Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የአላና ፖታሽ የማዕድን ማውጫንና ንብረቶቹን ተረከበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፖታሽ ማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት አላና ፖታሽ ከተባለው ኩባንያ ሙሉ አክሲዮኖችን በመግዛት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው የእሥራኤሉን አይሲኤል ኩባንያ፣ የፓታሽ ማምረቻ ይዞታውንና ንብረቱን መንግሥት ተረከበ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የእስራኤሉ ኩባንያ በአፋር ክልል ደንከል አካባቢ ለፖታሽ ማዕድን ማምረቻ የተከለው ንብረት፣ ከአላና ፓታሽ ተላልፎለት የነበረውን ይዞታና ሌሎችም ቁሳቁሶቹን መንግሥት ለመረከብ ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ ያጠናቀቀው ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

ርክክቡም አይሲኤል በኢትዮጵያ ሊያካሄድ የነበረውን ፖታሽ የማምረት ሥራ ማቋረጡን ካስታወቀ በኋላ የማምረቻ ቦታውን መንግሥት እንዲረከበው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡

ኩባንያው በኢትየጵያ የነበረውን ሥራ በማቋረጡና ሠራተኞችንም በማሰናበቱ ለፓታሽ ማዕድን ማምረቻው ሥራ የተዘጋጁ ንብረቶች እንዳይበላሹና እንዳይባክኑ ለማድረግ በቦታው ተገኝተው በመንግሥት ወገን ንብረቱን የተረከቡበት ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የተወከሉ ባለሙያዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ከንብረት ርክክቡ በኋላ ግን አይሲኤል የተሰጠው ፈቃድ ስለመሰረዙ የሚገልጽ ሠርተፍኬት ይሰጠኝ በማለት ጥያቄ ማቅረቡም ታውቋል፡፡ አይሲኤል ብዙ ተስፋ የተጣለትን የፓታሽ ማዕድን አምርቶ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ሲጠበቅበት የነበረውን ፕሮጀክት አቅርጦ የወጣው፣ የቀድሞው ባለይዞታ አላና ፓታሽ መክፈል የሚጠበቅበትን ታክስ ባለመክፈሉ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡ ያልታሰበውና መንግሥት ዕውቅና የነፈገው የሽያጭ ስምምነት በአላና ፖታሽና በአይሲኤል ኩባንያዎች መካከል ውለታ የደረገበው መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ውጭ በተፈጸመ ሲሆን፣ በወቅቱ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት የማዕድን ሚኒስቴር በሕጋዊ መንገድ የቀረበልኝ ጥያቄ የለም በማለት እንደማይቀበለው መግለጹ ይታወሳል፡፡ አላና ፓታሽ ግን የኩባንያውን አክስዮኖች ለአይሲኤል መሸጡን ይናገራል፡፡ ትክክለኛው አካሄድ ግን የአክሲዮን ሽያጩ ከመፈጸሙ በፊት ለፈቃድ ሰጪው አካል (በወቅቱ ለማዕድን ሚኒስቴር) ቀርቦ ሒደቱ ታውቆ፣ ማረጋገጫም ሊሰጥበት ይገባ እንደነበር መገለጹም ይታወሳል፡፡ የሽያጭ ዝውውሩ እንዲህ ያሉ አነጋጋሪ ጉዳዮች ቢታዩበትም፣ መንግሥት የእስራኤሉ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ፈቅዶለት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ሥራው እንዳይቋረጥም በአላና ፖታሽ ፈቃድ አንድ ዓመት ሙሉ ወደ ፖታሽ ማዕድም አምራችነት በመግባት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ቢሆንም በአላና ፖታሽ ያልተሠሩ ጥልቅ የምርመራ፣ የንፁህ ውኃ ቁፋሮና የአሰሳ ሥራዎችን ሲያካሄድ ስለመቆየቱ የሚጠቁሙ መረጃዎች ይደመጣሉ፡፡ በአንድ ዓመት ቆይታው ለእንዲህ ያሉት ሥራዎች ኩባንያው ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉም ይነገራል፡፡ ይህ ቢባልም በፕሮጀክቱ ቦታ ላይ የሚገኙ ንብረቶች ግምት ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን ይፋ አልወጣም፡፡

በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. በአላናና በአይሲኤል መካከል የተደረገው የሽያጭ ስምምነት አጠያያቂ ቢሆንም፣ አይሲኤል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ ተፈቅዶለት ከቆየ በኋላ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደረገበትን ኢንቨስትመንት አላና ፓታሽ በራሱ ስም ሳያስመዘግብ ቆይቷል፡፡ አላና የሚለውን ስያሜ ወደ አይሲኤል ለመቀየር ለማዕድን ሚኒስቴር ያቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ይህ ጥያቄ መስተናገድ የሚችለው አላና ፓታሽ መጀመሪያ ያለበትን ግዴታ በመወጣት ከጉምሩክ የዕዳ ነፃ ማስረጃ ሲያቀርብ እንደሆነ አስታውቆታል፡፡ በዚሁ መሠረት ለጉምሩክ ጥያቄውን ሲያቀርብ፣ አላና ፓታሽ 55 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ያለበት ታክስ ስላለ ከዕዳ ነፃ ማስረጃውን ማግኘት የሚችለው ዕዳውን ከከፈለ ብቻ እንደሆነ ተገልጾለታል፡፡ አይሲኤል በኢትዮጵያ የነበረውን ኢንቨስትመንት ለመቀጠል ያለው አማራጭ አላና ፓታሽ አለበት የተባለውን ዕዳ ሲከፍል ብቻ መሆኑም ለመቀጠል አስቸጋሪ ከሆኑበት ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡

የአይሲኤል ማኔጅመንት አላና ፓታሽ አለበት የተባለውን ታክስ መርምሮ መክፈል የሚችለው በ20 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተውን ብቻ እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡ ቀሪውን ለመክፈል የኩባንያው አሠራር እንደማይፈቅድለት በማመልከት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቢያሳውቅም፣ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት እየሠፋ በመሔዱ፣ ለኩባንያው ከኢትዮጵያ መውጣት ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን አይሲኤል መጀመሪያውኑ አላና ፓታሽ ይህንን ያህል የመንግሥት ዕዳ እንደነበረበት አያውቅም ነበርም ይባላል፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ተስፋ የተጣለበትና ከሰባት ዓመታት በላይ የቆየው ፕሮጀክት ሳይታሰብ መሐል መንገድ ቀርቷል፡፡

አላና ፓታሽ ይዞታውን በሽያጭ ለአይሲኤል ከማስተላለፉ ቀደም ብሎ በዳሎል የተካሄደው የፓታሽ ማዕድን የማምረት ሥራ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ወጪ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አስታውቆ ነበር፡፡

በአላና ስም የተያዘው እስራኤሉ ኩባንያ ለፓታሽ ማዕድን ማምረቻ የተረከበው ይዞታ፣ 300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ ለፓታሽ ማምረቻ ይሆናል ተብሎ የተለየው 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ሲሆን፣ በወቅቱ በተደረገ ጥናት በዚህ ይዞታ ብቻ 3.2 ቢሊዮን ቶን የሚገመት የፓታሽ ማዕድን ክምችት እንዳለ ተጠቁሟል፡፡

አይሲኤል በፓታሽና ሌሎች ማዕድናት ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት እንዳለው የሚነገርለት ይህ ኩባንያ፣ በእስራኤልና በእንግሊዝ የፓታሽ ማውጫዎች አሉት፡፡

አላና ፓታሽ በሚል ስያሜ የፓታሽ ማዕድን ለማምረት ፈቃድ የተሰጠውና መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ኩባንያ፣ ባጠናው መሠረት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚችል ይታሰብ ነበር፡፡

ይህንኑ ውጥን ተከትሎም ፓታሹን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ መንግሥት ድጋፍ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ በተለይ ምርቱን ሲጀምር ከማምረቻ ቦታው ታጁራ ወደብ ድረስ የአዲስ መንገድ ግንባታ እንዲካሄድ መወሰኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ወገኖች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ፓታሽ ማውጫው አካባቢ ከሚገኙ ንብረቶች ውስጥ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎችና ጨረር አመንጪ ቁሳቁሶች ስለሚጉባቸው በጥንቃቄ መወገድ እንዳለባቸው እየተነገረ ነው፡፡

ንብረቱን የተረከቡት የመንግሥት ተቋማት፣ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ ስለተባሉት ንብረቶች ትኩረት በመስጠት በባለሙያ በጥንያቃቄ ማስወገድ እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ እየቀረበባቸው ነው፡፡ ባለሥልጣኑ እንዳይንቀሳቀሱ ያገዳቸው ንብረቶችን ተሸጠው ወደ ካዝናው እንደሚያስገባ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ወደፊት ከአላና ጋር የሚኖረው ግንኙነት ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች