Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፍርድ መዘግየትና የዳኞች ውሳኔን በሐሰተኛ ሰነድ ማስቀየር የፍትሕ ሥርዓቱ ተጠቃሽ አደጋዎች መሆናቸው...

የፍርድ መዘግየትና የዳኞች ውሳኔን በሐሰተኛ ሰነድ ማስቀየር የፍትሕ ሥርዓቱ ተጠቃሽ አደጋዎች መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የፍርድ ውሳኔ መዘግየትና መዛነፍ፣ የዳኛን ውሳኔ በሐሰተኛ ሰነድ ማስቀየርን ጨምሮ የዳኞችና የጠበቆች ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ለፍትሕ ሥርዓቱ ተጠቃሽ አደጋዎች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ከሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚከበረውን የፍትሕ ሳምንት አስመልክቶ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የወረዳ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ የተለያዩ ወንጀሎች በመፈጸም ክስ የሚመሠረትባቸው ግለሰቦችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ያሉ ቢሆንም የተፋጠነ ፍትሕ ሲሰጥ አይታይም፡፡ ማስረጃ በማሰባሰብ፣ ምስክሮች በመስማት፣ ዳኞች ባለመሟላትና ችሎቶችን በተገቢው የሥራ ሰዓት አለመጀመርን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ክርክሮች ዓመት ሁለት ዓመትና ከዚያም በላይ ይወስዳሉ፡፡

‹‹የዘገየ ፍትሕ እንደቀረ ይቆጠራል›› እንዲሉ፣ ተከሳሹ የቀረበበትን የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ክስ ማስተባባል ካልቻለ ፍርድ ቤቱ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት ሲገባው፣ በራሱም ሆነ በጣልቃ ገቦች ምክንያት ተከሳሹ በክሱ የተጠቀሰበት የወንጀል ሕግ ድንጋጌ አንቀጽ ከሚያስቀጣው ጊዜ በላይ ታስሮ እንደሚቆይም አስረድተዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ባይሆንም አልፎ አልፎ የዳኞች ውሳኔ በሐሰተኛ ሰነድ እየተቀየረ ተከሳሾች ያላግባብ የሚለቀቁበትና የሚታሰሩበት አጋጣሚ እንዳለ አክለው፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት በዚህ ላይ ጠንክረው በመሥራት የፍትሕ ሥርዓቱን መታደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የጉለሌ፣ የአራዳና የቂርቆስ ክፍላተ ከተሞች ነዋሪዎች ትኩረት ሰጥተው ያነሱት ጥያቄ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣን ለምን ለፍርድ ማቅረብ እንደሚፈራ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙትንም የተፋጠነ ፍትሕ መስጠት እንደማይቻል ነው፡፡ ነዋሪውም ሆነ የፖሊስ አካል በወንጀል የተጠረጠረን አካል እጅ ከፍንጅ ይዞ ሲያቀርብ ‹‹መረጃ አልተገኘም›› በማለት መልቀቅ፣ ማስረጃ ቀርቦባቸውና ተመስክሮባቸው ባሉ ተከሳሾች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት ሲገባ የፍትሕ መዘግየትም በስፋት እንደሚስተዋል አክለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በተለይ ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ፍትሕ ፍለጋ ወደ ፍርድ ቤቶች በሚያመራበት ጊዜ በፍርድ ቤት ሬጅስትራሮች በር ላይ የሚገኙና በየክፍላተ ከተሞቹ የተደራጁ ራፖር ጸሐፊዎች በጥቅም በመተሳሰር ለአንድ ገጽ ማመልከቻ ከ200 ብር እስከ 300 ብር እንደሚጠይቁ ጠቁመው፣ መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ እያለ በተደጋጋሚ ቢናገርም በጥልቅ ተሃድሶው ያልታረሙ እንዲያውም የባሰባቸው አካላት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

የመልካም አስተዳደርና የሕግ ጥሰት ችግሮች በፍትሕ ዘርፍ የሚስተዋሉና ያልተፈቱ መሆናቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ በፍርድ ቤት ለምስክርነት የሚቀርቡ ሰዎች የሕግ ከለላ አለማግኘት፣ በአንዳንድ የፖሊስ አባላት ላይ የሚታዩ የሥነ ምግባር ጉድለቶች፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ አስገድዶ መድፈር በፈጸሙ ጥፋተኞች ላይ የሚሰጠው ቅጣት አስተማሪ አለመሆን፣ በየፖሊስ ጣቢያዎቹ የተመደቡ ተሽከርካሪዎችን ለወንጀል መከላከል ሥራ ከማዋል ይልቅ ለኃላፊዎችና ለሠራተኞች እንደሚገለገሉባቸው ጠቁመዋል፡፡ በከተማው የተንሰራፋውን የልመናና የማጭበርበር ተግባርን በተመለከተ በትራፊክ መብራቶችና በመተላለፊያ መንገዶች ላይ የትራፊክ ፖሊሶች ሕግ አለማስከበራቸው፣ ለፖሊስ የድረሱልኝ ጥሪ ሲደወል ስልኩ ካለመነሳቱም በተጨማሪ ቢነሳም ፈጥነው ባለመድረሳቸው ኅብረተሰቡ የሚተማመንበት ነገር እያጣ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በቂርቆስ፣ በጉለሌና በአራዳ ክፍላተ ከተማ ሰባተኛውን የፍትሕ ሳምንት አስመልክቶ በተደረገው ውይይት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ሽመልስ ሽፈራው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጉለሌ ምድብ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አሰፋ፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አስተባባሪ አቶ ሙሉ ክንፈ ለከተማው ነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ፍትሕን ለማረጋገጥ ትልቁን ድርሻ ካልወሰደ ችግሩን መፍታት እንደማይቻል የገለጹት ረዳት ኮሚሽነር ሽመልስ፣ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ ችግሮች የሚደርሱት ራሱ ሕዝቡ ለፖሊስ መረጃ ባለመስጠቱና ለፍርድ ቤት ምስክር ሆኖ እንዲቀርብ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የፍርድ ውሳኔ መዘግየቱን በሚመለከት ኅብረተሰቡ ያነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የቂርቆስ ምድብ ዳኞች አስተባባሪ አቶ አርዓያ በየነ ሲሆኑ፣ ለፍርድ መጓተት ከዳኞች በተጨማሪ የባለጉዳዩ እጅ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ፍትሕን ከማስፈን ጋር በተያያዘ ግን ኅብረተሰቡ ወንጀለኛ መሆንን እንጂ ወንጀለኛን መጠቆም መፍራት እንደሌለበትና መተባበር እንዳለበት የተናገሩት፣ የአራዳ ምድብ ችሎት አስተባባሪ ዳኛ አቶ ሙሉ ክንፈ ናቸው፡፡ የቅጣት ውሳኔ ከወንጀሉ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ የወጣ የቅጣት አወሳሰን መመርያ መኖሩን፣ ዳኞችም ውሳኔ ሲሰጡ መመርያውን መሠረት በማድረግ እንጂ፣ ‹‹ቅጣቱን መጨመርም ሆነ መቀነስ አይችሉም›› በማለት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአራዳ ምድብ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አባቡ ለከተማው ነዋሪዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፍትሕ ሳምንት ከሚያዝያ 30 ቀን እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ‹‹የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት›› በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...