Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩዋንዳ ጉብኝታቸው ከቱሪዝም እስከ ወንጀለኛ ልውውጥ የሚካትቱ 11 ስምምነቶችን ፈርመው ተመለሱ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የዓለም ባንክ የንግድ አሠራር መለኪዎችን ለማሻሻል ሩዋንዳ ሞዴል ተደርጋለች

ካቻምና በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ለመዘከር የሩዋንዳ መንግሥት በመሠረተው ፋውንዴሽን ሲምፖዚየም ላይ ለመታደም ቢሆንም ከሰሞኑ ግን በ11 መስኮች ላይ የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ለመፈራረም ነበር ወደ ኪጋሊ ያቀኑት፡፡

ከሩዋንዳ መንግሥት የመረጃ አውታሮች ለሪፖርተር በተላከው ኮሚዩኒኬ መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ባደረጓቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችና ከፈረሟቸው የመግባቢያ ሰነዶች መካከል በሁለቱ አገሮች መካከል በባህልና በቱሪዝም መስክ የተደረጉትን ጨምሮ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት፣ የማረሚያ ቤቶች አያያዝ አስተዳደር፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የሚደረጉ የሕግ ድጋፍ ልውውጦች፣ በመረጃና ተግባቦት መስክ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን መስክ፣ በወጣቶችና በስፖርት እንዲሁም በጤና ዙሪያ የተደረጉት የመግባቢያና የሁለትዮሽ ስምምነቶች ጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሕፃናትና ሴቶች መስክ የሁለትዮሽ ትብብር በመመሥረት አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

ከሚያዝያ 19 ቀን እስከ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በዘለቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሩዋንዳ ጉብኝት ወቅት አንዱ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው የገለጹበት መስክ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ በተለይ በንግድ አሠራር ሒደት የሚታዩ እንቅፋቶችን በመቀነስ፣ የዓለም ባንክ በየዓመቱ በሚያወጣው ለንግድና ኢንቨስትመንት ቀልጣፋ አሠራርን በሚለካው ‹‹ኤዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራም መተግር መጀመሯን አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የንግድ አሠራር ሪፎርም ሩዋንዳን ተምሳሌት እንደምታደርግም አስውቀዋል፡፡ በአፍሪካ እያስመዘገበች ከምትገኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ባላት ምቹነት ሩዋንዳ በዓለም ባንክ መለኪያ ጥሩ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ የሩዋንዳን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መስህ እንዲኖራት ለማድረግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሪፎርም ሥራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ሩዋንዳን ውጤታማ ካደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመማር መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መካተቻ ወቅት የተጀመረው የሪፎርም ፕሮግራም፣ የዓለም ባንክን ዓመታዊ ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካይነት መተግበር የጀመረውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የዓለም ባንክ በዋና ዋና መመዘኛ መሥፈርትነት የሚጠቅሳቸው የሚከተሉት አሥር መለኪያዎች ናቸው፡፡ የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች፣ የግንባታ ፈቃድ በቀላሉ ለማግኘት መቻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት፣ ንብረት ማስመዝገብ፣ ብድር በቀላሉ ማግኘት መቻል፣ ለአነስተኛ ኢንቨስተሮች ከለላ መስጠት፣ ታክስ መክፈል፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማካሄድ፣ የውል ስምምነቶችን መተግበር እንዲሁም የኪሳራ እወጃን ያለ ውጣ ውረድ መፍታት የሚሉት ዋና ዋና መለኪያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ 190 ያህል አገሮች በማካተት ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡

ሪፖርቱ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትና ተቀባይነትን ያተረፈ፣ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችም ለእንቅስቃሴያቸው መመዘኛ ከሚያደርጓቸው ነጥቦች መካከል አንዱ በማድረግ የሚጠቅሱት ይኼንኑ የዓለም ባንክ ሪፖርት ነው፡፡ የዚህ ዓመቱን የአገሮችን ደረጃ ይፋ ያደረገው የባንኩ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በ159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮችም 31ኛዋ ሆናለች ያለው የዓለም ባንክ፣ አገሪቱ ከወትሮው ይልቅ 12 ነጥቦችን ወደ ታች በማሽቆልቆል ይብሱን ወደታች እንደወረደች አስፍሯል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ በኢንቨስትመንት መስህብነት ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር ካሻት ከታች እስከ ላይ መሠረታዊ የለውጥ ሪፎርሞችን መተግበር እንደሚጠበቅባት አሳስቧል፡፡ ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ይልቅ ለየት ባለ አደረጃጀትና የአመራር ኃይል መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ፣ የተመቻቸ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዱትን የዓለም ባንክ መመዘኛዎችን በጥሩ ውጤት መተግበር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ መንቀሳቀስ የጀመረው ኮሚሽኑ በአራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከዓለም 50 አገሮች ምርጧ አገር እንድትሆን የሚያስችል ‹‹ራዕይ 2020›› የተባለ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ይኼ እንዲሳካም በየአመቱ የ40 ከመቶ ለውጥ ማስመዝገብን መሠረት ያደረገ ውጤት እንዲመዘገብና የአገሪቱ አጠቃላይ ውጤትም አሁን ካለበት 159ኛ ወደ 34ኛ እንዲመጣ ማቀዱን ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ትልልቅ ለውጦችን ለማስመዝገብ ምሳሌ እንደምትሆን የተጠቀሰችው ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ይልቅ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ትገኛለች፡፡ እንዲህ ያሉ ልውውጦችን በሁለቱ አገሮች መካከል ለማካሄድ በመንግሥታቱ መካከል የተቋቋመ ቋሚ የጋራ ኮሚሽን ተሰይሟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች