Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዴሞክራሲን የማሳካት ጭንጋፍነት መቼ ይሆን የሚያከትመው?

ዴሞክራሲን የማሳካት ጭንጋፍነት መቼ ይሆን የሚያከትመው?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ትናንትናችን በዛሬያችን ውስጥ፣ ዛሬያችንም በነጋችን ውስጥ ተካትቶ መኖሩ በተፈጥሮም ሆነ በኅብረተሰብ ኑሮ ውስጥ እውነት ነው፡፡ የ1888 ዓ.ም. ዓድዋ ድል ከአኩሪነቱና ከአርዓያነቱ ጋር ሁሌም አብሮን ይኖራል፡፡ በታሪካችን ውስጥ የነበሩ የግስጋሴ ጉድለቶች ያስከተሏቸው ዳፋዎችና ጥብሳቶችም በተለያየ መልክ አብረውን ይዘልቃሉ፡፡ ዛሬን ስንቦተልክና ዛሬን ስናንፅ ለነገ ጠንቅ እንዳናወርስ መጠንቀቅን መርሳት የሌለብን ለዚህ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከተገነባችበት ንጉሠ ነገሥታዊ አስገባሪነት ታሪክ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርት የሚሰጡ ልምዶች በርካቶች ናቸው፡፡

በውድመትና ምርኮ በማጋዝ የተሞላ፣ ከጥንት አንስቶ የጀመረና ማብቂያ አጥቶ 20ኛ ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ ግዛት የማስፋፋት ጎታታነት ያሳደረብን ገጸ ብዙ ጉዳት እስከ ዛሬም ይስበናል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፓርቹጋሎችንም ሆነ ቱርኮችን ወደ ኢትዮጵያ የጠራቸው (ቱርክ ምፅዋ ላይ እንድትቀመጥ ያስቻላት) ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጉልበት አስጨራሽ የመዋዋጥ ትንቅንቅ ነበር፡፡ ከቱርክ የለጠቀው የግብፅ ተስፋፋፊነት እየተዋጋም እያረፈም መቆየት የቻለው፣ ጣሊያንም በግዢ ሰበብ መሰስ ብሎ በጉልበቱ ካደረገው በላይ ከምንሊክ ጋር ውል የያዘ መሬት ሊይዝ ችሎ የነበረው፣ ወራሪንም ሆነ ግዛት ደፋሪን የመመከቱን አገራዊ ተግባር፣ አፈንግጦና ተመሳጥሮ ከበላይ የመሆን ውስጣዊ የሥልጣን ትግል ይሻማው ስለነበር ማለትም አድማና ሴራን አኮላሽቶ ከማዕከላዊ እስከ አካባቢዎች ለመስፈን የበቃ አይደፈሬ ሥልጣን መሟላት ስላልቻለ ነበር፡፡

ዕደ ጥበብና የከተማ ሥልጣኔ የማበብ ዕድል ያላገኙት፣ የነበሩትም ቢሆኑ ቀጭጨው/መክነው የቆዩት፣ ከአሮጌነት የመውጣት እንቅስቃሴ መታየትም እስከ 20ኛ ክፍለ ዘመን መባት ድረስ ሊዘገይ የቻለው፣ ያኔም ቢሆን የነበሩት ለውጠኞች ከአውሮፓውያን ካዩት፣ ከሰሙትና በትምህርት መልክ ከቆነጣጠሩት በቀር የአዲስ ዕድገት ብቅለት ስንቅ የለሾች ሊሆኑ የቻሉት፣ የጊዜው የውጭ ንግድና እስከ ትንሽ ሱቅ ድረስ የነበረ ሥራ በአውሮፓውያን፣ በህንዶችና በዓረቦች የተዋጠ ሊሆን የቻለው መዘማመት የተመላለሰበት የመጠቃለል ሒደት ዘመነ ዘመናት በመፍጀቱና ከጦርነት እሳት የተላቀቀ ሕይወት ትንፋሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ነበር፡፡

የዓለም ጥቁሮች መኩሪያ በሆነው የዓድዋ ድል የታጀበው የምንሊክ ጠቅላይ ገዢነት እንኳ በ20ኛ ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎች ላይ የተረጋጋ የሥልጣን ቅብብል ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ጊዜ የረፈደበት የለውጥ እንቅስቃሴም ከጊዜው የሥልጣን ትንቅንቅ ጋር ከመመናተል አላመለጠም ነበር፡፡ ባሪያ ፍንገላን፣ የባርነትና የከፊል ባርነት ግንኙነቶችን ለመታገል እንኳ ብዙ መሳቀቅ ነበረበት፡፡ ለዚያውም፣ በተንሰራፋ አሮጌነት ውስጥ የለውጥ ንፋስ መንፈስ ከመጀማመሩ የፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ደረሰበት፡፡ በጥቅሉ ከጣሊያን ወረራ በፊት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የታዩ የዘመናዊ ለውጥ ጥረቶችን ስናስተውል፣ ውስጣዊ የዕድገት ብቅለት የማጣት ሥር ያላቸው የሰንካላነት ችግሮች ለውድቀት ሲዳርጉ ወይም ከረባ ውጤት ሲያርቁ እናገኛለን፡፡

አፄውና መሳፍንቱ ገንዘብ ጭነው ወደ ውጭ የኮበለሉበትና ይመሩት የነበረው አሮጌ የገባር ጭሰኝነት ሥርዓት የደነዘዘበት የፋሽሰት ጣሊያን አጭር የወረራ ዘመን፣ ፀረ ገባርነትን ከፀረ ቅኝነት ጋር ላዛመደ ፖለቲካና ባላገሩን ከደቡብ እስከ ሰሜን ለነዘረ የአርበኝነት ትግል መስፋፋት የሚስማማ ድፍን ዕድል ብቅ ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ በአውሮፓ የተማሩና ከሆለታ ጦር ትምህርት ቤት የተገኙ የአገር ልጆች የተገናኙበት (የኤርትራ ሰዎች ከአመራር እስከ ውትድርና የነበሩበት)፣ በመተዳደሪያ ደንብና በኮሚቴ ይመራ የነበረው፣ ባላገር አለመዝረፍን መመርያው ያደረገው የጥቁር አንበሳ ድርጅት ለለውጥ አምጪ አርበኝት መንደርደሪያ (እንዲያውም ለኢትዮ – ኤርትራ ሓርነት አስኳል)  የመሆን ፍንጥቃት ነበር፡፡

ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አፈግፍጎ ወደ ነበረውና በራስ እምሩ ይመራ ወደ ነበረው ሠራዊት ጥቁር አንበሶች ሄደው በተቀላቀሉበት ጊዜም አሮጌው ሥርዓት በአካባቢው ሕዝብ ላይ ምን ያህል ቁስል እንደተወ፣ ጣሊያንም ለጊዜውም ቢሆን ምን ያህል አንዱን በአንዱ ለማጣፋት እንደነገደበት፣ ሁለንተናዊ የአርበኝነት ትግልም ፀረ ገባር ፖለቲካዊ አቋምን ምን ያህል ይሻ እንደነበረ ከሚያሳይ ሁኔታ ጋር ተገጣጥመው ነበር፡፡ በራስ እምሩ ይመራ የነበረው ሠራዊት ከግፈኛው ሥርዓት ጋር ተዛምዶ በመታየት ምክንያትና በቦምብ/በመርዝ ታስጨርሱናላችሁ በሚል ሥጋት ከአካባቢ አካባቢ የገጠመው የተቀባይነት ማነስ፣ በቀል እያፈራ በሚሸሽ የሰው ጓዝ ሠራዊቱ መጥለቅለቁ፣ በተጨማሪ የጣሊያን ብዙ ብልጫ (በመረጃ ፍጥነት፣ በታክቲክና በኃይል) በአንድ ላይ፣ እንኳን አዲስ አበባን የማስመለስን ቅዠትነት ይቅርና ፊት ለፊት የመዋጋትንም ስህተትነት ይናገር ነበር፡፡

