Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልባህላዊ እሴቶችን ለቱሪስት መስህብነት

ባህላዊ እሴቶችን ለቱሪስት መስህብነት

ቀን:

በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ዕለት ተዕለት የሚከናውኑት እንደ ሠርግ፣ ለቅሶ፣ እርቅና በዓላትን የመሰሉ ባህላዊ ሁነቶች የኅብረተሰቡን ትስስር ከማጥበቃቸው በላይ የማንነቱ መገለጫም ናቸው፡፡ ባህላዊ እሴቶች አንድ ማኅበረሰብ ከሌላው በተለየ መነጽር የሚታይባቸው ዘመን ተሻጋሪ ሀብቶች መሆናቸውም እሙን ነው፡፡

የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ) አንድ ማኅበረሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ ጨብጦ የሚያቆያቸው እንደመሆናቸው የዛው ማኅበረሰብ ወይም የሌላ አባላት ለጥናትና ምርምር ሲመርጧችው ይስተዋላል፡፡ በግንባር ቀደምትነት ከመደበኛ ትምህርት ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጥናቶች መነሻ የሚሆኑት ባህላዊ እሴቶች፣ በተመራማሪዎች ስለመነሻቸው፣ የክንውኖቹ ቅደም ተከተልና ማኅበረሰባዊ ፋይዳቸውም ይፈተሻል፡፡ ጥናቶቹ አንድም ለመረጃ ምንጭነት ሲውሉ በሌላ በኩል ባህላዊ እሴቶቹ ጎብኚዎችን እንዲስቡ ግብዓት የማድረግ አማራጭም አለ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች ባህላዊ እሴቶችን አጉልተው በማሳየት ቱሪስቶችን ወደ አገሪቱ ሊስቡ የሚችሉ ጥናቶችን በማቅረብ ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ይናገራሉ፡፡ በአብዛኛው የሚሠሩ ጥናቶች ተመራማሪዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች መምህራን ተወያይተውባቸው ወደ ቤተ መጻሕፍት የሚላኩ ናቸው፡፡ ጥናቶቹ ከመጻሕፍት መደርደሪያ ሳይወርዱ ዓመታትን ያስቆጥራሉ፡፡ የጥናቶቹ መነሻ የሚሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ በተመራማሪዎቹና በቱሪዝሙ ዘርፍ ሙያተኞች መካከል ድልድይ አለመኖሩን የሚተቹ ባለሙያዎች በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የጥናት ውጤቶችን መነሻ ያደረገ አካሄድ መፈጠር እንዳለበት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

- Advertisement -

ይህንን መሠረታዊ ሐሳብ የተመረኮዘ የባህልና ቱሪዝም ዓመታዊ ጉባኤ በጎንደር ከተማ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በባህል እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ልዩ ጥናቶች የተስተናገዱባቸው በርካታ መርሐ ግብሮች ቢኖሩም፣ ሁለቱን በማጣመር ማለትም አንዱ ለሌላው መሠረት እንዲጥል በሚያስችል መንገድ የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ሌሎችም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጥምረት ያሰናዱት ጉባኤ ከመጋቢት 18 እስከ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. የተከናወነ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ መምህራን፣ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና ተማሪዎችም ታድመዋል፡፡

በጉባኤው ከተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ባህላዊ እሴቶችን ከቱሪዝም ጋር የማስተሳሰር ሒደት አንዱ ነው፡፡ የጎብኚዎችን ቁጥር ከመጨመርና ወደ አገሪቱ ከመጡ በኋላ የቆይታ ጊዜያቸውን ከማራዘም አንፃር የባህላዊ እሴቶች ጥናት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል፡፡ የሚሠሩ ጥናቶች ከቱሪዝም ጋር ተመጋጋቢ እንዲሆኑ መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎችም ተገልጿል፡፡

‹‹ዘ ኮመን ካልቸራል ቫይልዩስ ዛት ቢውልድ ዘ ኢሜጅ ኦፍ ዘ ካንትሪ ኤንድ ኮንትርቢውት ፎር ሶሳይቲ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ጥናት የሠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ የፎክሎር አጥኚ ፍሬሕይወት ባዩ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ትስስር የሚንፀባረቅባቸው ባህላዊ እሴቶች በአንድ አካባቢና በሌላው የሚያመሳስላቸውን ለይቶ በማውጣት የጋራ ሊባሉ የሚችሉ ባህላዊ እሴቶች መኖራቸውን የሚያመላክት ጥናት ነው አጥኚዎች እንደ መነሻ የወሰዷቸው እንደ ዕድር ያሉ ባህላዊ መረዳጃ እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት፣ ባህላዊ ሕክምናና ጋብቻ በየማኅበረሰቡ ሲከናወኑ የሚከተሏቸው ሥርዓቶች መካከል ያለው የጋራ አካሄድ በጥልቅ ሊፈተሽ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የፎክሎር ባለሙያዋ ፍሬሕይወት (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ለባህላዊ ሕክምና እና ለባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት፣ እንዲሁም ለሌሎችም እሴቶች ዕውቅና የመስጠት ሥራ በቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች እየተጫወቱ ስላለው አዎንታዊ ሚና ማኅበረሰቡ እንዲገነዘብ ከተደረገ በኋላ በተለያየ መንገድ ለቱሪስቶች ማስተዋወቅ ይቻላል ይላሉ፡፡ ‹‹በቅድሚያ ማኅብረሰቡ ስላለው እሴት ጠቀሜታ እንዲረዳና ለባህላዊ እሴቶቹ ዋጋ እንዲሰጥ ማነሳሳት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

አገር በቀል ዕውቀቶችን በማኅበረሰቡ ተገቢው ቦታ ተነፍጓቸው ሳለ ተጠንተው ለጎብኚዎች መስህብነት ይቅረቡ ለማለት እንደሚያዳግት ያስረዳሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ለባህላዊ እሴቶቹ የሚሰጠው ዋጋ ለህልውናቸው መሠረት ሲሆን፣ እሴቶች ድንበር ተሻግረው ጎብኚ እንዲስቡ ማድረግ የተመራማሪዎች ድርሻ መሆኑንም ያክላሉ፡፡ የተመራማሪዎች ድርሻ ጥናቶቹን መሥራት ብቻ ሳይሆን ለአስፈጻሚ አካላት ግኝታቸውን በማሳወቅ ለአንዳች ዕርምጃ ማነሳሳት መሆኑን አያይዘው የሚገልጹት አጥኚዋ፣ በዘርፉ ባለሙያዎች መካከል ያለው ክፍተት ተዳፍኖ በጋራ የሚሠሩበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

ሐሳባቸውን የምትጋራው የሐረር ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ተቋማት አደራጅና የባህል ጥናትና ምርምር ባለሙያ ወይዘሪት አሲያ ኢማን፣ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በላቀ ግዙፍነት ላላቸው ባህላዊ ቅርሶች (ታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅስ) ትኩረት እንደሚሰጥ ትናገራለች፡፡

እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው በሐረሪ ክልል ለጁጎል ግንብና በግንቡ ውስጥ ለሚገኙ ቅርሶች ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራም የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ርቀት አልተሄደም፡፡ ወይዘሪት አሲያ ‹‹በሐረሪ ብሔረሰብ ከማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው የአፎቻ ማኅበራዊ አደረጃጀትና ጠቀሜታው›› በሚል በሠራችው ጥናት፣ የአፎቻ ሥርዓት ማኅበረሰቡ በሐዘንም ይሁን በደስታ እርስ በርስ የሚደጋገፍበት ስለመሆኑ ትገልጻለች፡፡ የማኅበረሰቡ አባላት ከሥርዓቱ ውጪ ለመኖር ስለሚቸገሩ ሕግና ደንቦቹን አክብረው በትስስር ይኖራሉ፡፡ ሥርዓቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ሁሉም የማኅበረሰቡ አባላት የአፎቻ አባላት ሆነው ሁነቱን የሚያስቀጥሉበት መንገድም ተፈጥሯል፡፡

አጥኚዋ እንደምትለው፣ አፎቻና ሌሎችም ባህላዊ መስተጋብሮች ጥናት ተደርጎባቸው በስፋት አልተዋወቁም፡፡ አለመተዋወቃቸው ሥርዓቶቹ በወጣቱ ትውልድ የሚሰጣቸውን ቦታና ከአገር ውጪ ያላቸውን ዕውቅናም ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል ትላለች፡፡ ‹‹ለምሳሌ ስለ አፎቻ የተሠራው ኢንቬንተሪ [ምዝገባ] በሐረሪ ቋንቋ የተዘጋጀ ነው፡፡ በሌሎች ቋንቋዎችም ካልተዘጋጀ ተደራሽነቱን ይወስነዋል፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ ባህላዊ እሴቶቹ በስፋት ተጠንተው አለመቅረባቸው ለቱሪዝሙ ያላቸውን ሚና ከማነሳሳቱም በላይ ማኅበረሰቡ ሊያደርግላቸው የሚገባውን ጥበቃ እንዳይሰጣቸውም ማገዱን ታክላለች፡፡ ‹‹ባህላዊ እሴቶቹ ዘጋቢ ጽሑፍና ፊልም ቢዘጋጅና የሚዲያ ሽፋንም ቢያገኝ ከእሴቶቹ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል፡፡ ማኅበረሰቡን ባላማከለ ሁኔታ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ ብቻ የምንሠራው ዘላቂ ለውጥ አያመጣም፤›› በማለት ታስረዳለች፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት የማይዳሰሱ ባህላዊ ሀብቶች ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ደስታ ሎሬንሶ፣ ባህላዊ እሴቶቹ በትውፊታዊ ተውኔት ወይም ሌሎችም ኪነ ጥበባዊ መንገዶች ቢገለጹ ያላቸው ዕውቅና ይጨምራል፡፡ ተመራማሪው እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በጉራጌ ማኅበረሰብ ረዥም ዓመታት ቢያስቆጥርም ዕውቅና ሳያገኝ የቆየውን የቃቄ ውርዶት ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ ተጠንቶ በቴአትር ሲቀርብ የታሪኩ ባለቤት በሆነው ማኅበረሰብና በሌሎችም መታወቁና ተወዳጅነት ማትረፉን ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም ጥናትና ምርምሮች በተለያዩ ተቋሞች በተናጠል ከሚሠሩ በተዋቀረ መንገድ የሚቀርቡበት ሥርዓት አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

‹‹የጥናትና ምርምር ጉባኤ መኖሩ ጥናቶች ከመሥራት ባለፈ በተግባር የሚውልበት መንገድ ይፈጥራል፤›› ይላሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ችላ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ከማድረግ ጎን ለጎን ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ያክላሉ፡፡ አሁን ያለው ባህላዊ እሴቶችን ከቱሪዝሙ ጋር አጣምሮ ያለመሥራት ሒደት መለወጥ እንዳለበት አስረድተው፣ ‹‹እስካሁን ሀብታችንን አላወቅነውም፡፡ አላስተዋወቅነውም፡፡ አልሸጥነውም፡፡ ጥናትና ምርምሮች ይህንን ክፍተት ይሞላሉ፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት የሚስማሙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ  ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር)፣ ባህላዊ እሴቶች ለቱሪዝሙ ግብዓት ለማድረግ ጥናትና ምርምር አስፈላጊ በመሆኑ በጎንደር ከተማ የተካሄደው ጉባኤ መልካም ጅማሮ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን የሚያውቅበት ገጽታ ባህላዊ እሴቶችን ያማከለ እንዲሆን መሥራት እንደሚያሻም ይናገራሉ፡፡

‹‹አገሪቷ በታሪክ፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በባህላዊ እሴቶችና በብዙ ዘርፎች የበርካታ ሀብት ባለቤት በመሆኗ ሀብቶቹን ልናጠናና ልንመራመር፣ አስተዋውቀን የቱሪስት መዳረሻ ልናደርጋቸውም ይገባል፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ይናገራሉ፡፡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባላቸው ቅርሶች ረገድ ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) የመዘገባቸው ቅርሶችን ጨምሮ የበርካታ መስህቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በላቀ፣ ከአጎራባች አገሮች ቱሪዝም በተሻለ ደረጃ ይገኛል፡፡ ይህ ሊለወጥ የሚችለው ሀብቶቹ ተጠንተው ዕውቅና ሲሰጣቸውና የዓለም ሕዝብ እንዲጎበኛቸው ባማረ ሁኔታ ሲተዋወቁ መሆኑን ሚኒስትሯ ይጠቁማሉ፡፡

‹‹የአገሪቱ ቱባ ባህሎች ከቱሪዝም አንፃር በተገቢ መንገድ ጥቅም ላይ አልዋሉም፤›› የሚሉት የሚኒስቴሩ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ ተጠንተው ሲቀርቡ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ታሳቢ በማድረግ መሆን እንዳለበት፣ ባህላዊ እሴቶቹም በጉብኝት ፓኬጅ አካቶ ለቱሪስቶች ማስጎብኘትና ማስተዋወቅ አስፈላጊነቱን አስታውሰዋል፡፡

 

 

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...