አድናቆትን ያተረፈው የዕውቁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘው አልበም ባለፈው ረቡዕ አደባባይ ውሏል፡፡ በአድናቂዎቹ ሲጠበቅ የቆየው ሙሉ አልበሙ ከመለቀቁ ሳምንታት በፊት በነጠላ ዜማነት ‹‹ኢትዮጵያ›› እና በፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ ታሪክ ላይ የተመሠረተው ‹‹ማር እስከ ጧፍ›› በማኅበራዊ ገጾችና በብሮድካስት ሚዲያው ሲሰራጭ ባገር ቤትም ሆነ በባሕር ማዶ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አልበሙ ሚያዝያ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ለገበያ ሲውል፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ የሚቸረችሩና የአልበሙ መውጣትን የሚያበስሩ ማስታወቂያዎች በየተሽከርካሪው በሙዚቃው ታጅበው ሲቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ 570 ሺሕ ኮፒዎችም ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ በደራው የአልበሙ ሽያጭ ከመደበኛው ዋጋ 50 ብር በእጥፍ እስከ 100 ብር እየተቸበቸበ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ተመልካች የተመለከተውን ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘ ሥራ የያዘው አልበም ሸመታ ከመደብሮች ባለፈ በየጎዳናው በሚተላለፉት ተሸከርካሪዎች ለተሳፋሪዎች ሲሸጥ ታይቷል፡፡ ባለ 14 ዘፈኖች መድብሉ ግጥሞቹን ከተለያዩ ፎቶዎች ጋር የያዘ ክርታስ አለው፡፡ ከተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸውን ታዋቂዎች ምስል ይዟል፡፡ ቴዲ አፍሮ ከዘፈነላቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ፎቶና ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሆኖ የሚታይበት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች በአንዱ አልበሙን እያስተዋወቁ የሚሸጡ ይታያሉ፡፡
(ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው)
***
ቀለም ያዘ ልቤ
ከእምነት – ተለይቶ
ከፍቅር – ተፋ’ቶ
ሰው ፈርቶ – ሰው ጠልቶ
ቀለም ላይቀበል – ምሎ ተገዝቶ
የተሸሸገውን
የተደበቀውን
አገኘሽውና የልቤ ስፍራውን፣
አንኳኩተሽ – ብትከፍችው
ከፍተሽ – ብታጸጂው
አጽድተሽ – ብታጥኚው
አጥነሽ – ብታጠምቂው፣…
የተሸሸገበት – ምሽጉን ናደና
ፊደል አልቀበል – ማለቱ ቀረና
ለእውቀት ተሸንፎ – ልቤ እጁን ሰጠና፣…
በአንቺው ፍቅር ጠርቶ
በአንቺው እውነት ጸድቶ
በእምነትሽ ተረ’ቶ
‹‹ወውደድ›› ተጻፈበት፡-
ቀለም ያዘ ልቤ፣ ልብሽን አግኝቶ፡፡
ጌትነት እንየው ‹‹ዕውቀትን ፍለጋ›› (2004)