Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጅ ይባርክ የሚያሰኙ የአገር ምርቶች!

የሠርግ ወቅት እንደመሆኑ እስካሁን ሁለት የሠርግ ጥሪዎች ደርሰውኛል፡፡ አንደኛው የሥራ ባልደረባዬ ባለፈው ሳምንት፣ ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንድገኝ የተጋበዝኩበት ነው፡፡ የባልደረባዬ የሠርግ ጥሪ ከደረሰኝ ሰነባብቷል፡፡ ወዲህ ወዲያ ስባዝን ሳይታሰብ የሠርጉ ቀን ድቅን አለ፡፡ በሠርጉ ላይ ለመታደም ሳስብ ስለምለብሰው ልብስ ማውጠንጠን የጀመሩኩት ግን በመጨረሻው ሰዓት ላይ ነበር፡፡ ጋብቻው በሚካሄድበት ዕለት ማለት ነው፡፡

የክት ልብሴን መርጬ ከለበስኩት ልብስ ጋር ሊሄድ የሚችል መጫሚያ ግን አልነበረኝም፡፡ መጫሚያዎቼ እርጅና የተጫጫናቸው፣ ለዕለቱ አለባበሴም የተመቹ አልነበሩም፡፡ ነገሬ ሁሉ ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንደሆነብኝ ሳውቅ፣ መፍትሔው እንደምንም ብዬ ጫማ መግዛት ብቻ ሆነ፡፡ ያልታሰበ ወጪ ማለት ይኼ ነው፡፡

ዓውደ ዓመት የደቆሰው ኪሴ ረብጣ የሚቆጠርበት ጫማ ሊያስገዛኝ ባይችልም፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለዕለቱ አለባበስ የሚስማማ ጫማ ለመግዛት ግን እንደሚያስቸለኝ በመገመት ለመግዛት ወሰንኩ፡፡ ለስምንት ሰዓት ጥሪ ረፋዱ ሲደርስ ጫማ ልገዛ ወጣሁ፡፡

ሳሪስ አካባቢ ካሉ የጫማ መደብሮች በብዛት የአገር ውስጥ ጫማ ወደ ሚሸጥበት ወደ አንዱ ጎራ አልኩ፡፡ መደብሩ በልዩ ልዩ ጫማዎች ተሞልቷል፡፡ በቆይታዬ ጥቂት የማይባሉ ሸማቾች ወጣ ገባ ሲሉ በማየቴ በርካታ ደንበኞች እንዳሉት ታዝቤለሁ፡፡ አብዛኞቹም የምርጫቸውን ገዝተው ወጥተዋል፡፡ እኔም ለመግዛት ያሰብኩትን ጫማ በማገላበጥ ተመልክቻለሁ፡፡ አምስት የተለያዩ ጫማዎችን ተመለከትኩ፡፡ ጫማዎቹ በሙሉ የአገር ውስጥ ናቸው፡፡ በጥሩ ዲዛይን የተሠሩ አሪፎች ነበሩ፡፡

በጣም የገረመኝ ግን የጫማዎቹ ዋጋ ነው፡፡ በንፁህ ቆዳ የተሠሩት ጫማዎች ከፍተኛ ዋጋቸው 700 ብር ነው፡፡ የአብዛኛዎቹ ዋጋም ከ400 እስከ 600 ብር ባለው ውስጥ የሚገኝ ነበር፡፡ የምፈልገውን ጫማ ባገኝም የአገር ውስጥ ጫማዎች የጥራት ደረጃና ዋጋቸው አስደምሞኝ፣ እንደው ለምርጫም እገረ መንገዴንም የምርቶቹን ጥራት ለመፈተሽ ወደድኩና ሌሎችንም የጫማ መደብሮችን ለመቃኘት ወደድኩ፡፡ በአካባቢው  የአገር ውስጥ ጫማ የሚሸጥባቸውን መደብሮች በጥቂቱ አዳረስኩ፡፡ አራት መደብሮችን አይቻለሁ፡፡ ቅኝቴ የአገር ውስጥ ጫማዎች አሪፍ እየሆኑ መምጣታቸውን እንድገነዘብ ረድቶኛል፡፡ በእርግጥ ብዙ መሻሻል ቢኖርባቸውም በአምስቱ መደብሮች ያየሁት ግን ‹‹በአገሬ ምርት እኮራለሁ፤›› የሚለው መፈክር ከአንገት በላይ ሳይሆን ከልብ በተግባር እየታየ መምጣቱን እንዳምን አስገድዶኛል፡፡

