የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው ታላላቅ የጎዳና ሩጫዎች የለንደን ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ከተመሠረተ ሦስት አሠርታትን እንዳጋመሰ የሚነገርለት የለንደን ማራቶን ታላላቅ የዓለም አትሌቶችን በማሳተፍ ይታወቃል፡፡ በውድድር ዓመቱ ሲጠበቅ የቆየው ይኼው የለንደን ማራቶን ባለፈው እሑድ ሲካሄድ በሁለቱም ጾታ ኬንያውያን የአሸናፊነቱን ክብር ወስደዋል፡፡ በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ ተከታዩን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካውያኑ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነት በተጠናቀቀው የለንደን ማራቶን፣ በወደንዶች ኬንያዊ ዳንኤል ዋንጅሩ 2 ሰዓት 05፡ 48 በሆነ ጊዜ ርቀቱን አጠናቆ አንደኛ ሆኗል፡፡ ለውድድሩ ትልቅ ቅድመ ግምት ተሰጥቶት የቆየው ቀነኒሳ በቀለ በሰባት ሰከንድ ተቀድሞ 2 ሰዓት 05፡57 አጠናቆ ሁለተኛ ለመሆን ተገዷል፡፡ ሌላው ኬንያዊ ቤዳን ካሮኪ 2 ሰዓት 07፡ 42 በመግባት ሦስተኛ መውጣቱ ታውቋል፡፡
በሴቶች መካከል በተደረገው ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር አሁንም ከኬንያ ሜሪ ኬይታኒ 2 ሰዓት 17፡ 01 በመግባት አሸናፊ ሆናለች፡፡ እንደ ቀነኒሳ ሁሉ ለርቀቱ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷት የነበረው የረዥም ርቀቷ ንግሥት ጥሩነሽ ዲባባ በውድድሩ ወቅት ሲገጥማት የተስተዋለውን የሕመም ስሜት ተቋቁማ ርቀቱ 2 ሰዓት 17፡ 58 በመሆነ ጊዜ አጠናቃ ሁለተኛ አጠናቃለች፡፡ የገባችበት ጊዜ የኢትዮጵያ ክበረወሰን ሆኗል፡፡ ሦስተኛ በሆን ያጠናቀቀችው ሌላዋ ኢትዮጵያ አሰለፈች መርጊያ ስትሆን፣ 2 ሰዓት 23፡ 05 ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ጊዜ እንደነበር የአይኤኤኤፍ ዘገባ አመልክቷል፡፡