በሺህ የሚቆጠሩ የሜዳ አህዮች በተንጣለለው የአፍሪካ መስክ ላይ እንደ ልብ ይፈነጫሉ። ባለ ሽንትር ዳሌያቸውን ወደ ላይ አቅንተው፣ ዘንፈል ብሎ የወረደውን ጋማቸውን ከሶምሶማ ግልቢያቸው ጋር አስማምተው ጎንበስ ቀና እያደረጉ ይሮጣሉ። ፀሐይ ያከረረውን መሬት የሚጎደፍረው የኮቴያቸው ድምፅ ከሩቅ ይሰማል። ከኋላቸው ቦለል እያለ የሚወጣው የቀይ አቧራ ጉም ከብዙ ርቀት ይታያል። ከዚህ ተመለሱ የሚላቸው ሳይኖር እንደልባቸው በነጻነት ይሮጣሉ።
ወዲያው አንድ የማይታይ ምልክት የተሰጣቸው ይመስል ዝግ ካሉ በኋላ ቀጥ ብለው ይቆማሉ። ችምችም ባለው ጠንካራ ጥርሳቸው የደረቀውን ሣር ጋጥ ጋጥ ያደርጋሉ። መንጋው አካባቢውን በንቃት ይከታተላል። በየጊዜው ቀና ብሎ በመመልከት ያዳምጣል፣ አየሩን ያነፈንፋል። ከሩቅ የሚነፍሰው ነፋስ ይዞት የመጣው የአንድ አንበሳ ግሳት ተሰማቸውና በተጠንቀቅ ቆሙ። ድምፁን በሚገባ ያውቁታል። የሜዳ አህዮቹ ጆሮአቸውን ቀስረውና ነጭተው በአፋቸው የያዙትን ሣር ማኘክ ትተው የሚያስገመግመው ድምፅ ወደመጣበት አቅጣጫ ተመለከቱ። የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ካረጋገጡ በኋላ አንገታቸውን ጎንበስ አድርገው ሣራቸውን መጋጥ ቀጠሉ።
የቀኑ ፀሐይ እየከረር ሲመጣ እንደገና ጉዟቸውን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ለማዳ ያልሆኑ ፈረሶች የውኃ ሽታ እያነፈነፉ ወንዝ ፍለጋ ይጓዛሉ። በወንዙ ዳርቻ ላይ ይቆሙና በቀስታ የሚወርደውን ድፍርስ ውኃ እየተመለከቱ ደረቁን አቧራ እየጎደፈሩ ያናፋሉ። ፀጥ ብሎ ከሚፈሰው ወንዝ ግርጌ አደጋ ይኖር ይሆናል ብለው ስለሚጠረጥሩ ቆም ይላሉ። ቢሆንም የያዛቸው ጥም ከባድ ስለሆነ አንዳንዶቹ ተጋፍተው ወደፊት ያመራሉ። አንዱ በድፍረት ወደፊት ሲሄድ ሁሉም ተንጋግተው ወደ ወንዙ ጠርዝ ይሮጣሉ። ተራ በተራ እስኪበቃቸው ከጠጡ በኋላ ወደተንጣለለው መስካቸው ይመለሳሉ።
መሸት ሲል መንጋው ቀስ ብሎ እያዘገመ በረዣዥሙ ሣር ውስጥ ያልፋል። በቀይ ቀለም የጋመችው ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል የምትጥልባቸው ጥላ ከአፍሪካ ዱር ጋር ተነጻጽሮ ሲታይ በጣም ያምራል።
ንቁ! (2002)