Tuesday, July 23, 2024

የፕሬስ ነፃነት ሕጉና ያልተጣጣመው አፈጻጸም

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣ ቁጥር የሰው ልጅ ፍላጎትም አብሮ እያደገ መጥቷል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ደግሞ መረጃ የማግኘት ፍላጎቱና ዝንባሌው መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ሚና ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መረጃ እንደሆነ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

በኢፌዴሪ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ላይ እንደሰፈረው ‹‹መረጃ›› ማለት በማናቸውም ዓይነት ቅርጽ የተዘጋጀ ማንኛውም ሰነድ ማለት ነው፡፡ ይኼንን ከማንኛውም ሰነድ የሚገኘው መረጃ በጽሑፍም ሆነ በቃል መግለጽ ደግሞ ተፈጥሮአዊ መብት እንደሆነ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ይህ መብት ተፈጥሮአዊ እንጂ ሰው ሠራሽ ባለመሆኑ ሊነጠቅ የማይችል ጉዳይ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

አንድ ሰው የሚመስለውን ሐሳብ በፈለገው መንገድ የመግለጽ፣ መንግሥትን የመተቸት ወይም የመደገፍ፣ በራስ ፈቃድ መናገርና ያለመናገር ያለማንም አስገዳጅነትና ጣልቃ ገብነት የመሰለውን እምነት የመከተልና የማስፋፋት መብቶች ሁሉ ተግባራዊ የሚሆኑት፣ የመናገርና የመረጃ ነፃነት መብት ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይደመጣል፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በተመለከተ በንጉሡ ዘመን ተሻሽሎ በ1948 ዓ.ም. በወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 41 ላይ ‹‹ከመላው የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ በሕግ መሠረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው፤›› በማለት ተደንግጎ ነበር፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ በ1980 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ላይ ኢትዮጵያዊያን የንግግር፣ የጽሑፍና የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ደግሞ በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕጋዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡

ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥት ደረጃ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋትንም የተቀበለችና ያፀደቀች አገር ነች፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ላይ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ይኼን ዓለም አቀፍ ሕግ የተቀበለችና የፈቀደች ቢሆንም፣ የፕሬስ ነፃነት አያያዟ በተደጋጋሚ ጊዜ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲወቀስ ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ ይኼን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ተቀብላ ማክበር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዕለቱን በዚህ ደረጃ አስቦ መዋል ዓላማ ያደረገውም የፕሬስ ነፃነት በመላው ዓለም የሚገኝበትን ሁኔታ ለመገምገም፣ በመገናኛና ብዙኃን ሙያዊ ነፃነት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ሙያዊ ግዴታቸውን ለመውጣት ሲሉ ሕይወታቸውን ያጡ ጋዜጠኞችንም አስቦ ለመዋል ነው፡፡

የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ውስጥ ማክበር ደግሞ፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የሚገኙበትን ሁኔታ ቆም ብሎ ለማሰብ እንደሚረዳ ተጠቁሟል፡፡

የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ‹‹ክሪቲካል ማይንድስ ፎር ክሪቲካል ታይምስ፣ ሚዲያስ ሮል ኢን አድቫንሲንግ ፒስፉል፣ ጀስት ኤንድ ኢንክሉሲቭ ፍሪደም ዴይ›› የሚል መሪ ቃል ያለው ሲሆን፣ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በኢሌሌ ሆቴል ረቡዕ ሚያዝያ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል፡፡

በዕለቱ የመንግሥት የሚዲያ አካላት፣ የግል ሚዲያ ኃላፊዎችና የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተገኙ ሲሆን፣ ለሚዲያ አካላት ካለው ክብደትና ፋይዳ አንፃር ሲታይ ግን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አካቶ የተካሄደ ዝግጅት እንዳልነበረ በመድረኩ ላይ የታደሙ ሰዎች ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት የተውጣጡ የሕዝብ ግንኙነትና አንዳንድ ባለሙያዎች የተገኙ ቢሆንም፣ የክብረ በዓሉ ባለቤቶች የሆኑ ጋዜጠኞች (ከመንግሥትም ሆነ ከግል) በብዛት አለመገኘታቸውና ዕለቱ ሲታሰብ በመንግሥትም ሆነ በግሉ የሚዲያ አካላት ዘንድ የሚታዩ ክፍተቶች ተነቅሰው ወጥተው እርምት እንዲወሰድበት ያደረገ ዝግጅት እንዳልነበር ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ ነበሩ፡፡ ይኼ ዕለት በተለይ ለጋዜጠኛው ካለው ፋይዳ አንፃር፣ በዕለቱ ተሰባስቦ ችግሩን ነቅሶ አውጥቶና ለሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጠቁሞ በመሄድ ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩ የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዕለት የኢትዮጵያ ፕሬስ አሁን ያለበትን ቁመና የሚያመለክቱ ሁለት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጽሑፍ የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ የሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ‹‹የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጽሑፍ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር አቶ ተሻገር ሽፈራው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የኀትመት መገናኛ ብዙኃንና አንዳንድ ወቅታዊ ገጽታዎች›› በሚል ርዕስ ቀርቧል፡፡

የዕለቱን ፕሮግራም በንግግር የከፈቱት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ዕለቱ የሚከበረው መንግሥት በኮሙዩኒኬሽንና በሚዲያ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ባለበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ አንዳንድ ተሳታፊዎች ግን መንግሥት እስከ መቼ ድረስ ዛሬ ነገ አሻሽለዋለሁና አሳካዋለሁ እያለ ይኖራል በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በንግግራቸው የፕሬስ ነፃነት ሲባል ሐሳብን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የመግለጽ መብት ሲሆን፣ ይህ መብት ደግሞ መረጃን ጠይቆ የማግኘትና የማሠራጨት መብትን እንደሚያጠቃልል ተናግረዋል፡፡ ይኼንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ እየተደረገለት የሚተገበር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ መሠረት አታላይ ‹‹መንግሥት ነፃነት፣ ነፃነት ቢልም ኢትዮጵያ በዓለም በአሁኑ ጊዜ በፕሬስ ነፃነት 150ኛ ደረጃ ላይ ነው ያለችው፡፡ ይህ ደግሞ የሚዲያ ነፃነት እንደሌለ ያመላክታል፤›› ብለዋል፡፡

ጠንካራ ሚዲያ ከመፍጠር አንፃርም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ከግሉ ፕሬስ የዕውቀት፣ የክህሎትና የሙያ ብቃት ክፍተቶች በማኅበረሰቡ በኩል ደግሞ የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ ምክንያት ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ሚዲያው በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንቅፋት የሚሆኑ ምክንያቶችን በአግባቡ እየነቀሰ ለማውጣትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ በኩል እየተጫወተ ያለው ሚና ገና የሚቀረው ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሚዲያው በተገቢው ሙያዊ ሥነ ምግባርና  ክህሎት እንዲደራጅና በአገሪቱ የዕድገት ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችል ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ጋር በማያያዝ አቶ መሠረት፣ ‹‹ሚዲያው በተገቢው ሙያዊ ሥነ ምግባርና ክህሎት ተደራጅቶ በአገሪቱ የዕድገት ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳያደርግ ያደረገው መንግሥት ራሱ ነው፤›› በማለት ከሚኒስትሩ መልዕክት በተቃራኒ አስተያየታቸውን አሰምተዋል፡፡  

አቶ አማረ ደግሞ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ድንበር ሳይወስነው ሐሳቡን የመግለጽ መብት እንዳለው በማያሻማ ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በጣም ትክክልና ብቁ ሕግ ነው ያለን፤›› በማለት ሕግ መንግሥቱ ለፕሬስ የሰጠውን ነፃነት አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ራሱ ያወጣውን ሕግ ተግባራዊ እንደማያደርገውና ሕጉም ራሱ የማያሠራ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የቁም ነገር መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ኃይሉ ናቸው፡፡

አቶ አማረ የመረጃ ተደራሽነት ማለት ጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት መረጃ ሲጠይቅ የማግኘት መብት እንዳለው አብራርተዋል፡፡ መረጃ የማግኘት መብት በሕጉ ላይ የተደነገገ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን አመቺ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመጡ ተወካይ ጉዳዩ በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ትልቁ ፈተና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመረጃ ተደራሽነት አፈጻጸሙ ላይ እንኳን ለግል ሚዲያዎች ይቅርና ለመንግሥት ሚዲያዎች ትልቁ ፈተና ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተለይ በመንግሥት አካላትና በአመራሮች አካባቢ ያለው ችግር እስካሁን ያልተፈታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ አማረ በመነሻ ጽሑፋቸው ላይ እንዳብራሩት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሌሎች መብቶች ለየት ባለ መንገድ የሚታይና የሰብዓዊ መብትም የመጀመሪያው ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አቶ መሠረት፣ ‹‹ይህን የመሰለ መብትና ነፃነት በሕጉ ላይ ሰፍሮልን መንግሥት ጣልቃ በመግባት ይኼን አድርጉ፣ ይኼን አታድርጉ እያለ የግል ሚዲያውን እየጎዳው ነው፡፡ በሕጉ ላይ የሰፈሩ መብቶች አይከበሩም፡፡ ለዚህም ከዓመታት በፊት የነበሩት ሃያና ሰላሳ ጋዜጦች ዛሬ ወደ አራትና አምስት ዝቅ ብለዋል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ታምራት በበኩላቸው፣ ‹‹ሐሳብን በነፃነት የማስተላለፍ መብት በአዋጁ ተገድቧል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አማረ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ አራት ወሳኝ አካላት እንዳሉና እነዚህ አካላትም በፕሬሱ ላይ የራሳቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ሚዲያ ራሱና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዲያ ተቋማት የሚባሉት እንደሆኑ ጠቅሰው እያንዳንዳቸው በፕሬስ ነፃነት ላይ ያላቸውን ጠንካራና ደካማ ጎን አብራርተዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ያለው ጠንካራ ጎን ብለው ካስቀመጧቸው መካከል መንግሥት የመረጃ ተደራሽነት ሕጎችን ማውጣቱ፣ የግል ሚዲያ መቋቋም ይችላል የሚል አቋም መኖሩ፣ ሚዲያ የመንግሥት ብቻ አይደለም ማለቱ፣ በኢትዮጵያ ቅድመ ምርመራ መቅረቱ፣ እስካሁን ድረስ ባይመዘግበውም መንግሥት የሚዲያ ካውንስል እንዲቋቋም አዋጅ ማውጣቱ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥት ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ ተግባራዊ አለማድረጉ፣ ለሚዲያው ድንበርና ክልል ማበጀቱ፣ የሚገለጸው ሐሳብ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ትክክል አይደለም ማለቱ፣ ሕገ መንግሥቱ ስትፈልግ ኒዮ ሊብራሊዝም ሐሳብም አሠራጭ ቢልምና ሚዲያው ጥቃት እንዳይደርስበት የሕገ መንግሥት ከለላ የተደረገለት ቢሆንም ተፈጻሚ አለመሆን፣ ለሚዲያው ከቀረጥ ነፃ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የመንግሥት ሚዲያ ተጠርቶ የግሉን አለመጥራት የሚሉት ችግሮች በፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን አቶ አማረ ጠቁመዋል፡፡

በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ሐሳባቸውን መግለጻቸውና በመደራጀታቸው ለፕሬሱ ነፃነት በአዎንታዊ ጎኑ የሚጠቀስ ቢሆንም፣ በቋሚነት ስለፕሬስ ነፃነት ሲሞግቱና ሲከራከሩ አለመታየት፣ የሚደግፏቸውን ብቻ ነፃ ፕሬሶች አድርገው መሳል፣ አንዳንዴም ገፋ ሲል ሙስና የሚንፀባረቅበት መሆኑ የፕሬሱን ነፃነት የሚገዳደሩ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ አማረ በጽሑፋቸው ዳሰዋል፡፡

አቶ አማረ ሚዲያው ራሱ ለፕሬስ ነፃነት  ያለውን አዎንታዊ ጎን ገልጸዋል፡፡ ሚዲያው ራሱ ካለው ችግር ጋር ተጋፍቶ የፋይናንስ ድጋፍ ባይደረግለትምና ራሱም በፋይናንስ የተደራጀ ባይሆንም፣ እየተንገዳገደ መቀጠል መቻሉና ኅብረተሰቡ አማራጭ ሐሳብ እንዲያገኝ ማድረጉን እንደ ጠንካራ ጎን ወስደው፣ አንዳንዱ የግል ፕሬስ ሀቁን ለይቶ የመሄድ ችግር፣ ሕጉን ለመተግበር መቸገር፣ ለፕሬስ ነፃነት ቆመናል ብለው ፀረ ፕሬስ ሆነው የቆሙ መኖራቸው፣ ከእነሱ የማይስማማ ሚዲያ ካለ መብቱ ነው ከማለት ይልቅ ከእኔ የተለየ ሚዲያ መኖር የለበትም ብሎ መንቀሳቀስ፣ ዓለም አቀፍ ሕጉን የመተግበር ችግር፣ ፕሬሱ ራሱ ያልተደራጀ መሆኑ ደግሞ ለፕሬሱ ነፃነት በራሱ በሚዲያው ያሉ እንቅፋቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያው ለፕሬስ ነፃነት የሚጫወተው ሚና አነስተኛ መሆኑን አቶ አማረ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እንደ ጋዜጠኛ የሚያደንቁህና ክብር የሚሰጡህ ሁለት ነገሮች ስትሆን ነው፡፡ አንደኛው ቃሊቲና ቂሊንጦ ስትወርድ፣ ሁለተኛ ደግሞ ተሰደህ አውሮፓና አሜሪካ ስተገባ ነው፤›› በማለት ለፕሬሱ ነፃነት ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ አብራርተዋል፡፡

አቶ ተሻገር ሽፈራው ደግሞ ለሃያ ስድስት ዓመታት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ታሪክ ቀድሞ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብዙ ውስብስብ ገጽታዎች፣ ውጣ ወረድ የበዛባቸው ጎዳናዎች፣ የተስፋ ጭላንጭሎችና መልከ ብዙ ፈተናዎች እንደተከሰተበት አስረድተዋል፡፡ በየወቅቱ ብዙ የግል ኅትመት መገናኛ ብዙኃን (ጋዜጦችና መጽሔቶች) ተወልደው እንደ ሞቱ አቶ ተሻገር ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ የኅትመትና መገናኛ ብዙኃን እየተጓዘበት ያለው መንገድ በእሾህ የታጠረ እንጂ የተመቸና የተመቻቸ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲታሰብም አስቸጋሪውን ጎዳና መዝለቅ ተስኗቸው በአጭሩ የቀሩ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ማሰብም አንዱ የዕለቱ ዓላማ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አቶ ተሻገር በጽሑፋቸው የኅትመት መገናኛ ብዙኃን በብዙ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በኅትመትና መገናኛ ብዙኃን ላይ የፖለቲካ ወገንተኝነትና አወዳሽ ጋዜጠኝነት፣ የተቃውሞ ዝንባሌና ተዋጊ ጋዜጠኝነት፣ የመገናኛ ብዙኃን ዴሞክራሲ ዕጦት፣ መገናኛ ብዙኃን ወደ ተቋም ማደግ አለመቻላቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ተደራሲያን ፍላጎቶች፣ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የማንበብ ባህል አለማደግ፣ ያልበለጸገና ያልተረጋጋ የመገናኛ ብዙኃን ገበያና የመረጃ ተደራሽነት ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

አቶ ተሻገር ይህን ይበሉ እንጂ የግል ኅትመት ሚዲያው በዚህ ደረጃ ሊወቀስ የሚገባው እንዳልነ አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡ አቶ መሠረት፣ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ የግል የኅትመት ብዙኃን መገናኛ እንዲያድግና ራሱን በራሱ እንዲለወጥ ዕድሉን የከፈተለት የለም፡፡ ከዚህ በፊትም አልነበረም፤›› በማለት አቶ ተሻገር ኅትመት መገናኛ ብዙኃኑ ላይ ያቀረቡትን ትችት አልተቀበሉትም፡፡

አቶ መሠረት፣ ‹‹ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የግሉ ፕሬስ አለ ወይ? ለ103 ሚሊዮን ሕዝብ ሪፖርተር፣ ካፒታል፣ ፎርቹን፣ ሰንደቅና አዲስ አድማስ ጋዜጦች አሉ ብሎ መናገርና እነሱም በችግር የተተበተቡ ናቸው ብሎ መወንጀሉ አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ መንግሥት ጠንካራ ፕሬስ እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተጫወተ መሆኑን ቢገልጽም፣ ሙስና አፍ አውጥቶ ሰው ሊበላ በደረሰበትና በችግር ላይ ችግር ገኖ በወጣበት ማግሥት አገሪቷ ለዚህ ሁሉ ትርምስ እንደተዳረገች አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡

ለፕሬሱ መጠናከር ትልቁን ሚና የሚጫወተው መንግሥት እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ አማረ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማቅረብ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የሴኔጋል መንግሥት ሚዲያውን ለማጠናከርና ለማስፋፋት ካለው ፍላጎት አንፃር በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚመድብ የገለጹ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከእዚያ ልምድ በመውሰድ ለሚዲያው ማደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዲያ ካውንስል መቋቋም ተገቢነት በአዋጁ ላይ የሰፈረ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን እስካሁን ድረስ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  

አቶ አማረ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚዲያ ካውንስል ይቋቋም ብሎ ቢፈቅድ ኖሮ የቂሊንጦና የቃሊቲ ጉዳይ ሊቀር ይችል እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዚህ አስከፊ ጊዜ ግለሰቦች በግሉ ሚዲያ መሳተፍ እንደማይፈልጉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ ለዚህ አገር ሊጠቅማት የሚችለው የግሉ ፕሬስ ቢሆንም፣ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ ዜጋ በአሁኑ ጊዜ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ አቶ ታምራት ኃይሉ ደግሞ በየሳምንቱ ስለሚወጣው መጽሔት ጭንቅ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ እንቀጥል ወይስ አንቀጥል በማለት ሐሳብ ውስጥ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

አቶ አማረ በጽሑፋቸው ላይ በአሁኑ ጊዜ ጋዜጠኞች ሆነው ክብርና ሞገስ ሊያገኙ የሚችሉት ቃሊቲና ቂሊንጦ ከወረዱ ወይም ደግሞ ወደ አውሮፓ ከተሰደዱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የመጡት አቶ ታምራት ደጀኔ በጉዳዩ ላይ እንደሚስማሙ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ውጭ አገር በቀላሉ ለመውጣት አንዱ መንገድም እንደሆነ አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የግሉ ፕሬስ እየተደፈቀ እንደሆነና በተቃራኒው የመንግሥት ሚዲያው እያበበ መምጣቱን የሚገልጹት አቶ ታምራት ኃይሉ፣ ለዚህ ምክንያት ደግሞ መንግሥት ለግል ሚዲያው ድጋፍ ካለማድረጉም ባሻገር የማበረታቻ ዘዴ አለመኖሩ፣ ይባስ ብሎም የመንግሥት ማስታወቂዎች በመንግሥት ሚዲያ ብቻ እንዲወጡ መደረጉ የግሉን ፕሬስ የሚጎዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ይኼንን ሁሉ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እስከ ክልልና ወረዳ ድረስ ሲያቋቁምም ዓላማውን ለማሳካት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ታምራት ኃይሉ፣ ገንዘብ ከኪሱ አውጥቶ ጋዜጣና መጽሔት የሚያሳትመው ደግሞ ሐሳቡን በነፃነት ለመግለጽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ሚዛናዊነት የምርጫ ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

አቶ ታምራት ይህን ይበሉ እንጂ ሚዛናዊነት የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚናገሩት ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዛድግ አብርሃ ናቸው፡፡ አቶ ዛዲግ ሚዛናዊነት የምርጫ ሁኔታ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ተሻገር በበኩላቸው፣ ሚዛናዊነት ሲባል ብዙ መርሆዎች ያሉትና ሚዛንን መጠበቅ የግዴታ እንጂ የውዴታ ሥራ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡  

በአሁኑ ጊዜ ያለው የፕሬስ ሕግ የማያሠራና ሚዲያው እንዳያቆጠቁጥ እንቅፋት እንደሆነ የሚናገሩት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት አስተያየት ሰጪ፣ የፕሬስ ሕጉ እንደገና መፈተሽ እንዳበት አሳስበዋል፡፡ መፈተሽና እንደገና መታየት ያለበት በአሁኑ ጊዜ ሕጉ ላይ ግልጽ የሆኑ ችግሮች ስላሉበት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የአመራር ችግር ተንሠራፍቶ እያለ ፕሬሱ ሊያድግ እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ ፕሬሱ ካደገ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል የሚያስቡ በፕሬሱ ዕድገት ላይ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደ በበኩላቸው፣ አገሪቱ ውስጥ ዘመናዊ የኅትመት መሣሪያ አለመኖርና የወረቀት መወደድ በግሉ ፕሬስ  ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሚዲያው በኩል እንደ ችግር ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ከተደራሽነት አንፃር የግሉም ሆነ የመንግሥት ሚዲዎች አዲስ አበባ ላይ ብቻ በመታጠር ተደራሽነታቸው የተገደበ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም ወደ ተቋም ደረጃ አለማደግ እንቅፋት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል፣ በኤዲቶሪያል ፖሊሲና በሙያ ሥነ ምግባር ችግሮች መተብተቡ የውድቀቱ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል፡፡

አቶ አማረ በነፃ ሚዲያ ግንባታው ላይ ሕጉ የፈቀደና የተመቸ ቢሆንም፣ መንግሥት ያወጣውን ሕግ ራሱ ተግባር ላይ እንደማያውል ገልጸዋል፡፡ አቶ ዛዲግ ግን ነቅፈውታል፡፡

አቶ ዛዲግ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን የሚቃወም ሕግ አይወጣም፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያ አዋጅና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የገመገሙት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት እንዲወጣ በግንባር ቀደምትነት የተፋለመ ነው፤›› በማለት ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ ሊጥስ የሚችልበት አግባብ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ለፕሬሱ ማደግ የመንግሥት የቁጥጥር ሥርዓት ጠንካራ መሆኑን ታዳሚዎች የጠቀሱ ሲሆን፣ በዚህ ዙሪያ ምላሻቸውን የሰጡት አቶ ዛዲግ አንድን ተቆጣጣሪ አካል ነፃ የሚያሰኙት ሁለት ነገሮች እንዳሉ ገልጸው፣ እነሱም የተቋቋመበት አዋጅና ከዚያ በኋላ ያለው ልምድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ የተከበረው የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ያለውን የፕሬስ ሁኔታ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የዳሰሰ ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ስለፕሬስ ነፃነት የተቀመጡት መርሆዎች በአፈጻጸም ወቅት በእክሎች የታጀበ በመሆኑና መንግሥት በዘርፉ ውስጥ እጁን በረዥሙ በማስገባቱ ምክንያት፣ ፕሬሱ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ማድረስ እንዳልተቻለ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የመረጃ ተደራሽነት ባለመኖሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ብሎም በመላ አገሪቱ የመልካም አስተዳደር እክል መፈጠሩን የገለጹት ታዳሚዎች፣ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የመረጃ ተደራሽነትንና የፕሬስ ነፃነትን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -