኃላፊነት ከተረከበበት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግንባታው አሁን እስከሚገኝበት ደረጃ 539 ሚሊዮን ወጪ አድርጓል፡፡ ይኽም ክልሉ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚንቀሳቀስባቸው መሠረተ ልማቶች ጎን ለጎን እንዲካሄድ በመደረጉ ለግንባታው መዘግየት ምክንያት ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡ እንደ ኃላፊው የትግራይ ስታዲየም ሁለገብና ዘመናዊ እንደመሆኑ መጠን የሚጠይቀው የበጀት አቅም ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱንም ከከተማዋ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ጋር ያያይዙታል፡፡ የውኃው ነገር ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑና ሁለቱን አጣጥሞ ማስኬድ ግድ መሆኑን ጭምር በመግለጽ የስታዲየሙ ግንባታ ተጓቷል የሚለውን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡

ክልሉ ለከርሞ አገራዊና አኅጉራዊ ስፖርታዊ ውድድሮችን አስተናጋጅ እንደመሆኑ መጠንና ስታዲየሙ አሁን ያለበት የግንባታ ሒደት አኳያ አያሠጋም ወይ? ለሚለው አቶ ጎይተኦም ምላሽ አላቸው፡፡ ‹‹የስታዲየሙ ግንባታ እግር ኳስንና ሌሎች ተያያዥ ውድድሮችን ማከናወን የሚያስችል አቋም ላይ ነው፡፡ የቀረው ነገር ቢኖር ሩጫና ከሩጫ ጋር የተገናኙ የውድድር ዓይነቶችን ለማከናወን የሚያስችለውን ትራክ (መም) ማንጠፍ ስለሆነ ይህንኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነቶች ተደርገዋል፤›› ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለዚህና መሰል ግንባታዎች 241 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ጭምር ይናገራሉ፡፡

ስፖርታዊ ውድድሮቹን ከክልሉ ጋር በመሆን የሚከታተሉት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ልዑካኖችም ውድድሮቹ ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ስታንዳርድ የጠበቁ ሊሆኑ እንደሚገባ በማመን ከስታዲየሙ የግንባታ ሒደት ጋር ተያይዞ ሊሟሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን መሠረታዊ ነጥቦችን በጉብኝቱ ወቅት አንስተው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከተነሱት ነጥቦች መካከል አወዳዳሪዎችና ተወዳዳሪዎች የሚጠቀሙባቸው ክፍሎች፣ የውኃና የኤሌክትሪክ እንዲሁም ልዑካኖች የሚጠቀሙባቸው መፀዳጃ ክፍሎች፣ ማወዳደሪያ ቁሳቁሶችና ሁሉም ስፖርቶች እንደየባህሪያቸው የሚዘወተርባቸው መሠረተ ልማቶች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ሪፖርተር በትግራይ ስታዲየም የግንባታ ሒደት ዙሪያ ያነጋገራቸው አንዳንድ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ለግንባታው መጓተት የሚቀርበውን ምክንያት አይቀበሉትም፡፡ ስታዲየሙ አሁን ባለበት ሁኔታ መጠሪያው ‹‹ቆሞ ቀር›› እና ‹‹ማቱሳላ›› (ረዥም ዕድሜ) በሚለው ተቀይሮ እንደሚጠራ ይናገራሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ምክንያቱን አስመልክቶ፣ ግንባታው ከተጀመረ ከዓመታት በኋላ ተመሳሳይ የስታዲየም ግንባታ የጀመሩ ሌሎች ክልሎች ያስገነቧቸው ዘመናዊ ስታዲየሞች ሙሉ ለሙሉ ባይጠናቀቁም በካፍና ፊፋ ዕውቅና አግኝተው የተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ጎይተኦም በበኩላቸው፣ ስታዲየሙ ከፕሮጀክቱ ስፋትና ከሚጠይቀው በጀት አንፃር ለግንባታው የክልሉ መንግሥት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ያደንቃሉ፡፡ ምክንያቱም ስታዲየሙ 120 ሺሕ ካሬ ሜትር (12 ሔክታር) መሬት ይሸፍናል፡፡ በውስጡ ከዋናው የእግር ኳስ ሜዳ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሁለት ሜዳዎችን የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የውድድር ዓይነቶችን ማለትም መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ እንዲሁም ለውኃ ዋና የሚያገለግሉ ዘመናዊ ገንዳዎች አሟልቶ የያዘ መሆኑን ጭምር ይጠቅሳል፡፡ ሌላው ደግሞ ግንባታው በአብዛኛው ከመሬት በታች ለተለያዩ አገለግሎቶች ለተሽከርካሪዎች ማቆያ የሚውሉ ግንባታዎችን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማቶችን አካቶ የያዘ መሆኑ፣ በሌሎች ክልሎች እየተገነቡ ካሉት ስታዲየሞች ለየት የሚልባቸው መገለጫዎቹ መሆኑን በመግለጽ ግምት ሊወሰድ እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አበረታች ጅምሮች

ከዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ጎን ለጎን በክልሉ ከሚከናወኑ የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች መካከል የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የአትሌቲክስ ፕሮጀክትትና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ለክልሉና ለአገሪቱ ስፖርት ዕድገት እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ የልዑካን ቡድኑ የጉብኝት አንዱ አካል ነበር፡፡

መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስና በብስክሌት አገሪቱን በአህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች መወከል የቻሉ አትሌቶች ማፍራት የቻለ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ የአትሌቶች መኖሪያና የመወዳደሪያ ቁሳቁሶችን በማሟላት በዕድሜ ለገፉት የስፖርት ተቋማት ምሳሌ እየሆነ መምጣቱንም ጭምር ከፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሌላው የልዑካን ቡድኑን ትኩረት በእጅጉ ስቦ የነበረው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ለስፖርቱ ክፍል እየሰጠ ያለው ትኩረትና በማስፋፋት ላይ የሚገኘው የስፖርት መሠረተ ልማት ይጠቀሳል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በስፖርት ክፍሉ አማካይነት በአሁኑ ወቅት ከመጀመሪያ ዲግሪ እስክ ዶክትሬት ዲግሪ እየሰጠ እንደሚገኝ ለልዑካን ቡድኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  ክንዳያ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ከስፖርት ሳይንስ ፋኩልቲ ከሳቴ ለገሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በመቐለ ከተማ ዋናውን ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ ሦስት ካምፓሶች አሉት፡፡ በሦስቱም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዘውተሪያዎች እንዲሁም የአገሪቱንና የክልሉን ስፖርት በተመለከተ ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው የተለያዩ ማዕከሎች ባለቤት ነው፡፡ እነዚህና መሰል የዩኒቨርሲቲው እንቅስቃሴዎች የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በመጪው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የሚደረገውን የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ክንውኖችን እንዲያስተናግድ አስመርጦታል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚደረገው የኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት ስፖርታዊ ውድድሮችን ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጅ መሆኑን ጭምር አቶ ከሳቴ አስረድተዋል፡፡ ለውድድሮቹ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል የእግር ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ የውኃ ዋና፣ የብስክሌት፣ የሩጫና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ተሟልተው ለውድድር ዝግጁ መሆናቸውንም ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተመርቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...