Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሙገር ሲሚንቶ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ተማርሬአለሁ አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንጋፋው የሲሚንቶ አምራች የሆነውና በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደረው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በምርታማነቱ ላይ ትልቅ ሳንካ እንደፈጠረበት አስታወቀ፡፡

በተደጋጋሚ የሚገጥመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሲሚንቶ በማምረት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንና ማሽኖች ለብልሽት እንደሚዳረጉበት፣ ይህም ለምርት መቋረጥና ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረገው ፋብሪካው አስታውቋል፡፡ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ጥናትና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተባባል ውድነህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦት ተብሎ ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከተተከለ ትራንስፎርመር የተቀጠለ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር በመኖሩ በገጠር ቀበሌዎች መስመር ላይ የቴክኒክ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ችግሩ ወደ ፋብሪካውም መስመር ይመጣል፡፡

‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በፋብሪካው ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፤›› ያሉት አቶ ተባባል፣ ከፋብሪካው ትራንስፎርመር ላይ ለገጠር ቀበሌዎች ተብሎ የተዘረጋው መስመር የሚነጣጠልበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማመልከታቸውንና በኮሚቴም ደረጃ በተደጋጋሚ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እመርታ ባሳየበት ወቅት የተፈጠረውን የሲሚንቶ እጥረት በመመልከት የሙገር ሲሚንቶ በ138 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በማካሄድ የማምረት አቅሙን 150 በመቶ በማድረስ በዓመት ወደ 2.2 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ አሳድጓል፡፡ ይሁን እንጂ ባለበት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የተተከለውን አዲስ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንዳልተቻለ የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ ለገበያ ቅርበት ሲባል የፋብሪካው ሁለተኛ ክፍል የሆነው ወፍጮና ሲሚንቶ ማሸጊያ በታጠቅ አካባቢ ተገንብቷል፡፡ አቶ ተባባል እንዳሉት በታጠቅ ሁለት ትልልቅ እያንዳንዳቸው በሰዓት 105 ቶን የመፍጨት አቅም ያላቸው ማሽኖች የተተከሉ ቢሆንም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በግማሽ አቅም ብቻ እየሠሩ ነው፡፡ ‹‹በታጠቅ እየሠራን ያለነው በ50 በመቶ አቅም ብቻ ነው፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተደጋጋሚ ጥረት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ታጠቅ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ፋብሪካውን እንደጎዳው የሚናገሩት አቶ ተባባል፣ ሙገር ዋና ፋብሪካው ላይ የክሊንከር ምርት በሙሉ አቅም ማምረት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለው በጥሬ ዕቃ አቅርቦት በኩል በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ከኳሪ የጥሬ ዕቃዎች ዝግጅት በአግባቡ ማካሄድ ባለመቻሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ውድ የሆኑ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍሎች እንደሚቃጠሉ፣ መሣሪያዎቹን ከውጭ በትዕዛዝ ለማስመጣት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ አንድነት ደጉ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ለብቻው የተተከለ በመሆኑ ከገጠር መስመር ጋር አይገናኝም ብለዋል፡፡ ‹‹ብሬከር የመለየት ሥራ በቅርቡ ሠርተናል፡፡ የገጠር መስመሩ ለብቻ ተለይቶ የሚያስወጣ ተሠርቷል፤›› ያሉት አቶ አንድነት፣ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን አልፎ የሚሄድ 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት ምሰሶ የመለወጥ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታጠቅ ፋብሪካ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በተመለከተ አቶ አንድነት የሰብስቴሽን አቅም ውስንነት መኖሩን አምነዋል፡፡ ‹‹የፋብሪካው ማስፋፊያ ከስምንት ዓመት በፊት ሲሰሠራ ከነበረው የሲሚንቶ እጥረት አኳያ፣ አዲሱ ፋብሪካ በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገባ ከመንግሥት በተሰጠ መመርያ አማካይነት ሰብስቴሽን ሳይገነባ ነው የኤሌክትሪክ መስመር በቀጥታ የተሰጠው፤›› ያሉት አቶ አንድነት፣ በአሁኑ ወቅት ገፈርሳ ያለው ሰብስቴሽን ከፍተኛ የአቅም ውስንነት እንዳለበት ገልጸው፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሰብስቴሽን ማሻሻያ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ችግሩን ለመፍታት ሁላችንም እየተረባረብን ነው፡፡ የሰብስቴሽኑ ግንባታ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ መስመር የማገናኘት ሥራ በቅርቡ ይሠራል፡፡ ለፋብሪካው ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡም ስለምንፈልገው በጉጉት እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዓመት 2.2 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሙገር ሲሚንቶ የአቅሙን ከ55 እስከ 60 በመቶ ያህል እየተጠቀመ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በቀድሞ ወታደራዊ መንግሥት በ1976 ዓ.ም. የተቋቋሙ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በምሥራቅ ጀርመን ባለሙያዎች የተተከለ የጀርመን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በ1990 ዓ.ም. የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካንና የአዲስ አበባ ሲሚንቶ ፋብሪካን በማዋሀድ እንደ አዲስ በ334.7 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሦስት የምርት መስመሮች ሲኖሩት የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ1984፣ ሁለተኛው በ1990 እና በ2011 ሥራ ጀምረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሙገር ሲሚንቶ የሚተዳደረው በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሥር ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የአገሪቱን የኬሚካል አምራች ንዑስ ዘርፍ ልማት እንዲያስተባብርና እንዲመራ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እ.ኤ.እ. በ2012 በ21.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በተጨማሪ በማጂ ዞን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጎማ ዛፍ ልማት ምርትና የዩሪያ ልማት ፕሮጀክቶችን ያስተዳድራል፡፡

ሙገር ሲሚንቶ ባለፉት ዓመታት ትርፋማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ለዚህም አንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ፋብሪካው ሲጠቀም የነበረው የፈርነስ ነዳጅ ለከፍተኛ ወጪ ስለዳረገው እንደሆነ አቶ ተባባል አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የፈርነስ ነዳጅ መጠቀሙን አቁሞ ወደ ድንጋይ ከሰል በመዞሩ፣ በአሁኑ ወቅት በወደ ትርፋማነት በመሸጋገር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው በብር ምንዛሪ ማሽቆልቆል ከቻይናው ኤግዚም ባንክ ለማስፋፊያው ፕሮጀክት የተበደረውን ብድር ክፍያ ፈታኝ እንዳደረገበት ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካው የጎማ ዛፍ ፕሮጀክቱንና ዋና መሥሪያ ቤቱን (የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን) በገንዘብ የሚደግፍ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ኃላፊነቶች የተጣሉበት እንደሆነ አቶ ተባባል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ የድንጋይ ከሰል መጠቀም ከጀመረ በኋላ ወደ ትርፍ በመምጣት ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች