Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየአፍሪካ ቀንድ አገሮች “በአንድ አልጋ ሁለት አራስ”

የአፍሪካ ቀንድ አገሮች “በአንድ አልጋ ሁለት አራስ”

ቀን:

አንድ አልጋ ከመጋራት ውጪ ምርጫ የሌላቸው አራሶች ቢኳረፉ፣ ቢገፋፉና ቢናጩ ራሳቸውንና ጨቅሎቻቸውን ችግር ውስጥ ይከታሉ፡፡ አስቸጋሪ ኑሯቸው መተሳሰብን፣ በአንዷ ማሸለብ ጊዜ የሌላዋን ነቅቶ መጠበቅ ይጠይቃቸዋል፡፡ የግጭትና የጦርነት፣ የድርቅና የረሃብ፣ የአክራሪነትና የሽብር አውሎ ንፋስ የሚጎበኛቸው የአፍሪካ ቀንድ አገሮችም እንደዚያው ናቸው፡፡ ቢኳረፉ፣ ቢፋቱና ቤት ለየን ቢሉ እንኳ መላቀቅ አይችሉም፡፡ አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚያደሩጉት ተንኮል ጉዳቱ ለራስም ይተርፋል፡፡ አንዱ ዘንድ የተነሳ እሳትና ትርምስ የሌላውም አበሳ ነው፡፡ ካልተቃቀፉና ካልተጋገዙ በቀር ለውጥ ማምጣት አይችሉም፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ችግር በተለወጠ አዲስ ሁኔታና ገጽታ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ የአክራሪነት ንፋስ የቀንዱን አካባቢ አገሮች ቤተ መንግሥታትን ቢታከክ ወይም ሥልጣን ላይ የነበሩ ገዢዎች ቢቀያየሩ፣ በደጅ የተከተለው ለውጥ የወደብ በር አማራጭ መጥበብን እንዲያውም መዘጋጋትን ይዞ ሊመጣ የሚችልበት ሥጋት ገና አልተቃለለም፡፡ ከማይቆራረጡት የሥጋ – ሕዝብ አገር ጋር ተጠማምዶ፣ ለማንኛውም መሸሻና መወላጃ (የሚያወላዳ) እንዳላጣ እያሉ ከሱዳን እስከ ታንዛኒያ ድረስ ቢወዛወዙ፣ የበር ቁልፉ ይዞታ ውስጥ ኢትዮጵያ (በተሳሰረ የጋራ ልማት በኩል) እስካልገባችበት ድረስ የሥጋት ኑሮዋ አይቀየርም፡፡ የገዛ ራሷን ችግር ሳታይና ለማረም ሳትታትር የሌላውን ጠንቅ ሠሪነት ማድከምና ማምከንስ እንዴት ይቻላታል!!

በማግለልና በማስገለል የተሰነገው የኢሳያስ ወታደራዊ አምባገነንነት ከለመደው ግልጽና ሥውር ተንኮል ባይርቅ ምን ያስገርማል! ሥራ የፈታ ወደብን አከራይቶም ሆነ በየመን ጣጣ ውስጥ ወታደራዊ እገዛ አድርጎ ትንሽ ጉርሻ ለማግኘትና ራሱን ለማቆየት ቢሞክር ይፈርድበታል!? የኤርትራን ሕዝብ ጥቅም ጉዳይ እንተወው፣ ከተረገጠና ከተዘነጋ 26 ዓመታት ሞልተውታል፡፡ በኢሳያስ ሻዕቢያ ቆሻሻ ቅስቀሳና ዘረፋ ሕዝብ ከሕዝብ ቢቀያየም፣ ከመቀያየምም አልፎ በጦርነት ቢተጫጨድና መከራ ቢታቀፍ እነ ኢሳያስ ደንታ እንደሌላቸው የታየና ዛሬም እየታየ ያለ ነው፡፡ ከእስካሁኑ እንደምንረዳው የኢሳያስ እውር በቀልና ሸር ለግብፅ የጦር ሠፈር ሰጥቶ በኤርትራ ላይ ሌላ ጦርነት ከማስከፈት (አንድ እጅን በሌላ እጅ ከመቁረጥ) የበለጠ ጣጣ በራሱም በኤርትራ ሕዝብ ላይ እስከ መጋበዝ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ ከአንድ ናይል በቀር ዓይን የሌላት ግብፅም ጦር ሠፈር በኤርትራ በመትከልም ሆነ በሌላ መንገድ የህዳሴ ግድብ ‹‹የተባለ››ን ነገር በምን ላክሽፍ ብላ እንቅልፍ ብታጣ አያስገርምም፡፡ የሚያስገርመው እነዚህን የሚጠበቁ ምናልባቶች አውቆ ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ሁኔታዎችን የሚቀይር ብልህነት በአካባቢው ከታጣ ነው፡፡

ከወደብ አገልግሎት ንግድ ውጪ ሌላ ዓብይ መተዳዳሪያ የሌላት ሚጢጢዋ ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ትስስር በስተቀር፣ ከበላዩዋ የየመን መናወጥና የኢሳያስ ነገረኛነት፣ ከበታቿ የሶማሊያ ቀውስ ከቧታል፡፡ ከዚህ ሁሉ ወጀብ የቀጣናው የጋራ ደኅንነት ጥበቃ ይታደገኛ አትል፣ የዚያ ዓይነት ቅንብር የለ፡፡ ከቅኝ ገዢዋ ፈረንሣይ ጦር ሠፈር አንስቶ ከውጭ ጦር ጥበቃ ተለይታ አታቅም፡፡ የኤርትራው ኢሳያስ ሲተነኩሳት የተቆጣላት የፈረንሣይ ጦር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ለአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ ጣቢያ ሆና የምታገለግለው እሷው ነች፡፡ እንዲህ ከጦር ሠፈር ጋር የተላመደች አገር አቅም ያለውና የንግድና የተፈላጊነት ክልሉን ለማስፋት የሚሻ ወዳጅ ወታደራዊ ሠፈር መሥርቼ ቢያንስ በገቢ ረገድ ልደግፍሽ ስትባል እንቢ ማለት አይጠበቅባትም፡፡

ከሶማሊያ ተቆርሷና ከእርስ በርስ ውጊያና ከሽብር ምስቅልቅሎሽ ራሷን አትርፋ ተስፋ ያላት አገር መሆኗ እንዲታይላት ለዓመታት ስትውተረተር የቆየችውና እስከ ዛሬ የረባ ዕውቅናና ዕገዛ ያላገኘችው (አሁን ደግሞ ድርቅና ረሃብ የሚገርፋት) ሶማሌላንድስ ብትሆን፣ ወታደራዊ ሠፈር ከማቆም ጋር ዕገዛን ይዞ የመጣ ወዳጅ ላይ ብትጠመጠም ምኑ ጥፋት ይሆንባታል! እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ በአንፃራዊነት የመበላለጥ ነገር ካልሆነ በቀር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አንካሳነት የማይነካካው ለመታዘብና ለወቀሳ የሚበቃስ ማን አለና!

አዲሷን ደቡብ ሱዳን በእግሯ በማቆም ኃላፊነት ረገድ የቅርብ ጎረቤቶቿ ምን ያህል አሳቢዎች እንደሆኑ ጉድ አይተናል እኮ! ዕርዳታና የነዳጅ ሀብት ከተገሸረበት ቤት ተስማምተው መቀላወጥ እንኳ ያልሆነላቸው ዓይን አውጣዎች! ለአዲስ መጦቹ ገዢዎች ዘረፋ ማሸሻ ጎሬ በመሆን፣ አንዱ ወይም ሌላው ገዢ ላይ ተጣብቆ በመወስወስና መጪ ጥቅምን በማድራት፣ ከዚህ ሁሉ ቢቆጠቡ እንኳ እየመጣ የነበረውን አደጋ እንዳላዩ በማየት ለደቡብ ሱዳን መበጥበጥ ድርሻ ያላዋጡ እነማን ናቸው? የደቡብ ሱዳን አዲስ ገዢዎች ቅራኔ ውስጥ የመግባትና ውጊያ የማባባስ ችግር ከተፈጠረ በኋላስ፣ ጥለኞቹ እንደገና ተቻችለው አገሪቱን ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲወስዱ በተቀየሰው መፍትሔ ተግባራዊነት ላይ ጎረቤቶቿ ምን ያህል የአንጀት ሚና ተጫውተው ነበር? ስምምነቱ ሕይወት እንዲያገኝና እንዲቀጥል ደፋ ቀና ሲባል ከቆየ በኋላ የኡጋንዳው ሙሴቬኒ የሽግግሩን መንግሥት መሪነት ለሳልቫ ኪር ጠቅሎ የሚሰጥ አቋም ሲያራምድ ጦርነት አባባሽ መሆኑን አጋልጦ ያሳፈረ፣ ሰላምን ለሚያመጣ መፍትሔ በፅናት የታገለ ማን ነበር? ስምምነቱ ከተቆለመመ በኋላስ አንዱ ጦር አስገብቶ ሳልቫ ኪርን ሲደግፍ ሌላው ተቃዋሚውን ሲያቅፍ አልታየም? ይኼ ሁሉ ክሽፈት እንደምን?

የተሟላ ፊርማ ያላገኘው የናይል ውኃ ስምምነት እክል እንዳያገኘው መጨነቅ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ አንዱ ለያዘው አቋምና ሚና ሌላው ተቃራኒ የመሆን አዚም፣ የደቡብ ሱዳን በእርስ በርስ ውጊያ መወላለቅ በአንጥልጥል ላደረ (ከነዳጅ ጋር ለተያያዘ) የግዛት ጉዳዬ የበለጠ ይጠቅመኛል የሚል ሥሌት ሁሉ፣ ለደቡብ ሱዳን ሰላማዊ የሽግግር ጊዜ መፍትሔ መክሸፍ አስተዋጽኦ አላደረጉም? በጋምቤላ የደረሰውን ተደጋጋሚ የሙሩሌ ጎሳዎች ጥቃትን ከሳልቫ ኪር የሥልጣን ባላንጣዎች ጋር አያይዞ ኢትዮጵያን በሳልቫ ኪር ቀለበት ውስጥ እንዳቅሚቲ የማስገባት የፖለተካ ጨዋታ፣ ከደቡብ ሱዳን የጊዜው መንግሥት በኩል እንዲሞከር ያስቻለውስ ጎረቤቶች የተጠለፉበት አንጃዎችን የማጫፈር አዙሪት አልነበር? ቀጣናዋን በልማት ለማስተሳሰር የምትጣጣረው ኢትዮጵያስ ለጎረቤቶቿ መኩሪያ መተማመኛ ትሆናለች ሲባል ራሷንም ማትረፍ ስለመቻሏ የሚያጣራጥር የውስጥ ጉድ እንዳለበት በሚያስደነግጥ አኳኋን አልታየም!? በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያለው የጋራ ጥቅም መንሸዋረርና ድኩምነት እስከዚህ ድረስ የዘለቀ ነው፡፡

እናም የመንን ለእሳትና ለችጋር ዳርገውም ቢሆን የሺዓንና የኢራንን ተፅዕኖ ለመገደብና ከሱኒነት ጋር የተጋባ ገዢነታቸውን እንደነበረ ለማቆየት የሚዋደቁት የባህረ ሰላጤው አገሮች የአፍሪካ ቀንድን በድክመቶቹ ተጠቅመው የስንቅና ትጥቅ ማንቀሳቀሻና ማኮብኮቢያ ጣቢያ አድርገው ቢገለገሉበት፣ ከዚያም ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካ (በኢትዮጵያ ጭምር) እየተስፋፋ የመጣውን ንግዳቸውንና የመዋዕለ ንዋይ ሥምሪታቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ እስከ ሶማሊያ ቀንድ ቢዘረጋጉ  ምን ሊደንቅ!

ታዲያ ምን ይበጃል? “ተከበብን እኮ! ዘራፍ!” ቢባል፣ ወይም ደረት ቢመታ፣ ወይም፣ “እንዲያው በመላ የፈስ መልክ ዳለቻ ነው” የማለት ዓይነት ጥንቆላ ቢሞከር ጠብ የሚልልን ነገር አይኖርም፡፡ የሚያዋጣው ሊኖር የሚችለውን ጉዳትና ጥቅም አውቆ መደረግ ካለባቸው ነገሮች ውስጥ በየደረጃው ማድረግ የሚችሏቸውን ማሳካት ብቻ ነው፡፡ የአሜሪካ በአካባቢው የመገኘት ዓላማ የርቀት ጥቅሟን ከተዛማች ቀውስና ከሽብር አደጋ መጠበቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የባህረ ሰላጤው አገሮችም በአካባቢያችን መሠራጨታቸው እስካሁን በታየው ልክ ብንናገር፣ የሺኢ—ኢራንን የተነቃቃ እንቅስቃሴ ቢያንስ ወደ ነበረበት የመመለስ፣ የሽብርን ንፋስ የመቆጣጠር፣ የንግድ ጥቅምን የማስፋትና የመንከባከብ ጉዳይ ነው፡፡

ይኼ ሳይለወጥ እስከቀጠለ ድረስ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች መንግሥታት ውስጥም ሽብርን የማራመድ ወይም ኢራንን የማጫፈር ባህርይ እስካልተከሰተ ድረስ በቀጣናችን ውስጥ ያሉት የውጭ ኃይሎች ፀጥታ አደፍራሽና ግጭት አነሳሽ የመሆናቸው ዕድል እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንዲያውም ለአቅመ ቢሱ አካባቢያችን የከለላ ብጤ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ከለላ ውስጥ የሽብርተኝነት መፈልፈያ የሚሆነው ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ተደብቆ ሊሰርግና ሊሰረስር እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ በኢራቅ ውስጥ ዛሬ መከራ የሚያሳየው ፅንፈኝነት – አሸባሪነት የተቀፈቀፈው የአሜሪካ ወራሪነትን ጉያና የሳዑዲ ዓረቢያን የሱኒ “ተገንነት” ተጠቅሞ ነበር፡፡ በሶማሊያ የበቀለውንም የፅንፈኛነት አሸባሪነት አመጣጥ “ፋውንዴሽን”/“ቻሪቲ” የሚል ስም ከያዙ ሃይማኖታዊ ተራድኦዎች ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በግልም ሆነ በተራድኦ መልክ ተሸፋፍነው ለሚመጡ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴዎች መንገድ አለመስጠት የማይዘናጉበት ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ኃላፊነት ጋር የባህረ ሰላጤውን አገሮች በቅርብ መገኘት እንደ ጊዜያዊ የፀጥታ ዕገዛ አይቶ የራስን ነፃ ቀጣናዊ አቅም በማደራጀት ሥራ ውስጥ መፍጠን ለቀንዱ አገሮች ግድ ነው፡፡

የዚህ ግብ መቃናት በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ተቀዳሚ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠይቃል፡-

ኤርትራ ለግብፅ የጦር ሠፈር እንድትመሠርት ቦታ ፈቅዳላታለች እየተባለ የሚወራው ወሬ እርግጥ ከመሆንና ካለመሆኑ በበለጠ በአሳሳቢነት መጤን ያለበት፣ ዛሬ በኤርትራ ያለው መንግሥት እንዲህ ያለውን ጦርነት የሚጠራ ወፈፌ ሥራ ሊያደርግ የሚችል መሆኑ፣ በሌላ በኩል እንኳን እንዲህ መሰሉ ትልቅ ማመካኛ ተገኝቶ፣ በትንሽ ሰበብም ኢትዮጵያ ፈጣን ወታደራዊ ዕርምጃ ወስዳ ወፈፌውን ገዢ እንድታስወግድ የሚፀልዩ ኢትዮጵያውያንም ኤርትራውያንም መኖራቸው ነው፡፡

በቋፍ ባለ አካባቢ ውስጥ በየትኛውም ምክንያት የሚከፈት ጦርነት ምን ይዞ እንደሚመጣ፣ በአጭር ጊዜ እንኳ ስለማለቅና አለማለቁ፣ ብሎም የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን ግንኙነት ስማለምለሙም ሆነ ይብስ ስለማባላሸቱ አስቀድሞ ሊታወቅ አይችልም፡፡ በቀይ ባህር አካባቢ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እጅግ የተዳከመው የኢትዮ – ኤርትራ ታፋሪነት እንዳለ እንዲቀጥል (ማለትም የኤርትራና የኢትዮጵያ መቀያየም ወደ ወዳጅነት እንዳይቀየር) የሚሹ መኖራቸው አይረሳ፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች የማይነጣጠል የጋራ ዕጣ ደግሞ ዛሬ ሁለቱ አገሮች ያሉበትን ከሰላምም ከጦርነትም ያልለየለትን ፍጥጫ ይቃረናል፡፡ ኤርትራ በስደት ስትራገፍ የቆየችበት፣ ኢትዮጵያም ስደተኛ ተቀባይና ከአሁን አሁን ኢሳያስ ወደቀልኝ እያለች ስትቁለጨለጭ የኖረችበት የደነዘዘ ሁኔታ ከጉዳት በቀር ማንንም እንዳልጠቀመ ቁልጭ ብሎ ታይቷል፡፡ ከዚህ ወጥቶ በወዳጃዊ ግንኙነት ወደ ጋራ ልማት ውስጥ መግባት የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ጥቅሞች ላይ ነፍስ መዝራቱም የማያከራክር ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን ዕውን በማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ማወላወል ሊኖር አይገባም፡፡ አንደኛው ይኼ ነው፡፡

ማንም አገር ለዘመናት የኖረ ተጠቃሚነትን በዋዛ አያስነካም፡፡ ጥቅሙ መተኪያ የለሽ ሲሆን ደግሞ፣ በሌላ አገር ድርሻ ውስጥ የገባ ቢሆን እንኳ ሳይወራጭ ፈቀቅ የሚል አይኖርም፡፡ የግብፆችን ፈተና መረዳት የምንችለው እንዲህ በእነሱ ጫማ ውስጥ ራሳችንን አስገብተን ለማየት ከቻልን ብቻ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት፣

 • በግብፆች የጭንቅ ነገረ ሥራ ላይ አጉል ፍርድ ለመስጠት አለመቸኮል፣
 • የኢትዮጵያ ዓላማ ግብፅን መጉዳት ሳይሆን ፍትሐዊ ድርሻን የማስከበር መሆኑን ሳይታክቱ ማስረዳት፣
 • በፍትሐዊ ድርሻ ሥሌት ውስጥ የግብፆችን አንድ ዓይናነት ከእኛ ጋር አስተያይቶ ከእኛ ይቅር የሚባል የተወሰነ ብልጫ መፍቀድ፣ አማራጭ ውኃ ለሌለው ጎረቤት መቆርቆርም ለዘላቂ ሰላም ማሰብም መሆኑን ማስተዋል (ፍትሐዊነትን ማሳየት)፣
 • በዚህ በመጨረሻው መሠረት ሐሳብ ላይ ሕዝብ እንዲነጋገርበትና አቋም እንዲያደርገው መትጋት፡፡ ይኼ ሁለተኛው ጉዳይ ነው፡፡

ሁለቱ ነገሮች ከተሳኩ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነትንና ሽብርን የመከላከል፣ ግጭቶችንና ትርምሶችን የማስቆምና የማምከን አቅማቸው አዲስ ጉልበትና አዎንታዊ ሁኔታ ያገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የተረጋጋ አገረ መንግሥት ላይ እንዲደርሱ የማገዙ ሥራ ዕመርታዊ ዕርምጃ የማሳየት ዕድል ያገኛል፡፡ ከዚህ ጋር በመሠረት ልማት ዝርጋታ፣ በንግድ፣ ልምድና ቴክኖሎጂ በመለዋወጥ መተሳሰሩ ሁሉንም አካትቶ ሲዳብርና የኢኮኖሚ የልማት ተራክቦው ሁሉም የሚሳሳለት ጥቅም ሲሆን፣ ያለ ጥርጥር ኢኮኖሚ ነክ ጥቅምን የማስጠበቅ ፍላጎት የጋራ ፀጥታ አካባቢያዊ ጉድኝትንም ይዞ ይመጣል፡፡ እናም የተወሰኑ “ሉዓላዊ” መብቶችን ወደ ጋራ መብትነት አዙሮ የእያንዳንዱን ተጠቃሚነት በጋራ ስምምነቶችና ውሳኔዎች የሚመራ፣ ከደካማው “ኢጋድ” እጅግ የተለየና የአፍሪካ ኅብረት መሠረታዊ መርሆዎችን ያከበረ መንግሥታዊ ባህርያትን በማሟላት ላይ የተግባባ ቀጣናዊ ማኅበረሰብ የመፈጠሩ ተስፋ ሊጨበጥ የሚችል ዕድል ይሆናል፡፡ የባህር በር ማስፈራሪያና መስፈራሪያ መሆኑ የሚቋረጠው (የጂቡቲም በኪራይ ገቢ ላይ የተንጠለጠለ ህልውና ከኢትዮጵያ በተለይም ከአፋርና ከሶማሊያ ክልሎች የማዕድን የግብርና የፋብሪካ ልማት ጋር የሚጋባው) በዚህ ዓይነት ጉዞ ነው፡፡

ለቀጣናችንም ለኢትዮጵያችንም ከዚህ የጋራ ጉዞ የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ በየብስ የተከበበችው ኢትዮጵያ በዚህ የጋራ ዕድገት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወትን ልትቦዝንበት አይገባትም፡፡ ይህንን መተኪያ የሌለውን ሚናዋን ልትወጣ የምትችለውም በሆዷ ያለውን የፖለቲካ ጣጣ ወደ ድል ከቀየረችው (ባጭሩ የአገሪቱን ሕዝቦችና ፓርቲዎች ያተመመ፣ በውጭ ያለውንም ፖለቲከኛ ወደ ውስጥ የሳበ የዴሞክራሲ ለውጥ መሠረት ከያዘ) ብቻ ነው፡፡

አሁን የምንገኘው ይህ ለውጥ ወደ ፊት ተራምዶ የአገሪቱ ዕድል ብሩህ በሚሆንበት ወይም በማይረባ ብልጣ ብልጥነት ተጨናግፎ ከአደጋዎች አለመላቀቃችን በሚለይበት መሀል መንገድ ላይ ነው፡፡ “የዴሞክራሲ መጥለቅና መስፋፋት” የሚባለውን ነገር ኢሕአዴግ በሥልጣን ለመቀጠል መፍጨርጨሪያ አድርጎ እንደሚጠቀምበት የታወቀና የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ማድረጉም ነውር አይደለም፡፡ ትልቁ ጥያቄ ዴሞክራሲን መሠረት የማስያዙን ተግባር ከሌሎች የዴሞክራሲ ወገኖች ጋር እያራመደ በዚያ ሒደት ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እየሠራ ነው? ወይስ ሒደቱን አልኮስኩሶ እንደ ቀድሞው በዴሞክራሲ እያደናገረ ለመግዛት እየተጠቀመበት ነው የሚለው ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሁለቱም ዝንባሌዎች አሉ ማለት ይቻላል፡፡ የዴሞክራሲ ለውጡ እንዲተባ፣ ኢሕአዴግም አዲስ ሆኖ እንዲታነፀና በሕዝብ ታቅፎ እንዲወጣ የሚሹ ዴሞክራት ኢሕአዴጎች እንዳሉ ሁሉ፣ “ለውጡ” መንግሥት ወይም ታማኞቹ ከሚያቀናብሯቸው መድረኮች አልፎ ወደ ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴ መሸጋገሩን የሚፈሩ ኢሕአዴጎች አሉ፡፡ ከሁለቱ ዝንባሌዎች የትኛው አይሎ እንደሚገኝ ለመናገር ጊዜው ገና እና አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ እንዲያው ሁለቱም ዝንባሌዎች ወደ ፊትም ወደ ኋላም ለመሄድ የተቸገሩ ይመስላል፡፡

አንደኛ ገለልተኛ ተቋማት ስለመኖራቸው የጋራ መተማመን ባልተፈጠረበት፣ በዚሁ ቅጡ ባለየለት ምዕራፍ ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰፊ ተደማጭነት ባላቸው ሰዎች አለመጎልበቱ፣ አልፎ ተርፎም ከቅዋሜ የፈለቁ ቀውሶችን መንስዔዎችና ተጠያቂ አካላትን በማጣራት ተግባሩ ውስጥ ከተቃውሞና ከታሰሩ ወገኖች በኩል ሊገኝ የሚችለውን የመረጃ ፈርጅ ሰብስቦና አገናዝቦ አለማቅረቡ ወሳኝ ድክመት መሆኑ ጎልቶ አለመውጣቱ፣ በዚህ ፈንታ የኮሚሽኑ ሪፖርት ገለልተኛ ነው የሚለው ማሞካሸት መድመቁ፣ በዚህ ውስጥም የተወሰኑ ፓርቲዎች አጫፋሪ መሆናቸው፡፡ ሁለተኛ በድርድሩ ተስፋ አጣን ብለው “መድረክ”፣ “መኢአድ” እና “ሰማያዊ ፓርቲ” ራሳቸውን ማግለላቸው፣ በድርድሩ ውስጥ ከቀሩት ተቃዋሚዎች መሀል ካለው አንድ ብቸኛ ትልቅ ፓርቲ (ኢዴፓ) በኩልም ድርድሩ ብዙም ተስፋ የሚያሳድር እየሆነ እንዳልሆነ መነገሩ (ልደቱ አያሌው በ“ኢኤንኤን” ፊት ለፊት ቃለ መጠይቅ ላይ)፣ የተሳትፎ ክብደቱና ተስፋ ሰጪነቱ የቀለለው ድርድር እስካሁን ቅለቱን አለመቀየሩ፡፡ ሦስተኛ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት ከመንግሥትም ከፓርቲም መሣሪያነት ነፃ መሆን አለባችሁ በተባሉበት አፍ የመንግሥት አጋር ናችሁ የተባሉበትን መንግሥት ቀመስ ውስወሳ አልፈው በነፃነት ራሳቸውን ለማደስ ገና አለመድፈራቸው ሁሉ የተፋዘዘ እውነታ እንዳለ ለመረዳት ያግዛሉ፡፡ አራተኛ ከእነዚህ ሁሉ በላይ፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ለውይይት አቅርቦት በነበረ ጥናት መሠረት ሥራ አስፈጻሚው ላይ ሲታይ ቆይቷል ስለተባለ ጠያቂ የለሽ እላፊ የሥልጣን አጠቃቀም ጉዳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተጠይቀው ደስተኛ ባልሆነ ስሜት ጥናት ስለመደረጉ የማያውቁና ጥናት ሊባል የሚበቃ ሥራ የተሠራም እንደማይመስላቸው መናገራቸው፣ በፊት ይድበሰበስ የነበረውን የክፍፍል ሐሜት አጠናክሯል፡፡

የዚህ ዓይነቱ የተሸፋፈነ መጓተት ለሴራ መነሳሻ የመሆኑን ያህል፣ መሣሪያ የታጠቁም ሆኑ ያልታጠቁ የመንግሥት አውታራትን በፓርቲ ወገናዊነት መጠረዝ አደገኛ ጥፋት መሆኑን አጉልቶ ያሳያል፡፡ ለረዥም ጊዜ አውታራት ፖለቲካዊ አጋዳይነት ሊኖራቸው አይገባም እየተባለ ሲወተወት የነበረውም የትኛውም ፓርቲ ሆነ አንጃ እንደ ከዘራ እንዳይጠቀምባቸው ነው፡፡

አሁን ባለንበት ምዕራፍም ዴሞክራሲን ሥር የማስያዝ እንቅስቃሴው እንዳይታገትና ወደ ኋላ እንዳይመለስ የምንሻ ወገኖችና ፓርቲዎች ሁሉ ኢሕአደግ ነህ፣ ተቃዋሚ ነህ ሳንባባል ለሚከተሉት የለውጥ አንኳሮች አንድ ላይ መቆም ያስፈልገናል፡፡

 • የመንግሥታዊ ተቋማትን ከፓርቲ ፖለቲካ ታማኝነት ማላቀቅን ፅኑ የትግል አቋም አድርጎ መያዝ፣
 • መአት ጥያቄዎችን አንጋግቶ ለፍርኃትና ለግራ መጋባት ምክንያት ከመሆን መቆጠብና ተቀዳሚ በሆነው የጥርጊያ ተግባር (ጤናማ የፓርቲዎች ግንኙነትን በማጠናከር፣ ለመጪው ምርጫ ተስማሚ የሕግና የአሠራር ሁኔታዎችን እንዲሁም ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚነትና የታዛቢነት አየርን በማበልፀግ፣ በነፃ ሐሳብን በማንሸራሸርና በነፃ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ ልምምዶች) ላይ ማተኮር፡፡

ከዚሁ ተግባር አኳያ፣

 • የፓርቲዎቹ ድርድር ያፈገፈጉትንም አካቶና ፓርቲዎቹን ከመገምገም የሕዝብ  መብት ጋር ተጣጥሞ ወደ ውጤት እንዲደርስ መታገል፣
 • የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የመንግሥትን ፊት ሳያዩ በአዲስ የነፃነት ስሜት ማኅበሮቻቸውን እንዲያድሱ፣ ለየትኛውም ፓርቲ መሣሪያ ሳይሆኑ እንዲንቀሳቀሱ ማበረታት፣
 • ከማበረታትም ባሻገር በዛሬው የዴሞክራሲን መሠረት የመጣል ሥራ ውስጥ የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የየትኛውም ፓርቲ አጫፋሪ አለመሆን እጅግ ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው ማስጤን፣
 • ከ2008 ዓ.ም. ድፍን ዓመት እስከ 2009 ዓ.ም. የመጀመሪያው ወር ድረስ በነበረው ጊዜ እየተምዘገዘገ ባደገው ቅዋሜ ውስጥ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂነቱ የቁጣ ተሳታፊዎችም የመንግሥትም (የሁለቱም) ስለነበር፣ ተጠያቂነቱም ጥቂት ግለሰቦችን ለፍርድ በማቅረብ የማይጠናቀቅ በመሆኑ፣ ሕዝብ ውስጥ ውለው ያደሩ ቅሬታዎች ከፍርድ ይበልጥ የእርቅ ሒደትን የሚሹ ስለሆነ፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት የተነገረው የ20 ሺሕ ያህል ሰው መፈናቀልም ይህንኑ መፍትሔ የሚደግፍ በመሆኑ፣ በአግባቡ ተመርምረው ፍርድ ሊያገኙ ከሚገባቸው ግድያዎች በቀር ቀሪዎቹ ተያያዥ ክሶች ተቋርጠው ማኅበረሰቦችን በእርቅ የማቀራረብ ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝና ለዚሁም ሥራ አስፈላጊው መሰናዶ እንዲደረግ ጥረት ማድረግ፡፡
 • በመጨረሻም በእርቅ መንፈስ ውስጥ በመሆን አሉ የተባሉ ችግሮችን መመርመር፣ መለየትና በመፍትሔዎቻቸው ላይ መነጋገር፣ በጊዜው ሊፈቱ የሚችሉትን መፍታት መጀመር፣
 • አብሮም ለነፃና ለፍትሐዊ የምርጫ ውድድር የሚቻለው የጥርጊያ ሥራ ሁሉ በመከናወኑ ላይ ተግባብቶ ወደ ምርጫ መግባት፡፡  

በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ ማለፍ ከቻልን እስከ ዛሬ ካየናቸው በተሻሉ ንቁና ብርቱ እንደራሴዎች/ምክር ቤቶች አማካይነት የዴሞክራሲን መሠረት ይበልጥ የማጠናከርና ትልልቅ ችግሮችን የማቃለል ድል ላይ እንደርሳለን፡፡ እንቅስቃሴያችን በመንግሥታዊ መድረኮች ውስጥና መንግሥት በፈቀደልን ልክ ከተመጠነ ግን የዴሞክራሲ ለውጡን አሽመድምዶ ‹በዱሮ በሬ ማረስ› በሚሻው መስመር ውስጥ መስመጣችን የማይቀር ነው፡፡ እስከ ዛሬ በአሥራ ምናም ሺሕ ቁጥር የተካሄደው ሹምሽር፣ በስቱዲዮና በአዳራሽ መድረኮች የተወራው ወሬና ድርድሩ ሁሉ “አለው አለውና ሳይመታው ቀረ!” የሚባለው ተረት ይደርስባቸዋል፡፡ ውጤቱ ይህ ከሆነ እንደለመድነው ለክሽፈት ታማኝነታችንን አረጋግጠን እንዲህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እያልን ያመለጡ ዕድሎችን መቁጠራችንን እንቀጥላለን፡፡

ያመለጡ ዕድሎች ቆጠራው በዴሞክራሲ መሰናከልና በአምባገነንት መቀጠል ብቻ ጠቦ መታየት የለበትም፡፡ ዴሞክራሲ ሥር ያዘ ማለት የፖለቲካ ሰላም ቀጥታ ተገኘ ማለት ባይሆንም፣ የፖለቲካ ሰላም ግንባታ መሠረቱ እሱ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲ ተሰናከለ ማለት የአገሪቱ የፖለቲካ ጣጣዎችም እየተባባሱ መሄድ ማለት ነው፡፡ ችግሩ ከከፉ ፖለቲካዊ ውጤቶች በመለስ ባሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ እንኳ የሚገባ ነው፡፡ ያለንበት የዛሬው ዓለም የበለፀጉ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት መንቀራፈፍና ከቀውስ/ከሽብር መስፋፋት ጋር የተያያዘ የደሃ አገሮች ዕርዳታ ፈላጊነት የተበራከተበት እንደመሆኑ፣ ለድርቅና ለረሃብ  አደጋ እንኳ ከውጭ ልገሳ የማግኘት ዕድል ዛሬ በተግባር እንደታየው ከባድና ራስን በራስ ለመርዳት አስቀድሞ መዘጋጀትን ጠይቋል፡፡ በደሃ አገር ደረጃ የተገኘ የውጭ ምንዛሪን በስደት እያስመነተፉ እንደገና በሕገ ወጥነትም ሆነ በሌላ ቀውስ ምክንያት የሚመለስ የስደተኛ ጎርፍን መልሶ በማቋቋም ተግባር ውስጥ የመንግሥትን፣ የዜጎችንና የግል ባለሀብቶችን አቅም እየተሻሙ በአዙሪቱ ውስጥ መዳፋት ራስን ከማዘጋጀት ጋር ይቃረናል፡፡ ወደ ውጭ አገር ገንዘብ እስከ ማሸሽ የረዘመ ጫፍ ያለው በተለያየ ሥልት የሚካሄድ የገንዘብ ቡጥቦጣም ልማትን ከማሰናከል አልፎ የኢኮኖሚ መቃወስን የሚጎትት ነው፡፡ አሁን አሁን እንደ ወረርሽኝ እየተበራከቱ የመጡት የዕርዳታ መጠየቂያ መድረኮች ለከት ካልተበጀላቸው ሄደው ሄደው የግል ባለሀብቱን የውዴታ በጎ አድራጊነት ገና በታዳጊነቱ ልሰው የሚያደርቁና ባለሀብቱ ሌላ ሥውር የወጪ ማካካሻ እንዲፈልግ ወይም የተሻለ የሥራ ሁኔታን ከአገሩ ውጭ እንዲያማትር የሚገፋፉ ናቸው፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች እስካልተዳከሙ ድረስም ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በጤና ዋስትና፣ በገንዘብና በሥራ በመድገፍ ረገድ የተጀማመረው የማኅበራዊ ዋስትና እንቅስቃሴ ማደጉ ቀርቶ ለመክሸፍ አደጋም ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ይኼ እንዳይሆን፣ መንግሥትም በማይወጣው የዕዳና የወጪ አዙሪት እንዳይመታ መዳኛው በዴሞክራሲ በኩል የመንግሥትን ህልውና በሰፊ የፖለቲካ ተቀባይነት ላይ መገንባት ነው፡፡ ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት ያለበት መንግሥትነት እጅግ ወጪ ቆጣቢ ነው፣ ዘረፋን የማኮላሸት አቅም ይኖረዋል፣ በሥልጣን ለመቆየት ሲባል የሚከሰከስን የተስፋፋ የስለላና የፕሮፓጋንዳ ወጪ ለሌላ ሥራ ነፃ ያወጣል፡፡ ከሕዝብ በምን ዘዴ ገንዘብ ልምጠጥ በሚል ጭንቀት ሳይጠመድ አግባብና ኢባካና የሆነ የግብር/የቀረጥ አሰባሰብና አጠፋፍ ለማካሄድ ዕድል ያገኛል፡፡ የመንግሥት በሕዝብ መፈቀር ይኼን ያህል ኢኮኖሚ ገብ ውጤት አለው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...