Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ንግድ ምክር ቤት እንደ አዲስ ተመሠረተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ምርጫ ቀን ተቆርጦለታል

ከስምንት ወራት በላይ ሲያወዛግብ ከመቆየቱም ባሻገር ለአገር አቀፉ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ መዘግየት ምክንያት እንደሆነ ሲጠቀስ የቆየው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፈርሶ እንደ አዲስ ተመሠረተ፡፡ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዲስ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ተመርጠዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱን የቀድሞ አመራሮች ታግደገው፣ የዕውቅና ሠርተፊኬቱም ተሰርዞ መቆየቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም እንደ አዲስ ምክር ቤቱን ለመመሥረት በተጠራው መሥራች ጉባዔ ወቅት በተደረገ የቦርድ አባላት ምርጫ፣ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ አዘዘው (ኢንጂነር)፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅራት ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ አቶ መላኩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት 118 ድምፅ በማግኘት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው በዚሁ መሥራች ጉባዔ ወቅት በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ በአብላጫ ድምፅ የተመረጡት ከደሴ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተወከሉት አቶ እንግዳወርቅ ኪዳኔ ናቸው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ በጉባዔተኛው የተመረጡት አዳዲሶቹ የቦርድ አባላት ወ/ሮ ተምኔት ሰለሞን (ከደቡብ ጎንደር)፣ አቶ ሰለሞን ተስፋሁን (ከሰሜን ጎንደር)፣ አቶ አማረ ገብረ ዮሐንስ (ከሰሜን ሸዋ)፣ ወ/ሮ አስረበብ አሰፋ (ከደቡብ ወሎ)፣ አቶ አበበ ደርሰህ (ከጎንደር ከተማ)፤ አቶ ኢስማኤል አሊ (ከደሴ ከተማ)፣ አቶ አዋይ አበራ (ከሰሜን ወሎ)፣ አቶ አማረ ሰለሞን (ከዘርፍ ምክር ቤት) አቶ ያረጋል አይቼው (ከምሥራቅ ጎጃም) እንደተወከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ምርጫ ሒደት ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ 12 አባላትን ካካተው ቦርድ ውስጥ፣ የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቦርዱ ውስጥ የሚወክለውን ወኪል አባል እንዳላስመረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሥራች ጉባዔው ወቅት ከቀድሞው የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች መካከል አቶ ጌታቸው አየነውና (የቀድሞ ፕሬዚዳንት) እና ሌላ የቦርድ አባል የድምፅ ተሳትፎ ሳይኖራቸው በአስረጅነት እንደቀረቡም ታውቋል፡፡

ለወራት ከዘለቀው ውዝግብ እንዲሁም በሚያዝያ 20 ቀን እስከተካሄው ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ የነበሩት ሒደቶች ምን ይመስሉ እንደነበር የሚያመላክት ሪፖርት በአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በኩል ቀርቧል፡፡ በተሰናባቹ ቦርድ ላይ የነበሩትን ቅሬታዎች በተመለከተ፣ አቤቱታውን ማን እንዳቀረበው፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ከክልሉ ባሻገር ለፌዴራል መንግሥት ጭምር አቤት ማለታቸውን አቶ ተዋቸው በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ ለሕግ መከበር የሚታገል አካል መኖሩ በመልካም ጎኑ በተጠቀሰው ሪፖርት ተመልክቶ ጉዳዩን እንዲፈታና እልባት እንዲሰጥበት የተመረጠው ቦርድ፣ ከሳሾችና ከባህር ዳር ነጋዴዎች ጋር ውይይት ተጠርቶ ከሳሾቹ አለመገኘታቸው አግባብ እንዳልነበር ተጠቅሷል፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ስላለው ችግር የሕግ ባለሙያ ምክር እንደሚጠየቅበት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡ የቀድሞው ቦርድ ላይ ከቀረቡት አምስት አቤቱታዎች በአንደኛው ብቻ የሕግ ክፍተት መገኘቱን፣ ይህንንም የቢሮው የሕግ አማካሪና የክልሉ ፕሬዚዳንት የሕግ አማካሪ በማረጋገጣቸው መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ጉባዔ የሕግ ጥሰት እንዳለበት መረጋገጡን ሪፖርት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ተሽሮ ዳግመኛ ምርጫ እንዲደረግ ቢሮው መወሰኑንም አስረድተዋል፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ጥሪውን ማስተላለፍ ያለበት ማን ነው ተብሎ ቢሮው በቀረበበት ጥያቄ የድሮው ቦርድ እንደገና ተሰብስቦ መጥራት ይችላል ተብሎ በደብዳቤ ተገልጾላቸው እንደበር በዕለቱ ከቀረበው ሪፖርት መገንዘብ ተችሏል፡፡

ቢሮው በዚህ መንገድ ያደረገው ጣልቃገብነት የክልሉን ንግድ ምክር ቤት ያግዛል ብሎ ቢያምንም፣ የወቅቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው፣ የቦርድ አባላቱን በመጥራት ፈንታ አዲሱን ቦርድ ጠርተው በማወያየት፣ ለመጋቢት 20 ቀን 2009 የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማስተላለፋቸው ስህተት ነበር ተብሏል፡፡

የጠቅላላ ጉባዔው ጥሪ ደብዳቤ ከተላለፈ በኋላ የደብዳቤው ይዘት ችግር እንዳለበት ከአባል ምክር ቤቶች በስልክ እንደደርሳቸው፣ ለቢሮው የተጻፈለት ደብዳቤና ለአባል ምክር ቤቶች የተጻፈላቸው ደብዳቤ የይዘት ልዩነት እንዳለበት መረጋገጡንም በሪፖርታቸው አካትተዋል፡፡ ‹‹አንድን ግለሰብ ለማግለል በማሰብ የተጻፈ ነው፤›› ያሉት የቢሮው ኃላፊ፣ ተሰናባቹ ፕሬዘዳንት የቀድሞውን ቦርድ ሳያሰባስቡ በአዲሱ ቦርድ በኩል ጥሪው እንደተላለፈ በማረጋገጡ ቢሮው ወደ ዕርምጃ ሊገባ መቻሉን ለጠቅላላ ጉባዔው አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በዕለቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ለምን መሥራች ጉባዔ ይባላል የሚለው ነጥብ እንደነበር ታውቋል፡፡ በመሆኑም መሥራች ጉባዔ ለምን እንደተባለ በዕለቱ የተገኙት የቢሮ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡

የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና የገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው፣ መሥራች ጉባዔ ከሚባል ይልቅ አስቸኳይ ጉባዔ ተብሎ እንዲጠራና ምርጫው በዚሁ አግባብ እንዲካሄድ የቢሮው ፍላጎት እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ የቀድሞው የንግድ ምክር ቤቱ አመራር በቢሮው የተላለፈውን ውሳኔ ያለመቀበልና ያለማክበር ብሎም በተዛባ ደብዳቤ ጥሪ በማስተላለፉ ምክንያት፣ ቢሮው ሳይፈልግ መሥራች ጉባዔ ተብሎ እንዲጠራ አስገድቶታል ብለዋል፡፡ ‹‹በእኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫ በመዘግየቱ አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት ስለነበረብን የተወሰደ ዕርምጃ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ይህ ሁሉ በውይይት ወቅት ከተደመጠ በኋላ በቢሮው የቀረበው ሪፖርት፣ በማጠቃለያው በ14 ተቃውሞ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ እንደፀደቀ የሪፖርተር መረጃ ያስረዳል፡፡

የምርጫውን ሒደት ለመከታተል በቦታው የተገኙት የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ማብራሪያ እንደሰጡበት ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት ምርጫ መጓተት ምክንያት ሆኖ የቆየውና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዕገዳ የተጣለበት የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ ምርጫ እንዲያካሂድ መወሰኑ ታውቋል፡፡

እንደ አማራ ንግድ ምክር ቤት ተሰናባች አመራሮች ሁሉ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት አመራሮችም ከሕግ ውጭ ምርጫ አካሂደዋል ተብለው የሚመሩት ቦርድ ዕግድ እንደወጣበት ይታወሳል፡፡ ያለአግባብ ከሁለት ምርጫ ዘመን በላይ በአመራርነት ቦታው ላይ ቆይተዋል ተብለው በአመራሮቹ ላይ በቀረበባቸው ክስ መሠረት፣ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. የተካሄው ምርጫ ተሽሮ በምትኩ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ በተወሰነው መሠረት ምርጫው ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ ቀጠሮ እንደተያዘለት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች