Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ታክሲዎችን በሦስት ጎራ የከፈለው አሠራር አለመግባባቶችን አባብሷል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

-‹‹130 ሚሊዮን ብር ወጪ ካደረግን በኋላ በህልውናችን ላይ አደጋ ተደቅኗል›› ያሉ የቦሌ ታክሲዎች አቤቱታ ፍርድ ቤት ደርሷል

-አቫንዛ ታክሲዎች ወደ ቦሌ እንዳንገባ የተከለከልነው ሆን ተብሎ በሚደረግ ጫና ነው ይላሉ

መንግሥት ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመስጠት ያስገባቸው 1,163 ታክሲዎች ብዙም ሳይቆዩ አነጋጋሪ ሆነው መቆየታቸው ታይቷል፡፡ ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃንን የአየር ሰዓት የተቆጣጠረው ጉዳይም ከእነዚሁ ታክሲዎች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት በአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ውስጥ የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት በመስጠት ሲያገለግሉ የቆዩ የታክሲ ባለንብረቶች ከሰሞኑ የፍርድ ዕግድ በማውጣት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያወጣውን የስምሪት ድልድል መቃወማቸው ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም ዕግዱን በማስመልከት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ዘገባውን ተክትሎም በቦሌ ኤርፖርት የቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ አባላት ያደራጇቸው ማኅበራት አመራሮች ከሪፖርተር ጋር ዕግዱን ማውጣት ስላስፈለገበት ምክንያት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኤርፖረቱ የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ የተደራጁ 454 አባላትን የሚወክሉ ስድስት ማኅበራት ሲኖሩ፣ እነዚህን ማኅበራት የሚያስተባብር የጥምረት አሠራርም አላቸው፡፡ አቶ ሳሙኤል አመነ የጥምረቱ ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፣ እዮብ ወልዳይ እና አቶ አቤሴሎም መኮንን፣ በጥምረቱ የስምሪት እንዲሁም የምክትል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ድርሻዎችን በመያዝ ይሠራሉ፡፡ ስኬት፣ መቅደላ፣ ወንድማማቾች፣ ህዳሴ፣ ጥምረትና አንድነት የተባሉትን ስድስት ማኅበራት የሚወክሉት ኃላፊዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኤርፖርት ውስጥ አብራቸው ይሠሩ በነበሩና አቫንዛ ሜትር ታክሲዎችን ለመግዛት የወጡ ከ100 በላይ ባለንብረቶች የፈጠሯቸው ጫናዎች በህልውናችን ላይ አደጋ ጋርጠዋል ይላሉ፡፡

ይኸውም ባለሥልጣኑ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በተሰጠው ውክልና መሠረት በ2007 ዓ.ም. ‹‹የሳሎን ሜትር የከተማ ታክሲ ተሽከርካሪዎች›› ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ለመፍቀድ የወጣውን መመሪያ አላከበረም የሚል ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ በቀድሞው ትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተፈርሞ የወጣው መመሪያ ቁጥር 8/2007 በግንቦት ወር ወደ ሥራ ሲገባ የታክሲ አገልግሎትን በአራት መደቦች የሚፈርጅ ትርጓሜ አስቀምጦ ነበር፡፡

በመመሪያው መሠረት፣ ‹‹የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጓሜ የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር›› በማለት የሚጀምረው ትርጓሜ፣ ‹‹ሳሎን ሜትር ታክሲ››፣ ‹‹ቱሪስት ታክሲ››፣ ‹‹አውቶሞቢል ታክሲ››፣ እንዲሁም ‹‹ሚኒባስ ታክሲ›› በማለት የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትን ተሽከርካሪዎች መድቧል፡፡ በመሆኑም ‹‹ሳሎን ሜትር ታክሲ ማለት ከ4 እስከ 7 መቀመጫ፣ የተሳፋሪውን ሻንጣ ለመጫን የሚያስችል ቦታ ያላቸው፣ ካብ ሜትር የተገጠመላቸውና በስልክ ወይም በሬዲዮ መገናኛ ወይም በአካል ጥሪ/ጥያቄ በከተማው ክልል ውስጥ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፤›› ይላቸዋል፡፡

‹‹ቱሪስት ታክሲ ማለት በአውሮፕላን ማረፊያና በባለኮከብ ሆቴሎች በመቆም በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዕውቅና ባገኙ ማኅበራት፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሙያ ፈቃድ አግኝተው ለቱሪስቱ በስምምነት በሚወሰን ታሪፍ መሠረት በውል የታክሲ አግልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፤›› ሲል ስለ ቦሌ ታክሲዎች ትርጓሜ ይሰጣል፡፡ መመሪያው ነጭና ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ፣ አራት ሰው የመጫን አቅም ያላቸውንና በተለምዶ ላዳ ታክሲ የሚባሉትን አውቶሞቢል ታክሲዎች ይላቸዋል፡፡

እነዚህ ከላይ የቀረቡት ሁለት ትርጓሜዎች ናቸው በከተማው አስተዳደር ሥር የሚገኙትን የትራንስፖርት ባለሥልጣንና የባህልና ቱሪዝም ቢሮን ካለመግባባት ውስጥ ከመክተታቸውም ባሻገር፣ ከቀረጥ ነፃ በገቡት ታክሲዎችና በቦሌዎቹ የቱሪስት ታክሲዎች መካከል እንዲሁም እነዚህ ሁለቱም ከባለሥልጣኑ ጋር በየፊናቸው ያልተግባቡባቸው ነጥቦች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆነው ይኸው መመሪያ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች አቋም

እነ አቶ ሳሙኤል እንደሚከራከሩት ከሆነ በሕጉ መሠረት በግልጽ በተጠቀሰ ቦታ፣ በተወሰነ ክልል በመቆም የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ ምክንያት እንደሌሎቹ ታክሲዎች በከተማው እየተዘዋወሩ መሥራት የማይፈቀድላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም በኤርፖርትና ሆቴሎች አካባቢ በሚወጣ ድልድል አማካይነት የሚሠሩ፣ የየራሳቸው ሕግና ደንብ ያላቸው፣ በደንብ ልብስ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የዲስፕለን ቁጥጥር በማድረግ ጭምር አባሎቻቸውን ለሥነ ሥርዓት ተገዥ በማድረግ እንደሚሠሩና የዲስፕሊን ግድፈት የፈጸሙትንም እስከ ሁለት ሳምንት በሚደርስ ቅጣት ከስምሪት የሚያግዱበት አሠራር የዘረጉ መሆናቸውን ሁሉ ይጠቅሳሉ፡፡

ይሁንና እንዲህ እየሠሩ ባሉበት ወቅት፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ በሚሽር አኳኋን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አዲስ አሠራር ማምጣቱ ከስጋት በላይ የህልውና ጥያቄ እንደጋረጠባቸው ይናገራሉ፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረት ሁሉም ታክሲዎች ወደ ኤርፖርት በመግባት መሥራት ይችላሉ የሚለው የባለሥልጣኑ አቋም ችግር ፈጥሮብናል ይላሉ፡፡ በቅርቡ በወጣው ድልድል መሠረትም ኤርፖርቱ በቀን ማስተናገድ የሚችለው ታክሲ 150 በመሆኑ፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በእኩል ድርሻ የሜትር ታክሲዎችም የቦሌዎቹም እንዲሠሩ መደልደሉ ፈጽሞ ተቀባይነት የለው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በአዲሱ ድልድል መሠረት የስድስቱ የቦሌ ታክሲዎች ማኅበር አባላት በዙር የሚደርሳቸው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሳምንት ብቻ እንደሆነ በማብራራትም የባለሥልጣኑን ስምሪት አጣጥለውታል፡፡

ከዚህም ባሻገር ባለሥልጣኑ ባወጣው አስገዳጅ አሠራር ሳቢያ አሮጌ መኪኖቻቸውን በ2002 ሞዴልና ከዚያ በላይ ባሉ መኪኖች እንዲተኩ በመባሉም አብዛኞቹ የሊፋን 520፣ 530 ሞዴሎችን፣ የቶዮታ ኤክዚኪዩቲቭ መኪኖችን በመግዛት እንዳሠማሩ የሚናገሩት የጥምረቱ ኃላፊዎች፣ እነሱም እደሌሎቹ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚዎች ባነሰ ዋጋ መግዛት ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መመሪያ የሥራ ክልልና መደባቸውን ለይቶ በማስቀመጡ፣ በዚያ ዕድል በሕጉ መሠረት ስለማይፈቀድላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይልቁንም በማኅበር ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል መንግሥት ግልጽ ባመደረገው መሠረት ከተጠቃሚነት ውጭ ለመሆን መገደዳቸውን የሚገልጹት የቦሌ ታክሲዎች፣ ሸጠው በወጡ የቀድሞ የቦሌ ታክሲዎች የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሕግ ውጭ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በመስከረም ወር ረቂቅ መመሪያ ሲያዘጋጅ፣ ቀድሞ ሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ 8/2007 የሚቃረን በመሆኑ አስተያየት እንደማይሰጡበት በመግለጽ እንዳልተሳተፉ ገልጸዋል፡፡ ይህን ቢሉም አዲሱ መመሪያ ወደ ስምሪት ተለውጦ ሁሉንም በእኩል ማስተናገድ የሚል አካሄድ ይዞ በመምጣቱ መመሪያው እንዳይተገበርባቸው ወደ ፍርድ ቤት ማቅናታቸውን የጥምረቱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ‹‹የዘርፍ ልዩነት መደበላለቅ የለበትም አልን እንጂ ሌሎች ታክሲዎች ደንበኞቻቸውን ኤርፖርት አድርሰው እንዳያወርዱም ሆነ እንዳይገቡ አልከለከልንም፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

የአቫንዛ ታክሲዎች ቅሬታ

የቶዮታ ኩባንያ ሥሪት የሆኑትን አቫንዛ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ በማስገበት የሚንቀሳቀሱ ከ100 በላይ ባለንብረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ በሁለት ማኅበራት ማለትም ቦሌ ሜትር ታክሲ አክሲዮን ማኅበርና አዲስ ሜትር ታክሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚሉ አደረጃጀቶች የተዋቀሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ባለንብረቶች ቀድሞውንም በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይሁንና መንግሥት ከቀረጥ ነፃ መኪኖችን እንዲያስገቡ በፈቀደው መሠረት አዳዲስ መኪኖችን ለመግዛት የነበሯቸውብ አሮጌ መኪኖች እንደሸጡ ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ ሜትር ታክሲ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሙላትም ሆኑ ምክትላቸው አቶ ፍቃዱ መስፍን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከመነሻውም ከቀረጥ ነፃ ዕድሉን በመጠቀም አቫንዛ ሞዴል ሰባት ሰው የሚጭኑ ታክሲዎችን የገዙት የኤርፖርት አገልግሎትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ድረስ የቀረጥ ነፃ ዕድል ለቦቴ ታክሲዎች እንዲመቻች ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን አቶ ዮናስና አቶ ፍቃዱ ይናራሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተጻፈ ደብዳቤም ‹‹ቁጥር አንድ ቦሌ ኢንተርናሽናል፣ ቦሌ አለምአቀፍ ኢንተርናሽናል፣ መቅደላ፣ ስኬት እንዲሁም ህዳሴ የተባሉ ማኅበራት በስም ተጠቅሰው የቀረጥ ነፃ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ መጠየቃቸውን አመሳክረዋል፡፡ 

ላለፉት አራት ዓመታት ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንዲፈቀድ በቦሌ ኤርፖርት የጥምር ኮሚቴው ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን የሚገልጹት አቶ ዮናስ፣ ጥያቄው ተፈቅዶ መኪኖቹ ከገቡ በኋላ ግን በከተማው ተዘዋውራችሁ ሥሩ መባላቸው ከአቫንዛ መኪኖች ጋር የማይሄድ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ለቱሪስት አገልግሎት እንጂ ለሕዝብ አገልግሎት አስበን አልነበረም ጥያቄ ያቀረብነው፡፡ ለዚያ ቢሆንማ ኑሮ ተደራጅተን ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ አውቶቡሶችን እንገዛ ነበር፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ የቱሪስት አገልግሎት ለመስጠት ስላልተፈወደላቸው ግን አቫንዛ መኪኖችን የገዙ አባላት ‹‹ባልለመዱት የሥራ መስክ›› በከተማው እየዞሩ አገልግሎት እንዲሰጡ መገደዳቸውን ኮንነዋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የባንክ ብድር ዕዳ መክፈል እየተሳናቸው እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

በዚህም ሳያበቁ በቅርቡ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ እስከ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይመለከታቸዋል ላላቸው ተቋማት የሜትር ታክሲዎች በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ትብብር እንዲያደርጉላቸው፣ በሜትር ታክሲዎቹ ጠያቂነት ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ሆኖም ይህ የትብብር ደብዳቤ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ አቶ ዮናስ ገልጸው፣ አስፈጻሚው አካል ማን እንደሆነ ግራ እያጋባቸው እንደመጣ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በአክሲዮን ማኅበርና በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩንባንያ ለመደራጀት የተገደዱትና መኪኖቻቸውን ለመሸጥ የተገደዱት አባላት በማኅበር ከቀረጥ ነፃ ማስገባት አትችሉም የሚል መመሪያ ከመንግሥት ስለተላለፈባቸው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዮናስ ይህንን በመከተል ከቦሌ በመውጣት የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የበቁት ተመልሰው መግባት እንደሚችሉ ቃል ስለተገባላቸው መሆኑንም አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የመንግሥት ቃል ከታች ሲወርድ ሊተገበር ባለመቻሉ መቸገራቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዮናስ ይህን ይበሉ እንጂ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሕጉ መሠረት የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው፣ የቦሌዎቹ ቢጫዎቹ ታክሲዎች በመሆናቸው ከእነዚህ ውጭ ላሉት የቱሪስት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ የብቃት ማረጋገጫ ከመስጠት እንደሚቆጠብ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት አገልግሎት ፈቃድ የሚሰጠውን ክፍል የሚመሩት አቶ መሳይ ደምሴ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆኑ በመመሪያ ቁጥር 8/2007ም ሆነ በአዲሱ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መመሪያ 1/2009 መሠረት የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ሆነው በትርጉም የተሰጠቀሱት ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች በመሆናቸው ከዚህ ውጭ ላሉት የብቃት ማረጋገጫ እንደማይሰጥ ግልጽ አድርገዋል፡፡

‹‹መመሪያው እነሱን [ሜትር ታክሲዎችን] አያካትትም፡፡ ሁሉም ታክሲዎችም ቦሌ ኤርፖርት ገብተው መሥራት አይችሉም፡፡ በከተማው እየዞራችሁ አገልግሎት ስጡ ስለተባሉ እኛ ፈቃድ አንሰጥም፤›› ብልዋል፡፡ አክለውም ‹‹ችግሩ እኛ ሳይሆን ባለሥልጣኑ ጋ ነው፤›› የሚሉት አቶ መሳይ፣ በቱሪስት ንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣት ፍላጎት ላላቸው ሁሉ የብቃት ማረጋገጫ ቢሮው እንደሚሰጥ አስታውሰው፣ ሆኖም ፈቃድ የሚሰጣቸው ሁሉ በመመሪያው መሠረት በቦሌ ኤርፖርትና በሆቴሎች አካባቢ በመቆም አገልግሎት መስጠት እንጂ እንደሌሎች ታክሲዎች በከተማው እየተዘዋወሩ መሥራቱ እንደማይፈቀድላቸው አሳስበዋል፡፡

የቦሌዎቹም ሆኑ የአቫንዛ ታክሲ ባልንብረቶች በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ ኤርፖርት ውስጥ መሥራት የሚገባቸው ከድኅንነት አኳያ የሚጠበቅባቸውን የሚያሟሉ፣ ብቃትና ፈቃድ ያላቸው ታክሲዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደ አቶ ዮናስም ሆነ አቶ ፍቃዱ አስተያየት ሊፋን 530 ሞዴል የሆኑት ሜትር ታክሲዎች ቦሌ ኤርፖርት ገብተው መሥራት አይገባቸውም ይላሉ፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም ነጭ በሰማያዊ ቀለም የሚቀቡና በተለምዶ ላዳ ታክሲ የሚባሉትን በመተካት የመጡት ሜትር ታክሲዎች ዱሮውንም የሥራ ክልላቸው በከተማው ተዘዋውረው መሥራት በመሆኑ ኤርፖርት ውስጥ የሚሠሩበት ሥምሪት ሊፈቅዳላቸው አይገባም ይላሉ፡፡

የዘ ሉሲ ሜትር ታክሲዎች ማኅበር ኃላፊ አቶ አንተነህ ትሪሎ ይህንን ይቃወማሉ፡፡ ሁሉም በሚገባው ልክ እኩል በመሥራት እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት የሚገልጹት አቶ አንተነህ፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣንን አቋም በመደገፍ ሁላችንም በእኩል እንድንሠራ የሚያደርግ አሠራር ለመከተል መነሳቱ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ይሁንና የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ ሊደረግ የነበረውን የኤርፖርት ስምሪትም ሆነ የኤርፖርት ታክሲዎችም ወደ ከተማው እየዞሩ ይሥሩ የሚለውን የባለሥልኑን አቋም በመቃወም ወደ ፍርድ ቤት ያቀኑት ቢጫዎቹ የቦሌ ታክሲዎች፣ ሥምሪቱን ማሳገዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ሳቢያም ለተፈጠረው ችግር የዘ ሉሲ ታክሲዎች ማኅበርን ይቅርታ መጠየቁን እንደገለጹ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወጣው የሥምሪት ዕግድ ሳቢያ ለደረሰባቸው ኪሳራም ካሳ እንደሚጠይቁ መገልጻቸውን ሪፖርተር ዘግቦ ነበር፡፡

በአራት ወገን የተከፋፈውን አለመግባባት በማስመልከት በተለይም በ2007 በወጣውና በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በወጣው መመሪያ ላይ የባለሥልጣኑን አስተያየት ለማካተት ተሞክሮ ነበር፡፡ ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ከባለሥልጣኑ ሥምሪት ክፍል ለመረዳት የተቻለው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ምክንያት ምላሽና አስተያየት ለመስጠት እንደሚያስቸግር ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ እልባት እስኪሰጠው ድረስ ባለሥልጣኑ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግረው አስታውቋል፡፡

በአዲሱ የባለሥጣኑ መመሪያ መሠረት የብቃት ማረጋገጫ ሰጪነት ሚናው የተቀነሰበት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅሬታውን አስታውቆ እኛን ከሥርዓቱ ውጭ ማድረግ ተገቢ አልነበረም ሲል በአቶ መሳይ በኩል ገልጿል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ መሳይ ዘርፉን የተመለከተ ጥናት በቢሮው እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጥናት አሁን ለተነሱት አለመግባባቶች መፍትሄ እንደሚያመላክት ተስፋ አላቸው፡፡

በአራቱም አቅጣጫ የሚነሱት ቅሬታዎች ማጠንጠኛቸው ግን የመንግሥት አሠራር ላይ ይሽከረከራሉ፡፡ በፌደራልና በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መካከል ስላለው የአሠራር ክፍተትና አለመናበብ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ከላይ ያለው አካል ያወጣውን መመሪያ የታች ተጠሪው መሥሪያ ቤት በምን መልኩ እንደሚተገብረውና የራሱን አካሄድ እንዴት እንደሚያራምድ ያሳየ አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ ወደላይም ወደ ጎንም በማይነጋገሩ መሥሪያ ቤቶች አማካይነት በተፈጠረው አመግባባት በርካቶች ባለንብረቶች ስጋት ውስጥ እንዲወድቁና፣ በመንግሥት አሠራር ላይ እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የታክሲ ባለንብረቶች ምሳሌ ዋቢ ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በከተማው ከሚታየው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ይልቅ በቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ለመሥራት የሚታየው ግብግብ ሌላም ለጥያቄ የሚጋብዝ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ የፌደራሉም ሆነ ውክልና የሰጠው የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአብነት ያህል በየካቲት ወር መጀመሪያ አስገዳጅ እንደሆነ መግለጫ ሰጥተው በሜትር ታክሲዎች ላይ የጣሉትን የአገልግሎት ታሪፍ በአግባቡ መተግበር አልቻሉም፡፡ በቀረበባቸው ተደጋጋሚ አቤቱታ ሳቢያም ማሻሻያ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ነገር ግን አንዱን ችግር በቅጡ ከመፍታት ይልቅ ሌላውንም እየደረራረቡ እንደሚገኙ ስሞታ እየቀረበባቸው ይገኛሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች