Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበስዊፍት መልዕክት ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጭበርብረዋል የተባሉ የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞች ተከሰሱ

በስዊፍት መልዕክት ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጭበርብረዋል የተባሉ የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኞች ተከሰሱ

ቀን:

የአቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር አራት ሠራተኞች በተጭበረበረ ስዊፍት (ከውጭ ባንክ ጋር በጥብቅ ሚስጥር የገንዘብ መላላኪያ መንገድ) መልክዕት፣ ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረዋል ተብለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ በአቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ዓለም አቀፍ የውጭ ባንኮች ግንኙነት መምርያ ውስጥ ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎትና ኮረስፖንዳት ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሰይድ፣ የትራንስፈር ሰርቪስና ኮረስፖንዳት ባንኪንግ ኦፊሰሮች ሔለን አሰፋ ወልደ ሥላሴ፣ እሱባለው ሲሳይና አለልኝ ጽጌ ናቸው፡፡ ትክክለኛ የስዊፍት መልዕክት መለያ ቁጥርን በመቀየር አጭበርብረው መዝብረዋል ከተባለው ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ውስጥ፣ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለባንኩ ለማስመለስ መቻሉን ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

ተከሳሾች የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው ከባንኩ ፈቃድና ዕውቅና ውጪ በትክክለኛ ሁኔታ ተዘጋጅተው፣ የማስተካከያ ቋት ውስጥ የነበሩ አምስት የስዊፍት መልዕክቶች ላይ የተቀባይ ስም፣ የገንዘብ መጠንና የመለያ ቁጥሩን በመቀየር የተጭበረበሩ አምስት የስዊፍት መልክዕቶችን መሥራታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

በትክክለኛው ሁኔታ ተዘጋጅተው የማስተካከያ ቋት ውስጥ የነበሩና በተጭበረበሩ አምስት የስዊፍት መልዕክቶች የተቀየሩት የመለያ ቁጥሮች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት፣ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ የጁጋል ሲንግ ሻራም፣ የፔትራ ኢንዱስትሪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በድጋሚ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ውጭ አገር ወዳለው የራሱ ሒሳብ 3,546,482 ዶላር ለመላክ በስዊፍት የክፍያ መልዕክት ላይ እያለ ተከሳሾቹ በሚጠቀሙበት ኮምፒዩተር የሶፍትዌር የተጠቃሚን ስምና ሚስጥር ኮድ በመጠቀም፣ የመለያ ቁጥሩንና የተቀባዩን ኩባንያ በመቀየር የሚላከውን ገንዘብ 177,850 ዶላር በማድረግ አንደኛው ተከሳሽ ለሌላኛው ተከሳሽ ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕም ለተቀባዩ ኔላ ሮዝ ሃርዲ 9,001 ዶላር ልኮ በማስተካከያ ስዊፍት መልዕክት ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ መንገድ ተከሳሾቹ መለያ ቁጥሩንና የተቀባይን ስም በመቀየር 190,501 ዶላር ለሌሎቹ ተከሳሾች ሲልኩላቸው ሌሎቹ ተከሳሾች የስዊፍት ተጠቃሚ ስምና የሚስጥር ኮድ በመቀየር መልዕክቱ እንዲፀድቅ ለሌላኛው ተከሳሽ መላካቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ጁጋል ሲንግ ሻራም ለተቀባዩ ሳነቶሽ ዴቭ 650 ዶላር ተልኮ ነገር ግን በማስተካከያ ቋት ውስጥ የነበረን የስዊፍት ክፍያ መልዕክት ወደ 189,600 ዶላር መቀየሩንም ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል፡፡ ፔትራ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ ለተቀባዩ ካልፓካ ኬሚካልስ 4,650 ዶላር ልኮ ነገር ግን ሳይደርስ የማስተካከያ ቋት ውስጥ የነበረን የስዊት ክፍያ መልክዕት የመለያ ቁጥር በመቀየር 189,600 ዶላር ተከሳሾቹ እርስ በርሳቸው መላላካቸውን አክሏል፡፡ ተከሳሾቹ በድጋሚ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በውጭ አገር ለሚገኘው የራሱ ሒሳብ 3,070,311 ዶላር ልኮ ነገር ግን የማስተካከያ ቋት ውስጥ የነበረን የስዊፍት የክፍያ መልክዕት የላኪውን ስም፣ የሚስጥር ኮድና የተቀባዩን ስም በመቀየር 465,800 ዶላር እርስ በርሳቸው በመላላክና ሌላኛው ተከሳሽ እንዲያፀድቁት በማድረግ በአጠቃላይ 1,213,351 ዶላር ወይም 28,057,164 ብር መመዝበራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በመሆኑም የወንጀል ሕግ 32(1ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1ሀ እና 2)ን መተላለፋቸውን በመግለጽ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ወንጀል የሙስና ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ አቶ መሐመድ ሰይድ የተባሉት ተከሳሽ ደግሞ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ አንቀጽ 13 1ሐ እና (2)ን በመተላለፋቸው፣ የመንግሥትን ወይም የሕዝባዊ ድርጅቶችን ሥራ በሚያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ ክሱ እንዲደርስ ካደረገ በኋላ፣ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ትዕዛዝ ሰጥቶ የዓቃቤ ሕግ ክስን ለመስማት ለግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...