Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

አዲስ አበቤን ማን ይታደግ?

ትኩስ ፅሁፎች

መዲናይቱ አዲስ አበባ በቁሳዊ ለውጥ ላይ ትገኛለች፤ ትፈርሳለች፣ ትገነባለች፡፡ አሮጌ ቤቶች ቅርስ የሆኑትም ጭምር እየተናዱ ነው (ቅርሶቹን የሚጠብቅ ቢኖር ምንኛ ባማረብን)፡፡ ፈርሰው ለልማት ከተዘጋጁ ክፍት ቦታዎች ላይ ያልፈረሱ ክፋዮች በየቦታው ከመታየት አላመለጡም፡፡ ግን ለመውደቅ፣ ለመደርመስ አንድ ሐሙስ የቀራቸው፣ ለተመላላሽ  እግረኞችም ሆነ ለተሽከርካሪዎች ሥጋት የፈጠሩ በካዛንቺስና በሃያ ሁለት ያዘመሙ ተክለ ፍራሾች ይታያሉ፡፡ ጠንከር ያለ ነፋስም ሆነ የላቀው አውሎ ነፋስ ከተነሳ፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ ሲታሰብ ይዘገንናል፡፡

ከድሮው የካዛንቺስ ግርማ ክትፎ ቤት አጠገብ፣ ከኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል ባሻገር ከፈረሱት ቤቶች የተረፉት የመደብሮች መግቢያ በር ቅስቶች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የከተማ አውቶቡስና አልፎ አልፎ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪን የሚጭኑበትና የሚያወርዱበት ፌርማታ ላይ የሚኮለኮሉት ሰዎች የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ይሆን? ድንገት አደጋ ቢያደርስ ማን ነው ኃላፊው? የመዲናይቱም ሆነ የክፍለ ከተማው፣ ብሎም የወረዳው የተለያዩ አካሎች ፖሊስን ጨምሮ ሳይመላለሱበት፣ ገጽታውን ሳይመለከቱ አይቀርም፡፡ ኃላፊነታቸውስ እስከምን ድረስ ነው?

ሃያ ሁለት ትራፊክ ጽሕፈት ቤት ደጃፍም ያለው ተረፈ  ፍራሽ (ቅሪተ ፍራሽ) ያለበትም  ገጽታ አሳሳቢ ነው፡፡ ሌሎች ሹማምንቶች ቀርተው ዐሥሬ የሚመላለሱት ትራፊኮችና አለቆቻቸው መንገደኞች እየታከኩ ሲያልፉ እያዩ ምነው ዝምታን መረጡ? የምሥራቅ ነፋስ ያየለና የጠነከረ እንደሆነ ተረፈ ፍራሹ መናዱ፣ ጉዳትም ማድረሱ አይቀርም፡፡ አዲስ አበባ ሆይ ቃፊር የለሽም ወይ? ‹‹በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ

አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ›› የሚለው ከመድረሱ በፊት አንድ በሉ!!

                                                                                                ***

      ምን አይቶ ነው?

መንገዴን ከልሎ – እንዳልሄድ ያገደኝ
አዝግሜ ስነሳ – ደሞ ያንገዳገደኝ
ዛሬ ምን አይቶ ነው – እንዲህ የወደደኝ?

ሲያጠፋ የነበረ – እየተከተለ – የእግሮቼን ዳና
እሾህ አሜኬላ – ያበጅ የነበረ – በሰፊው ጎዳና
ዛሬ ምን አይቶ ነው – ገፋፊ የሆነ – የፊቴን ደመና?

አይችልም እያለ – መቻሌን ሲደልዝ
አያውቅም እያለ – ዕውቀቴን ሲበርዝ
ላገኘው በሙሉ – ስሜን ያጠለሸው
ዛሬ ምን አይቶ ነው – እኔን ያሞካሸው?

የክስ ወረቁቱን – በአርባ ገፅ አስፅፎ
ይሁዳው አድርጎ – በደሌን አግዝፎ
በየአደበባዩ – እንዳላሳቀለኝ
ዛሬ ምን አይቶ ነው – ልሙትልህ ያለኝ?

እስከማውቀው ድረስ – እስከማስታውሰው
ወጪ ወራጁ ሁሉ – የሚንከላወሰው
ለዓይኑ የማልሞላ – ነበርኩ የተናቅሁኝ
ምን አይተው ነው ዛሬ – በሰው ተከበብሁኝ?

ትናንትም ያው ነበርኩ – ያው እንዳለሁ አለሁ
ሲመጡም ሲሄዱም – በአርምሞ አያለሁ፤
ሂዱ ሳልል ሄደው – ኑ ሳልል ቢመጡ – ሰው መሆን ደነቀኝ
ምን አይተው ነው የሚል – ጥያቄ አስጠየቀኝ፡፡
እውነት ምን አይተው ነው???

  • ከደመቀ ከበደ ገጽ የተገኘ
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች