ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በተመራው ስብሰባ፣ የጋዜጣ አሳታሚዎችና የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤቶች የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ መከሩ፡፡ ለዚህም ሲባል ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተገልጿል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ በተደረገው ስብሰባ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎቹ ረዥም ጊዜያቸውን የወሰዱት፣ በሚዲያ ሥራ ላይ ስለሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ በመወያየት ነበር፡፡
ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት በጽሕፈት ቤቱ ባለሙያዎች በቀረበ አጭር የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር ከመንግሥት በኩል ድጋፍ እያገኘ እንዳልሆነና ይኼም በአገሪቱ የግብር ሥርዓት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ሕጎች ላይ እንደሚስተዋል ተገልጿል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ ጥናቱ በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኘው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከኅትመት ጥራትና መዘግየት ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለበት፣ በዚህም ምክንያት በጋዜጦች ገበያ ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኅትመትና የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች፣ በመንግሥት በኩል እንደ ቀረጥ ነፃ የመሳሰሉ ማበረታቻዎች አዲስ ለሚገቡም ሆኑ በሥራ ላይ ላሉት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፋና ብሮድካስቲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመልስ በመገናኛ ብዙኃን ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቅድ ለማውጣት አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ምክንያቱ ደግሞ ሥራው ራሱ እንደ ኢንቨስትመንት ስለማይቆጠር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እነዚህ ተቋማት የተጋነነ የሚባል ግብር እንደተጫነባቸው፣ ሌላው ቢቀር ማስፋፋት ቢፈልጉ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ግብር እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
እንደ ፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ገለጻ፣ ከግብር ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ችግሮች በጣም ውስብስብ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የግብር ሥርዓት የመገናኛ ብዙኃን እንዴት እንደሚሠሩ መረዳት እንደሚቸግረው አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡
‹‹ግብር አስከፋዮች እኛን ከማርስ እንደመጣን ነው የሚቆጥሩን፤›› ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በስብሰባው ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ ምንም ዓይነት ድጋፍ አላገኘም ለማለት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኢንዱስትሪው ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ነው ብለዋል፡፡
ነገር ግን አቶ ወልዱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በሚያቀርቡት የዜና ጥራትና ዓይነት ከውጭ መገናኛ ብዙኃን ፉክክር እንዳለባቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ መሆናቸው ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡
‹‹ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሪ እንኳን እያመጣ አይደለም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ታምራት ሲመልሱ፣ ዘመናዊ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት በሌለበት የመገናኛ ብዙኃን ውጭ አገር ድረስ ተደራሽ ቢሆኑም ገቢውን ለመሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ልዑል ገብሩ በበኩላቸው፣ ፈቃድ ከተሰጣቸው ዓመታት ያስቆጠሩ ጋዜጦችና ወደ ሦስት የሚሆኑ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ባለው የድጋፍ ማነስ እስካሁን ሥራ እንዳልጀመሩ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ሌላው አከራካሪ ነጥብ የነበረው ከማስታወቂያ ፍትሐዊ ክፍፍል ጋር የተነሳው ነጥብ ሲሆን፣ ሦስት የተለያዩ ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ አንዱ ወገን ለመገናኛ ብዙኃን የሚሰጡ ማስታወቂያዎች ለሁሉም በፍትሐዊነት መከፈፈል አለበት ብሎ ሲከራከር፣ አቶ ታምራት ይኼንን ሐሳብ ተቃውመውታል፡፡
ከሁለቱ ሐሳብ በተለየ ማስታወቂያዎች ፍትሐዊነትንና የመገናኛ ብዙኃን ብቃት ላይ መሠረት በማድረግ መሰጠት አለባቸው ተብሏል፡፡
በመጨረሻም ስብሰባውን የመሩት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ ጉዳዩን ይከታተላል የተባለው ኮሚቴ እንዴት እንደሚቋቋም ጽሕፈት ቤታቸው እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት አንድ ወጥ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፀድቀው በሥራ ላይ በሚገኙት የተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ መንግሥት ስለመገናኛ ብዙኃን አመራር ያለው አቋም ሰፍሮ ይገኛል፡፡