Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያካሄደችው ሁለተኛ ወረራና የሕዝባችን ተጋድሎ

ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያካሄደችው ሁለተኛ ወረራና የሕዝባችን ተጋድሎ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ኢጣሊያ ኤርትራንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ህልሟ በአንፀባራቂው በዓድዋ ጦርነት ድል ቢከሽፍም አርፋ አልተቀመጠችም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ኤርትራውያን በዓድዋ ዘመቻ ወደ ወንድሞቻቸው ማድላታቸውን፣ ማለትም ኢጣሊያን ከድተው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው፣ እንዲሁም ስመ ገናናዋና አፍሪካን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንደምትችል ተደርጎ ሲነገርላት የነበረችው ታላቋ ኢጣሊያ በአብዛኛው በጦርና በጎራዴ ከሚዋጋ ሐበሻ ጋር ጦርነት ገጥማ የመሸነፏ ጉዳይ በእጅጉ አሳፋሪ ሆኖ ስለተገኘ፣ ይልቁንም ከዓድዋ ጦርነት በኋላ በሚገዟት ኤርትራ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ይኼንን ገጽታ የሚለወጥበትን መንገድ መፈለግ ነበረባት፡፡

በዚህም መሠረት የኤርትራን ሕዝብ እርስ በርስ በብሔር ብሔረሰብና በሃይማኖት እየከፋፈለች ማናቆርና ማጣላት ጀመረች፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረች ሙስሊሙንና ሌላውን የክርስትናና የኦሪት እምነት ተከታይ የተሻለ ነፃነት እንዲኖረው አደረገች፡፡ በአስመራና በሌሎች የኤርትራ ትልልቅ ከተሞችም ትልልቅ መስጊዶች ተሠሩ፡፡ የቫቲካን የበላይነትም እየጎላ መጣ፡፡ ሕዝቡን በተጠቀሰው መንገድ በሃይማኖት እየከፋፈለች ትግሬውን (የሐማሴን፣ የሰራዬና የአከለ ጉዛይ ነዋሪን) መጤ፣ ሌላውን ደግሞ የኤርትራ ጥንታዊ ነዋሪ አድርጋ ለማሳየት ሞከረች፡፡ የሐበሻ አገዛዝ አንዱን ብሔረሰብ ገዥ ሌላውን ተገዥ በማለት መስበክ ጀመረች፡፡

በመሠረቱ ኢጣሊያ ኤርትራን ቅኝ ግዛት አድርጋ ከያዘች በኋላ በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ትግሬ፣ ዓፋር፣ ሳሆ፣ በለው፣ ቤጃ፣ ቤን አሚር፣ ኩናማ ቢለን ሲሆኑ፣ እነዚህም ብሔር ብሔረሰቦች በአብዛኛው ማለትም የደጋማው (ኸበሳ) ሕዝብ ትግርኛን እንደ ጋራ መግባቢያቸው አድርገው የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ደጋማዎቹ ኤርትራውያንም ሌሎች ሳይሆኑ ከአጋመ፣ ከሽረ፣ ከዓድዋ፣ ከአክሱም ትግሬዎች ጋር አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ ባህል፣ ተመሳሳይ እምነትና ሥነ ባህርይ ያላቸው ናቸው፡፡ ከትግሬዎችም በተጨማሪ ከጎንደር፣ ከወሎና ከሌላ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ግዛት ወደ ሥፍራው በልዩ ልዩ ምክንያቶች በመሄድ ቋንቋቸውን ትግርኛ አድርገውና ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስረው የኖሩ ከጊዜ በኋላም ልጆቻቸውና  የልጅ ልጆቻቸው ኤርትራዊ አድርገው የቆጠሩ ናቸው፡፡

እነዚህም የኸበሳ ሰዎች ከሌላው የኤርትራ ነዋሪ ጋር ሥልጣን እየተጋሩ ኖረዋል፡፡ በመሠረቱ አፋሮች፣ ሳሆዎች፣ ቤጃዎች፣ በለዎች የተለያየ ስም ይሰጣቸው እንጂ ዋነኛውን የዘር ግንዳቸውን ከኩሽ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ከአፋር የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ አፋሮችም የክርስቲያን መንግሥት አድርጎ ራሱን ከሚጠራው አመራር ጋር የሃይማኖት ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ ከ12ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ያልተቋረጠ ጦርነት ቢያደርጉም፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው የማያውቁ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የኢጣሊያ ወረራ ሲመጣም አንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ነጥሎ ለመግዛት፣ ወይም አንዱን ብሔረሰብ የበላይ ሌላውን ብሔረሰብ የበታች አድርጎ ለመያዝ ሳይሆን ሁሉንም ገዝቶ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ እንድትችል፣ ጭቁን የተባለው ሕዝብ በቁጭት ከኢጣሊያ ጋር እንዲሠለፍ ለማድረግ ነበር፡፡

ኢጣሊያውያን ቅኝ ገዥዎች ይሉት እንደነበረው ከኢጣሊያ በፊት የአማራና የትግራይ ተወላጆች (ባላባቶች) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በፍፁማዊው ንጉሠ ነገሥት ሥርዓት አስተባባሪነት በእርሻ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ገንብተው በኤርትራ (ባህረ ነጋሽ) የበላይነት ነበራቸው፡፡ ቆላ ውስጥ የሚኖሩት ወገኖች ብዙውን ጊዜ ከብት በማርባት ተነጣጥለው ይኖሩ ስለነበረ ደገኞቹ የአማራና የትግሬ መሳፍንት በቀላሉ ጥቃት ያደረሱባቸው፣ አማራና ትግሬው በሚዳከሙበት ወቅት የቆላው መሳፍንት የደጋውን ሕዝብ ይገርፉትና ይዘርፉት ነበር፡፡ ግንኙነታቸው በጣም ግትርና ጥላቻ የተሞላበት ነበር፡፡ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ለዚህ ቅራኔ መሣሪያዎች ነበሩ፡፡ ኢጣሊያውያኑ ቅኝ ገዥዎች ይሉት እንደነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ ዋና ጨቋኝ ብሔረሰብ ትግሬ ትግሪኛው ነበር፡፡ መሳፍንቱ ከሐማሴን፣ ሽረ፣ ወልቃይት በተለይም የአጋመ መሳፍንት ንዑሳን ብሔረሰቦችን ሲዘርፉና ሲያቃጥሉ ኖረዋል፡፡ እነዚህም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጣሊያኖች በደጋው መሬት ጣሊያኖችን ማስፈር ስለጀመሩና በዚህ አቅጣጫ ሰፋ ያለ ዕቅድ ስለነበራቸው፣ የፊውዳላዊ የጉልት ምርት ግንኙነት እንቅፋት ስለሆነባቸው የተጠቀሰውን መርዛማ ፕሮፓጋንዳ በማሠራጨት ለማዳከም ሞክረዋል፡፡

ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጣሊያኖች በፊት ማደርያ ተብሎ ለዘመናት የያዘችውን ምርት መሬት ልዩ ልዩ ሰበቦችን በማቅረብ መቀማት እንደ ዋነኛ ሥራዋ አድርጋ ተያያዘችው፡፡

ኢጣሊያውያን የትግራይ ትግሪኛውን የብሔረሰብ ክፍል የኢኮኖሚያዊ ይዞታውን በመንጠቅ ማዳከሙ በቂ ሆኖ ስላላገኙት፣ በውስጣቸው የነበረውን የተወላጅነት ስሜት እንደገና በመቀስቀስና አጉልተው በማውጣት ለዓላማቸው መሳካት እንደ መሣሪያ ተጠቀሙበት፡፡ በዚሁ ተግባራቸው የሳህለ ሥላሴ ሥርወ መንግሥትና የሰባጋዲስ (የዮሐንስና መሰሎቹ) ሥርወ መንግሥት የመሳሰሉትን አንዴ አንዱን፣ አንዴ ሌላውን በመደገፍ ሲከፋፍሏቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ኅብረተሰቡን ብቻ ሳይሆን አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒሊክን፣ እንዲሁም በፋሽስት ጊዜ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴና ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳን አንዱን በአንዱ ላይ በማስነሳት ኢትዮጵያን ለመግዛት ያደርጉት የነበረውን ተንኮል ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህን ፖሊሲያቸውን በተለይ በኤርትራ ትግራይ ትግሪኛው ክፍል ገፉበት፡፡

ቅኝ ገዥዋ ኢጣሊያ በአንድ በኩል ሕዝቡን በሃይማኖትና በብሔር ብሔረሰብ በመከፋፈል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራዊ ምንም ቢሆን ከሐበሻ ሕዝብ የበለጠ መሆኑን፣ ቅኝ ተገዥዎቿን የበላይ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ያልሠለጠኑና ድሆች አድርጋ በማቅረብ ለመለያየት ያልተቆጠበ ጥረት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወገኑ መሆኑን የተረዳው የኤርትራ ሕዝብ ሰፊውን የኤርትራ ድንበር እያቋረጠ ወደ ዓጋሜ፣ አክሱም፣ ዓድዋ፣ ሽረ በብዛት በመግባት የኢጣሊያን መንግሥት መውጋትና ማስጨነቅ ጀመረ፡፡ የትግራይ ሕዝብም ከኤትራውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ኢጣሊያውያንን ወጋ፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ተማራኪዎች በኤርትራ ውስጥ መቀጣጫ ይሆኑ ዘንድ በየአደባባዩ ተገደሉ፡፡ ይኼም የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን አጠቃሎ ካልገዛ በስተቀር እረፍት እንደማይኖረው አስገነዘበው፡፡ ወረራውም የማይቀር ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት በኅዳር ወር 1927 ዓ.ም. ወልወል ላይ በተደረገው የትንኮሳ ጦርነት 150 ኢትዮጵያውያን ሲሞቱ ሁለት ኢጣሊያውያን ተገድለዋል፡፡ ኢትዮጵያም የጦርነት ትንኮሳውን ለሊግ ኦፍ ኔሽን አሳውቃለች፡፡

ኢጣሊያ በአፍሪካ ቅኝ ግዛት ለመመሥረት በነበራት ፅኑ ዓላማ ሰሜን ኢትዮጵያን በመውረር ኤርትራን ይዛ በሰላም መኖር እንደማትችል በተግባር ስላረጋገጠች በሰሜን በኩል በማርሻል ኢሚሎ ደቦኖ (የኢጣልያ ቅኝ ግዛት አገሮች ኮሚሽነር) የሚመራ 250,000 ነጮችንና 150,000 አፍሪካውያንን ከሊቢያ፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ ሠራዊት ኢትዮጵያን አጠቃሎ ለመግዛት ከ1920ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ ተጀመረች፡፡ ይህንን ዘመቻ በማያዳግም ሁኔታ ለማከናወን 300 የጦር አውሮፕላኖች ዝግጁ ሆኑ፡፡ በደቡብ በኩል በ100 የጦር አውሮፕላኖች የታገዘ በማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራ ኃይል ወደ ሰሜን ተንቀሳቀሰ፡፡ ይኼም የተደረገው አዲስ አበባን እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ በመቆጣጠርና ሕዝቡ በደስታ ተቀብሎኛል በማሰኘት ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደርስ የነበረውን ተፅዕኖ ለማስቀረት ነበር፡፡ 

የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኤርትራ ከነበረው በ3,300 መትረየሶች፣ በ200 ታንኮችና በ275 መድፎች የተጠናከረ 400,000 ጦር በተጨማሪ በሶማሊያ የነበረው 285,000 ሠራዊት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም. በርካታ ቶኖች የሚመዝኑ ጥይቶች፣ ለወራት የሚበቁ ምግቦችና ሌሎች ድጋፍ የሚሠጡ አገልግሎቶች፣ በበርካታ ሞተር ብስክሌቶች፣ በ6,000 አውቶማቲክ የጦር መሣሪያ (መትረየስ)፣ በ2,000 መድፍ፣ በ599 ታንክ፣ በ390 አውሮፕላኖች የተጠናከረ ከኢጣሊያ ዘውዳዊ መንግሥት የጦር ኃይል ተቀንሶ 650,000 ሠራዊት  ኤርትራ ገባ፡፡ ይኼም ጦር የገባው በከፍተኛ ስንቅና ትጥቅ ተጠናክሮ ሲሆን፣ ጦርነቱንም ለመከታተል 200 ያህል ጋዜጠኞች መጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ  በዚያን ጊዜ ያንቀሳቀሰችው በራሶች የሚመራ 300,000 ሠራዊት ሲሆን (ይኼንን ቁጥር አንዳንዶች 500,000 እንደሚደርስ ይገምታሉ፣ የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ግን ኢትዮጵያ ከ350,000 እስከ 760,000 የሚገመት ሠራዊት ነበራት ብለው፣ ንጉሠ ነገሥቱ የነበራቸው 200 መድፎች፣ 1,000 መትረየሶች ከሠራዊቱ ጋር የማይመጣጠን ጠመንጃ የታጠቀ ነበር፡፡ አብዛኛው ሠራዊት የተሠለፈው ጎራዴ፣ ጦርና ጋሻ ይዞ ሲሆን የተወሰነው ደግሞ ከሚወድቁ ወገኖቹ የጦር መሣሪያ አንስቶ ለመዋጋት ጀሌውን የተሠለፈ ነበር፡፡ ሠራዊቱ ሲመች ከሚሰጠው ጥይት በስተቀር ስንቁንም ሆነ የጦር መሣሪያውን ይዞ የተሠለፈው ከግሉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት የራሱ የሆነ በቅሎ፣ ፈረስ፣ ግመልና አህያ ይዞ ከመዝመቱ በስተቀር የጦር ተሸከርካሪ የጦር አውሮፕላንና ታንክ የሚባል አልነበረውም፡፡ ይኼም ሆኖ የኢጣሊያ ወታደራዊ ምንጮች ኢትዮጵያ 400,000 ያህል ጥንታዊና ዘመናዊ ጠመንጃዎች፣ 200 ያህል ያረጁ መድፎች 50 ያህል ቀላልና ከባድ የአየር መቃወሚያዎች፣ 3,000 ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት አገልግሎት ላይ የዋሉ መድፎች፣ ለአየር አምቡላንስ የሚውሉ ጥቂት አውሮፕላኖች፣ አራት አብራሪዎች የነበሯቸው 13 የአየር ኃይል አውሮፕላኖች ነበሩ ብለዋል፡፡

እጅግ ኋላ ቀር የጦር መሣሪያ የታጠቀውና ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና ያላገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ከታጠቀው የኢጣሊያ ሠራዊት ጋር በሽሬ ታኅሳስ 7 እና 8 ቀን 1927 ዓ.ም.፣ በእንዳባጉና ከጥር 12 እስከ 16 ቀን 1928 ዓ.ም.፣ በወርቃምባ/ተንቤን ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 1928 ዓ.ም.፣ በዓቢይ ዓዲ/ተንቤን ከየካቲት 24 እስ 27 ቀን 1928 ዓ.ም.፣ ከዚያም ቀጥሎ በሰለኽለኻ፣ በእምባ አርአዶምና በአምባ አላጌ ጦርነት አካሄደ፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች በተደረገው ጦርነት ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኢትዮጵያዊ ቢሞትም፣ በተለይም በሽረ በተደረገው ጦርነት 300 ያህል መትረየሶች፣ ታንኮችና ሌሎችም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ተማረኩ፡፡

በዚህ ጦርነት በኢጣሊያ በኩል የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት ማርሻል ባዶግሊዮ በላከው ሪፖርት በሽረ ጦርነት ብቻ 63 የጦር መኮንኖች፣ 894 ኢጣሊያውያን፣ 12 ኤርትሪያውያን ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያ በኩል 4,000 ያህል ሞተዋል በማለት ገልጿል፡፡ በዚህ ጊዜ 400 የሚሆኑ ኤርትራውያን ኢጣሊያን በመክዳት ሽረ ከነበረው ከራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡

በደቡብ ግንባር በኩል በማርሻል ግራዚያኒ የሚመራውን የጦር ኃይል የእነ ራስ ደስታ፣ ደጃዝማች ነሲቡ፣ የራስ መኮንን የጦር ኃይል በኦጋዴን በተደረገው ጦርነት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ጊዜ የማርሻል ግራዚያኒ የጦር ኃይል የገጠመው በጦር አውሮፕላች በሚረጭ የጋዝ መርዝ ጭምር ነበር፡፡ ምንም እንኳን በጦርነቱ አያሌ ኢትዮጵያውያን ቢጨፈጨፉም፣ 400 ያህል ኤርትራውያን የወገኖቻቸው መጨፍጨፍ አሳዝኗቸው ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ 

ቦነያ ነቀምት ውስጥ በደጃዝማች ሀብተ ማሪያም ከሚመራው አርበኛ ጋር በተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ምክትል መስፍንን ጨምሮ ከ13 የኢጣሊያ መኮንኖች 12ቱ፣ የአየር ማርሻሉ ማግሎዮኮው ሰኔ 18 ቀን 1928 ዓ.ም. ተገደሉ፡፡ በዚህ ጦርነት የተረፈ ኢጣሊያዊ ቢኖር አባ ቦሬሎ የተባሉ መንገድ መሪያቸውና ቡራኬ የሚሰጧቸው ነፍስ አባታቸው ብቻ ነበሩ፡፡

በራስ ደስታ ዳምጠው የጦር አበጋዝነት በሲዳሞ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ዕልቂት የተፈጸመበት ሲሆን፣ በዚህም ጦርነት ጄኔራል ናቫሪኒ በሦስት አቅጣጫዎች ባደረገው ከበባ 4,000 የሚሆኑ ኢትጵያውያን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 1,600 ያህሉ ምርኮኞች ሲሆኑ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተደርጓል፡፡

ጥቅምት 1 ቀን 1928 ዓ.ም. ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ ከ1,200 ተከታዮቻቸው ጋር ዕዳጋ ሐሙስ ላይ ለማርሻል ደቦኖ እጃቸውን ሰጡ፡፡

ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ከጎጃም ወደ ተንቤን በተለይም ማይ ጥምቀት ተብላ ወደምትጠራው ሥፍራ 40,000 ሠራዊት አስከትለው ዘመቱ፡፡ ራስ ሥዩም መንገሻ ከ30,000 ሠራዊታቸው ጋር ዓቢይ ዓዲ አካባቢ ነበሩ፡፡ ራስ ካሣ ኃይሌ ዳርጌ 40,000 ያህል ሠራዊታቸውን አስከትለው ከደሴ ራስ ሥዩምን ለመርዳት ወደ ተንቤን ዘመቱ፡፡ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ (የጦር ሚኒስትር) 80,000 ያህል ሠራዊታቸውን አሠልፈው ከራስ ሥዩም በስተቀኝ አምባ አርዓደ ላይ መሸጉ፡፡ አራቱም የጦር አበጋዞች በአጠቃላይ 190,000 ያህል ሠራዊት ነበራቸው፡፡

ተንቤን ላይ በተደረገው እጅግ አስከፊ ጦርነት 8,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፡፡ ከዚህ በኋላም መቀሌ በኢጣሊያ ተያዘች፡፡ እምባ አርአደ ላይ በተደረገው የእንደርታ ጦርነት ራስ ሙሉጌታና ልጃቸውን ጨምሮ 6,000 ሰዎች ሲሞቱ፣ 120,000 ያህል ቆሰሉ፡፡ በሽረ በተደረገው ጦርነት 1,000 ያህል ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ 4,000 ያህል ቆሠሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትም ተበታተነ፡፡

የራስ ካሣ ሠራዊት ተንቤን ላይ በጋዝ መርዝ አለቀ፡፡ 1,000 ያህል ሠራዊት ከበጌ ምድር ተከዜን ተሻግሮ እንዳባጉና ደረሰ፡፡ በሽሬ ግንባር በኩል የኢጣሊያው የጦር መሪ ሜጀር ከሪኒቲ በሦስት ታንኮችና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘ 1,000 ሠራዊት አሠልፏል፡፡ እርሱም እዚያ እንደ ደረሰ አካባቢውን የሚቆጣጠሩት 2,000 ያህል የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት እንደሆነ ተገነዘበ፡፡ ስለሆነም የነበረው ዘመናዊ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የሰው ኃይል ከበባ በማድረግ በቦምብ ድብደባ ድል ሆነ፡፡ ነገር ግን እርሱና የተረፉት ጥቂት ወታደሮቹ አመለጡ፡፡ ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ 3,000 ባንዳዎችን መግደሏን አስታወቃ ነበር፡፡

መጋቢት ወር 1928 ዓ.ም. ማይጨው ላይ በተደረገው ጦርነት በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራና ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ሠራዊት ቢሆንም 400 ኢጣሊያውያን፣ 837 ኤርትሪያውያና 11,000 ያህል ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ስለነበር የንጉሠ ነገሥቱ ጦር ድል ሆነ፡፡

በደቡብ በኩል ማርሻል ግራዚያኒ በደጃዝማች ነሱቡ ጦር ላይ ባካሄደው ዘመቻ 200 ኢጣሊያውያን ቢሞቱበትም፣ 15,000 ኢትዮጵያውያንን ገድሎ ኦጋዴንን ተቆጣጠረ፡፡

ማርሻል ባዶጋሊዮ የማይጨው ድል ከቀናው በኋላ ጉዞውን በደሴ በኩል በመቀጠል በግንቦት ወር አዲስ አበባ ገባ፡፡ ግንቦት 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና ሶማሊያን በማዋሀድ በምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት መሆናቸውን በይፋ አወጀች፡፡ 

ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቷ አማካይነት የጠየቀችው የድረሱልኝ ጥያቄንም የዓለም መንግሥታት ጆሮ ነፈጉት፡፡ ይባስ ብለው በኢጣሊያ ላይ አስተላልፈውት የነበረውን ማዕቀብ በነሐሴ ወር 1928 ዓ.ም. አነሱ፡፡ በታኅሳስ ወር 1929 ዓ.ም. ጃፓን የኢጣሊያን ቅኝ ገዥነት ተቀበለች፡፡ ፈረንሣይና እንግሊዝም ተጨመሩበት፡፡ ከዓለም አገሮች ሁሉ የኢጣሊያን ቅኝ አገዛዝ የሚቃወሙ ሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ኒውዚላንድ፣ ሶቪየት ኅብረት፣ ስፔይን ሪፐብሊክና አሜሪካ ብቻ ሆነው ተገኙ፡፡ ኢጣሊያን ሲወጉ ከነበሩት የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች የተወሰኑት ለኢጣሊያ ፋሽሽት መንግሥት አደሩ፡፡ የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ የነበረውን መረጋጋት ሲመለከት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የፈጸመው ማርሻል ግራዚያኒን በማንሳት የአዎስታውን መስፍን (ሲቪል መሆኑ ነው) ሾመ፡፡

ኢጣሊያ ትግራይና ኤርትራ አንድ ላይ፣ ኦጋዴንና ሶማሊያ ደግሞ አንድ ላይ አድርጋ ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ ከፋፈለችው፡፡ በ1930 ዓ.ም. ላይ ብሪታንያና ፈረንሣይ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ቅኝ ገዥነት ከቃል ድጋፍ ወደ ጽሑፍ ስምምነት ቀየሩት፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና ሶማሊያን በአንድ ላይ በምትገዛበት ጊዜ መንገድ፣ ስልክና መብራት መዘርጋት እንደ ዋነኛ የሕዝብ ማሳመኛና መግዣ ጥበብ አድርጋ ተጠቀመችበት፡፡ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል መገንባትን፣ ዘመናዊ እርሻዎችን ፋብሪካዎችን ማቋቋምን እንደ ዋነኛ ሥራዋ አድርጋ ወሰደችው፡፡ ሕዝቡን ሰጥ ለጥ አድርጋ ለመግዛትም 150,000 ሠራዊቷን በመላው ኢትዮጵያ አሠራጨች፡፡ ይኸው አኃዝ ባንዶቿን ጨምሮ በሦስት ዓመት ውስጥ ወደ ሩብ ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡

የሠራዊቱ ቁጥር ከፍ በማለቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ብዝበዛውንና ጭቆናውን መፈጸም ሲጀምር ‹‹አልገዛም›› ያለው ወደ ጫካ ገባ፡፡ የሽምቅ ውጊያ ተጀመረ፡፡ በቅኝ ገዥዋ ኢጣሊያ መሪዎች ላይ ጥቃት የመፈጸም ጥይት በየቦታው ተተኮሰ፡፡ የሽምቅ ውጊያውን የሚያካሂዱት መኳንንቱና መሳፍንቱ ናቸው በሚል ጥርጣሬ በርካታዎቹ ታሠሩ፡፡ የአንዳንዶቹ ልጆችም በፋሽስታዊው መንግሥት ላይ በመሸፈታቸው ምክንያትና እነርሱ ራሳቸውም በመሸፈታቸው ይገደሉ ጀመር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እነ ራስ ካሣ፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ፣ እነ ጄኔራል ኃይሉ ከበደ፣ እነ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ ይገኙበታል፡፡

ይሁንና የቅኝ አገዛዝን የማይቀበለው የኢትዮጵያ ጅግና ሕዝብ ወራሪውን ጦር ወግቶ በማሸነፍ ከምድረ ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ያባረረ ሲሆን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያም እንዲወጣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኢትዮጵያን በአርበኝነት የመሯትን ጀግኖች መዘርዘር አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ አንዱን አንስቶ ሌላውን መተው ስለሚሆን ጸሐፊው ነፃ ያወጡንን አርበኞች በማመስገን በደፈናው መተውን ይመርጣል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected].  ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...