ተዋጊ ቡድን አደራጅቶ ወደ ራስ እምሩ ሄዶ የነበረው ታከለ ወልደ ሐዋርያት ከሽምቅ ውጊያ በቀር የሚያዋጣ አማራጭ እንዳልነበር አጢኖ የወሰደው ከግትልትሉ፣ የመለየትን ዕርምጃ ጥቁር አንበሶች ሊወስዱት አልቻሉም፡፡ ቅዠት በንኖ ለጣሊያን ኃይል በስምምነት እጅ ወደ መስጠት በተዞረበት ደረጃ እንኳ፣ የጣሊያን ኤርትራን ከድተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ወገኖች ጭዳ እንዳይሆኑ የተካሄደውን ጥሩ ጥሩ መሣሪያ አስታጥቆ የማስመለጥ ተግባር ጥቁር አንበሶች ለራሳቸውም ሳይፈጽሙት ቀሩ፡፡ የጥቁር አንበሳ ድርጅት ወጣቶች እጅ ከመስጠት በበለጠ የተወሰነ ኃይል ማሹለክ የአርበኝነት ትግሉን እጅግ ይጠቅመው እንደነበር አጢነው፣ ለጎጀብ ወንዝ ከተዳረገው መሣሪያ ጋር የቡድን ጥንስሳቸውን ማትረፍ ሞክረውና ሰምሮላቸው ቢሆን ኖሮ፣ የአብዲሳ አጋ ጀግንነት መታያ በኢትዮጵያ ተራሮችና ሸለቆዎች ውስጥ በሆነ ነበር፡፡

የመጪ መንግሥት ቅርፅ፣ ምንትስ የሚባል ነገር ውስጥ ሳይገቡ ከባላባት/ጉልተኛ እስከ ጭቃ ሹም ድረስ የነበረ አበሳ አስቆጣሪነት ተወግዶ ሁሉም ገበሬ ባለርስት የሚሆንበትን የአዲስ ዘመን ተስፋን ያስተጋባ ከዘርፎ በልነት የፀዳ፣ በዚህም ገበሬውን ጫካው ያደረገና በውጊያ ድሎች ያጌጠ የአርበኝነት ጮራ በአገሪቱ አንዲት ጠባብ አካባቢ ላይ እንኳ አብርተው ቢሆን ኖሮ፣ ብርሃናቸው ወደ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በፍጥነት ተዳርሶ በመኳንንታዊ ተፅዕኖ ሥር የነበሩ የአርበኝነት እንቅስቀሴዎችን ሁሉ ለለውጥ በጎተጎታቸው ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ወላፈን ያገኛቸው የአርበኝነት ትግሎችም ለተሻሻለ ሥርዓት መምጣት መሠረት መሆናቸው አይቀሬ በሆነ ነበር፡፡ የአገሪቱን ታሪክ ይቀይር የነበረ ይኼንን ድፍን ዕድል የሚያለማው አልተገኝም፡፡ ብርቆቹ የጥቁር አንበሳ ልጀችም ሆኑ ሌሎች ለውጥ ናፋቂዎች የየካቲት 12ን (የእነ ሞገስ አስገዶምን) ሙከራ ተከትሎ በመጣው የፋሽስት ጭፍጭፋ መረፍረፍ፣ ከዚያ ቢተርፉ ከአገር ውጭ ተግዞ መታሰርና በስደት መራገፍ ዕጣቸው ሆነ፡፡

ከዚያ ወዲያ በአገሪቱ የተዛመተው የአርበኝነት ትግል ጣሊያንን ከማባረር ዓላማ ያልዘለለ መሆኑ፣ አለፈ ቢባል የእያሱን ልጀች በማንገሥ ወይም አፄ ኃይለ ሥላሴን በማፍቀርና በመናፈቅ ውስጥ መዳከሩ፣ ስደተኛው ንጉሥም (በተለይ ጣሊያን የእነ ጀርመንን የአክሲስ ቡድን መቀላቀሏ ለይቶ የእንግሊዞችን ድጋፍ ካገኘ በኋላ) የኢትዮጵያን ፀረ ፋሽስት ትግል ከርቀት በመምራት ወግ ራሱን ለማስጌጥ መቻሉ የሚያስገርም አልነበረም፡፡ በስደት ሥፍራዎችና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ገባ ወጣ በማለትም ሆነ ለመንግሥታቱ ማኅበር አቤቱታ በማቅረብ ለሪፐብሊክ ሥርዓት ተደረገ የሚባለውም ትግል ሁሉ አየር ላይ የተካሄደ (ሥር የለሽ) ትግል ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ዕልልታ ታጅቦ ለመግባት አልከበደውም፡፡ ገብቶም ከአርበኞች ይበልጥ ስደተኛና ባንዳን በዙፋኑ ዙሪያ ሲያሰባሰብ እንኳ የተያያዘ ቅዋሜ አልገነፈለበትም፡፡

ዙፋን ከተመለሰ ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትምህርት ቀመሶች እየተበራከቱ የመጡ ቢሆንም፣ ከለውጥ ቁስቆሳ ይልቅ የአፄው ተመላኪነት እየደረጀ የመጣበት ዘመን ነበር፡፡ በዚያ ዓይነቱ እውነታ ውስጥ ተካሂደው የነበሩት የሕዝብ እትብት ያልነበራቸው ወይም የተሳላ የመንግሥት ግልበጣ ቅንብር ያልተቆናጠጡ ሙከራዎች ከግለሰቦች መወራጨት የዘለሉ አልነበሩም፡፡

የእርሻ ሚኒስቴርንና የንግድ ሚኒስቴርን፣ የጽሕፈት ሚኒስቴርንና የአገር ግዛት ሚኒስቴርን እስከ መምራት ሥልጣን ደርቶላቸው የነበሩት መኮንን ሀብተ ወልድና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የነበራቸው የኃይለ ሥላሴ ታማኝ ከመሆን ጋር የተጣበቀ የሥርዓት መሻሻል ፈላጊነት፣ የንጉሡን ሥልጣን ከማጠናከር አልፎ ከእነ ታከለ ወልደ ሐዋርያት ጋር የአንድ አካባቢ ልጅነትንም ሆነ የሥጋ ዝምድናን ወይም የሥራ ግንኙነት አጋጣሚን ተንተርሶ መደራረስ አልቻለም ነበር፡፡ (መኮንን ሀብተ ወልድና ታከለ የወንድምና እህት ልጆች ነበሩ፡፡ ወልደ ጊዮርጊስ በሚያስተዳድረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ውስጥም ታከለ ምክትልነትን የተሾመበት ጊዜ ነበር)

