የቶኪዮ ኦሊምፒክ ሊካሄድ ሦስት ዓመታት ቀርቶታል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ፈርጀ ብዙ ሥራ ለመሥራት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በውጤት የታገዘ ተሳትፎ ለማድረግ ይችሉ ዘንድም የሚገባውን በጀት መድበው ለነገ ሳይሉ መሥራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በአይቮሪኮስት አቢጃን የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ያደረጉት የሁለት ቀን የውይይት መድረክ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡
የሚያዝያ 12 እና 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሎ፣ አፍሪካ በ2020 በሚካሄደው ኦሊምፒክ ሊኖራት በሚገባው ሚና ላይ ተነጋግሯል፡፡ በስብሰባው እንደተመለከተው ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የአትሌቲክሱ ቁንጮዎች የቤት ሥራቸውን በሚፈለገው መጠን ካልሠሩት ውስጥ እንደሚመደቡ ለማየት ተችሏል፡፡ ይኼውም በአትሌቲክሱ የሜዳ ተግባራት ተብለው በሚታወቁት ልዩ ልዩ ኩነቶች እንደ ኢትዮጵያ ያሉት በዓለም መድረክ የሚወደሱት በረዥም ሩጫው ለዚያውም በተወሰኑ የውድድር ርቀቶች ብቻ ከሆነ መሰነባበቱ የተወሳበት መድረክ መሆኑ ጭምር ተነግሯል፡፡
ይህ ሁኔታ ያሳሰበው አኖካ የአፍሪካ አገሮች የውጤትና የተሳትፎ አድማሳቸውን በማስፋት በርካታ ስፖርተኞችንና ሜዳሊያዎችን ለዓለም እንደሚያበረክቱ እስከዛሬ እንደነበረው በተወሰን ደረጃ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲቀይሩም አሳስቧል፡፡
‹‹እንደ አፍሪካ በቶኪዮ 2020 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአሸናፊነታችንን ስልት በጋራ እንንደፍ›› በሚል መሪ ቃል በአቢጃን የመከረው በዋናነት አፍሪካ በ2020 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ትችል ዘንድ በመርህ ደረጃ ያቀደ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ባለፈው ነሐሴ በሪዮ ኦሊምፒክ አፍሪካ ያገኘችው ሜዳሊያ 45 ብቻ መሆኑን የጠቀሰው አኖካ፣ በሩጫው ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው ምሥራቅ አፍሪካውያኑ የኢትዮጵያና የኬንያ የሜዳሊያ ቁጥር ብቻ ቢታይ አፍሪካ ያገኘችውን የሜዳሊያ ብዛት 50 በመቶ እንደሚሸፍን ጭምር ማሳያ አድርጎ ማቅረቡን ጭምር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በላከው መግለጫ አውስቷል፡፡