Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገራዊ መግባባት ለብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ወሳኝ ዕርምጃ ነው!

አገራዊ መግባባት ለብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ወሳኝ ዕርምጃ ነው!

ቀን:

በአበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው ሁኔታ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውጥረትና ሁከት የታየበት፣ የአጭር ጊዜ፣ መካከለኛና ስትራቴጂካዊ የረዥም ጊዜ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ባለመቻሉ ፖለቲካዊ ችግሩ ሄዶ ሄዶ ወደ ደኅንነት ችግር (Security Problem) ተሸጋግሮ አገራችን በአስቸዃይ ጊዜ አዋጅ እየተዳደረች ትገኛለች፡፡ ለዚያውም ስድስት ወራት ያልበቃው አራት ወራት ጭማሪ የጠየቀ ክስተት ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ማለት የገጠመን ችግር አገርን ሊበትን የሚችል፣ የግዛት አንድነቷንና የሕዝቦቿን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል የደኅንነት ችግር ነው ማለት ነው።

ጉዳዩን እንዲህ ባለ ከፍታ አጉልተን ስናይ ነው ለመፍትሔው የምናደርገው እንቅስቃሴ እርባና የሚኖረው። በሰላም ወጥቶ በስላም መመለስ ያለመቻል፣ ስለነገ ውሎ እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት የሥጋት ኑሮ፣ ኢንቨስትመንትና የሕዝቦች ሀብት በአድማ እሳት የሚበላበት፣ በአንድ ቀን በርከት ያሉ ፋብሪካዎች የሚወድሙበት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎቶች መውደምና መሽመድመድ፣ ሥራና የቀን ተቀን ግብይት መቆምና የትራንስፖርት ዘርፍ መቆራረጥ ማለት የአንድ አገር አጠቃላይ ደኅንነት አደጋ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው።

ሕዝቦች እርሰ በርስ የሚጠራጠሩበትና አንዱ ሌላው ላይ የሚያቄምበት አዝማሚያ የፖለቲካ ችግር ተብሎ በቀላሉ የሚወሰድ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የአገርና የሕዝቦች ድኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል ማለት ነው። ልማትና ዴሞክራሲ እክል ገጥሞታል ማለት የደኅንነት ችግር ገጥሞናል ማለት ነው። ስለዚህ ፖለቲካዊ ችግሩ ወደ ደኅንነት ችግር ልቆ ተሻግሯል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ አኳያ ነው መታየት ያለበት።

ሰሞኑን መንግሥት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተነገረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ለውይይትና ለድርድር ተቀምጠዋል፡፡ አካሄዳዊ (Procedural) ጉዳዮችን አጠናቀው አሁን የውይይት አጀንዳዎችን በመቅረፅ ላይ እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን እየሰማን ነው፡፡ ፖሊሲውን የማሻሻል ሒደትና የፓርቲዎች ውይይትና ድርድር ለየቅል የሚሄዱ ሒደቶች ናቸው እንዴ? ፓርቲዎች የሚደራደሩበት ዋነኛው አጀንዳ ምን መሆን አለበት? በዝርዝር ጉዳዮች ወይስ የፖሊሲዎች ቁንጮ በሆነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ? በሌላ አነጋገር ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ጠቀሜታ ባለው የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ወይስ በቅርንጫፍ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ነው መወያየት ያለባቸው? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን መዳሰስ ተገቢ ነው፡፡

ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉዋቸው ውይይቶችና ድርድሮች በብሔራዊ ደኅንነት መግባባትን ለመፍጠር ከሆነ ይዘቱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱ ጭምር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በአንድ በኩል ጥናትና ምርምርን መሠረት ያደረገ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሒደቱ አሳታፊ (Participatory)፣ እንዲሁም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት (Stakeholders) የሚያቅፉ (Inclusive) እንዲሆን ምን መደረግ አለበት? የሚለው መመለስ አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የማዳን ድርድር ከሆነ መግባባት የሚያስፈልገው በተጋረጠብን ከፖለቲካዊ ችግር በላይ ጎልቶ በወጣው የደኅንነት ሥጋታችን ላይ መሆን ያለበት ይመስለኛል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ የውጭና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ግምገማ” የሚል የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሱን የሚዳሰስ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ የፖሊሲው መሠረታዊ ጥንካሬዎችና ድክመቶች ምን መደረግ አለባቸው? የሚለውን ንድፍና ጽንፈ ሐሳባዊ ማዕቀፎች (Concepts and Theories of Security) መሠረት አድርጎ የተጻፈ ነበር፡፡ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር አዛምዶ ለጋዜጣ በሚሆን መልኩ ያለኝን አስተያየት ለመዘርዘር ነው፡፡ የደኅንነት ጉዳይ ከፖለቲካ በላይ ቁንጮ በመሆኑ ለፓርቲዎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን እንደየአቅማችን እንድንሳተፍ ይጠይቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በጉዳዩ ዙሪያ የግል አስተያየት በመሰንዘር ሌሎችም እንዲሳተፉ ለመጋበዝ ነው፡፡

ጽሑፉ አገራዊ መግባባት ስንል ምን ማለታችን ነው? በሚለው ይጀምርና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ለምን የሁሉም ፖሊሲዎችና ሕጎች ቁንጮ እንደሆነ ያብራራል (ከሕገ መንግሥቱ በመለስ):: ቀጥሎም የ1994 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ይገመግማል፡፡ በመጨረሻም ምን መደረግ አለበት? የሚለውን የግል አስተያየት ያስቀምጣል፡፡ የሕዝቦቻችንና የአገራችን ደኅንነት የሚጠበቀው ፈጣን ልማት ሲረጋገጥና የዴሞክራሲ መስተዳደር በቀጣይነት መሠረት ሲጥል ነው፡፡ ከዚህም ተነስቶ ዋናው የደኅንነት አደጋ የዴሞክራሲ እጥረት ነው ይላል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጠባብነት፣ ወዘተ. የሚሉት ቅርንጫፎችና አጫፋሪዎች ችግሮች ቢሆኑም ከዋናው ችግራችን ማለት ከዴሞክራሲ እጥረት ሊያዛንፉን አይገባም፡፡

መሠረታዊ ችግሮቻችን ሕገ መንግሥታችን በግልጽና በተሟላ መንገድ ያስቀመጠውን የሦስት ትውልድ መብቶች (Three Generations Of Human Rights) አለመተግበር ነው፡፡ መላውን ኅብረተሰብ የሚመለከት ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ልዩ ቦታ አላቸው፡፡ ትምክህትና ጠባብነት ማምለጫ መሆን የለባቸውም፡፡ በ1990 የኤርትራ መንግሥት ባልተዘጋጀንበት ለምን እንደወረረን ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በዋናነት የተደራጀ የደኅንነት ፖሊሲና አስተዳደር ባለመኖሩ መሆኑን አጠር ባለ መንገድ ያስቀምጣል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው አመፅ ለምን እንደ አገር ዱብ እዳ ሆነብን? አመፅ እየመጣ መሆኑን ከወዲሁ ለመገመት ለምን አልቻልንም? በ2008 ዓ.ም. ኅዳር አካባቢ የተከሰተው የኦሮሞ ተቃውሞ እንዴት የመጀመርያ ዙር መሆኑን ለማወቅ ተሳነን? እንዴት አመፅ ከመምጣቱ በፊት ልንከላከለው አልቻልንም? አሁንስ እንደዚያ ዓይነት ነገር አመፅ እንዳይከሰት መሠረታዊ መፍትሔዎች አስቀምጠናል ወይ? በሒደት ይዳሰሳሉ፡፡

አገራዊ መግባባት ስንል?

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስንል በውሳኔ አሰጣጥ ባለድርሻ አካላት በአገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች (በየደረጃው) በፖሊሲ ሕግ በይዘቱ ይሁን በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት የሚመለከት ነው፡፡ ሕዝቦች በቀጥታ ይሁን የሚወክላቸው አደረጃጀት (ፍላጎታቸውን) የሚያንፀባርቁና የሚገልጹዋቸው (Articulate) የሚያደርጉባቸው ፓርቲዎች፣ ማኅበራት፣ ወዘተ. ፖሊሲው ሕጉን እንዲያውቁትና እንዲተቹት፣ ሐሳባቸውን የሚያሳርፉበት፣ በቀጣይነት ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡበት ሒደት መግባባትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሒደቱ ከይዘቱ አይተናነስም የሚባለውም ለዚህ ነው።

የፖሊሲ/ሕጉ አመንጪዎች (ከፍተኛ አመራር) ጭምር በመግባባት የሚጀምር የአብላጫው ሐሳብ ብቻ ሳይሆን፣ የውህዳን ድምፅ (Minority’s Voice) በሚገባ የሚሰማበት ሒደት ነው:: በፖሊሲው/ሕጉ የተወሰነ አንቀጾች ልዩነት ቢኖርም አጠቃላይ ይዘቱና በውሳኔ አካሄዱ ዴሞክራሲዊ ከሆነ ሁሉም በየኔነት ስሜት ለተግባራዊነቱ የሚረባረቡበትና መሻሻል ያለባቸው ላይ ቀጣይ ትግል እንደሚያስፈልገው አምነው፣ ባለድርሻ አካላት መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ብሔራዊ መግባባት ደረጃ በደረጃ እየተረጋገጠ ነው እንላለን፡፡ በብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ብሔራዊ መግባባት ለምን አስፈለገ የሚለውን ቀጥሎ እናየዋለን?

ብሔራዊ የደኅንነት ፖሊሲ የሁሉም ፖሊሲዎች ቁንጮ ነው ለምን?

በተለምዶ አስተሳሰብ ብሔራዊ ደኅንነት ማለት በዋናነት ውጫዊና ወታደራዊ አድርጎ ማሰብ የተለመደ ነው፡፡ ሉዓላዊነት (Sovereignty) እና የግዛት አንድነት (Territorial Integrity) በውጭ ሥጋት የሚሽከረከር እንደ ታሪካዊ ጠላቶችን ዓይነት አስተሳሰብ ገዥ ሐሳብ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ባደጉ አገሮች አሁንም ወሳኝ አስተሳሰብ ነው፡፡ ያደጉ የምዕራብ አገሮች በብዙ ምዕተ ዓመታት የአገር ግንባታ ሒደት (State Building Process) የሕዝባቸውን መሠረታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች አሟልተናል ስለሚሉ፣ በሌላ በኩል ዴሞክራሲ በማረጋገጥ የአገርና የባንዲራ ፍቅር እንደ መንግሥት ያላቸው እምነት ጥሩ ነው ብለው ስለሚያስቡ፣ ከውስጥ የሚነሳ አደገኛ የሕዝብ ተቃውሞ አይኖርም ብለው ስለሚያምኑና ከግሎባላይዜሽን የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆንና ተፅዕኖቻቸውን ለማሳደግ ዋናው የደኅንነት ሥጋት ከውጫዊ አድርገው ያስቀምጡታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለይ በሦስተኛ ዓለም አገሮች ይህ የተለምዶ አስተሳሰብ እንደገና ከሁኔታቸው ጋር አዛምደው ማየት የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሽግግር ላይ ያሉና የተከፋፈለ ኅብረተሰብ (Divided Society) ያላቸው አገሮች ዋናው የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ውስጣዊና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መዋቅር (Structure) የፈጠረውና በኅብረተሰቡ ኋላቀር አስተሳሰብ የሚታጀብ በተለይ ብቃት ባለው የዴሞክራቲክ አስተዳደር እጥረት የሚነሳ ነው፡፡ ስለዚህ በዋናነት ውስጣዊ ነው፡፡

የውጭ ጠላቶች ይህን ተንተርሰው የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን መሞከራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከውጭ የሚገኘውን በጎ ዕድል (Opportunity) ለመጠቀምና ሥጋት (Threat) ለመከላከል ከፍተኛ ሥራ መሥራት ቢኖርብንም፣ ዋናው ዕድልና ለደኅንነት የሥጋት ምንጭ ግን የውስጣችን ሁኔታ ነው፡፡ እኛ ስንደክም ነው የውጭ ጠላቶችም ለማጥቃት የሚቃጡት፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የመጀመርያው ክፍል በዋናነት የሕዝቦቻችን ስስት ትውልድ ሰብዓዊ መብቶች ዕውቅና ሰጥቶ በግልጽና በተሟላ አኳኋን ያስቀምጣል፡፡ ሁለተኛው ክፍል እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ አገር (State) እና መንግሥት  (Government) እንዴት መደራጀት እንዳለበትና ተዛማጅ ፖሊሲዎችና ሕጎችን ያስቀምጣል፡፡ በሌላ አገላለጽ አገር/መንግሥት በዚያ መልክ እንደ ደረጃ የተደረገው የሕዝቦቻችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ መብቶች ለማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚያ የዘለለም ከዚያም ያነሰም ዓላማ የለውም፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎቶች የአገራችን ጥቅሞችና ያሉንን ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን አጣምሮ ሰላምና ልማት፣ ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ ከውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኙትን ዕድሎች/ፀጋዎች በሚገባ አጢኖ፣ የሕዝቦችን ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ ለማደፍረስ ከውስጥ ሆነ ከውጭ የሚገኘውን ሥጋቶች አንጥሮና ቀምሮ የአገራችን፣ የአካባቢያችንና ዓለም አቀፋዊ አካባቢውን በጥናት አረጋግጦ እንዴት ሥጋቶችን መቀነስ እንደሚችልና መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂዎችን ያቀፈ በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ ለሁሉም የአገራችን እንቅስቃሴዎች አቅጣጫ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ነው የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ የፖሊሲዎች ሁሉ ቁንጮ የሚያስብለው፡፡ ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችም አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ፖሊሲ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ በጥቂት ጄኔራሎች፣ የደኅንነት ባለሙያዎች (Experts) እና በሥልጣን ላይ ባሉ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የመላው ኅብረተሰብና የኅብረተሰብ የተለያዩ አመለካከት የሚያንፀባርቁና የሚገልጹ ፓርቲዎች፣ ሲቪልና ፕሮፌሽናል ማኅበራት ጉዳይ የሚሆነው፡፡ በብሔራዊ የደኅንነት ፖሊሲ መግባባት ማለት የአገራችንን ዕድሎችና ሥጋቶች መሠረት አድርጎ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የወታደራዊና የደኅንነት ክፍል እንዴት መመራትና መደራጀት እንዳለበት በአጠቃላይ መስማማት ማለት ነው፡፡ ፖለቲካዊ የኛው የሁላችን፣ ኢኮኖሚያዊ የኛው የሁላችን፣ ወታደራዊና ደኅንነት ክፍሎች የኛው የሁላችን ናቸው ብለን በአጠቃላይ ተስማምተናል ማለት ነው፡፡ የሚያለያዩን ጉዳዮች መኖራቸው አይቀርም፡፡ የሚታዩት ግን በዚህ ማዕቀፍና የተመቻቸ ሁኔታ ስላለ በሰላምና በሰላም ብቻ ለመታገል የምንችልበት የጋራ አስተሳሰብ አለ ማለት ነው፡፡ ከፅንፈኞች በስተቀር፡፡

የ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ የአመለካከት አቅጣጫ ለውጥ

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ አገር በቀልና ከደኅንነት አኳያ ያሉት በቂ ዕድሎች/ፀጋዎችና ሥጋቶች ዋናዎቹ ውስጣዊ መሆናቸውንና ድህነትና ኢዴሞክራሲያዊነት የአገሪቱ ህልውና ከሚፈታተኑን ሥጋቶች ዋናዎቹ መሆናቸውን በማያሻማ መንገድ ያስቀምጣል፡፡ የአገርና የሕዝብ ፍላጎትን አስተሳስሮ የአገር የመበታተን አደጋ የሚያጋጥመው በዋናነት በውስጣችን ባሉት ችግሮች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ደኅንነት ጥቂቶች ባለሥልጣናት/ጄኔራሎች የደኅንነት ባለሙያዎች ብቻ አለመሆኑናቸውን የመላው ሕዝቦች አጀንዳ ሆኖ እንደ ፖሊሲ ያላስፈላጊ ሚስጥርነት ድባብ ያገለለ (በሚስጥር የሚጠበቁ እንዳሉ ሁሉ) መለያው ነው፡፡ የደኅንነት የድብብቆሽ ሥራን ድባቅ የመታ ለውጥ ነው ያሳየው።

የደኅንነት ጽንሰና ንድፈ ሐሳባዊ ማዕቀፎችን በዓለም ዕውቅ ከሆኑ አስተምህሮዎችን (Schools of Thoughts) ቀደም ብሎ በዘውዳዊ ሥርዓትና በወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት ከነበሩት ፖሊሲዎች አንፃር ሲታይ፣ መሠረታዊ የአቅጣጫ ለውጥን (Paradigm Shift) የሚያመላክት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎትና ተስፋ ከፈጣን የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጠቃሚ መሆን ማለትም ከደኅንነት፣ ከኋላቀርነት፣ ከመሃይምነትና ከበሽታ የፀዳ ሕይወት መኖር ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላትን ኢትዮጵያ በመፍጠር የቡድንና የግለሰቦችን መብት ማስከበር፣ መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥና ለኑሮና ለሥራ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው ብሎ ያስቀምጠዋል፡፡ የብሔራዊ ጥቅም (National Interest) በማያሻማና በተሟላ መንገድ እንዲህ ያቀርበዋል፡፡ “ብሔራዊ ጥቅም ማለት የሁሉም ሕዝብ ጥቅም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ያነሰም የበለጠም ማለት አይደለም” (16) ትንተናው ልዑላዊነትና የድንበር አንድነት (Sovereignty and Territorial Integrity) ከሕዝቦች ፍላጎትና ጥቅም ጋር ብቻ አቀናብሮ ያየዋል፡፡ ከእነዚህ ጽንሰ ሐሳብ ውጫዊ አመለካከት ቋንቋዎች (External-looking Orientations) ይለያል፡፡ ፖሊሲው እየደጋገመ እንደሚያሰምረው ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትን፣ ዴሞክራሲና ሰላምን ማምጣት በከፍተኛ ድህነትና ኋላቀርነት ለምትገኝ አገር መሠረታዊ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

በአጠቃላይ የፖሊሲው ስትራቴጂዎች ከላይ የተጠቀሱትን ወሳኝ የደኅንነት አካባቢ መፍጠር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ብሔራዊ ኩራትን (ነፃነታችን ጠብቀን መኖራችንን) እንደ አንድ እሴት፣ ድህነታችን (Poverty) እንደ አሳፋሪ ታሪክ አስቀምጦ፣ የተለዋዋጩ ምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ እንደ መልካም ዕድልና ሥጋት፣ ሉላዊነት (Globalization) ለልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን ተፅዕኖ እንደ መልካም ዕድልና የሥጋት ምንጭ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅን በተመለከተ ፖሊሲው እንዲህ ይላል፡፡ “መካከለኛው ምሥራቅ በእኛ ሰላምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእኛ ኢኮኖሚ ላይ በእጅጉ ተፅዕኖ ያደርጋል፣ ለዚህ ነው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ በእኛ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡” (ኢውጉብደፓ፡ 46)

የመከላከያ መዋቅርን (Military Establishment) በተመለከተ ስትራቴጂዎችን ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ (Comprehensive and Coherent) ሆኖ የአገሪቱን የልማት እንቅስቃሴ መሠረት አድርጎ የሚገነባና በጥልቅ የአደጋ ትንተና ላይ የተመሠረተ አቅም ግንባታ ላይ ሲሆን፣ ብቃት ያለውና ዘመኑ የደረሰበት የመረጃ መረብ ዕድገትን በማቋቋምና የሰው ልማት ላይ በማተኮር የሚታነፅ መሆን አለበት ይላል፡፡ ይህ ማለት በሁለት ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው ኃይሎች መካከል ጦርነት ቢነሳ ወሳኝ ልዩነት የሚፈጥረው ሰው ነው፡፡ (ኢውጉብደፓ፡ 43) በሚል ነው፡፡ የአፍሪካን ትልቁ ሠራዊት ከመገንባት የደርግ እብደትና ድንፋታ ተወጥቶ ከአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተዛምዶ በልክ (Right Size) ሠራዊት ለመገንባት የሚቀነቅነው ሐሳብም ሌላው የአቅጣጫ ለውጥ ነው፡፡ ፖሊሲው የፋይናንስ ሀብትን በጥንቃቄ መጠቀምን በኢኮኖሚያዊና በመከላከያ ወጪ መካከል ቁርኝትን፣ የሠራዊቱና የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች አቅም ግንባታ ከኢኮኖሚ ልማት አንፃርና ከአደጋዎች ጋር ያለውን ትስስር በሚገባ ያስቀምጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጠመንጃ ወይም ቅቤ (Gun or Butter) ያለውን ግጭት ለመፍታት የታሰበለት አማራጭ ያስቀመጠ ይመስላል፡፡

ፖሊሲው ስለጠንካራ የማስፈጸም አቅም ግንባታ በሚመለከት “በትክክል የተቀረፀ የውጭ የአገር ውስጥ ፖሊሲዎች ዓላማዎች፣ ግቦች ፕሮግራሞች ስትራቴጂዎች በአግባቡ ተግባር ላይ ካልዋሉ የትም ሊያደርሱ አይችሉም፣ ለዚህም ነው ውጤታማ የማስፈጸም ብቃት እንደ መሠረታዊ ስትራቴጂ የሚታየው፤” (ኢውጉብዴፓ፡ 49):: ይህ አንድ ቁልፍ ነገር ነው። ፖሊሲው ከዘውዳዊውናና ከወታደራዊው አገዛዝ በተለየ ከበባ አስተሳሰብ (Siege Mentality) ወጥቶ “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” የሁሉም ችግሮቻችን ምንጭ እንደሆነ በቀጣይነት ከማላዘን አልፎና በተቻለ መጠን የሥጋት ምንጮችን በመቀነስና ትብብርን የማስፋት አቅጣጫ ተከትለዋል፡፡ “የትኞቹ ጥቅሞቻችን አስፈላጊ እንደሆኑና የትኞቹ ኃይሎች ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ እንደሚፈልጉ በሚጠቅም አቅምና ኃይል ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ከግንዛቤ በመነጨ አደጋዎችን መጋፈጥና በትብብርና ገንቢ በሆነ መንገድ የሥጋት ምንጮችን ማስወገድ አስፈላጊ ነው፤” ይላል የፖሊሲ ሰነዱ በገጽ 33፡፡ በአጠቃላይ ፖሊሲዎቻችን ጥልቅ በሆነ ጥናትና ምርምር መቅረፅ እንዳለባቸው እያስቀመጠ እየተመላለሰ አጽንኦት የሚሰጠው ግን፣ “ለእኛ ዋነኛው የደኅንነት ሥጋት ምንጭ ውስጣዊ ነው፡፡ የድህነት መስፋፋት የአገሪቱ ህልውና አደጋ ሊሆን ይችላል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የዴሞክራሲ አለመኖር ወደ ደም መፋሰስና ጥፋት ሊከተን ይችላል፤” (91)፡፡ ሆኖም ፖሊሲው አጠቃላይ የአቅጣጫ ለውጥ የሚያመለክት ቢሆንም ቀጣይነት (Consistency) እና ሙሉዕነት (Comprehensiveness) ይጎድለዋል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና ኅብረ ብሔራዊነት እንደ መልካም ዕድል በሚገባ አያስቀምጥም፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እጅጉን መሠረታዊና ፋውንዴሽናል (Very Basic and Foundational) የግጭቶች መሠረታዊ የአፈታት አቅጣጫዎች በመተንተን ውስጣዊ ደኅንነት የሚረጋገጥበት ሁኔታን አመቻችተዋል፡፡ በተሟላ ሁኔታ መብቶችን በማወቅ ሕገ መንግሥቱ አንድነት ማራኪ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብን የመፍጠር ሒደትም አመቻችቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ማኅበራዊ ቡድኖች (Societal Groups) ተጨባጭ የሆነ ፍላጎታቸውን ለማጠናከርና ተጨባጭ ያልሆኑትን ሊሟሉ የማይችሉ ፍላጎቶች መሆኑን ለመገንዘብ የሚያስችል ሒደት አቀናጅቷል፡፡

ፖሊሲው ለደኅንነት አካባቢ (Security Environment) ሕገ መንግሥታዊ ዓውደ ጽሑፍ (Context) ከማስቀመጥ አኳያ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ ብዝኃነት በአጠቃላይ የኅብረ ብሔራዊነት እሴት በተለየ፣ በዋጋ የማይተመን ሀብት መሆኑንና ለአገር ግንባታ ሒደትና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማፋጠን ያሉትን አዎንታዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ሐሳቦች፣ መልካም ዝንባሌዎች የጋራ ልምዶች የግጭት መቆጣጠርና የአስተዳደር ዘዴዎች እንደ ዋነኛ አቅም አድርጎ አያስቀምጥም፡፡ ከዓለም አቀፍ የሚገኘውን የቴክኖሎጂና የቁስ ድጋፍ በከፍተኛ ድጋፍ ደረጃ ሲያደንቅና አስፈላጊነቱን ሲያስረግጥ፣ ብዝኃነትንና ኅብረ ብሔራዊነትን የመሳሰሉ ፀጋዎችን በመርሳት “የኢትዮጵያ ሕዝቦች” የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ጎን በመተው፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚለውን ሐሳብ ሲያራምድ ከላይ የተገለጸውን የአቅጣጫ ለውጥ ስንኩል ያደርገዋል፡፡ ይህ የቃላት ጨዋታ ሳይሆን የራሱ ጥልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ነገር ነው። የ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ መሠረታዊ የሆነ ከውስጥ የሚነሱ ፀረ ዴሞክራሲ ሥጋቶችን ችላ ያለ ነው፡፡ የአገራችን ደኅንነት ዋናው ውስጣዊ ነው ብሎ ለሚነሳ አስተሳሰብ የዴሞክራሲ ግንባታ በድህነት ማስወገጃ ትግል ሒደትን ሊያኮላሹ የሚችሉትን በውስጥ ተቋማት፣ ኃይሎችና ዝንባሌዎች ምንም ነገር ሳይል ማለፍ የሚያስገርም ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የውስጥ ተቋማት፣ ኃይሎችና ዝንባሌዎች በአዎንታዊ ይሁን በአሉታ ውስጥ መሆንን እንደታወቀ ያለመጥቀሱ አሁንም ያስተዛዝባል፡፡ በመንግሥት ይሁን በኅብረተሰቡ ሁልጊዜ በከፍተኛ ውጥረት (Tension) የሚኖሩት የፍፁም አንድነትና የመበተን ኃይሎች (Centripetal and Centrifugal Forces) መሳሳብ ቀጣይነት ያለው የደኅንነት ሥጋት መሆናቸውን የተገነዘበ አይመስልም፡፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓት መሠረታዊ የደኅንነታችን ዋስትናና መሠረት ቢሆንም፣ እንደ ማናቸውም ሥርዓት የራሱ ተግዳሮቶች ያሉት አደረጃጀት ነው፡፡ ማይክል በርጊስ የተባለ ምሁር የፌዴራል መዋቅርን አስቸጋሪነት በጽሑፍ “In Seymour and Gugnoned” (2012፡24)  እንዲህ ሲል ያብራራል፡፡ “የፌዴራል አገር ግንባታ በተፃራሪዎች ችግሮችና አደጋዎች የተሞላ በመሆኑ ከመጀመርያው በጭንቀትና በውጥረት የተሞላ ሊሆን ይችላል፡፡ “በመቀጠልም ትራዱን (1968፡12) በመጥቀስ “እንደ የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን ሐሳብ ፌዴራሊዝም እንዲኖር ቢያስገድድም እዚያ ሳለ የፌዴራል ሥርዓቱን ያልተረጋጋ ያደርጋል፤” ይላል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ መሠረታዊ ጥቅሞቻቸው የሚረጋገጥ ቢሆንም፣ ተጨባጭ ሁኔታው ግን የተለያየ ትርጉምና አመለካከት (Perceptions) እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከፈጣን የኢኮኖሚ ልማት የሚያገኙት ድርሻ በተግባርም ይሁን በአስተሳሰብ የተለያዩ ባህሎችና የሕዝብ ብዛት ላላቸው አካሎች የተለያዩ ትርጉም ያለው ነው ወይም ሊኖረው ይችላል፡፡ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች በሕገ መንግሥታዊ ዲዛይን፣ በምርጫ ሥርዓቱና በመንግሥት ተቋማት አወቃቀር፣ በተለይም በሥራ አስፈጻሚና በደኅንነት ኃይሎች ብሔራዊ ተዋጽኦ (National Composition of the Executive, Military and Security Forces) ላይ ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የታላላቅ ብሔሮች ልሂቃን (Elites) ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ያልተሟሉ ፍላጎቶች ሊኖራቸው ሲችል፣ ትንንሽ ብሔሮች መሬታቸውን፣ ሀብታቸውንና ማንነታቸውን የማጣት ሥጋት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡

እነዚህ ክስተቶች ቀጣይነት ባለው ሰፊ ጥናትና ምርምር መሠረት አድርጎ በሕዝቦች መካከል ቀጣይነት ያለው ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማድረግ መስተካከል ያሉበትን በወቅቱ መሟላት፣ የማይቻለውን በማስረዳት የሕዝቦች አንድነት ብሎም የአገሪቱ ደኅንነት ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ትምክህትና ጠባብነት ከሚባሉ አጫፋሪ ሐሳቦች በየጊዜው መውደቅ ያባብሰው እንደሆነ እንጂ የሚፈይደው የለም፡፡ አሁንም መፍትሔው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በማጠንከርና የሕዝቦችን ሁለንተናዊ መብቶች በማስከበር ሁለንተናዊ ጥቅሞቻቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ እነዚህ ተግዳሮቶችን በዝምታ ለምን እንዳለፍናቸው ለመረዳት ያስቸግራል፡፡

ከደኅንነት አንፃር ወደብ የለሽዋ ኢትዮጵያ ሊያጋጥሟት የሚችሉ የደኅንነት ተፅዕኖዎችን የ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ በዝምታ ነው ያለፈው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን፣ አስተማማኝ፣ ብቃት ያለውና ወጪ ቆጣቢ ዓለም አቀፍ ግብይትን ይጠይቃል፡፡ የባህር በር ዕጦት የኢኮኖሚ ብሎም የደኅንነት ማነቆ ሊሆን ይችላል፡፡ ግጭት በማይጠፋበትና ራሳቸውን ለመቻል በትግል ላይ ያሉ መንግሥታት ባሉበት የአፍሪካ ቀንድንና ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር ላይና ታች የሚሉት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቀጣይ እንቅስቃሴ ባለበት ሁኔታ፣ የባህር በር ዕጦት የሚፈጥረውን ሥጋት ቸል ማለት አይገባም፡፡  

አጥንትና ሥጋ እንጂ ደም የሌለው ፖሊሲ

ፖሊሲው አገር በቀል የመሆኑን ያህል አዲስ የአቅጣጫ ለውጥ በማምጣት በደኅንነት ዙሪያ መሠረታዊ የአመለካከት አረጋግጧል፡፡ ሆኖም የአቅጣጫ ለውጡ ቀጣይነት ባለው መልኩ የተተነተነ ባለመሆኑ ከላይ የተገለጹትን መሠረታዊ ድክመቶችም ያዘለ ነው፡፡ ፖሊሲው በሰፊ ጥናትና ምርምር እንዲታጀብ በቂ አቅም በመፍጠር አስፈላጊነትና አገራዊ መግባባት እንዲኖር ቢያውጅም ይህን ለማስፈጸም የሚችለው የተሟላ የደኅንነት አስተዳደር (Security Governance) በሚመለከት ዝምታን መርጧል፡፡ አንድ ፖሊሲ የተሟላ ቢሆንም ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር በጥበብ አዛምዶ ለመተግበርና ለማበልፀግ፣ ጉድለቶች ካሉትም ለማረም የግድ ጠንካራ አስተዳደር ያስፈልገዋል፡፡ ቀጣይነት ያለውና የተሟላ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚከሰቱትን ዕድሎችና ሥጋቶች ቀጣይነትና ሰፊ በሆነ ጥናትና ምርምር ለማጎልበት የተደራጀ የደኅንነት አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ሲባል አጥንትና ሥጋ የምንለው የደኅንነት አካባቢ (Security Environment) እና Hardware ጨምሮ አጠቃላይ የደኅንነት ቅርፅ (Security Posture) ሲሆን፣ “ደም” ደግሞ የፖሊሲው ስስ ‹Software› ነው፡፡ የደኅንነት ቅርፅ ያለ “ስስ” ደም የሌለው አጥንትና ሥጋ ይሆናልና፡፡ እንደ ታዋቂዎቹ የደኅንነት ምሁራን አዘርና ሙን (Azar and Moon 1988) ገለጻ፣ “የደኅንነት አካባቢ ሥጋቶችና ዕድሎችን ከቁሳዊ አቅሞች (ወታደራዊ ኢኮኖሚያዊ ኃይል) እና ተጨባጭ የፖሊሲ መሠረተ ልማት፣ ወታደራዊ ዶክትሪን የኃይል አወቃቀር (Force Structure)፣ መረጃ (Intelligence)፣ የመሣሪያ አመራረጥ፣ ወዘተ. የሚያካትተው የደኅንነት ቅርፅ (Security Posture) “ደም” (Software) ከመጨረሻው የፖሊሲ ውጤቶችና አጠቃላይ የፖሊሲ አፈጻጸም የሚያስተሳስር ነው፤” ይላል። በሌላ አገላለጽ የፖሊሲው ዶክመንት ወደ ተግባር/መሬት ለማውረድ የሚያስችል “ለአጥንቱና ሥጋ” ሕይወት የሚዘራ ደም ነው ሶፍትዌር የሚባለው፡፡

የደኅንነት አስተዳደሩ ፖሊሲው የተሟላና ዘላቂ ቅቡልነት (Legitimacy) እንዲያረጋግጥ፣ የሁሉም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኃይሎችና የደኅንነት ክፍሎች ቅንጅት/ውህደት (Integration) እንዲኖር የሚያረጋግጥና የፖሊሲው አቅም በቀጣይነት ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡ ፖሊሲው በትክክል ያነጠረው የአገሪቱ ህልውና ዋናው ሥጋቶች ድህነትና የዴሞክራሲ እጥረት መሆኑን አስቀምጧል፡፡ በሌላ አገላለጽ ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ባረጋገጥን ቁጥር የአገራችን ህልውና የሚያስተማምን መሠረት እየተጣለ ይሄዳል ማለት ነው፡፡

ቅቡልነት ለማረጋገጥ “የመጀመርያ ቅቡልነት” (Prema-facie Legitimacy) ማንፀባረቅን ይጠይቃል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብሔራዊ ተዋጽኦ፣ የአመራሮቹ ብቃት፣ የሕዝብ ባህል/ወግ የማክበርና አመርቂ ሕገ መንግሥትን ይጠይቃል፡፡ ቅቡልነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕገ መንግሥቱን የመተግበር ህያው ፖለቲካ ለመምራት የሚወጡት ፖሊሲዎችና ሕጎች ጥራትና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ ሥርዓቱ እኛን ይወክላል፣ ፍላጎታችን ቀስ በቀስ እያሟላ ይሄዳል፣ በአገራችን ጉዳይ እኩል እየተሳተፍን፣ ወዘተ. የሚል አመለካከት (Perception) ካለ “አጥንቱና ሥጋ” ነፍስ ለመዝራት ህያው ሆኖ እንዲተገብር የመጀመርያው ፈተና አልፏል ማለት ነው፡፡ ቅቡልነት የሚባል ደም፡፡

በእውነትም ይሁን በተሳሳተ መንገድ “የአንድ ብሔር የበላይነት አለ”፣ “የሚገባን ሥልጣን እያገኘን አይደለም”፣ “በበጀት አድልኦ አለ”፣ “ፍትሕ የለም” የሚባል ሰፊ አስተሳሰብ ካለ ሕይወት የሚዘራ ደም መሆኑ ቀርቶ “አጥንትንና ሥጋውን” የሚፈጅ እሳት ይሆናል፡፡ ሕግ ካልተስተካከለ አገሪቱ ባልፈነዳ እሳተ ጎመራ ላይ እንደተቀመጠች ሊቆጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ አቅም ያለው የደኅንነት አስተዳደር ካለ ቀጣይ በሆነ ጥናት እያካሄደ ቅቡልነት የሚያሰጡ እውነተኛ ምክንያቶችን ያለማወላወል በማስተካከል፣ በተሳሳተ አመለካከት (Perception) በግልጽ ከሕዝቦች ወኪሎች ጋር እየተወያዩ ረመጡን በጊዜው በማጥፋት ቅቡልነት እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ውህደት (Integration) የሚባለው “ደምም” በብዛትና በጥራት መገኘት ይኖርበታል፡፡ በአገራችን ሁኔታ ዴሞክራሲ ያለ ፈጣን ልማት፣ ልማት ያለ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መረጋገጥ አይችሉም፡፡ ልማቱን እናፋጥነው ዴሞክራሲው ቢቆይም ቀስ ብሎ ይደርሳል ማለት የዋህነት ነው፣ ወይም ደግሞ አውቆ አጥፊነት ነው፡፡ የፈጣን ልማት ጉዞና ዴሞክራሲያዊ ግንባታ መዋሀድ ይኖርበታል፡፡ ፖለቲካው ከኢኮኖሚ፣ የውጭ ሥጋት ከውስጥ፣ ሲቪል አስተዳደሩ ከወታደሩ፣ ፌዴራል መንግሥቱ ከክልል ካልተዋሀደና መነጣጠል ከመጣ፣ የተለያዩ ማኅበራዊ ኃይሎችን ወደ አንድ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ለመምጣት ካልተቻለ የአደጋ ምልክት ነው፡፡ የፖለቲካው መበታተን በአገር አደጋ እንዲያንዣብብ ያደርጋል፡፡ የውህደት ደሙ ካልደረቀ ወይም መሳሳት ካሳየ፣ ወይም ከቆሸሸ አጥንቱ ይጎብጣል ሥጋው ይበሰብሳል፡፡

የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ቅቡልነትና ውህደት እየተረጋገጠ ሲሄድ (ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ) የዴሞክራሲ ትውልድን ዕድገት ያፋጥናል፡፡ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን እንደሚሉት የ“ቁቤ ትውልድ” (Qubee Generation) የኦሮሞ ሕዝብ ትግልን ውጤት መሠረት አድርጎ አዲስ ታሪክ በመጻፍ፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን ዴሞክራቲክ ሥርዓትን ለመገንባት ወይም በትግራይ እንደሚባለው “ሳልሳይ ወያኔ” ትውልድ ማለት የሁለተኛው ወያኔ ድል መሠረት አድርጎ አመራሩን በመንጠቅ፣ ፖለቲካዊ መንሸራተቱን ከሌሎች ወጣቶች ሆነው ለመፍታት የሚሞክር በሌሎች ሕዝቦችም ተመሳሳይ ምሳሌዎች ሊጠቀሱ ይችላል፡፡ ተቀባይነትና ውህደት ለማረጋገጥና የግድ ፖሊሲውን የማስፈጸም አቅም (Policy Capacity) ይጠይቃል፡፡ አቅም ለመገንባት የጠራ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ተቀባይነትና ውህደት እያረጋገጠ የሚገነባ አቅም፡፡ የዴሞክራሲያዊ ትውልዱ፣ የቴክኖሎጂ ትውልድ፣ የአፍላ ጉልበት ትውልድ መሠረት አድርጎ መገንባት ይጠይቃል፡፡

ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ፖለቲካዊ ሳይንቲስቶች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የፀጥታ ባለሙያዎች. . . ወዘተ. ማእከል ያደረገ የአገራችን የውስጥ ዕድሎችንና ሥጋቶች ከአፍሪቃ ቀንድ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከግሎባላይዜሽን ጋር አስተሳስሮ ፖሊሲው ያስቀመጠውን አቅጣጫ በተሟላ መንገድ የሚረዳና የሚያጎለብት፣ አጥንቱና ሥጋው ከበቂ የደም ጥራት ጋር አዋህዶ የደኅንነት አቅሞችን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅሞ ሥጋቶችን በቀጣይነት በመቀነስ፣ በፈጣን ዕድገት ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩ እየሰፋ የተረጋጋች አገራችንን የሚገነባ አቅም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የተሟላ የደኅንነት ቅርፅ (Security Posture) እንዲኖር ተቀባይነት፣ ውህደትና የፖሊሲ አቅም እያዳበረ እንዲሄድ የሚያስችል አደረጃጀት ያስፈልገዋል፡፡ በተለምዶ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል (National Security Council) እየተባለ የሚጠራውና በሥሩ በጣም ጠንካራና የተሟላ የደኅንነት ሴክሬተሪያት (Secreteriat) እንዲኖር የግድ ነው፡፡

የ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ ስለ ካውንስሉና ሴክሪታሪያቱ ዝምታ መርጧል፡፡ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ደኅንነትን የሚመለከት ከፍተኛው የሥራ አስፈጻሚው አካል ሲሆን፣ በየጊዜው እየተሰባሰበ ወሳኝና ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍና ተግባራዊነቱ በሴክሬታሪያቱ በኩል የሚከታተል ነው፡፡ ሴክሪታሪያቱ በቁጥር ሆነ በብቃት ከሁሉም ዘርፍ የተውጣጡ በቂ ባለሙያዎችን ያካተተ ሆኖ በራሱ ዘርፈ ብዙ ጥናት የሚያካሄድ መሆን አለበት፡፡ የመከላከያና የውስጥ ደኅንነት ጥናቶች፣ መረጃዎችና የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርትና የዲፕሎማሲያዊና ፕሮፌሽናል ተቋማትን ተጠቅሞ የውስጥም ሆነ የውጭ ሥጋቶችንና ዕድሎችን መሠረት አድርጎ የተለያዩ ቢጋር/ቢሆኖች (Scenarious) በማደራጀት፣ ለውሳኔ ወደ ካውንስሉ የሚያቀርብና ተግባራዊነቱን የሚከታተል ነው፡፡  

የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ይሁን ሴክሪታሪያት ተቀባይነትን (ውህደትን) አቅሙን በሚያረጋግጥበት መንገድ መዋቀር ይኖርበታል፡፡ ብሔራዊ ተዋጽኦ አገሪቱን የሚያንፀባርቅ፣ በተለምዶ ደኅንነት (ወታደራዊ ደኅንነት) የሚባሉትን ብቻ ሳይሆን ዋናው ሥጋት ድህነትና የዴሞክራሲ እጥረት በመሆኑ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የዴሞክራቲክ ተቋማትን ጭምር በማሳተፍ ውህደት የሚያረጋግጥ፣ በከፍተኛ ደረጃ ሁሉን አቀፍ ባለሙያዎችን (በተለይ ሴክሪታሪያቱ) መሠረት ያደረገ አቅም ፈጣሪ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ካውንስልና ሴክሪታሪያት በማናቸውም አደረጃጀት ሊተካ አይችልም፡፡ የመከላከያ ተቋም ዋናው ተልዕኮ አገሪቱን ከውጭ ጥቃት መከላከል ነው፡፡ የውስጥ ደኅንነት ክፍሉ በውስጥ ፀረ ኢትዮጵያና ሽብርተኛነትን ተከታትሎ የሚያድን እንጂ፣ አጠቃላይ ከድህነትና የዴሞክራሲ እጥረት የሚነሱት ሥጋቶችን ለመከታተል የተደራጀ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ቀዳዳ ካልተሞላ እስካሁን የከፈልነው ሳይበቃ ከውስጥም ከውጭም ለከፍተኛ ጥፋት ልንዳረግ እንችላለን፡፡

በጠንካራ ሴክሪታሪያት እየታገዘ የሚንቀሳቀስ ካውንስል መኖሩ ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍተኛ ነው፡፡ የሲቪሎች አመራር (Civilian Administration) ወሳኝነት በመከላከያና የውስጥ ደኅንነት ክፍል የሚያረጋግጥበት መንገድ ጭምር ነው፡፡ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስሉ እንደተቋቋመ ይታወቃል፡፡ መሪነቱን እስከምን ድረስ እያረጋገጠ ነው? የሚለው በጥናት የሚታይ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ የሚመራ ቡድን በጣም ጥቂት አባላት ቢኖሩትም፣ የሴክሪታሪያት ሚና ለመጫወት ይችል ይሆን እንዴ? እያሉ የደኅንነት ባለሙያዎች ጥያቄዎች እያነሱ እያለ፣ በ2009 ዓ.ም. በተደረገው አዲስ የመንግሥት አደረጃጀት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማካሪዎች ቡድን ሲፈርስ የደኅንነት አማካሪ ቦታ በተለይ መልሶ ሳይደረግ ቀሩ፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ይሏል ይኼ ነው!

የጠራ የደኅንነት ፖሊሲ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ተቀባይነት፣ ውህደትና የፖሊሲ አቅም የተላበሰ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስልና ሴክሪታሪያት ባለመኖሩ በ1990 ብዙ ምልክቶች እያሉም የኤርትራ መንግሥት ስትራቴጂካዊ ድንገተኝነት አግኝቶ አገራችንን ወረረ፡፡ መጨረሻው በኢትዮጵያ አሸናፊነት (ከዚያ በላይ ድሉ ሊሰፋ ይችል ነበር ወይ? የሚለውን ለጊዜው ትተን በተለይ አሁን ካለው ‹ወይ ሰላም ወይ ጦርነት› ካለመኖር ጋር ተያይዞ) ቢረጋገጥም፣ የከፈልነው መስዕዋትነት በሰው ሕይወትም በንብረትም ከፍተኛ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ አገራችን ተያይዛ ከነበረው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ለጥቂት ዓመታት ቢሆንም ያደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው፡፡ ከኤርትራም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖረን በፖሊሲ ለውጥ በአዋጅ እናጠናዋለን እየተባለ ሳይሆን፣ የካውንስሉ ሴክሪታሪያት ዋናውና በቀጣይነት የሚሠራ ነው መሆን የነበረበት፡፡ የ1994 ዓ.ም. ፖሊሲ ማሻሻል ከተፈለገ ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም ሳይሆን፣ ከምንም ረቂቅ  አዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት ለውይይት ማቅረብ ይገባ ነበር፡፡ ያ ተቋም ወሳኝ ነው፡፡ የ2008 ዓ.ም. ግርግርና ጥፋት፣ እሱ ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድህነትና የዴሞክራሲ እጥረት አገራችንን ወደ መበታተን ሊያደርሱ የሚችሉ ወሳኝ ሥጋቶች ናቸው የሚለውን በተግባር ያሳየን ሁነት ነው፡፡ ኃይላችንን ሳንበታትን በእነሱ ላይ በመረባረብ የተረጋጋ ሰላም፣ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር እንገንባ፡፡ ይህን ለማድረግ በብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲና አመራሩ መግባባት ይፈጠር፡፡

በተለይ የዴሞክራሲያዊ ምኅዳር እየጠበበ መሄድ ከሁሉም በላይ የሚያሳስብ ነው፡፡ ምኅዳሩ የመጥበብ ጉዳይ የጥቂት ፓርቲዎች መሳተፍ አለመሳተፍ፣ የጥቂት ሰዎች የመጻፍና ያለመጻፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን እንዴት እናስፋው? ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥቱን ብቻ ማዕከል አድርገው እንዴት በተግባር ይዋሉ? የሥራ አስፈጻሚውን አምባገነንነት እንዴት እንቆጣጠር? ፓርቲ፣ መንግሥት (Government)፣ አገር (State) በተመለከተ የሚታየውን መዘባረቅ እንዴት እንቀንሰው? በአጠቃላይ ሕገ መንግሥታችን በፖለቲካው የበላይት የሚያገኝበት፣ ብሎም ግልጽነትና ተጠያቂነት የነገሠበት ምኅዳር ለማንገሥ መረባረብ ይኖርብናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት ከድህነትና ከዴሞክራሲያዊ እጥረት የሚመነጩ በፈጣን ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ብቻ የሚሸነፉ ናቸው፡፡

በተለይ ትምክህትና ጠባብነት የሚባሉ ጉዳዮች ዴሞክራሲን ማዕከል በማድረግ ካልታዩ አደገኞች ናቸው፡፡ የአመራሩ ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን የጎንዮሽ ግጭት (Horizontal Conflict) የማስፋትና የትችት ትኩረትን ወደ ውጭ የማዞር (Externalization) ሥልት ሊሆን ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡ ወደ ላይ አንጋጦ በአመራሩ ያለውን ችግር እንደ ዋነኛ አድርጎ እንዳይረባረብ እርስ በርሱ እንዲገማገም ለማድረግ የታሰበ እንዳይሆን፡፡ እስኪ ይግረማችሁ አስተማሪ በሙያው ሳይሆን እርስ በርሱ በትምክህትና በጠባብነት ሲገመገም፣ ድስት ስታቁላላ ወጥ ያረረባት ሠራተኛ የማረሩ ምንጭ በትምክህትና በጠባብነት ምክንያቱ እየተፈለገ ነው፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ሆነ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ወይም በጠባብነትና በትምክህት በላይኛው አመራር ላይ ስለተወሰደ ዕርምጃ የምናውቀው የለም፡፡ የተሰጠን መልስ ማስረጃ የለም ነው፡፡ ፖለቲካዊ ሙስና ባለበት ሁኔታ የገንዘብ/ኢኮኖሚ ሙስና እንዴት ማስረጃ ሊገኝበት ይችላል?

በተለይ ጠባብነትና ትምክህት የሚባሉት የአጫፋሪ ቃላት አባዜ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እየታየ ያለውን የብርሃን ጭላንጭል እንዳይገድለው መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ብቃት ያለው ካቢኔ ለመመሥረት “የኢኮኖሚክ አብዮት” መጀመርና በራሱ ተማምኖ መወሰን (Assertiveness) የጠንካራ ክልላዊ መንግሥት ምልክት እያየን ነው፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በቅርቡ ባላሀብቶችን ሰብስበው ሲያናግሩ፣ “የምንወስንባቸውና ልንወስንባቸው የማንችልባቸው ሥልጣኖች አሉን፣ የተገደበ ሥልጣን ነው ያለን፣ እኔ በግልባጭ አልወስንም፤” ብለው የፀና ፌዴራሊስት አቋማቸውን ገልጸዋል። ይበል የሚያስብል ነው። ጠንካራ የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥት መኖር ለጠንካራ ኢትዮጵያ መሠረት ስለሆነ በጉድለቶቹ ላይ ተንተርሰን ደካማ ጎን እየፈለግን አናራግበው፡፡

ምክር ቤቶቻችን በትምክህትና በጠባብነት ምክንያት አልተሽመደመዱም፣ ፍትሕ የታጣው በትምክህትና በጠባብነት ምክንያት አይደለም፡፡ በ2008 ዓ.ም. የነበረው ተቃውሞ በዋናነት ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ነው (ጠባብነትና ትምክህት ቢያጅበውም)፡፡ ወጣት ፖለቲካል ሳይንቲስቱ ናሁሰናይ በላይ አስገራሚ ሐሳብ አለው፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ “በዲሞክራሲ ዕጦትና በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳስብና ተግባር መካከል ያለው መስተጋብር ልክ እንደ ዝንብና ቆሻሻ አድርገህ ማየት ይቻላል፤›› ይላል፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ቆሻሻ (የዴሞክራሲ እጥረቱ) በሌለበት አካባቢ አንድ ሁለት ዝንቦች (የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብና ተግባር) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድምፅ ካልሰማህ መኖራቸውን አታውቅም፡፡ ከዝንብ ነፃ የሆነ አካባቢ ያለህ ይመስልሃል፡፡ ከፍተኛ ቆሻሻ በሚከማችበት ግን የዝንብ መዓት አያስቀምጥህም፤›› በማለት የሁለቱን ምክንያታዊ ጥምረት ያብራራል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ረገድ ችግር በሚኖርበት ጊዜ እነዚህ ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡ ልሂቃን ያለምንም ከልካይ ወይም ሃይ ባይ ወለል ያለ ሜዳ ስለሚያገኙ እንደፈለጉ ይጋልቡበታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁኔታዎች ሁሉ አደገኛ ይሆናሉ፡፡ መፍትሔውም ዝንቦች (የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት) ከማስወገድ በላይ፣ ቆሻሻውን ማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ማለት ነው፡፡ ፀረ ዴሞክራቲክ አስተዳደር የሚባል ቆሻሻ፡፡

ማጠቃለያ

አገራችን የገጠማት ችግር ተራ ፖለቲካዊ ቀውስ ሳይሆን፣ እንደ አገር ቆሞ የመቀጠልን ሥጋት የጋረጠ ከፍተኛ የደኅንነት አደጋ መሆኑን ዓይተናል። ለዚህም ሲባል አገራዊ ችግራችን በአገራዊ መግባባት መፍታት ካለብን፣ መወያያትና መነጋገር ያለብን ከሕገ መንግሥቱ በታች የፖሊሲዎች ቁንጮ በሆነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ (ኢውጉብደፓ) ዙርያ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ጥልቅ ተሃድሶ ሲል የፓርቲ ተሃድሶ ነው? ወይስ የመንግሥታዊ መዋቅር ተሃድሶ? የሚባለውን በቅጡ ለይቶ መንቀሳቀስ አለበት። የደኅንነታችን ዋና የሥጋትም የኩራትም ምንጭ ውስጣዊ የዴሞክራሲና የልማት ሁኔታ መሆኑ በመገንዘብ፣ የችግሩን ሥረ መሠረት ትቶ አጫፋሪ በሆኑ ትምክህት፣ ጥበት፣ አክራሪነት በሚባሉ ቅርንጫፎች ላይ ተንጠላጥሎ የሚመጣ ለውጥ ሊኖር እንደማይችል መረዳት አለበት። እያጠናሁት ነው የሚለው የፖሊሲ ክለሳም ሆነ ጥልቅ ተሃድሶ የአገሪቱን መሠረታዊ ችግር የሆነውን የድህንነት ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ አካሄድ መከተል አለበት። ይዘቱ ብቻ ሳይሆን ሒደቱም ለአገራዊ መግባባት ወሳኝ ነው፡፡ የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ያሉንን አቅሞች አሟጦ፣ ድህነትና የዴሞክራሲ እጥረት እንደ ዋነኛ የውስጥ ሥጋት አድርጎ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት የአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እናረጋገጥ? የሚለው አጥንትና ሥጋ ከደም ጋር አዋህዶ የሚያስተማምን ፖሊሲ መቅረፅ የግድ ነው፡፡ ፖሊሲው በኢሕአዴግና በኢሕአዴግ ዙሪያ ባሉት ሰዎች ብቻ ተረቆና ውይይት ተደርጎበት መፅደቅ የለበትም፡፡ የፖለቲካዊ ፓርቲዎች፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራት፣ የክልል ምክር ቤቶች፣ ወዘተ. ተሳትፎና የተለያዩ አስተያየቶች ተጨምሮበት መሆን ይገባዋል፡፡ ባይሳካም ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ ከጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ የሰማሁትን ላካፍላችሁ፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ለማርቀቅ አንድ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ተሰጠው፡፡ በመጀመርያ ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡ ከፖለቲካዊ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ተደረገበት፡፡ ከዚያም ወደ አሥሩ ክልሎች ኮሚቴው ተሰማርቶ፣ የየክልል ሕገ አውጭንና ሕግ አስፈጻሚውና ሲቪል ማኅበረሰቡ የመጀመርያው ረቂቅ ቀርቦለት ለየብቻ ሰፋፊ ውይይት ተደረገበት፡፡ ብዙ ግብዓት ተገኘበት፡፡ ኮሚቴውም ግብረ መልሶችን እንደ ግብዓት በሚገባ አሰባሰበ እንደገና መሥራት ጀመረ፡፡ ይዘቱም ዳበረ፡፡ በመሀል ግርግሩ ተፈጠረ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የኅብረተሰብ ወኪሎች በስፋት መሳተፋቸው የፈጠረው የእኔነት ስሜት በብሰባው ይታይ ነበር፡፡ ውጤቱን ለማየት አልታደሉም፡፡

ኢውጉብደፓ ከውጭ ወደ ውስጥ ይመለከት የነበረው የደኅንነት አስተሳሰብ በግልጽ አሳይቶታል፡፡ አልቀጠለበትም እንጂ፡፡ አሁንም ስላልረፈደ አሳታፊ በሆነ መንገድ ሁሉም ኃይሎች የሚሳተፉበትና የእኔነት ስሜት በሚፈጥር መንገድ ዴሞክራሲና ፈጣን ልማት የዋስትናችን መሠረቶች መሆናቸው በተግባር መግባባት ግድ የሆነበት ሰዓት ላይ መድረሳችን ታውቆ፣ ዕርምጃችን በዚህ ቅኝት ቢሆን መልካም ነው እያልኩ ጽሑፌን በዚህ ልቋጨው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢሕአዴግ ነባር ታጋይና የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...