Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሴቶች የሚፈተኑበት የቴክኖሎጂ መድረክ

ሴቶች የሚፈተኑበት የቴክኖሎጂ መድረክ

ቀን:

በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው፡፡ አምስት አምስት ሆነው በቡድን ተደልድለዋል፡፡ የትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ሲወያዩ ለተመለከተ የተሰጣቸውን የቤት ስራ በጋራ እየሰሩ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹ ከመደበኛ ትምህርታቸው ዉጪ በሆነ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ ከሰሞኑን የወጣት ሴቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ፈጠራ ለመሥራት በስራ ተጠምደው ነው የሰነበቱት፡፡

ቴክኖቬሽን የተባለው ዓለም አቀፍ የሴቶች የፈጠራ ሥራ ውድድር ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ውድድሩ ከተጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ ከ78 አገሮች የተውጣጡ 10,000 ሴቶች በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ የውድድሩ ዓላማም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶት ልጆች የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዲሁም ሴቶች የአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ የሚያስሏቸውን የትምህርት ዕድሎች መፍጠር ነው፡፡

 በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑት ከ10 እስከ 18 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለየ የአይሲቲ ችሎታ ያላቸው ታዳጊ ሴቶች ናቸው፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉት ሴቶቹ በአካባቢያቸው ውስጥ ያስተዋሏቸውን ማኅበራዊ ችግሮች በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችል የተንቀሳቃሽ ስልክ አፕሊኬሽኖችን መስራትና የንግድ ዕቅድ ወይም ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ መሠረትም ከየትምህርት ቤቱ የተውጣጡት ሴት ተማሪዎች በማኀበረሰቡ ውስጥ ያስተዋሏቸውን ማኀበራዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚሏቸውን በሞባይል አፕሊኬሽኖች ለማዘጋጀት ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ ውይይቱም የዝግጅቱ አንድ አካል ነው፡፡ ከእነዚህ ታዳጊዎች መካከል የ17 ዓመቷ ተማሪ ሔርሜላ ቅዱስ አንዷ ነች፡፡

ሔርሜላ በካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነች፡፡ ለፈጠራ ሥራዎች ፍላጎት ያደረባት ገና ትንሽ ልጅ ሳለች እንደሆነ ‹‹ከድሮ ጀምሮ የአይቲ ነገሮች ይሰቡኝ ነበር፡፡ የምፈልጋቸውን ነገሮች ለማድረግም ብዙ አልቸገርም፡፡ ነገሮችን በቅርብ አገኛለሁ፤›› ትላለች፡፡ ይሁንና ለአይሲቲ የነበራት ፍቅር ከዝንባሌ ባለፈ የትም ሊያደርሳት የሚችል አልነበረም፡፡

የመሰናዶ ትምህርት ቤት ገብታ መሠረታዊ የኮምፒውተር ቋንቋ (ኮዲንግ) መማሯ ግን አይሲቲን ከጊዜ ማሳለፊያነት በዘለለ እንድታየው ማድረጉን ትገልጻለች፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለመሥራት ሙከራ ማድረግ የጀመረችውም ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በቅርቡ ተዘጋጅቶ በነበረ አንድ የፈጠራ ውድድርም ከጓደኞቿ ጋር ሆና በሠራችው የመገበያያ ዌብ ሳይት ተወዳድራ ነበር፡፡ በውድድሩ ሦስተኛ መውጣታቸውን ሔርሜላ ትናገራለች፡፡

በቴክኖቬሽን ውድድር ላይ ለመሳተፍ ደግሞ ከሌሎች አራት ጓደኞቿ ጋር በመሆን አንድ የፈጠራ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ለአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች ትልቅ ችግር ለሆነው የትራንስፖርትን ችግር ለመቀነስ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል የሞባይን አፕሊኬሽን ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

አፕሊኬሽኑ ጉግል ማፕን በመጠቀም በከተማው ውስጥ የታክሲ ዕጥረት ያለባቸውን ቦታዎች ለይቶ ማመልከት የሚችል ነው፡፡ አፕሊኬሽኑን በስልክ ላይ በመጫን ችግሩ ያለበት ቦታ ላይ ሆኖ ክሊክ በማድረግ ምልክት መስጠትና  ወደ ተባለው ቦታ ታክሲዎች እንዲላኩ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ሔርሜላ ትናገራለች፡፡

ሌላዋ ተሳታፊ የ18 ዓመቷ ቤቴል አለበል ነች፡፡ ከነ ሄርሜላ ግሩፕ ተደልድላለች፡፡ የ12ኛ  ክፍል ተማሪ ስትሆን 18 ዓመቷ ነው፡፡ ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ከመደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን በተለያዩ ክበባት በማገልገል ላይ ትገኛች፡፡ ወላጅ ለሌላቸው ታዳጊዎች ከጓደኞቿ ጋር በመሆን የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁሶችንና አልባሳትን የመስጠት ልምድ እንዳላት፣ በቀይ መስቀል ክበብ እንደምታገለግል ትገልጻለች፡፡ በትምህርት ቤታቸው በሚገኝ የአይቲ ክበብም አባል እንደሆነች ትገልጻለች፡፡

ለአይቲ የተለየ ዝንባሌ ያደረባት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ ይሁንና ፍላጎቷን በክህሎት ለማዳበር ኮምፒውተር ለማግኘት ብዙ ትቸገር እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ኮምፒውተር ፍለጋ በአካባቢዋ የሚገኙ የኢንተርኔት ካፌዎችን አልያም የትምህርት ቤት ላቦራቶሪዎች ውስጥ ብዙ ጊዜዋን ታሳልፍ ነበር፡፡

ዘጠነኛ ክፍል ከገባችና መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት ካዳበረች በኋላ የአይቲ ፍቅሯ ከወረት ያለፈ መሆኑን የተረዱት ወላጆቿ ይደግፏት ጀመረ፡፡ ላፕቶፕ ገዝተው በመስጠት ኮምፒውተር ፍለጋ ከመንከራተት አዳኗት፡፡ ይህም የአይቲ ክህሎቷ ይበልጥ እንዲጠነክር አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሞባይል አፕሊኬሽኖችን የመሥራት አቅም አዳብራለች፡፡ የቴክኖቬሽን ውድድር መኖሩን እንደሰማችም ለመመዝገብ አላቅማማችም፡፡ ‹‹ለመመዝገብ የተለያዩ የሞላናቸው ፎርሞችና ያስገባናቸው ጽሑፎች ነበሩ፡፡ በእዚያ ላይ የተሻለ ነገር በማሳየቴ ነው የተመረጥኩት›› ትላለች፡፡

ከፊት ለፊቷ አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይጠብቃታል፡፡ ይሁንና ከጥናት ጋር አይመቸኝም፣ ጊዜ ያጥረኛል  አልችልም ብላ እጅ አልሰጠችም፡፡ ጥናቱንና ፕሮጀክታቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጎን ለጎን ማስኬድ መርጣች፡፡ ‹‹በደንብ አጥንተን ለፍተን ነው የሠራነው ካሸነፍን የምናገኘውን የገንዘብ ሽልማት ለፕሮጀክቱ እናውላለን ትላለች፡፡

ኢትዮ ሞዛይክ ኢቨንትና ፌስቲቫል፤ ሲነርጂ ሐበሻ ፊልምና ኮሙኒኬሽን ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር አገሪቱ በዚህ ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውድድር እንድትሳተፍ ፕሮግራሙን አዘጋጅተዋል፡፡

የቴክኖቬሽን የሪጅን አምባሳደር ወ/ሮ ሳራ ታቢት እንደገለጹት፣ በውድድር የሚሳተፉ ተማሪዎች አራት ደረጃዎች ባሉት የሞባይል አፕሊኬሽን ፈጠራ ሒደት ያልፋሉ፡፡ ደረጃዎቹም ተማሪዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያስተዋሉትን ችግር የሚለዩበት፣ ለችግሩ መፍትሔ የሚያመጣ የተንቀሳቃሸ ስልክ አፕሊኬሽን የሚሠሩበት፣ ለሠሩት አፕሊኬሽን ቢዝነስ ፕላን የሚያዘጋጁበትና ሥራቸውን ወደ ገበያ አውጥተው የሚሸጡባቸው ናቸው፡፡

እነዚህ ሒደቶች በሦስት ወራት ጊዜ ተጠናቀው ፈጠራዎች ለውድድሩ መቅረብ አለባቸው፡፡ በዚህ ዓመት በሚካሄደው ውድድር ላይ በድህነት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ የፆታ እኩልነት፣ በትምህርት፣ በጤናና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ችግሮች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሥራዎች  ይቀርባሉ፡፡

የሲነርጂ ሐበሻ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ ታፈሰ  እንደሚሉት፣ በውድድሩ ከስምንት የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤት የተውጣጡ የአይቲ ተሰጥኦ ያላቸው 60 ሴት ተማሪዎች ተካተዋል፡፡ አምስት  አምስት ሆነው በአሥር ግሩፕ የተደለደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚያልፈው አንዱ ግሩፕ ብቻ ይሆናል፡፡ ወደ ዓለም አቀፍ ውድድር የሚያልፈውን ግሩፕ አወዳድሮ የመምረጡ ሥራ ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ አሸናፊው ግሩፕ በመጪው ሰኔ 2009 ዓ.ም. በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ባህር ማዶ ያቀናል፡፡

ዓምና በተካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ አሸናፊ የነበሩት ከሕንድ የመጡ ታዳጊዎች እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ሞገስ ‹‹የተማሪዎች፣ የትምህርት ቤቶች እንዲሁም የአሰልጣኞቻቸው ብቃት ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህ ውድድር ለማሸነፍ ይከብደናል፤›› ሲሉ በዚህኛው ውድድር ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ማሸነፍ የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ለወደ ፊት መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን፣ የተለያዩ ተቋማት ለፕሮጀክቱ የሙያና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ፣ ይህም የአገሪቱ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች የተሻለ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲያሸንፉ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቴክኖቬሽን ኢትዮጵያ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን 50,000 ብር የሚሸለም ሲሆን ለዓለም አቀፉ ውድድሩ በፍፃሜ እንደሚያልፍ ታውቋል፡፡ በዓለም አቀፉ ውድድር አሸናፊ 15,000፣ ሁለተኛ ለሚወጣ 10,000 እንዲሁም ሦስተኛ ለሚወጣ 5,000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚሸለም ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...