Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየከተሞች ፈጠራ

የከተሞች ፈጠራ

ቀን:

የኢትዮጵያ 231 ከተሞች ጎንደር ሰንብተዋል፡፡ ሰባተኛውን የከተሞች ፎረም ሚያዝያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም.  በይፋ የተከፈተው በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ሲሆን፣ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ዘልቋል፡፡ ፎረሙ በተጀመረበት ዕለት ከተሞቻቸውን ወክለው የተገኙ ግለሰቦች ጎንደርን ሞልተዋት ነበር፡፡ በተለይም በከተማዋ ስታዲየምና ፋሲል ግንብ ዙሪያ የየክልሉን ሰንደቅ ዓላማ በባህላዊ ልብስ አሰፍተው የለበሱን አስተውለናል፡፡ ዕለቱ እሑድ በመሆኑ ብዙ ሠርጎች ይከናወኑ ነበርና ሙሽሮች ከአጃቢዎቻው ጋር በአፄ ፋሲል ቅጥር ግቢ ተገኝተዋል፡፡ በግፊያው  ፎቶ ከተነሱ በኋላ በባጃጅና በቤት መኪና የከተማዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር ሠርጋቸውን አድምቀዋልም፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ይመስላል በፍርኃት የመሸበብ ነገር የነበረ ቢሆንም ፎረሙ በተከፈተበት ዕለት ይህ ስሜት ብዙም አልተስተዋለም፡፡ ከተማው ውስጥ በየጥቂት ሜትሮች ልዩነት የፀጥታ ኃይሎች ነበሩ፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውኑ ነበር፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ባዘጋጀው ፎረሙ ከተሞች ሥራዎቻቸውን ያስቃኙበት ባነር እንዲሁም የከተሞች መስፋፋት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡

ባዛሩ 231 ከተሞች ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቻቸውን በሚያሳዩ ድንኳኖች የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከተሞቹ የፈጠራ ውጤቶች፣ የዕደ ጥበብ ሥራዎችና የየክልላቸውን ተፈጥሯዊ ምርቶች አቅርበዋል፡፡ ከተሞቹ የየአካባቢያቸውን ባህል የሚያንፀባርቅ ምግብ፣ መጠጥ፣ አልባሳትና ጌጣ ጌጥ ለዕይታና ለሽያጭ አቅርበው ነበር፡፡ የየከተሞቻቸውን ታሪክ በፎቶግራፍና በሰነድ ከማሳየት ባሻገር የከተማ ፕላኖቻቸውን የሚያሳዩ የግንባታ ሞዴሎች ይዘውም በባዛሩ ተገኝተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስለ ከተሞቻቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ሁኔታ የሚገልጹ፣ የከተሞቹ ተወላጅ የሆኑ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና መሪዎችን በመጥቀስ አካባቢያቸውን የሚያስተዋውቁንም አስተውለናል፡፡ ከተሞቹ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ከተጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል እንደ ላሊበላ ያሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና አባ ጅፋርን የመሰሉ ሰዎችን የሚያሳዩ ግንባታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የበርካቶችን ቀልብ የሳቡት ግን ከየከተሞቹ የተውጣጡ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው፡፡ በየአካባቢያቸው ያለው ማኅበረሰብ የሚገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በመመርኮዝ የሰዎችን የዕለት ከዕለት ሕይወት የሚያቀሉ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል፡፡ በግብርና፣ በሽመና፣ በብረትና እንጨት ሥራ ለተሰማሩ ሰዎችና በሌሎች ዘርፎችም ለሚገኙ የፈጠራ ሥራዎቹ እንደተዘጋጁ፣ የሥራዎቹ ባለቤቶች ይገልጻሉ፡፡

በየከተማው ባሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚማሩ ሠልጣኞችና በግላቸውም የፈጠራ ሥራዎችን ያቀረቡ የነበሩ ሲሆን፣ ከፈጠራዎቹ መካከል ገበያ ላይ ውለው ማኅበረሰቡ እየተገለገለባቸው የሚገኙት በአዲስ መልክ የሚተዋወቁም ተካተዋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹ የማኅበረሰቡን ሕይወት ከማቅለል በተጨማሪ ጊዜ ቆጣቢና የብዙኃኑን የመግዛት አቅም ማማከልን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም አስተውለናል፡፡

የከሚሴ ከተማው አባቡ ወሌ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እንባ ጠባቂ የተባለ ሶፍትዌር ፈጥረዋል፡፡ ሶፍትዌሩ በወረቀት ያሉ ሰነዶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚቀመጡበት ሲሆን፣ የመረጃ አያያዝን ያዘምናል፡፡ ከፈጣሪዎቹ አንዱ አባቡ እንደሚለው፣ ሶፍትዌሩ የሰዎችን ሰነዶች ከመያዝ በተጨማሪ በአንድ መሥሪያ ቤት ያሉ ሠራተኞች ለተገልጋዮች ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ስለሚፈጥር ጊዜ ቆጣቢ ነው፡፡ ሶፍትዌሩ ከከሚሴ ባለፈ በሌሎች አካባቢዎች ጥቅም ላይ እንዲውል በማሰብ በባዛሩ ማካተታቸውንም ይገልጻል፡፡

የደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የገብስና ስንዴ መውቂያ ማሽን አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን፣ ከአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንፃር የአርሶ አደሮችን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ ነው፡፡ መሣሪያውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብና አርሶ አደሮች በማሽኑ እንዲገለገሉ በማድረግ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡ ፈጠራዎች በሚሠሩበት ወቅት ብቻ አስገራሚ ሆነውና ባለሙያዎቹም ተመስግነው የሚዘነጉ ሳይሆን በተግባር የማኅበረሰቡን ሕይወት ለመለወጥ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡

አብዛኞቹ የፈጠራ ሥራዎች በባዛሩ ከታዩ በኋላ ተደራሽነታቸው እንደሚሰፋ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በዘልማድ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ መሣሪያዎችን ከማዘመን ጎን ለጎን ከውጭ ይመጡ የነበሩ መገልገያዎችን በአገር ውስጥ መተካትንም ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ ማፍ የመኪና ባትሪ ይጠቀሳል፡፡ በሱሉልታ ከተማ የሚሠራው ባትሪው ከ36 አምፒር ጀምሮ ለቤት መኪና፣ ለገልባጭ፣ ለስካቫተር የሚሆኑ ባትሪዎችን ከ935 ብር ጀምሮ ይሸጣሉ፡፡ ከባለሙያዎቹ አንዱ ሚሊዮን አድነው እንደሚናገረው፣ ምርታቸው ከውጭ ከሚመጡ የመኪና ባትሪዎች ባነሰ ገንዘብ በሙሉ ዋስትና የሚቀርብ ነው፡፡ መሰል የአገር ውስጥ ፈጠራዎችን ኅብረተሰቡ በቶሎ ባይቀበልም ጥራታቸውን በማሳየት ገበያውን መጨመር እንደሚቻል ያምናል፡፡

የከተሞች ፎርም የፈጠራ ሥራዎች በስፋት የቀረበበት አንድ መድረክ ቢሆንም፣ በሌሎች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነክ ዐውደ ርዕዮችም በርካታ ፈጠራዎች ይስተዋላሉ፡፡ ፈጠራዎቹ ከመታየት ባለፈ ምን ያህል ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ናቸው? የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም ሥራ ይጠይቃል፡፡ ፈጠራዎቹ አገር በቀል ዕውቀትን ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ ሚና ቢኖራቸውም ግባቸው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መሆን እንደሚገባው አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

በበዛሩ በ3,500 ብር የሚሸጥ እህል የሚያበጥርና የሚነፋ ማሽን ተመልክተናል፡፡ በ45 ደቂቃ 30 ሊትር ወተት የሚንጥ ማሽን በ3,000 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡ ከተፈጥሯዊ ዕፅዋት የተሠራ ሰንደልና ቢንቢ መከላከያ፣ ዘመናዊ የሽመናና የማቅለሚያ ማሽንም ይጠቀሳሉ፡፡ የባቡር መንገድን ተመርኩዛ የተቆረቆረችው ድሬዳዋ በበዛሩ ያቀረበችው በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ በፀሐይ የሚሠራ ባቡር ነበር፡፡ ከፈጣሪዎቹ አንዱ የሆነ መኩሪያ መሓሪ እንደሚናገረው፣ የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ሠራተኞች ለሙከራ የሠሩት ባቡር ሲሆን፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከተገኘ ቴክኖሎጂውን አሳድጎ ብዙኃን የሚጠቀሙበት ማድረግ ይቻላል፡፡

አሥር እንጀራ ባንዴ የሚጋግር ማሽን፣ 11 ብሎኬት በአንዴ የሚያወጣ ማሽን፣ ዳቦና ቡና በአንድ ላይ እየተሠራበት ስልክ ቻርጅ የሚያደርግ መሣሪያ የቀረበው ከመቐለ ከተማ ነበር፡፡ ባጃጅ፣ የስፖርት መሥሪያ ማሽን፣ ትራክተር፣ ከወዳደቁ ዕቃዎች የተሠራ የአውሮፕላን ሞዴል፣ ተንቀሳቃሽ ማስታወቂያ ቦርድ፣ እህል በመስመር የሚዘራ ማሽን፣ የፀጉር ካስክና ቡና መፈልፈያ ከፈጠራ ሥራዎቹ ጥቂቱ ናቸው፡፡ የወዳደቁ ቁሳቁሶችን ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል የአካባቢ ደኅንነትን መጠበቅ ላይ ያተኮሩ ፈጠራዎችም ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ ከላስቲክ ተረፈ ምርት ቤንዚንና ጋዝ የሠሩን መጥቀስ ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...