Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጓሮ ሠራሽ ሳሙናዎች

ከዓመታት በፊት ቀልድ እንደሚያውቅ የሚነገርለት ኮሜዲያን፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሚተላለፉ ማስታወቂያዎች አብዛኛውየፈሳሽና የዱቄትሳሙና ምርት ቢሆንበት ጊዜ ‹‹አሁንስ ቴሌቪዥናችን ሳፋ እየመሰለኝ ነው››በማለትመቀለዱ ትዝ ይለኛል፡፡

በእርግጥም በዚያን ወቅት የሳሙናና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች መብዛት ብዙዎቻችንን ሳያስገርመን አይቀርም፡፡ ከሌሎች ማስታወቂያ ከሚያስነግሩ የንግድ ድርጅቶች ይልቅ የሳሙና አስመጪዎች ማስታወቂያ እንዲያ የመብዛቱ ምስጢር እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡

አሁን ደግሞ የጠፉ እስኪመስሉ ድረስ ቀንሰዋል፡፡ ቀድሞ እንደዚያ የበዙት፣ አሁን የቀነሱት በምን ምክንያት ነው ብለን ለመግለጽና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በቂ መረጃ ያስፈልገን ይሆናል፡፡

የማስታወቂያው ዘዴ ይለያይ እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በየመንደሩ የሚመረቱ የፈሳሽ ሳሙና ምርቶችን የሚገልጹ የጽሑፍ ማስታወቂያዎች በሽ ሆነዋል፡፡ በገበያው በሰፊው እየታዩ ያሉት ጓዳ ሠራሽ ፈሳሽ ሳሙናዎችን ለመሸጥ በየጎዳናው ከምናያቸው ማስታወቂያዎች ባሻገር፣ አገልግሎት በሰጡ የፕላስቲክ ውኃ ማሸጊያዎች ተሞልተው፣ በተለያዩ ቀለማት አሸብርቀው የሚወጡ ምርቶችም እየታዩ ነው፡፡ ወደየትኛውም የከተማው ክፍል ቢጓዙ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ለገበያው የሚቀርቡ ፈሳሽ ሳሙናዎች ደግሞ በፋብሪካ የተመረቱ እንዳልሆኑ ሻጮቹ ራሳቸው ይናገራሉ፡፡ በፋብሪካ ተመርቶ ከሚቀርበው ባነሰ ዋጋ መሸጣቸው ደግሞ ምርቶቹን የሚገዛቸው ሸማች ቁጥር እንዲበዛላቸው አድርጓል፡፡ ምርቱን የሚያቀርቡ፣ የሚያመርቱና የሚቸረችሩት ሁሉ ከባድ ፉክክር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡

እንደውም በየቤቱ ጓሮ እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበውን ፈሳሽ ሳሙና ለመሸጥ ብቻ በማሰብ መደብሮችን የሚከራዩ መብዛታቸው፣ ቢዝነሱ አዋጭ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ሳይታሰብ የተስፋፋው የፈሳሽ ሳሙና ገበያ፣ እዚህም እዚያም ሊበራከት የቻለው ተጠቃሚዎቻቸው እየጨመሩ ከመሄዳቸው ጋር ነው፡፡

ገበያ ባይኖረው ቤት ተከራይተው በማከፋፈል ተግባር ላይ የተሠማሩ ግለሰቦች ባልተበራከቱም ነበር፡፡ እንደ ገበያው ሁሉ ፈሳሽ ሳሙና ለመሥራት ወይም ለማምረት እንበለው ሥልጠና እንሰጣለን የሚሉትም ቁጥራቸው መጨመሩን እንታዘባለን፡፡ ለዚህም በየቦታው የተለጠፉና የተንጠለጠሉ የፈሳሽ ሳሙና የሥልጠና ማስታወቂያዎች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ፈሳሽ ሳሙና የሚያመርቱ ግለሰቦች ቢዝነሱ ውስጥ የገቡት ከዚሁ ሥልጠና በመነሳት ነው፡፡ ለአሠልጣኞቹ ድርጅቶች ማን ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ባይታወቅም፣ ገበያው የደራላቸው ይመስላል፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ማስነገር ነው፡፡

በነገራችን ላይ እንዲህ ያለው የሥራ ፈጠራ የሚበረታታ ስለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ብዙዎች በዚህ ይስማማሉ ብዬ ገምታለሁ፡፡ ችግሩ ግን ምርቱ በትክክል እየተመረተ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይቻላል ወይ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡ የሕጋዊነቱ ጉዳዩም ብዙ ያስብላል፡፡ እንዲህ ያሉ ምርቶች በጥንቃቄ ካልተመረቱ ለጤና ጠንቅ መሆናቸው ስለማይቀር ማነው የሚቆጣጠራቸው? ገበያውን የሞላው ምርት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት፣ የአካባ ብክለት ወይም የጥራት ደረጃየሚቆጣጠረውስ ማነው? ጉዳት ቢያደርሱስ ተጠያቂው ማን ነው? አሠልጣኞቹስ በትክክል ሥልጣናቸውን እየሰጡ ነው ወይ? ፈቃድስ ማን ሰጣቸው? የሚሉና ሌሎችምደርዘን ጥያቄዎች መልስ ያሻቸዋል፡፡

እንደ የሥራ ፈጠራ ልናየው ብንፈልግ እንኳጓሮ ሠራሹ የፈሳሽ ሳሙና ተመርቶ ለገበያ እየቀረበበት ያለው መንገድ አደገኛ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ የሰፋ ሰፊ ነው፡፡

በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻዎች ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ የሌላቸው፣ ለዚህ ተብሎ የተከለለ ቦታ ያልተሰጣቸው፣ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚሠሩ በመሆናቸው ለነዋሪዎች ሥጋት መሆናቸው አይቀርም፡፡ አደጋ ቢያስከትሉስ? የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎቻቸው ኬሚካል ስለሆኑ በየጓሮው መሥራቸው ለጤና ጎጂ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ደረጃም አልወጣላቸውም፡፡ ማረጋገጫ የላቸውም፡፡ የኬሚካል አወጋገዳቸውም ቢሆን ጥንቃቄ የለውም፡፡

ስለዚህ የሥራ ፈጠራው እንደተጠበቀ ሆኖ፣አምራቾቹ በአንድ ተሰባስበው የሚሠሩበት መንገድ ቢፈለግ አደጋውን መቀነስ ያችላል፡፡ ሥራውን እንደመተዳደሪያ የያዙ ወገኖቻችንም የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በትክክለኛው ቀመር ስለማምረታቸውም መቆጣጠር የሚቻለው በፈቃድ ሲሠሩ ነው፡፡ በፈቃድ ሲሠራ ለመቆጣጠር ያመቻል፡፡ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከተሠራ ሸማቾችም ያለሥጋት እንዲገዙ፣ ልበ ሙሉ ስለሚደርጋቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ መሥመር ያበጁለት ዘንድ ይመከራሉ፡፡ ችላ ከተባለ ግን ነገ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል እንደማይሆን ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት