Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ የንግድ ምልክቱንና ስያሜውን ለወጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመሪያው የግል ባንክ በመሆን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የንግድ ምልክትና የስያሜ ለውጥ ማደረጉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ላለፉት 22 ዓመታት ሲገለገልበት የነበረውን የኩባንያ አርማና ምልክት መቀየሩን ባለፈው ዓርብ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ አድርጓል፡፡ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የንግድ ምልክትና ማሻሻያ የተደረገበት ስያሜ ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ ከዚህ በኋላ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለው የባንኩ መጠሪያው ተሻሽሎ ‹‹አዋሽ ባንክ›› ብቻ እየተባለ እንደሚጠራ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

የአርማ ለውጡን በተመለከተም፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የሚለው መጠሪያው ሲጻፍ በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ (AIB) የሚል ምህጻረ ቃል የነበረበትን አርማ በማስቀረት በአዲስ አርማ ተክቷል፡፡ እስካሁን በሥራ ላይ የነበረው አርማ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሰረፀ ቢሆንም፣ ለውጥ ማድረጉ ባንኩን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር ብሎም እ.ኤ.አ. በ2025 በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አሥር ምርጥ የግል ባንኮች መካከል ለመሰለፍ የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር ከሚረዱት መካከል የአርማና የስያሜ ማሻሻል አንዱ መንገድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ ‹‹ራዕይ 2025›› የሚል ስያሜ የሰጠውን ጥናት አካሂዷል፡፡ በጥናቱ መሠረትም አዋሽ ባንክ አሁን የደረሰበትንና መጪውን ጊዜ ማዕከል በማድረግ ለውጡ መተግበሩም ተገልጿል፡፡

ባንኩ ያስጠናውን ጥናት ለመተግበር ከሚያስፈልጉት መካከል በየጊዜው እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት በዘመናዊ አገልግሎትና በሰፊ ተደራሽነት ማርካት እንዳለበት አመላክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ባንኮች መካከል እየተጠናከረ የመጣውን ብርቱ ውድድር፣ ወደፊትም ከውጭ ባንኮች ሊመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ፈተና ባንኩ መቋቋም የሚችልበት አቋም ላይ እንዲደርስ ግንዛቤ በመውሰዱ ጥናቱን ማካሄዱና ለውጦችን መተግበር መጀመሩን አቶ ፀሐይ ተናግረዋል፡፡

የባንኩን የወደፊት አቅጣጫ በዘመናዊ መንገድ ለመምራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ እየሠራ መሆኑ የተነገረለት አዋሽ ባንክ ይፋ ያደረገው አዲስ አርማ የቀደመውን እንዲተካ ያማከረው ‹‹KMPG›› የተባለው ኩባንያ ሲሆን፣ ለለውጡም ኩባንያው ያቀረበው ሐሳብ መነሻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አርማው ከመጽደቁ በፊት በባንኩ እንደተመከረበትም አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ አርማዬ ይሆናል ያለውን አዲሱን የንግድ ምልክት ለማሠራት አምስት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን አወዳድሯል፡፡ አርማው ለማሠራት በወጣው ጨረታ ያሸነፈው፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን በናይሮቢ ያደረገው የኬንያው ብራንድ ኢንተግሬትድ የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ኩባንያው ልዩ ልዩ የንግድ አርማዎችን በመሥራት ልምድ ያለው ነው፡፡ በአምስት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባንኮች አርማዎችን መሥራቱም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ስያሜ ከበፊቱ አጥሮ፣ አርማውም ቀላል በሚባል ዲዛይን ተቀይሮ መቀረጹን የባንኩ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ስለስያሜ ለውጡ ማብራሪያ ሲሰጥ እንደተባለው ‹‹አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ›› ከሚለው መጠሪያ ይልቅ አዋሽ ባንክ የሚለው በአጭሩ ባንኩን ገላጭ ሆኖ ስለተገኘ ተፈላጊነቱ ተብራርቷል፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ኅብረተሰቡም ከዚህ ቀደም በነበረው ልማድ መሠረት ባንኩን የሚጠራው ‹‹አዋሽ ባንክ›› እያለ በመሆኑም ጭምር የተደረገው ለውጥ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አማካሪ ኩባንያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ ባንኮች ሳይቀሩ ኢንተርናሽናል የሚል ቅጽል እንደሌላቸው፣ ይህም የባንኮቻቸው ስያሜ በቀላሉ በደንበኞቻቸው ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ እንደሚያግዝ በማመላከቱ፣ በዚሁ መሠረት የባንኩ መጠሪያ አዋሽ ባንክ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል ተብሏል፡፡

የባንኩ የብራንድ ቃል ኪዳንም (Brand Promise) ለኅብረተሰቡ ግልጽና ቀጥተኛ መልዕክት የሚያስተላልፍ፣ የባንኩን ራዕይና ሥራ በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲሠራ መደረጉን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድና በሥራ አመራሩ መካከል ውይይት ተደርጎም በአዲሱ የብራንድ ጥናት መሠረት የባንኩ የብራንድ ቃልኪዳን ከአዋሽ ወንዝ ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል፡፡ ይህም አዋሽ ባንክ ልክ እንደ አዋሽ ወንዝ ኅብረተሰቡን የሚያገለግል፣ አሳዳጊና ለስኬት የሚያበቃ እንደሆነ ለማመላከት የተደረገ ነው በማለት አቶ ፀሐይ አብራርተዋል፡፡

የባንኩ የኮርፖሬት ቀለሞችም ጥልቅ ሰማያዊና ብርቱካናማ እንዲሆኑ፣ የባንኩን ምልክት በግልጽና በቀላሉ ለመረዳት እንዲያስችሉ፣ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊያስታውሰው ታስቦበት እንደተሠራ ተብራርቷል፡፡

አዋሽ ባንክ ኅዳር 1987 ዓ.ም. በ486 ባለአክስዮኖች በ23.1 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ የግል ባንክ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ3,600 በላይ ባለአክስዮኖች ያሉት ይህ ባንክ፣ የተከፈለ ካፒታሉ 2.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሀብት መጠኑ፣ በብድር ክምችቱና በዓመታዊ የትርፍ መጠኑ ከ16ቱ የግል ባንኮች ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 1.04 ቢሊዮን ብር በማትረፉ ቀዳሚ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህም ከግል ባንኮች ከታክስና ከተንቀሳቃሽ በፊት ዓመታዊ ትርፉን አንድ ቢሊዮን ብር በማድረስ የመጀመሪያው ባንክ እንዳደረገውም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከ293 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት አዋሽ ባንክ፣ ከ6,400 በላይ ሠራተኞችንም ያስተዳድራል፡፡

ባንኩ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን አርማውንና ስያሜውን በአዲሱ አርማና ስያሜ በየቅርንጫፎቹ የመተካት ሥራም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንደሚጀመር ሲያስታውቅ፣ በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ኢጣፋ፣ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለአክስዮኖች በመገኘት አዲሱን የባንኩን መለያ አርማ ይፋ አድርገዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች