Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጋምቤላ ክልል የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት ከ100 በላይ ሰዎች ሞት የተጠረጠሩ 45...

በጋምቤላ ክልል የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት ከ100 በላይ ሰዎች ሞት የተጠረጠሩ 45 ግለሰቦች ተከሰሱ

ቀን:

-የክልሉ ልዩ ኃይልና የፀጥታ አስከባሪዎች በክሱ ተካተዋል

ከጥር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል የግለሰቦችን ፀብ ምክንያት በማድረግ የአኝዋና የኑዌር ተወላጆችን በብሔር በመከፋፈል፣ የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት ለ106 ሰዎች ሞት የተጠረጠሩ 45 የክልሉ ልዩ የፖሊስ አባላት፣ የፀጥታ አካላትና ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በክልሉ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ግለሰቦች በፈጠሩት ፀብና በጋምቤላ ከተማ ‹‹መሬት ይገባኛል›› ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው የግለሰቦች ፀብ ወደ በቀል በማምራቱ፣ የአኝዋና የኑዌር ተወላጆች በብሔር ተከፋፍለው ጎራ በመለየት እርስ በእርስ ውጊያ ጀምረው እንደነበር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

የአኝዋና የኑዌር ብሔረሰቦች በማለት ተከፋፍለው የመንግሥት ሥራንና የአካባቢውን ፀጥታ እንዲጠብቁ በተመደቡበት የጁሀር፣ ኝንኛንግ፣ ቢልዳግ፣ ፑልዴግና አድራ በተባሉ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በታጠቁት የጦር መሣሪያ እርስ በእርስ ተዋግተው 23 የፖሊስ አባላት መሞታቸውንና ሁለት መቁሰላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በአኝዋና በኑዌር ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች፣ በጋምቤላና ዙሪያው ባሉ ከተሞች ግጭቱ በመስፋፋቱ 83 ሰዎች መሞታቸውንና 73 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ግጭቱ ወደ ጋምቤላ ማረሚያ ቤትና አቦቦ ማረሚያ ቤት በመዛመቱ፣ ታራሚዎችና በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ያሉ ፖሊሶች በብሔር ተከፋፍለው በመጋጨታቸው፣ ስምንት ታራሚዎች መሞታቸውንና ስምንት ታራሚዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ በአቦቦ ማረሚያ ቤት ውስጥም ሦስት ታራሚዎች ተገድለው 127 ታራሚዎች የገበቡበት እንደጠፋና 259 ታራሚዎችና እስረኞች እንዲያመልጡ መደረጉን ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ በግጭቱ 18,339 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን፣ 835 የቤት እንስሳት ተቃጥለው መሞታቸውን፣ ንብረቶች መውደማቸውን፣ በከተማው ዙሪያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት አገልግሎት መስጠት አቁመው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ዳክ ኡጉት ኪሩ፣ አቡወላ ኡመድ፣ ኡባንግ ኡመድ፣ ሳጅን ኡማን ጆክ፣ ሳጅን ኡኬሎ ኡመድ፣ ሳጅን ኡማን ኡጅሉ፣ ሳጅን ኡባንግ ኡጉድ፣ ረዳት ሳጅን ኡጅሉ ኡፓንግ፣ ሳጅን ኡጁሉ ቲሮ፣ ኡጁሉ ቻሞ፣ ኡፑኝ ኡኮንጎ ኡቻላና ኡቶዋ አጉዋና ሌሎቹም ተከሳሾች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀናለ) እና 240 (3)፣ 35፣ 38፣ 539(1ሀ)፣ 555(ሐ)፣ 425(2)፣ 462(2ሀ)፣ 461፣ 445ን በመተላለፍ ወንጀሉን እንደፈጸሙ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ አብዛኛዎቹ ተከሳሾች የዞኖቹ የፀጥታ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የፖሊስ ኦፊሰሮች መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ማዕረጋቸውን በመግለጽ ያሰፈረው የስም ዝርዝራቸው ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ታራሚዎች እንዲያመልጡ በማድረጋቸው፣ የጦር መሣሪያ ይዘው በማመፅ ወይም የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት በመንግሥት ላይ ጦርነት በማነሳሳት ወንጀል፣ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል፣ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል፣ እስረኛን ሕገወጥ በሆነ መንገድ መፍታትና እንዲያመልጡ መርዳት ወንጀል፣ የመሸሸግና መርዳት ወንጀል ክስ መሥርቶ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለልደታ ምድብ ተዘዋዋሪ ችሎት አቅርቧል፡፡ በመሆኑም የተከሳሾቹን የክስ ሒደት በጋምቤላ ከተማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በተዘዋዋሪ ችሎት ለማየት ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...