Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢሠማኮ የሠራተኞች የመደራጀት መብት በአሠሪዎች እየተደፈጠጠ ነው አለ

ኢሠማኮ የሠራተኞች የመደራጀት መብት በአሠሪዎች እየተደፈጠጠ ነው አለ

ቀን:

የዓለም የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ42ኛ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደግሞ  ለ128ኛ ጊዜ ሲከበር፣ የሠራተኞች የመደራጀት መብት በአሠሪዎች እየተደፈጠጠ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ሰኞ ሚያዝያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሲከበር በሥፍራው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አሠሪዎች የሠራተኛውን በነፃነት የመደራጀት ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት ከመደፍጠጣቸውም በላይ የአሠሪው በጎ ፈቃድ ታክሎበት የሚፈጸም ጉዳይ አድርጎ መውሰድ የተለመደ ነው፡፡  

ኢሠማኮ ከሁለት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሠራተኞችን የማደራጀት ዘመቻ እንዲገባ የተገደደው፣ በአንዳንድ የግል ባለሀብቶች ሠራተኛው በማኅበራት የመደራጀት መብት ላይ የሚፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት እየተባባሰ በመምጣቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ኃላፊዎች ድረስ ያጋጠመው እንቢተኝነት ትልቁ ፈተና ነበር፤›› በማለት አቶ አያሌው ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሰው ጉልበት ምንነትን በተመለከተ በማያሻማ ቋንቋ ተቀምጦ ሳለ፣ ደላሎች ሠራተኞችን እየቀጠሩ ለተለያዩ ኩባንያዎች በማከራየት የዜጎችን ጉልበት ክፉኛ እየበዘበዙ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ከልብ እንደሚደግፉ በመጠቆም፣ የኦሮሚያ ክልል በሠራተኞች ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ አድንቀዋል፡፡ 

አቶ አያሌው፣ ‹‹በዛሬው ዕለት የሠራተኞችን ቀን ስናከብር መንግሥትን ብዙ የምንጠይቃቸው ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሠራተኛው በወር በሚያገኘው ደመወዝ በየቀኑ እየጨመረ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም ስላልቻለ፣ የመንግሥት የልማትና የግል ድርጅቶች ወቅቱን ያገናዘበ የደመወዝ ጭማሪ እንዲያደርጉ መንግሥት ውሳኔ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሠራተኞችን በነፃነት የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብትና በአዋጅ የተደነገጉ ሕጎችን እንዲያስከብሩ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ፖሊሲ ያወጣ ቢሆንም፣ በሥራ ላይ በሚደርሰው አደጋ ምክንያት በሠራተኛው ላይ የአካል ጉዳት ከመድረሱም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሌሎች ችግሮች እየተዳረገ መሆኑን ያብራሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የሠራተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ የሠራተኞች የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ጥበቃ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ሕግ በሚጥሱ አካላት ላይ አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በዜጎች ጉልበት የሚነግዱበትን የባርነት ሥርዓት የሚፈቅዱ አዋጆችና ደንቦች እንዲሻሩ መንግሥትን ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥት ወደ ግል የሚዛወሩ የልማት ተቋማትን ለሚገዙ ባለሀብቶች ግልጽ የብቃት መመዘኛ መሥፈርቶች እንዲቀመጡና ጥብቅ የሆነ የፕራይቬታይዜሽን ክትትል እየተደረገባቸው፣ የሠራተኞን የሥራ ዋስትና ማክበር አለባቸው፤›› በማለት አቶ አያሌው አቶ አያሌው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

አቶ አያሌው አክለውም፣ ‹‹መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች አገራችን እንዲመጡና ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ብዙ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር፣ በኢትዮጵያውያን ሊሸፈኑ በማይችሉ የሥራ መስኮች ላይ ከውጭ ቀጥረው እንዲያመጡና ለአገራችን ሠራተኞች የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ብቃት ያለው ሠራተኛ ሲገኝ እንዲመለሱ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ባለሙያዎች በቀላሉ ሊሸፈኑ የሚችሉ የሥራ መደቦች በውጭ ዜጎች ተይዘዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሊሸፍኑት በሚችሉት የሥራ መደብ ላይ የውጭ ዜጋ መቅጠር አግባብ ስላልሆነ መቆም አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በዕለቱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ፣ ሠራተኛው በተደራጀ መንገድ መብቱን ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ትግል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሠራተኛው ተደራጅቶ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራትን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ለሚያደርገው እንቅስቃሴና መብቱን ለማስከበር ለሚያደርገው ትግል መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ ይቀጥላል በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት በተደራጀ ሠራተኛ ይረጋገጣል›› በሚል መሪ ቃል በዓሉ የተከበረ ሲሆን በዕለቱም፣ ‹‹የሠራተኛው የመደራጀት መብትና መልካም አስተዳደር አይነጣጠሉም››፣ ‹‹የሠራተኛው በነፃ የመደራጀት መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ዕድገት››፣ ‹‹‹ሜይዴይ ለዘለዓለም ትኑር››፣ ‹‹የተደራጀ የሠራተኛው ተሳትፎ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን›› የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

የዓለም የሥራ ድርጅት ባልደረባና የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የሶማሊያ የጂቡቲና የደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ጆርጅ ኦኮቶ፣ ‹‹በአፍሪካ በአሠሪና በሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ ያልደረሰና በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የተውጣጡ ሠራተኞች የታደሙ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡

አንድ አስተያየት ሰጪ ግለሰብ፣ ‹‹አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ አካባቢ ያለው ችግር ከባድ ነው፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀቴ ጉልበት ያለቀው በእነሱ ቤት ሲሆን፣ ደመወዜን እስከ ዛሬ ድረስ አላውቀውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሠሪዎች እያሠሩን ያሉት በባርነት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሌላው ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ጥልቅ ተሃድሶ እያለ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ቢሆንም አሁንም ችግሩ እየባሰና እየገነነ ነው የመጣው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኛው እጅና ጓንት በመሆን እዚህ መድረክ ላይ ከመጮህ በዘለለ በሠራተኛው ላይ ጠብ የሚል ለውጥ አልመጣም፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሠራተኛው ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም መንግሥት ትኩረት እንዳልሰጠው አማረዋል፡፡

ሌላ ግለሰብም፣ ‹‹የሥራ ላይ ደኅንነት በአገራችን ትኩረት አልተሰጠውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በእዚህም የተነሳ በየጊዜው ከሕንፃዎች ላይና በሌሎች አደጋዎች ሕይወታቸው የሚያልፈው ሠራተኞች ቁጥር እየበዛ መጥቷል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለዚህ ክፍተት ደግሞ መንግሥት ለሠራተኛው ያለው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡  

የዕለቱ ዝግጅት የተቋጨው በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አበባ እሸቴ ንግግር ሲሆን፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለሠራተኛው ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ አዳዲስ ፖሊሲዎች እያወጣና ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን እየተፈተሸ ነው፤›› ብለዋል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...