በወልደ ጊዮርጊስና በመኮንን ሀብተ ወልድ ላይ ዳብሮ የነበረው በመሳፍንቱ መፈራትና መጠመድ ሥርዓቱን ይጠሉ በነበሩትም ሆነ  እጅ ሰጥተው ባደሩት ትምህርት ቀመሶች አካባቢ ይንፀባረቅ ነበር፡፡ እናም እነ ወልደ ጊዮርጊስ በነበራቸው ለአፄ ኃይለ ሥላሴ የመታመን ዝና ውስጥ የተደበቀ ፍንቀላ ሊገመድ አልቻለም፡፡ የእነ ወልደ ጊዮርጊስ ሥርዓቱን የማሻሻል ፍላጎትም ቢሆን ንጉሠ ነገሥቱ የአውሮፓውያንን ነቀፋ ለመገላገል ሲሉ በሕገ መንግሥት የተገደበ ዘውድንና ፓርላማዊ ዴሞክራሲን ያገናኘ ለውጥ ያደርጋሉ ብሎ እስከ መጓጓት፣ እንዲያውም የዚያ ዳር ዳርታ ያለበት ሐሳብ እስከ ማቅረብ ሳይቃዥ አልቀረም፡፡ (የዘውዴ ረታ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የተሰኘ መጽሐፍ ያቀረበልን ትረካ፣ ማለትም ማሻሻያ እንዲያቀርቡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ የታዘዙት መስፍኑ መኮንን እንዳልካቸው፣ መኮንን ሀብተ ወልድና ወልደ ጊዮርጊስ ለዚሁ ሥራ ተገናኝተው በመከሩ ጊዜ፣ መኮንን እንዳልካቸው በወልደ ጊዮርጊስ ሐሳብ የተማረከ መስሎና ይኼማ ጃንሆይ የሚቀበሉት ነው ብሎ የወልደ ጊዮርጊስን ማስታወሻዎች እጅ ማስገባቱና ነገር መሥራቱ ወልደ ጊዮርጊስም ጭጭ እንዳለ መቅረቱ ይህንኑ የሚያስጠረጥር ነው፡፡)

እነዚህን መሰሎቹ ለውጥ ፍለጋዎችና የተደጋገሙ የሴራ ልምዶች ለስኬት የሚያበቃ ትምህርት ለ1953 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ አላሸጋገሩለትም፡፡ የክብር ዘቡንና ፀጥታውን በሥሩ ማድረግ ችሎ የነበረ የግልበጣ እንቅስቃሴ ከመክሸፍ አላመለጠም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውህደትም ተስማሚ የለውጥ መሠረት ለማግኘት ሳይታደል ቀረ፡፡

እስከዚህ ጊዜ የታዩት የለውጥ ጥረቶች ከመጨንገፍ ያላመለጡት በተንሰራፋ አሮጌነት ውስጥ የተዋጡና የሚቆናጠጡት የአዲስ ዕድገት ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ በብዙ የጎደለባቸው ስለነበሩ ነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት የተከሰተበት ምዕራፍ ግን ሥርዓቱ ጥንዝትዝቱ የወጣበት፣ በቅዋሜ የተዋከበበት፣ የለውጥ ኃይሎችም ከበፊቱ ጋር ሲተያይ የተበራከቱበት ነበር፡፡ እናም አብዮቱ ይዞት የመጣው አሮጌዎቹን ገዢዎች ከእነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አውታሮቻቸው የነቃቀለ ተራማጅ የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የአፈጀ አፄነትን ሸኝቶ ለሌላ ዓይነት አፄነት ራሱን በመረማመጃነት ከመገበር ያላመለጠው ከነባራዊ ነገሮች መጓደል ይልቅ ራስን በራስ ለመብላት ባደረሰ ገንታራነትና መነካከስ ምክንያት ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያሉ የሰንካላነት ችግሮችም ከዚሁ መስመር የወጡ አይደሉም፡፡ የአፄው መንግሥት ያበላሸው፣ ደርግም ያቀረናው የኢትዮ – ኤርትራ ጉዳይና የሕዝቦቻቸው የነፃነት፣ የፍትሕና የዕድገት ጥያቄዎች እንደገና ሌላ የለውጥ ምዕራፍ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

ደርግ ተንኮታኩቶ የነፃነት ኃይሎች ነን ባዮቹ ሻዕቢያና ሕወሓት/ኢሕአዴግ አስቀድመው በተስማሙበት ድርሻ ሥልጣን ላይ ቢወጡም ለዘመዳሞቹ ሕዝቦች የነፃነት፣ የፍቅርና የሰላም መሠረት ጣይ ለመሆን አልበቁም፡፡ ጭራሹን ከተዛባ የዝርፊያ ግንኙነት በፈለቀ መቋሰልና መጠማመድ ወደ አስከፊ ጦርነት ከተቷቸው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የጎለበተው የአገር መውደድና ትግግዝ ለኢሕአዴግና ለተቃዋሚዎቹ ተባብሮ ለኢትዮጵያ ተስፋ የመሆን አጋጣሚን ሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፣ የብቻ ሥልጣን የበለጠበት ሕወሓት/ኢሕአዴግ የ1992 ዓ.ም. ምርጫን እንደለመደው የብቻ ሲሳዩ አድርጎ የጥላቻና የንቁሪያ ፖለቲካን መልሶ አደሰ፡፡

በእነ አሜሪካ ጫናም በኢሕአዴግ መደፋፈርም ሻል ያለ የመላወሻ ሜዳ የተገኘበትና የተቃዋሚዎች ገዘፍዘፍ ያለ መሰባሰብ የታየበት የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሲመጣ ደግሞ፣ ተቃዋሚዎቹ ያሉበትን እውነታ በቅጡ ማጤን ተስኗቸው ስለማይቀር ድል አድራጊነታቸው ሲፎልሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማዳን ስም ለተካሄደ መንግሥታዊ የጉልበት ሥራና ድቆሳ መነሳሻ ሆኑ፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ተነቃቅቶ የነበረው የፍትሕና የነፃነት እንቅስቃሴ በዓይነተ ብዙ ሥልቶች (በአሥር ሺዎች በተካሄደ እስራት፣ በማያፈናፍን ስለላ፣ በዛቻና በድብደባዎች፣ ከሥራ በመመንቀር፣ በፕወዛ፣ በኮናኝ ፕሮፓጋንዳና በልዩ ልዩ ሸሮች) ተሰባበረ፡፡

ጊዜያት አለፉ፡፡ ኢሕአዴግም ገዢነት የሰመረለትና ሕዝብን በልማት የረታ መሰለ፡፡ መንግሥታዊ የልማትና የዴሞክራሲ ተመፃዳቂነትን እየዘነጣጠለ በ2008 እና 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ቁጣ ሲስፋፋ ግን ስንት ዓይነት ብሶትና እሮሮ ሲጠራቀም እንደኖረ፣ ሕዝቦች ድረስ የዘለቀና እርስ በርስ ሊያፈራክስ ጫፍ የደረሰ መቃቃር ምን ያህል ግት እንዳበጀ ግልጽ ወጣ፡፡

በዚህ አስፈሪ የውስጥ ሰላም የለሸነት አናት ላይ ከሚሊኒየም (የህዳሴ) ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የመጣ የግብፆች ሥጋት ያንዣብባል፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለ ፍጥጫን ለማቃለል አለመትጋታችን ደግሞ፣ የግብፆች ሥጋት የጎረቤትና የተቃዋሚ ማረፊያ አግኝቶ ይሆን ወይ? ኤርትራ ውስጥ ምን ሲጠነሰስ ውሎ አደረ? እያልን በመቃበዝ ውስጥ እንድንኖር አድርጎናል፡፡ የኤርትራ መንግሥትን በማስገለል “ስኬታማ” በሆነው ፖሊሲያችን አማካይነት ዓረብ ኤምሬትስ አሰብ ወደብ ውስጥ እግሯን እንድታስገባ ድርሻ አዋጥተናል፡፡ የውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካን ከጥፋት ጋር አዛምዶ በሚያይ አያያዝ እያንገላታን ኤርትራ ውስጥ ለመሸገ የጠመንጃ ትግል ስንመግብ ቆይተናል፡፡ ከጥፋት ተምረንና ዴሞክራሲን ደልድለን ወደ ጠመንጃ የሰደድነውን ተቃውሞ ወደ አገር ውስጥ ሰላማዊ ሜዳ መሳብ ሞት ሆኖብን፣ ይኸው የህዳሴ ግድብ ላይ ከኤርትራ በገቡ ፀረ ሰላሞች ጥቃት ሊፈጸም ተሞክሮ ከሸፈ ብሎ ማውራትን ኩራት አድርገነዋል፡፡ ከዚህም ብሶ የአገሩን ሕዝብ በረሃብና በእርስ በርስ ውጊያ ከመርገፍ ለማውጣት የሚሆን ህሊና እንኳ ያጣው የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር ወደ ኤርትራ አንደኛውን አዘንብሎ የጥቃት ቀዳዳ እንዳይሆንብን እስከ መልመጥመጥ ደርሰናል፡፡ በዚህ ላይ ከሦስት አቅጣጫ የሚመጣው የሰው ፍልሰት የግጭትና የሽብር መዘዞችን ጎትቶ እንዳያመጣ ነቅቶ መጠበቅ አለ፡፡

ዓለም ላይ በማስገምገም ላይ ያለ ሌላም አደገኛ አውሎ ንፋስ አለብን፡፡ ከእኛና ከቢጤዎቻችን ወደ ምዕራብ ጌታ አገሮች የሚፈስስ የስደት ጎርፍና የተሰባሰበ ሕዝብን በትልቅ መኪና እስከ መዳመጥ ጭካኔውን እያከፋ የመጣው ሽብርተኝነት፣ በምዕራብያውያን የኢኮኖሚ ዕድገት መኮማተር ላይ ተደርበው የምዕራብ ሕዝቦችን እረፍት መንሳታቸውና ማስመረራቸው፣ በእነዚህ አገሮች ያሉ “የሰው ልጅ መከራ ያሳስበናል” ባዮቹ ሊብራሎችና “ግራ” ዘመሞች እየተፈራረቁም ሆነ እየተጣመሩ ሥልጣን ላይ ቢወጡ፣ ለእነዚህ ችግሮች የረባ መግቻ ለመስጠት አለመቻሉ፣ ፋሽስት ቀመስ ለሆኑ ፀረ ስደተኛ – ባዕድና ፀረ እስልምና የፖለቲካ መስመሮች የሕዝብ ድጋፍ እንዲበራከትላቸው እያደረገ ነው፡፡ የአሜሪካው ትራምፕ የሚያቀነቅነው “አሜሪካውያንን ማስቀድም”፣ “አሜሪካንና ባዲራዋን መውደድ”፣ “በጦር ኃይል ተወዳዳሪ የለሽ መሆን” የአደገኛ ሕዝበኛነት መገለጫዎችም ናቸው፡፡

የዚህ ዓይነት አስፈሪ የፖለቲካ አዝማሚያዎች ከመነሳሳታቸው አኳያ፣ የአውሮፓ ኅብረት ዕጣም ገና አልለየለትም፡፡ በ2009 ዓ.ም. መጋቢት ውስጥ የሆላንድ የምርጫ ውድድር በነበረበት ጊዜ፣ ሥልጣኑን በሪፈረንደም ለማስፋት ዘመቻ በማካሄድ ላይ የነበረው የቱርኩ ኤርዶዋን ሰዎቹን ጀርመንና ሆላንድ ወስጥ ልኮ እንዳይቀሰቅስ የመክከልከሉ ምክንያት፣ በፀረ እስላም፣ በፀረ ስደተኛና በፀረ አውሮፓ አቋም የታወቀው ዋይልደርስ የተባለ ተወዳዳሪ ፀረ እስላም ድጋፉ ጋሽቦለት ገዢ ፓርቲን ከማውረድ ባለፈ ለአውሮፓ ኅብረትም ጠንቅ እንዳይሆን ክፉኛ ተፈርቶ ስለነበር ነበር፡፡ የተፈራው ሰው ሲሸነፍ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርክልስ የእፎይታ ትንፋሽ የተነፈሰችው ለዚህ ነበር፡፡ በፈረንሣይ ምርጫ ውስጥም እንዲሁ ሌላ ከቀኝም ቀኝ የሆነ መስመር እየተንደረደረ መጥቶ የሚያዝያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ምርጫ፣ ፈረንሣይን በተለይም ከ1968 ዓ.ም. ወዲህ ያስተዳደራትን የሁለት ፓርቲ ሥርዓት የእንቧይ ካብ ሲያደርገው አይተናል፡፡ ማንም ተመረጠ ማን ግን፣ ስደትና የሽብር ጥቃት መመላለሱ እንደ መቀጠሉ ከቀኝም ቀኝ የሆኑ የፋሽስት ፓርቲዎች የድጋፍና የሥልጣን ጉዞ ማሸቀቡ የማይቀር ነው፡፡

ጌቶቹ አገሮች መዳፋቸውን ሲያራግቡ እንኳ ልንወላከፍ ለምንችል ለእንደኛ መሰሎቹ አገሮች የዚህ ዓይነቶቹ ፅንፈኛ የፖለቲካ ንፋሶች ዕርዳታን ከማሳጣትም ባለፈ፣ ቀውሶችንና ውጊያዎችን ሊቆሰቁሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ የአሜሪካው ትራምፕ በሶሪያው በሽር አል አሳድ ላይ ከነበረው አቋም ድንገት ዘወር ብሎ በተመረጠ ወታደራዊ ጣቢያ ላይ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚሳይል ጥቃት ማካሄዱና ከዚያም ወዲያ በሰሜን ኮሪያ ላይ እየተንጎማለለ መሆኑ የዚሁ አብነት ነው፡፡ ትራምፕ ለእስራኤል ያለው እዩኝ እዩኝ ያለ ወገንተኝነትና ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም የማዛወር ዕቅዱ ብቻውን ለሽብርተኝነት አዲስ ነዳጅ የሚሰጥ፣ በእኛም የቀንድ ቀጣና ውስጥ አሁን ካለበት በበለጠ ደረጃ ሽብርተኝነት እንቅስቃሴውን እንዲያሟሙቅ የሚጠቅም ነው፡፡ የፖለቲካ መስመሩ የታወቀ ቢሆንም መሽቶ ሲነጋ ምን እንደሚወስን ሊገመት የማይችለው ትራምፕ፣ ዓለምን ምን ውስጥ ይዘፍቃት ይሆን የሚል ሥጋትን ከአዕምሮ እንዳይጠፋ የሚያደርግ ነው፡፡

ለዚህም ነው ውስጣዊና ከጎረቤት ጋር የተገናኘ ሰላም የለሽነትን በቶሎ አስተካክሎ ችግሮችን ራስ በራስ የመቋቋምና የመፍታት አቅም ለማበጀት መጣደፍ ሊያባንነን የሚገባው፡፡ ይኼ ለነገ የማይባል ተግባር የእኛ አገር ፓርቲዎችን ዕውን እያስጨነቃቸው ነው? ወይስ ከመውሸልሸልና ከጭንጋፍነት ጋር ቆርበዋል? እንኳን ተዝረክርከን ለተሻለ ለውጥ ተጣድፈንም ከቁጥጥራችን ውጪ ሊመጣብን የሚችል ስንት የጣጣ ምናልባት እንዳለ፣ ሌላው ቀርቶ አውቀውም ሆነ ሳይታወቃቸው የእነ ሒትለርን ጎዳና እየጀማመሩ ካሉት ከጌቶቹ አገር ፓርቲዎች ውስጥ ለነጭ ጉድፍና ፀር “የሆኑ” ዘሮችን ለመጥረግ ያቀደ ዕብድ ገዢ በእኛ ዕድሜ ሊከሰት እንደሚችልAnchorስ ታስቦን ያውቅ ይሆን?  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...