[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ውስጥ ሆነው ቴሌቪዥን እያዩ ሳሉ ጸሐፊያቸው ገባች]
- ለምን መጣሽ?
- ክቡር ሚኒስትር ሥጋት ገብቶኝ ነው፡፡
- የምን ሥጋት?
- የሚወራውን አልሰሙም እንዴ?
- አንቺ ንገሪኛ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፓላርማ የነበረውን ውይይት ማለቴ ነው፡፡
- ስለምን ጉዳይ?
- ሚኒስትሮች ካጠፉ ከሥልጣናቸው ይነሳሉ ስለተባለው ነዋ?
- አይ አንቺ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- የሚያጠፋማ መነሳቱ የት ይቀራል?
- አልሰሙም ማለት ነው?
- ምንድነው የምሰማው?
- በተደጋጋሚ የሚያጠፉ በፊት ዝም ይባሉ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁንም ይኖራሉ፡፡
- እርስዎስ?
- እኔን ማን ይነካኛል?
- ባለፈው ዓመት ፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ. . .
- እና?
- መታረም ያለባቸው ጉዳዮች ተነግረዎት ነበር እኮ?
- ስለዚህ?
- በተደጋጋሚ ተነግሮዎት ካላስተስተካከሉ ከኃላፊነት ይነሳሉ ብዬ ነው፡፡
- ማን ነው የነገረሽ?
- ዜና ላይ ነው የሰማሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላስ ምን ተባለ?
- ፓርላማው በሚኒስትሩ ላይ አመኔታ ካጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነሳው ማሳሰቢያ ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
- ተግባራዊ ሲደረግ ዓይቼ አላውቅም እባክሽ፡፡
- አሁን ግን ጥያቄው እየገፋ ሲመጣ ተግባራዊ መደረጉ አይቀርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዝም ብለሽ አትቃዢ፡፡
- ኧረ እየቃዠሁ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን እየሆንሽ ነው?
- ኧረ ሌላም ሰምቻለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሰማሽ?
- ሳቄ ነው የመጣው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አሳቀሽ?
- እርስዎም ቢሰሙት ሊስቁ ይችላሉ፡፡
- ምኑ ነው የሚያስቀኝ?
- የሚያኮርፉ ሚኒስትሮች አሉ ተብሏል፡፡
- ለምንድነው የሚያኮርፉት?
- አንዳንዶቹ በጥያቄ ሲፋጠጡ ዘመቻ ተከፈተብን ብለው ነው አሉ፡፡
- ሌሎቹስ እባክሽ?
- ሌሎቹማ. . .
- እህ?
- ለምን ተነካን እያሉ ያኮርፋሉ አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሃ. . . ሃ. . . ሃ. . .
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሰው እኮ ካልነኩት አያኮርፍም፡፡
- እርስዎ ግን በሆነው ባልሆነው ያኮርፉ የለ?
- እኔ?
- እኔ የፈራሁት. . .
- አንቺ የፈራሽው?
- ፓርላማ ላይ ስለርስዎ የተወራ ነው የመሰለኝ፡፡
- መናጢ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በቦርድ ሰብሳቢነት ከሚመሩት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጋር እየተነጋገሩ ነው]
- ለፓርላማ የሚቀርበው ሪፖርት ተዘጋጀ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንደ አምና እንዳንወቀስ ደግሞ፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ብዙ ጉድለቶች ሳይመዘዙብን አይቀርም፡፡
- ምን ማለትህ ነው?
- ያውቁ የለ ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑን ነው የማውቀው?
- የግዥ ሥርዓታችን መመሰቃቀሉን. . .
- እ. . .
- የጨረታ አወጣጣችንና አመራረጣችን ለሙስና መጋለጡ. . .
- እ. . .
- የፋይናንሳችን መዝረክረክ. . .
- እ. . .
- በሪፖርት አቀራረባችን ውሸት መብዛቱ. . .
- ይኼ ሁሉ ሲሆን አንተ የት የነበርክ?
- ድርጅቱን እኮ እኔ ሳልሆን እርስዎ ነው የሚመሩት፡፡
- እኔ እኮ የቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፡፡
- እኔ ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነኝ፡፡
- እናስ?
- እናማ አላሠራ እያሉኝ ነው፡፡
- እኔ?
- እኔ ነኝ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- ስለዚህ ሪፖርቱ ይህንን ሁሉ ይዟል እያልከኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ደስ እንዲልዎት ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ፓርላማ ስንሄድ ያው የሚያስረዱት እርስዎ ነዎት፡፡
- አንተ ደግሞ በጎደለ ትሞላለህ?
- ምናለበት በሌላውም በጎደለ ቢሞሉኝ?
- ለምሳሌ?
- ከጨረታ ከሚገኘው ኮሚሽን. . .
- ምን?
- ከግዥና ከመሳሰሉትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ምን እያልክ ነው?
- እኔም የድርሻዬን እያልኩ ነው፡፡
- ይኼ ያዋጣል?
- እርስዎስ ያዋጣዎታል?
- ምኑ ነው የሚያዋጣኝ?
- ፓርላማ ላይ ብንፋጠጥ ያዋጣዎታል?
- ለምንድነው የምንፋጠጠው?
- ጥያቄ እንደ ዶፍ ሲወርድ ነዋ፡፡
- የሚመለከትህን ትመልሳለህ ገባህ?
- ኧረ ምን በወጣኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እና ምን ልትሆን ነው?
- ዝም! ጭጭ! ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ደሜን አታፍላው እንግዲህ፡፡
- እንዲህ ሲሆኑ እኮ ደስ ይለኛል?
- ምን ስሆን?
- ሲያኮርፉ፡፡
- ይድፋህ!
[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው]
- ምነው መንገዱ ጭር አለ?
- ዛሬ እኮ በዓል ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የምን በዓል?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- እኔን ይጠይቁኛል እንዴ?
- አታናደኝ ንገረኝ፡፡
- ዛሬ እኮ ሜይ ዴይ ነው፡፡
- ነው እንዴ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይገርማል?
- ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ጊዜው እንዲህ መንጎዱ?
- የቱ ጊዜ ክቡር ሚኒስትር?
- የወጣትነታችን ነዋ፡፡
- ከሜይ ዴይ ጋር ምን አገናኘው ክቡር ሚኒስትር?
- የታገልነው እኮ ሠራተኛውን ከብዝበዛ ለማላቀቅ ነው፡፡
- ድንቄም. . .
- ምን አልክ አንተ?
- ገርሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ ነው የገረመህ?
- እናንተ ታገልን ብትሉም አሁንም ጉልበታችን ይበዘበዛል፡፡
- እንዴት እባክህ?
- ለምሳሌ እኔ ያለ አበልና ተጨማሪ ሰዓት ክፍያ በበዓል እየሠራሁ አይደል?
- እና ተጎዳሁ እያልክ ነው?
- የእኔ ለጊዜው ይቅርና. . .
- የማን ይወሳ ታዲያ?
- ታገልንለት የምትሉት ሠራተኛ ዛሬም አበሳ ውስጥ ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ግማሹ የሚለፋውን ያህል ሩቡን አያገኝም፡፡
- እሺ?
- ግማሹ የመደራጀት መብቱ ተገፏል፡፡
- እሺ?
- ሌላው በገዛ አገሩ በውጭ አሠሪዎች ይደበደባል፡፡
- ምን?
- ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት ጉልበት ጭምር ይበዘበዛል፡፡
- ሌላስ?
- የሥራ ቦታ ደኅንነት ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ለአደጋ የሚዳርጉ ሥራዎች ተገቢዎቹ አልባሳትና መጫሚያዎች የላቸውም፡፡
- ወይ ጉድ?
- ሌላም የባሰ አለ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- አካላዊ ጉዳትና ሞት በሽበሽ ነው፡፡
- ወቸ ጉድ?
- በዚህ ላይ ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ተገቢው ክፍያና ጥቅማ ጥቅም የላቸውም፡፡
- አንተ ይኼንን ሁሉ በምን አወቅክ?
- ከእናንተ ሪፖርት በተቃራኒ የሚወጡ መረጃዎችን እከታተላለሁ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- በቃ አይናደዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ብናደድ ምን አገባህ?
- ሲናደዱ ልጅ ይመስሉኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጅላ ጅል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ደርሰው ከባለቤታቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]
- ፓርላማ የማቀርበው ሪፖርት ስላለ እስኪ አብረን እንናበብ፡፡
- ይልቅ አንድ ዘዴ ልንገርህ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው እሱ?
- እኔ አንድ የፓርላማ ጥያቄ አቅራቢ አባል ልሁን፡፡
- ምን?
- ለአንተ ይጠቅምሃል፡፡
- ከዚያስ?
- አንተ ሪፖርት ታቀርባለህ፡፡
- እሺ?
- እኔ ማስታወሻ እይዛለሁ፡፡
- ከዚያስ?
- አንብበህ ስትጨርስ ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡
- ጥሩ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የተዘጋጀውን ሪፖርት አንብበው ከጨረሱ በኋላ ባለቤታቸው ጥያቄ ጀመሩ]
- ክቡር ሚኒስትር?
- አቤት?
- ይኼን ሪፖርት ካለፈው ዓመት የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?
- የህዳሴ ግድቡ 6ኛ ዓመት በተከበረ ማግሥት በመቅረቡ ልዩ ያደርገዋል፡፡
- አይቀልዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አጠፋሁ?
- የዘንድሮና የአምና ሪፖርት ይመሳሰላሉ ነው የተባሉት፡፡
- በእርግጥ. . .
- በእርግጥ ምን?
- ከአምና የተንከባለሉ. . .
- ምንድናቸው የሚንከባለሉት?
- ትልልቅ ስኬቶችና መጠነኛ ጉድለቶች፡፡
- ለምሳሌ በኦዲተር ጄኔራል የቀረበባችሁን 500 ሚሊዮን ብር የታለ ያወራረዳችሁት?
