በርካታዎቹ የአፍሪካ አገሮች በዓለም ላይ እጅግ ደሃ ተብለው ከሚመደቡ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ፡፡ በአኅጉሩ ድህነት መንሰራፋቱንና የኢኮኖሚ ለውጥ አለመምጣቱን ለየት የሚያደርገው፣ አፍሪካ የነዋሪዎቿን ሕይወት ሙሉ በሙሉ መቀየር የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሀብት ባለፀጋ መሆኑ ነው፡፡ ለአብነት ያህል አኅጉሩ ከዓለም የነዳጅ ሀብት ውስጥ 12 በመቶውን፣ ከዓለም የወርቅ ክምችት ውስጥ 40 በመቶውን፣ እንዲሁም በዓለም ላይ ካለ ለግብርና ሥራ አመቺ ከሆነ መሬትና ደን ውስጥ ሁለት ሦስተኛውን ይዟል፡፡
እንደ አለመታደል ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች አኅጉሩ ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገኘውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ እያገኘ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ላይ የተሠሩ ጥናቶችና ምርምሮች በአኅጉሩ ድህነት ለመንሰራፋቱና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለመኖሩ ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውን፣ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ለይተው ያስቀምጣሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ለግሉ ዘርፍ ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎች አለመመቻቸታቸው፣ ውጤት አልባ አመራር፣ ደካማ ተቋማት፣ ሙስና፣ ደካማ የፖሊሲ አፈጻጸም፣ የፖሊሲ ቀጣይነት አለመኖርና ፍትሐዊ ያልሆነ የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገባቸውን ዋጋ ባለማግኘታቸው አኅጉሩ በዓመት 50 ቢሊዮን ዶላር ያጣል፡፡ ይኼም አፍሪካ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ከውጭ የልማት ዕርዳታ በድምሩ ከምታገኘው ይበልጣል፡፡ በተጨማሪም እንደ ኦክስፋም ግምት ቀጥተኛ ወጪዎችን ሳይጨምር በአፍሪካ ከተፈጥሮ ሀብቶች ጋር የተያያዙ ግጭቶች በዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣሉ፡፡
እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ “የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደር” በሚል ርዕስ በባህር ዳር ከተማ ከሚያዝያ 15 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ዓመታዊው የጣና ከፍተኛ ደረጃ የአፍሪካ የደኅንነት ፎረም በስፋት መክሯል፡፡ የጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋምና እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተነሳሽነት የተቋቋመ ነው፡፡ ፎረሙ ለአፍሪካ ችግሮች “አፍሪካዊነትን ማዕከላዊ ያደረጉ መፍትሔዎች” ለመስጠት ያለመም ነው፡፡ ይኼን ዓላማውን ለማሳካትም የአፍሪካ ውሳኔ ሰጭዎችን፣ የሰላምና ደኅንነት ባለድርሻ ቡድኖችን፣ እንዲሁም ሰፊውን የድጋፍ መሠረታቸውን መደበኛ ባልሆነ መንገድ አሰባስቦ በግልጽ ውይይት እንዲሳተፉ ለማድረግ ይጥራል፡፡
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የጣና ፎረም ቦርድ ሊቀመንበር ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ ከዚህ ቀደምም እንደተለመደው ዘንድሮም በአፍሪካ ያለውን ወቅታዊ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታን አስቃኝተዋል፡፡ በዚህም አፍሪካ በራሱ ካለበት መጠነ ሰፊ የሰላምና ደኅንነት ችግር ባሻገር በዓለም ላይ እየዳበረ የመጣው የሰላምና ደኅንነት አዝማሚያ ለአፍሪካም አሥጊ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ኦባሳንጆ፣ “በበቂ ሁኔታ ሊበራል፣ የተረጋጋና ተገማች ከነበረው ዓለም ወደ ያልተረጋጋ፣ የማይገመትና በስሜት የሚነዳ ዓለም እየሄድን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዓለም ደግሞ ለየትኛውም አገርና አካባቢ አደጋ ነው፡፡ አፍሪካ ደግሞ በግልጽ በሚታወቀው ድክመቱ የተነሳ እንዲህ ዓይነት ዓለም ሊመኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም አኅጉሩ ካለበት አሥጊ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ አንፃር እስረኛና ተጠቂ ያደርገዋል፤” ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የጣና ፎረም በአፍሪካ ስላለው የነዳጅ፣ ጋዝና ማዕድናት አስተዳደር ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን እንደ መሬት፣ ውኃ፣ ውቅያኖስ፣ ደንና ብዝኃ ሕይወት ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደርንም በማካተት ውይይት ተደርጓል፡፡ ፎረሙ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም የሚደረጉ ጥረቶች የውጥረትና የግጭት ምንጮች መሆን የቀጠሉበትን ምክንያቶች ለመረዳትና ለመግለጽ፣ እንዲሁም በአኅጉሩ ሰላምና ደኅንነት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለማሳየትም ጥረት አድርጓል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ እ.ኤ.አ. በ2016 ያወጣው ሪፖርት ባለፉት 60 ዓመታት በአፍሪካ ከተከሰቱ ግጭቶች መካከል ከ40 በመቶ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት መነሻቸው ከተፈጥሮ ሀብቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ኮሙዩኒቲ (ሳድክ) ዋና ጸሐፊ ስቴርጎሜና ላውረንስ ታክስ (ዶ/ር) የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ለአኅጉሩ ከጥቅም ይልቅ፣ ጉዳት እያመጡ ያለው ደካማና ውጤት አልባ የአስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋቱ እንደሆን አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነርና የሰላምና ደኅንነት ተንታኝ ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር) ከፎረሙ አወያዮች አንዱ ነበሩ፡፡ ሰለሞን የአፍሪካ ኮሚሽን ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ፣ የአካባቢ ጥበቃና የሰብዓዊ መብት የሥራ ቡድን ሊቀመንበርም ናቸው፡፡ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የፖሊሲ ጥናት አማካሪ ቲንክ ታንክ አማኒ አፍሪካ ሪሰርች ኃላፊም ናቸው፡፡
“የተፈጥሮ ሀብቶች ከዓለም ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ ግማሹን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አፍሪካ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤” ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይህም እንደ ቻይና ያሉ በመመንደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የኢኮኖሚ እምርታ እንዲያሳዩና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ከድህነት ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ያስታውሳሉ፡፡
የፎረሙ ተሳታፊዎች በአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚወጡበት፣ የሚከፋፈልበትና ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች እንዳሉባቸው አብራርተዋል፡፡ እነዚህን ሀብቶች ከማስተዳደር ጋር በተገናኘ የፈቃድ አሰጣጥ፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ፍለጋ፣ ውልና አወጣጥ፣ የገቢ ምንጭና ክፍፍልን በሚመለከት የግልጽነትና የተጠያቂነት ችግር እንዳለ አመልክተዋል፡፡ የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች በአብዛኛው በውጭ ዜጎችና ድርጅቶች ባለቤትነት ሥር መተዳደራቸውም ትልቅ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡ ኦባሳንጆ የአፍሪካ አገሮች የውጭ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ፍላጎት እስረኛ በሆኑበት ሁኔታ ግልጽነት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ማስፈን አዳጋች እንደሆነ ሞግተዋል፡፡
ከጣና ፎረም መደበኛ ተሳታፊዎች አንዱ የሆኑት የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የውጭ ድርጅቶች በማይገባ ዋጋ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠቀም ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ ፔትሮሊየም፣ ዩራኒየም፣ ወርቅና ብረት የሚገባቸውን ዋጋ እስኪያገኙ ድረስ መሬት ውስጥ እንደሚቆዩም ገልጸዋል፡፡ “የራሳችንን የኑኩሌር ማዕከል እስክናቋቁም ድረስ ዩራኒየማችን መሬት ውስጥ ይቆያል፤” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን፣ “ሙሴቬኒ እንዳሉት የተፈጥሮ ሀብቶችን ለዓመታት ሳንጠቀምባቸው መቆየት አንችልም፤” ሲሉ የሐሳብ ልዩነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላው ተሳታፊዎቹ ትኩረት ያደረጉበት ነጥብ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገባቸውን ሰዎች ተጠቃሚ እያደረጉ አለመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየተደረጉ ያሉ ኢንቨስትመንቶች አካባቢ ላይ ዘላቂ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ኦባሳንጆ ለአብነት ያህል የነዳጅ ፍለጋ በናይጄሪያ ኒጀር ደልታ ክልል በአካባቢ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ጠቅሰዋል፡፡
የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት በአፍሪካ ያለውን ደካማ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ ይበልጥ እንዳባባሰውም ተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም እንደ ኮንጎ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ ያሉ አገሮች እየተሰቃዩ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ የውጭ ኃይሎች በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ያላቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲሉ የራሳቸውን ወታደራዊ ኃይል እስከ ማሰማራት እንደ ደረሱም ተመልክቷል፡፡
ሰለሞን፣ “በአፍሪካ ስለተፈጥሮ ሀብቶች ስናወራ ሁሌም የምናነሳው እነዚህ ሀብቶች ከአፍሪካ ስለሚወጡበት መንገድ ነው፡፡ እዚሁ አፍሪካ እሴት ተጨምሮባቸው ፕሮሰስ ስለሚደረጉበት መንገድ አንወያይም፤” ሲሉ መቁመዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ ከዘረዘሯቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል ዋነኛው በፍጥነት አቅምን መገንባት ነው፡፡ በተለይ ከውል ድርድርና አስተዳደር ጋር የተያያዘው አቅም ግንባታ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይችል ብዙዎች አሳስበዋል፡፡ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍን በድጋሚ መቃኘት አስፈላጊ መሆኑም ተሰምሮበታል፡፡ አገሮቹ በተናጠል አቅማቸውን ከማሳደግ ይልቅ በጋራ በትብብር ቢፈጽሙት የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡም ተመክረዋል፡፡
በአፍሪካ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ተፈጥሮ ሀብቶችን የተመለከቱ ውሎች ሁለቱንም ተዋዋይ ወገኖች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ አይደሉም ተብለው ይተቻሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም በድርድር ላይ የሚገኙ ረቂቅ ውሎች የአፍሪካ መንግሥታት በቀላሉ የሚረዷቸው እንዳልሆኑ ተመልክቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ችግር እንደገጠማት አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ ማዕድን በማውጣትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለባትን ችግር ለመወጣት፣ አገሮቹ ጥረቶቻቸውን ማቀናጀታቸው የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ “ጥቂቶቻችን ብቻ ትክክለኛ የተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደር መዘርጋታችን በቂ አይደለም፡፡ ሁላችንም ልክ መሆን አለብን፡፡ አንዱ አካባቢ ስህተት ቢፈጠር በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሚሊዮኖችን መንካቱ አይቀርም፤” ብለዋል፡፡ ትብብርን በተመለከተ ሰለሞን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይስማማሉ፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶች ውስብስብ በመሆናቸውና የተሻለ የመደራደር አቅም ላለው ስለሚያደሉ፣ በትብብር አቅም መገንባትና አስፈላጊ ከሆነም ወደ ውጭ በማየት መፍትሔ መፈለግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡.