Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን ለማስቆም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጥናቱን እያጠናቀቀ መሆኑ ታወቀ

ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን ለማስቆም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጥናቱን እያጠናቀቀ መሆኑ ታወቀ

ቀን:

  • የአሜሪካ ኤምባሲ ያለውን ለውጥ በሚመለከት መንግሥትን ማብራሪያ ጠይቋል

ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን ሙሉ በሙሉ ለማቆም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጥናቱን እያጠናቀቀ እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻን ለማቆም ምክንያት የሆነው፣ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚወሰዱ ሕፃናት የሚደርስባቸው ከባድ እንግልትና የማንነት ቀውስ መሆኑ በጥናቱ ተለይቶ ተቀምጧል፡፡

ጥናቱ ዓለም አቀፉ ጉዲፈቻን ማቆም ብቻም ሳይሆን በቀጣይ በአገር ውስጥ የሚካሄደው ተቋማዊ ጉዲፈቻም (Institutional Adoption) እንዲቆም፣ መሆኑን በተቃራኒው የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲበረታታ ማድረግን ያለመም ነው፡፡ ይህ ማለት ኅብረተሰቡ በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን እንደ አቅሙ እንድም ይሁን ሁለት ልጅ በመውሰድ ከልጆቹ ጋር ቀላቅሎ እንዲያሳድግ ነው የሚበረታታው፡፡

በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ጉዲፈቻ ላይ ነገሮች እንዲጠብቁ መደረጉን የጠቆሙት ምንጮቹ፣ ከቀድሞ በተለየ መልኩ የዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ ጥያቄዎች እየተስተናገዱ ያሉት ጉዳዮች በዋነኝነት በሚመለከተው የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ በአጠቃላይ ከአራት የመንግሥት ተቋሟት በተቋቋመ ኮሚቴ ታይተውና ተረጋግጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ልጆች በዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ እየተወሰዱ ያሉትም ከተወሰኑ ድርጅቶች ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፉ ጉዲፈቻ ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ ሕፃናት ቁጥር ከመቼውም በላይ መጨመሩ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. 2010 ላይ በዓለም አቀፉ ጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ከሄዱ ሕፃናት ከኢትዮጵያ የሄዱት አንድ አራተኛ ድርሻን ይዘው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሜሪካውያን ብቻም ሳይሆን በካናዳውያንና አውሮፓውያን የተወሰዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ በብዙ ሺሕዎች ጭማሪ ማሳየቱም እንዲሁ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከዚህ በዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ የሚወሰዱ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ቁጥር በፈጣን ሁኔታ መጨመር ጋር በተያያዘ የሙስና፣ ሕገወጥ የሕፃናት ዝውውርና ማጭበርበርን የመሰሉ ጉዳዮች በተለያየ ጊዜ እንደ ከባድ ችግር ተለይተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ጉዲፈቻ በከፍተኛ ሁኔታ ለብዙዎች የገንዘብ ምንጭ ከመሆኑም ጋር በተያያዘ ‹‹የኢትዮጵያ አዲሱ የኤክስፖርት ኢንዱስትሪ›› በሚል መዘገቡም ይታወሳል፡፡    

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) ያወጣው ማስጠንቀቂያ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ እንዲቆም መወሰኑን፣ ውሳኔውም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚፀና አለመታወቁን ጠቁሟል፡፡ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት በሒደት ላይ የነበሩ የጉዲፈቻ፣ ጉዳዮች እንዲቀጥሉም በስቴት ዲፓርትመንት ተጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ ላይ ያደረገውን የፖሊሲ ለውጥ በሚመለከት ከመንግሥት ማብራሪያ መጠየቁን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከውሳኔው በፊት የነበሩ ጉዳዮች ቀጣይነት በሚመለከትም እየሠራ መሆኑን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...