- በሒደት ላይ ነን፡፡
- ከመመርያ ውጪ ያለጨረታ የግንባታ ኮንትራት የሰጣችሁት ለምንድነው?
- እሱም በሒደት ላይ ነው፡፡
- ሒደት ምንድነው?
- ፕሮሰስ ማለት ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር 500 ሚሊዮን ብር ሒሳብ አላወራረዳችሁም፣ ያላግባብ የአንድ ቢሊዮን ብር የግንባታ ኮንትራት ሰጥታችኋል፣ የ600 ሚሊዮን ብር ግዥ ያላግባብ ተፈጽሟል. . .
- አለ አይደል?
- ቆይ! ቆይ!
- ምን?
- በሠራተኞች ቅጥር፣ ምደባ፣ ሹመት፣ ዝውውርና ጥቅማ ጥቅሞች ኢፍትሐዊነት በዝቷል፡፡
- እኛ እኮ?
- እናንተ ምን?
- አንቺ አሁንስ አበዛሺው [ተቆጡ]፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ ከእኔ ጋር ጣጣህን ብትጨርስ ይሻልሃል፡፡
- እሺ ቀጥይ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ልታዘዝ?
- ትዕዛዙ ይቆይና በመደበኛ ሥራ ውስጥ ለምን ጣልቃ ይገባሉ?
- የቦርድ ሰብሳቢ እኮ ነኝ፡፡
- ከቦርድ አባላት ጋር ይወስናሉ እንጂ ለምን ጣልቃ ይገባሉ?
- ማኔጅመንቱ ሲፈዝ ደስ ስለማይለኝ ነው፡፡
- ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ማገዝ ሲገባዎ እርስዎ እኮ እጁን ነው የሚጠመዝዙት?
- አንቺ ይኼ ፓርላማ ላይ ይነሳል ብለሽ ነው [ሥጋት ገባቸው]?
- መልስ ብዬሃለሁ መልስ፡፡
- ማኔጅመንቱ ሲልፈሰፈስ ምን ላድርግ ታዲያ?
- በቃ አስፈጻሚ ስትባሉ ጉልበት ብቻ ነው የሚታያችሁ?
- ጉልበት ከብልኃት ጋር ያዋጣል እኮ?
- የእርስዎ ደግሞ በዛ፡፡
- ምኑ ነው የበዛው?
- የፈለጉትን እያዘዙ ያስፈጽማሉ፣ ኮሚሽንዎትንም ይቀረጥፋሉ፡፡
- ማነ እኔ?
- እኔ ነኝ ታዲያ?
- አንቺ የእውነት አስመሰልሺው እኮ [ፈራ አሉ]?
- እንዳትክደኝ ብቻ?
- ምንድነው የምክድሽ?
- ሪፖርቱን በጥንቃቄ ለሚያየው እኮ በርካታ ሚሊዮን ብሮች መሰወራቸው ግራ አይገባውም፡፡
- አንቺም ጠረጠርሽኝ?
- ከመጠርጠር በላይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እኔንም የደበቅከኝ ብዙ ነገር አለ፡፡
- ይኼ ሁሉ ሪፖርቱ ውስጥ አለ ነው የምትይኝ?
- አንተ አላነበብከውም እንዴ?
- አንብቤዋለሁ፡፡
- በመስመሮቹ መካከል ያለውን ሐሳብ እንዴት መረዳት አቃተህ?
- የሚወሳሰብ ነገር ደስ ስለማይለኝ ነው፡፡
- እንግዲያው ተዘጋጅ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምኑ?
- ለፓርላማ ጥያቄ ጊዜ ነዋ፡፡
- ምን ይመጣል ብለሽ ነው?
- አንተ ሰውዬ የት አገር ነው ያለኸው?
- ምነው?
- የሚባለውን አልሰማህም እንዴ?
- ምን ተባለ?
- ሪፖርቱ ችግር ካለበት አደጋ አለ፡፡
- የምን አደጋ?
- ከሚኒስትርነት መሰናበት እስከ መታሰር፡፡
- ማን ነው ያለው?
- ደግሞ ይኼ ማስፈራራትህን ተው፡፡
- አንቺ ደግሞ አታናጂኝ፡፡
- ኧረ የሚያስፈራሩና የሚያኮርፉ ሚኒስትሮች አሉ እየተባለ ነው፡፡
- ይኼንን ነገር ማን ነው የሚያወራው?
- በአደባባይ ሲነገር አልሰማህም እንዴ?
- አሁንስ ደሜ ሊፈላ ነው፡፡
- ይልቅ በረድ ብትል ይሻልሃል፡፡
- እንዴት አድርጌ?
- ፓርላማ ቀርበህ እቆናጠራለሁ ብትል ዋ!
- በቃ ሳቅ በሳቅ እንድሆን አለማምጂኝ፡፡
- ምን ላድርግ?
- ኮርኩሪኝ!