በቅርቡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተብሎ የተደራጀው የቀድሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት (ኪቤአድ)፣ በ2000 ዓ.ም. የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ሆኖ እንዲደራጅ በመወሰኑ የፈረሰው የሠራተኛ ማኅበር በድጋሚ እንዲደራጅ ተጠየቀ፡፡
በወቅቱ በሠራተኛ ማኅበሩ የፈረሰው፣ ኪቤአድ በአዲስ አደረጃጀት ከመንግሥት የልማት ድርጅትነት መዝገብ ተሰርዞ በሲቪል ሰርቪስ ሕግ እንዲመራ በመደረጉ ሳቢያ፣ በሲቪል ሰርቪስ ማኅበራት ማደራጀት ስለማይፈቀድ ነው፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ቁጥር 398/2008 የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሆኖ በመደራጀቱ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በድጋሚ ተመዝግቧል፡፡
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ሥር የሚገኘው የቱሪዝም፣ የሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አበበ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ለሚመራው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ፣ የሠራተኛ ማኅበሩ በድጋሚ እንዲደራጅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹ቀደም ሲል የነበረው የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች ማኅበሩ ተጠናክሮ እንዲመጣ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ይመቻችላቸው፤›› ሲሉ አቶ አስፋው በላኩት ደብዳቤ ቦርዱን ጠይቀዋል፡፡
ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. የማኅበሩ የቀድሞ አመራሮች ለስብሰባ ተጠርተዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኛ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አረጋዊ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሠራተኛው ማግኘት ያለበትን ጥቅማ ጥቅሞች አላገኘም፡፡ አሁን ግን ማኅበሩ በድጋሚ ተጠናክሮ የሚመጣ በመሆኑ የተሻለ ጥቅማ ጥቅሞች፣ ሕክምና፣ የትምህርት ዕድልና የመሳሰሉትን ሊያገኝ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶችን እንዲገነባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የወደፊቱን ሥራቸውን በተመለከተ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