‹‹ከ80 በላይ ማኅበራት እንዲፈርሱ ሀብትና ንብረታቸው እንዲመዘበር ሲያደርግ የጠየቀው የለም›› ብለዋል
‹‹ማኅበር እንጂ የማኅበራት ማኅበር እንዳደራጅ ሥልጣን አልተሰጠኝም››
ፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን
ማኅበራትን በዩኒየን አደራጅተን የመንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ተጋፍቷል በማለት፣ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ላይ ወቀሳ አቀረቡ፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ረቡዕ ሚያዝያ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራውና የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በተወያየው ስብሰባ ወቅት ባለንብረቶቹ እንደገለጹት፣ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለዜጎች የተሰጡ በነፃ የመደራጀት መብቶችን እየጣሰ ነው፡፡ ብሔራዊ የትራንስፖርት ማኅበራት ኅብረት ከሌላቸው የደቡባዊና ምሥራቃዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) 16 አባል አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያና አንጎላ ብቻ፣ የዚህ ዓይነት ብሔራዊ የትራንስፖርት ኅብረት የሌላቸው አገሮች ናቸው ያሉት ባለንብረቶቹ፣ በኢትዮጵያ ይህንን ኅብረት ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ ባለሥልጣኑ ጣልቃ በመግባትና ሕግ በመጣስ እንዳንደራጅ አድርጓል በማለት ስሜት የቀላቀለበት ቅሬታና ወቀሳቸውን አሰምተዋል፡፡
‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 31 የተቀመጠውን የመደራጀት መብታችንን ከመጣሱ በላይ 80 ማኅበራት እንዲፈርሱ፣ ሀብትና ንብረታቸው እንዲመዘበር ሲያደርግ የጠየቀየው የለም፤›› ያሉት ባለንብረቶቹ፣ በማያገባው እየገባ የስብሰባ ፈቃድ እያስከለከለ፣ የሚካሄዱ ስብሰባዎችም ሕገወጥ ናቸው በማለት ለኮማንድ ፖስት ሳይቀር ደብዳቤ እንደጻፈባቸው ገልጸዋል፡፡
ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ባሻገር በሕዝብ ክንፍ አደረጃጀት የተዋቀረውን አካል፣ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ ማፈኛ እንዳይሆን ብለን ሥጋታችንን አቅርበን ነበር፤›› በማለትም በአሁኑ ወቅት የከባድ ጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶችን የሚወክለውን አካል አናውቀወም በማለትም ከረር ያሉ ቅሬታዎችን አሰምተዋል፡፡ ይልቁንም እነዚህ ጥያቄዎች መነሳት ከጀመሩ ከዓመት በላይ ቢያስቆጥሩም ትራንስፖርት ሚኒስቴርም ምላሽ ሊሰጥበት አለመቻሉንም አስታውሰዋል፡፡
ለእነዚህ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም፣ ባለንብረቶቹ ላነሷቸው ቅሬታዎች መነሻ ያደረጉት አብዛኞቹን በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያሉትን ተዋናዮች ከዩኒቨርሲቲ ከወጡበትና ዘርፉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚያውቋቸው በማስቀደም ነበር፡፡ ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት መስክ ኦፕሬተሮች በማኅበር እንዲደራጁ የተደረገበት አግባብ አብዛኞቹ ባለሀብቶች ያሏቸው ተሽከርካሪዎች ብዛት እጅግ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ አብራርተው ይህም ሆኖ፣ ‹‹ማኅበራትን አደራጁ ተብለን የሕግ ሥልጣን ተሰጥቶናል፡፡ የማኅበራት ማኅበር አደራጁ ግን አልተባልንም፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ከኮሜሳ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያና አንጎላ ዩኒየን የላቸውም የተባለውንም ‹‹ውሸት ነው›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹አንድ መቶ አባላትን መምራት ያቃተው ማኅበር 12 ሺሕ አባላትን እመራለሁ ማለቱም አጠያያቂ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ እሳቸውም ሆኑ የሚመሩት ተቋም መብት እንዳልገደቡ፣ አምባገነንም እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹80 ማኅበራትን አዘርፈዋል የተባለው ያሳዝናል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ባለሥልጣኑ የንግድ እንቅስቃሴን ማዕከል ያደረገ ኮሪደር ተኮር ሪፎርም በማካሄድ ከዚህ ቀደም አይሱዙም ሆነ ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎች በአንድነት የተደራጁበትን አግባብ በመለወጥ፣ ወደ አክሲዮን ኩባንያነት እንዲያድጉ የተደረገ ለውጥ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ለለውጥ ብለን ያደረግነው ነው፡፡ ከመርከብ ኮንትራት የሚወስድ ትራንስፖርተር ነው የፈጠርነው፡፡ የተዘረፈ ንብረት ካለ በሕግ እንጠይቃለን፤›› በማለት ማኅበራቱ ወደ አክሲዮን ኩባንያነት ሲለወጡ፣ በአግባቡ ንብረት ሳያስረክብ የሄደው አመራር ተጠያቂ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብ ክንፍ በሚለው አደረጃጀት አናውቃቸውም ተብለው ወቀሳ ስለቀረበባቸው አካላትም ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ የመጀመሪያውን የሕዝብ ክንፍ ምርጫ ሒደትን ራሳቸው እንደመሩት ገልጸው፣ ዓምና በተደረገ ምርጫ የነበሩት አመራሮች ይቀጥሉ በመባላቸው እንዲቀጥሉ እንደተደረገ አቶ ካሳሁን ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡
ስብሰባውን የመሩት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ባለንብረቶቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ከዚህ ቀደምም በቢሮ እንደተነጋገሩባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገ ስብሰባ፣ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተነስቶ ምላሽ እንደሰጡበት አስታውሰዋል፡፡
‹‹ድምፃችሁን ማሰማታችሁ ተገቢ ነው፡፡ ዩኒየን ለመመሥረት ያነሳችሁት ጥያቄ ከደረቅ ጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ አኳያ አጥንተን ምላሽ እንሰጥበታለን፡፡ ተደማምጠን እንቀጥላለን፡፡ ላልተገባ ንትርክ እንዳይዳርገን ረጋ ብላችሁ ብናየው ጥሩ ነው፡፡ ትልልቆች፣ አባቶች ናችሁ፡፡ እናዳምጣችኋለን፡፡ ስሜት የተቀላቀለበት አካሄድ ውስጥ አትግቡ፤›› በማለት ባለንብረቶቹን ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡ ይሁንና ዘርፉ በሞኖፖል እንዳይያዝ መንግሥት ሥጋት እንዳለውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
እንዲህ ያሉ ስሞታዎችን ያስተናገደው ስብሰባ፣ በጂቡቲ ወደብ የመጫኛ ማሽኖች እየተባለሹ መኪኖች ጭነት ይዘው መውጣት መቸገራቸውንም ያሳየ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በሁለት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ወደ አገሪቱ መግባት የሚጠበቅበት የማዳበሪያ መጠን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጓጉዞ አገር ውስጥ በመግባት ከክረምቱ በፊት ለገበሬው መዳረስ ስለመቻሉ ያሠጋቸው ትራንስፖርት አቅራቢዎች ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከሚገባው አንድ ሚሊዮን ቶን ገደማ ማዳበሪያ ውስጥ ከ200 ሺሕ ቶን ያላነሰው በፖርት ሱዳን ወደብ በኩል እንደሚገባ ሲጠበቅ፣ ከ50 ሺሕ ቶን ያላነሰው እስካሁን መግባቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በአቪዬሽን መስክ ሲያገለግሉ ቆይተው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ የበረራ መስመሮችን በማስተናበር ዘርፍ ለመሥራት ፈቃድ ጠይቀው ምላሽ ማጣታቸውን የገለጹ የዜብራ አቪዬሽን ድርጅት መሥራቾች ቅሬታቸውን ካቀረደቡት መካከል ይገኙበታል፡፡ ሆኖም የፖሊሲ ጥያቄ ስላስነሳ ያቀረቡት የሥራ ዘርፍ ፈቃድ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገልጾላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የአዳዲስ ኤርፖርቶች ግንባታ ሲካሄድ እንዲያውቅ ባለመደረጉ የአየር ንብረት መረጃዎችን በተገቢው መንገድ ለማቅረብ እንደተቸገረ አስታውቋል፡፡ የአቪዬሽን ሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታፈሰ ረጋሳ እንደገለጹት በነቀምቴ፣ በሽሬ እንዲሁም በደምቢዶሎ የተገነቡት ኤርፖርቶችን በሚመለከት ለኤጀንሲው ፈተና የሆነበት ጉዳይ ኤርፖርቶቹ ከተገነቡ በኋላ መጥታችሁ አገልግሎት ስጡ መባሉ ነው፡፡ ‹‹በሰመራ፣ በሮቤ እንዲሁም በጂንካ አገልግሎት ለመስጠት ስንሄድ ማስፋፊያ ስለሚደረግባቸው እየተባልን ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡ አብራሪዎች ከመብረራቸው በፊት የአየር ሁኔታ መረጃዎችን የግድ ማግኘት እንዳለባቸው ቢታወቅም፣ እነዚህ መረጃዎች በአግባቡ ተሟልተው እንዲቀርባለቸው እየተደረገ አይደለም ሲሉ በተለይ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን ወቅሰዋል፡፡ ‹‹አብረን በቅንጅት ልንሠራ ይገባል፣ የቅንጅት አሠራር የለንም፤›› ሲሉም አቶ ታፈሰ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኤርፖርቶች ድርጅት በበኩሉ የቀረቡበት ወቀሳዎች የራሱ የኤጀንሲው ኃላፊነት ነው በማለት ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት፣ በተለይ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ከሲቪል አቪዬሽን ተገንጥሎ ከወጣ በኋላ እስካሁን ያልተመለሱ ጉዳዮች አሉ በማለት በደፈናው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በክልሎች ስለሚገነቡ ኤርፖርቶች ማሳወቅ አለብን ወይ የሚለው መታየት አለበት፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ይሁንና ሁሌም ዕቅዶቹን እንደሚያሳውቅ ገልጸው አብረን በቅንጅት እንሥራ መባሉንም እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ያነሳውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ አቶ አህመድ ሺዴና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አብዲሳ ያደታ ምላሽ ሲሰጡ ተባብራችሁ ሥሩ በማለት አሳስበዋል፡፡ እንዲያውም አቶ አብዲሳ ከእንግዲህ ወዲህ የተጠያቂነት ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር አስጠንቅቀው፣ ኤጀንሲው ተቸገርኩበት ያለውን ጉዳይ በመደገፍ ኤርፖርቶች ድርጅትን ወርፈዋል፡፡