በገበያ ቅኝቴ ወቅት በአንዱ መደብር ውስጥ ካየሁት ጫማ ላይ ዓይኔ አረፈ፡፡ በእርግጥ በዕለቱ ለመግዛት ካሰብኩት የጫማ ዓይነት ጋር የሚገጥም አይደለም፡፡ ምርጫዬም አልነበረም፡፡ ጫማው ለጨርቅም ሆነ ለጅንስ ሱሪዎች ይስማማል፡፡ ዲዛይኑ ያምራል፡፡ ለወጣትም ለጎልማሳም የተመቸ ነው፡፡ ጫማው ትኩረቴን የሳበው ከሁለት ሳምንታት በፊት ወዳጄ ‹‹የውጭ ጫማ›› መሆኑን ገልጾልኝ ጥሩ ጫማ መግዛቱን አድንቄለት ስለነበር ነው፡፡ በመደብሩ ያየሁት ጫማ ወዳጄ የውጭ ጫማ ያለው ስለመሆኑ ጥርጣሬ አልገባኝም፡፡ በሺሕ ብሮች እንደገዛው ስለነገረኝም ይገባዋል ማለቴንም አስታውሳለሁ፡፡

ይህንኑ ጫማ አበክሬ ተመለከትኩ፡፡ የጫማው የመሸጫ ዋጋ ግን ወዳጄ ከነገረኝ ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ የጫማው ዋጋ 550 ብር ይላል፡፡ ደውዬ ብጠይቀው በጫማው በመደነቄ ምክንያት ዋጋውን ከፍ እንዳደረገው ገለጸልኝ፡፡

ይህ ለሁላችንም ምልካም ዜና ነው፡፡ ጠሩ ለውጥ አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን አጋጣሚ መልካም ነገር ቆጥሬ ዓይኔ አርፎበት የነበረውን ጫማ በ550 ብር ገዝቼ ወጣሁ፡፡ የተገዛው ጫማ ከአለባበሴ ጋር ሄዷል፡፡ ተመችቶኛል፡፡

ወደ ተጠራሁበት ሠርግ አቀናሁ፡፡ አዲስ ጫማ መጫማቴን የተረዱ ጓደኞቼ አሪፍ ጫማ መግዛቴን ሲናገሩ፣ የልብ ትርታቸውን ለማዳመጥ እንደ ወዳጄ ትክክለኛውን ዋጋ ትቼ የሌለ ዋጋ ነገርኳቸው፡፡ 1,400 ብር ነው የገዛት አልኩ፡፡ የተከራከረኝ አልነበረም፡፡ ቆይቼ ግን ትክክለኛውን ዋጋ ነገርኳቸው፡፡ በአገር ውስጥ የተሠራ መሆኑንና የዕለቱ የገበያ ቅኝቴን በሙሉ አብራራሁ፡፡ የአገር ውስጥ ጫማ እንዲህ ከሆነ ጥሩ ነው ከሚለው አስተያየት ጀምሮ ‹‹ነገ ብትንትኑ ይወጣል›› እስከሚለው የሥጋት አስተያየት ድረስ ሐሰቦች ተሰነዘሩ፡፡ ‹‹ሸማቹ ብዙ አላስተዋለውም እንጂ ጥሩ ጥሩ የአገር ውስጥ ጫማዎች ገበያው ላይ አሉ፤›› ያለኝም ነበር፡፡ ለውጭ ገበያ ተብለው የሚመረቱም አሉ በማለት አከለልኝ፡፡ ባይገርማችሁ እንደሰዉ አቅም 250 ብር ድረስ የሚሸጡ ጫማዎችን በመደብሮቹ አይቻለሁ፡፡ በእርግጥም 250 ብር የሚባለው ጫማ ከዚያ በለጠ ዋጋ ቢሸጥ ይገባዋል፡፡

የአገር ውስጥ ጫማዎች የቱንም ያህል ቢለወጡ ትኩረት ያገኙ አይመስሉም፡፡ ይልቁንም የቱርክ፣ የጣሊያን፣ የታይላንድ፣ የታይዋንና የቻይና ጫማዎች ገበያውን ይዘዋል፡፡ በገበያው የሰፈሱት የውጭ ጫማዎች በጥንካሬም ሆነ በዋጋቸው ከእኛዎቹ ምርቶች ጋር አይደራረሱም፡፡ የእኛዎቹ ‹‹ይቦንሷቸዋል››፡፡

የአገር ውስጥ ምርቶች ብዙ እንደሚቀራቸው አይካድም፤ ይሁንና በምርጫ ለመግዛት የምንችላቸው ምርቶች ግን እየወጡ ነው፡፡ የበለጠ መሻሻል የሚያስችል ዕድል አላቸው፡፡ ለወደፊቱ ግን ተስፋ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን መልካም ዕድል ለመጠቀም የአገር ውስጥ ጫማዎች በተለየ መንገድ መተዋወቅ አለባቸው፡፡ በጫማ ጥራት እዚህ ደርሰናል መባል አለበት፡፡ አምራቾቹ የአገር ውስጥ የጫማ ግብይትን ለማስፋት የገበያ ስትራቴጂያቸውን መለወጥ አለባቸው፡፡ እንደ አልባሳት ጁሉ ሙሉ የጫማ ፋሽን ትርዒት ተዘጋጅቶ ቢተዋወቅ አይከፋም፡፡ አዳዲስ ዲዛይን ያላቸው የዘመኑ ፋሽን ጫማዎች እየወጡ ለውድድር ቢቀርቡና አቅምን ማሳየት ቢቻል ብዙ ለውጥ ይመጣል፡፡ በአገር ልብሶቻችን ላይ የታየው ትጋት እዚህም ላይ ቢደረግ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡

በወር አንዴ አለያም ባመቸ ጊዜ ልክ የጫማ ትርዒቶች ቢካሄዱ፣ በውድድር ብዙ የተሻሉ ጫማዎች ማየት ይቻላል፡፡ ሸማቹም የአገሪቱን ምርት በማድነቅ እንዲገበይ ያስችለዋል፡፡ አደጉ የምንላቸው አገሮች ለደረሱበት ደረጃ አንዱ መሠረት የአገራቸውን ምርት መጠቀማቸው እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡

ጫማ ለማምረት የሚያስችሉ ጥሬ ዕቃዎች በአገራችን በርካታ ናቸው፡፡ ከየትኛውም አገር የተሻለ ጥሩ ቆዳ አለ፡፡ የዲዛይን፣ የፋሽን፣ የውበትና የቤት ሙያ ማሠልጠኛ እየተባለ በየአቅጣጫው የምናየው ማስታወቂያ ውስጥ የጫማ ዲዛይን ማሠልጠኛ የሚል አይታይም፡፡

በመንግሥት ይዞታ ሥር ያለው ማሠልጠኛ ብቻውን ከጊዜ ጋር የሚሄዱ ፋሽንና ተስማሚ ዲዛይኖችን የሚያወጡ በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት የአቅም ችግር ሊኖርበት እንደሚችል ይገመታል፡፡ ስለዚህ የጫማ ዲዛይን ማሠልጠኛዎች በግሉ ዘርፍም መከፈት ይኖርባቸዋል፡፡

ከሸመታ አንፃር ጥሩ የአገር ውስጥ ምርት ሲገኝ እያሳደዱ መሸመትና ስለ ምርቱ ጥራት መመስከር አንዱ የአገር ወዳድነት ማሳያ ነው፡፡ የአገር ውስጥ መጫሚያዎችን የመጠቀም ባህል ለማዳበር ብዙ አማራጮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አድናቆት የምንቸራቸው አርቲስቶቻችን፣ ታዋቂ ሰዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ጎንበስ ብለው ጫማቸውን ተመልክተው ከሚጫሙት ጫማ የአገር ውስጥ ቢቀላቅሉ ለውጥ ሊኖር አይችልም ትላላችሁ?

እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፡፡ ጫማ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያመርቱትን ጫማ ለራሳቸው ይጫሙታል ወይ? ልጆቻቸውስ? ይህ ካልሆነ የቱንም ያህል ቢደክሙ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለ አገር ካሰብን ሌሎች የምናመርተውን ምርት እንዲጠቀሙ ከተፈለገ ከራስ መጀመር መልካም ነው፡፡

   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት