Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ግባችን ሲሚንቶ አምርቶ ከመሸጥ በላይ ነው››

አቶ መስፍን አቢ (ኢንጂነር)፣ የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) ላለፉት ስምንት ዓመታት የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እየሠሩ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ሥራ ዓለም ከተቀላቀሉበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ከሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ ቆይተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ኮርፖሬሽን በሚል መጠሪያ ይታወቅ የነበረውን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ሥራ ጀምረዋል፡፡ በሙገርና በአዲስ አበባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ በዋናነትም በሁለቱም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የቴክኒክ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ከሁለቱ ፋብሪካዎች ይዘውት የነበረውን ኃላፊነት ከለቀቁ በኋላም፣ በሲሚንቶ ኢንዱስትሪና ተያያዥ በሆኑ ሥራዎች ላይ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት የሚሰጥ ኢለምቴክ ትሬዲንግ የሚል ስያሜ ያለው ኩባንያ በማቋቋም ሲሠሩም ነበር፡፡ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ኩባንያ እንዲቋቋም መሠረት የጣሉ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሥራ የጀመረውን የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ ለማስጀመር ከፍተኛ ድርሻ ከነበራቸው መሥራቾች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ምሥረታ ታሪክ በርካታ ባለአክሲዮኖችን ይዞ በተነሳው የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር የሥራ ሒደትና የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በአገሪቱ በአክሲዮን ከተቋቋሙ ኩባንያዎች በርካታ ባለአክሲዮኖችን (16,500) ይዞ የተነሳ ነው፡፡ በበርካታ  ባለአክሲዮኖች መቋቋሙ ምን ያመላክታል ይላሉ? በዚህ ደረጃ ማሰባሰብስ የተቻለው እንዴት ነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- እንደጠቀስከው ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በያዘው የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከሁሉም የአክሲዮን ኩባንያዎች የበለጠ ነው፡፡ በባለአክሲዮኖች ብዛት ብቻ ሳይሆን ያለውም ካፒታል ቢሆን ትልቅ ነው፡፡ አሁን ያለን ካፒታል ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ ይህንን ያህል ሕዝብ ተሳታፊ እንዲሆን በዚህን ያህል ደረጃ ካፒታል ማሰባሰብ የተቻለው በእኔ ግምት ሁለት ነገር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጀመሪያው በቢዝነሱ ላይ እምነት መጣል ነው፡፡ በቢዝነሱ እምነት መጣል ሲባልም በአገራችን ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ስለሚገኝ፣ ለግንባታ ዋናው ግብዓት ሲሚንቶ በመሆኑ ይህንን ግብዓት ማምረት የሚያዋጣ በመሆኑ ነው፡፡ የእኛን የሲሚንቶ በነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች ጋር ስናወዳድር እንኳን ከአማካይ በታች ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ግን በጣም ፈጣን ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ የገበያ ፍላጎት ማየት ይቻላል፡፡ በእኛ በኩል አድርገናል የምንለው ይህንን መልካም ዕድል አክሲዮኖችን ለሚገዙ ሰዎች በትክክል እንዲረዱት ማድረጋችን ነው፡፡ ሌላው በአደራጆቹና ኩባንያውን በሚመሩት ሰዎች እምነት በመጣሉ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ዳር ደርሶ የተጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንደሚችል በማመኑ ነው ይህንን ያህል ሕዝብ ሊሰባሰብ የቻለው፡፡ ፕሮጀክቱንም ዳር ማድረስ የተቻለው፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ፋብሪካ ገንብቶ ሥራ ለማስጀመር ረዥም ጊዜ ወስዷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ ይገለጻል፡፡ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ ከታሰበው ጊዜ በላይ ለመዘግየቱ ምክንያቱ ምን ነበር?  በመዘግየቱስ ከባለአክሲዮኖች የደረሰባችሁ ተፅዕኖ የለም? ዘግይቶ ዕውን ቢሆንም ሲፈትናችሁ የነበረው ምንድነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- ፕሮጀክቱ አዋጭ ስለመሆኑ ሁሉም የተረዳው ጉዳይ ነበር፡፡ በነሐሴ 2001 ዓ.ም. የአክሲዮን ሽያጩን ስናቆም 300 ሚሊዮን ብር ገደማ ሰብስበን ነበር፡፡  መጀመርያ የገጠመን ችግር በእኛ የፕሮጀክት ወጪ ግምት መሠረት 120 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣናል ተብሎ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢንቨስትመንቱ ከሚፈለግው ገንዘብ 30 በመቶውን ወይም (36 ሚሊዮን ዶላር) ካገኘን ቀሪውን በብድር በመሙላት ፕሮጀክቱን ማስጨረስ ያስችለናል ብለን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት 300 ሚሊዮን ብር ወደ 33 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይሆን ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የአክሲዮን ሽያጭ አቁመን የፕሮጀክት  ሥራ ስንጀምር የምንዛሪ ለውጥ በተከታታይ አጋጠመ፡፡ ይህንኑ ችግር ለባለአክሲዮኖቻችን ገለጽን፡፡ ለባንክ ብድር የመንግሥትን ድጋፍ ለማግኘት ካፒታላችንን ማሳደግ እንደሚኖርብንም ለባለአክሲዮኖቻችን አሳወቅን፡፡ በዶላር ሲታሰብ የፕሮጀክቱ ወጪ አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ የምንዛሪ ለውጡ የፈጠረውን ክፍተት ያህል ከባለአክሲዮኖች ካፒታል መሰብሰብ ነበረብን፡፡ ይህንን ለማድረግ ጥረት እያደረግን እያለ መስከረም 2004 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 1.5 ቢሊዮን ብር አበደረን፡፡ ባንኩ ይህንን ያህል ብድር ፈቅዶ ሌላ  ቅድመ ሁኔታ አቀረበ፡፡ ይህም ከባለአክሲዮኖች በመሰብሰብ ድርሻችሁን 655 ሚሊዮን ብር አድርሱ የሚል ነው፡፡ በተባለው መሠረት 655 ሚሊዮን ብር ለመድረስ ጊዜ ወደሰብን፡፡ የአገር ውስጥ ባለአክሲዮኖች የተፈለገውን ያህል መጠን ገንዘብ ማዋጣት  አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የውጭ አጋሮች አፈላልገን እስክናገኝ ጊዜው ደረሰ፡፡ ልማት ባንክም ላበድራችሁ የነበረውን ገንዘብ ይዤ መቆየት አልችልም አለ፡፡ ለእናንተ የተዘጋጀውን ገንዘብ ለሌላ አበድሬያለሁና የተሻለ ሐሳብ ፈልጉ አለ፡፡ ይኼ ብዙ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ይህ ሲሆን ጉዳያችንን ይዘን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ እስከ ማመልከት ደረስን፡፡

ሪፖርተር፡- የማመልከቻችሁ ጭብጥ ምንድነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- ብድሩ መሰረዙ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡ በዚያን ወቅት ለኮንትራክተሩ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ከፍለናል፡፡ ለግንባታ ግብዓት የሚሆኑ እንደ ብረት ያሉ ምርቶችን ገዝተን ነበር፡፡ ፋብሪካው ለሚተከልበትና የጥሬ ዕቃ ማውጫ ቦታዎች ይዞታቸው ለሚነካባቸው ካሳ ከፈልንና የተፈቀደልን ብድር ሊሰረዝብን አይገባም በማለት ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት መባከን የለበትም የሚል አቋም ይዘን ነው ያመለከትነው፡፡ ከዚያ በኋላ በመንግሥት በተፈቀደልን መሠረት ከውጭ ገንዘብ መበደር ትችላላችሁ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክም ከኢንቨስትመንት ወጪው እስከ 30 በመቶ ድረስ ይፈቀድላቸዋል ተባለ፡፡ እንዲህ እስኪሆን ድረስ ግን ጊዜ ወሰደ፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት እስከ 30 በመቶ ተበደሩ ሲል 70/30 የሚለው ቀርቶ ማለት ነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- 70/30 እንደተጠበቀ ሆኖ 40 በመቶው ከውጭ፣ 30 በመቶው ከልማት ባንክ፣ 30 በመቶው ደግሞ ከአኪዩቲ (ከአክሲዮን ኩባንያው) በሚለው ተስማማን፡፡ ይህ የተወሰነው ታኅሳስ 2005 ዓ.ም. ነው፡፡ እስከዚህ ውሳኔ ድረስ የፋይናንስ ችግሩ ምንም ሊያንቀሳቅሰን አልቻለም ነበር፡፡ ከመንግሥት በተሰጠን አቅጣጫ  በልዩ ሁኔታ ከውጭ እንድንበደር በተፈቀደልን መሠረት የፒቲኤ (አሁን ትሬድ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ባንክ ተብሏል) ነሐሴ 2005 ዓ.ም. 50.1 ሚሊዮን ዶላር ብድር አገኘን፡፡ የእኛ ግምት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወዲያውኑ ብድሩን ይሰጠናል የሚል ነበር፡፡ መንግሥት ግፊት እያደረገም ባንኩ በራሱ የውስጥ አሠራር ችግር ምክንያት ሳይሰጠን እስከ ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ድረስ አቆየው፡፡ በዚህ መሀል እየጠፋ ያለው እያንዳንዱ ጊዜ የፕሮጀክት ወጪ እየጨመረ ነው፡፡ ኮንትራተሩ የሚከፈለው ገንዘብ ሳይቀየር ሌሎች እንደ ባንክ ወለድ፣ የአስተዳደር ወጪ ያሉ እየጨመሩ ሄዱ፡፡ መጨረሻ ላይ ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ከልማት ባንክ ብድሩን አገኘን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈቱም ጊዜ ወሰደ፡፡ እንዲህ እያለ ሁሉ ነገር ተጠናቆ መጋቢት 2007 ዓ.ም. የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጀመረ፡፡ በ25 ወራት ግንባታው ተጠናቀቀ፡፡ ስለዚህ ትልቁ ችግር የነበረው ብድሩን የማግኝት ነው፡፡ ብድር ያገኘንበትን የመጀመሪያውን ዕርምጃ ሙሉ በሙሉ እንዳንጠቀም ካፒታል የማሳደግ ጉዳይ መጣ፡፡ በመካከል ሰዎች በአክሲዮን ኩባንያዎች ላይ እምነት እንዳይኖራቸው የሚገፋፉ ነገሮች ተፈጠሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለአክሲዮኖች እምነት እንዳይኖራቸው ያደረገው ነገር ምንድነው? ከእናንተ መዘግየት ጋር ምን ያገናኘዋል?

ኢንጂነር መስፍን፡- በወቅቱ ብዙ የአክሲዮን ኩባንያዎች ተፈጠሩና ግማሾቹ ተዘጉ፡፡ ሌሎቹም እርስ በርሳቸው ግጭት ሲፈጥሩ ብዙ ሰዎች ሐበሻ ሲሚንቶም ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመዋል ወደሚል ግምት ገቡ፡፡ ስለዚህ ካፒታል ማሰባሰብ አለብን የሚለውን ነገር በቀላሉ ለመወጣት አልተቻለም፡፡ ይህንን ችግር የፈቱልን ከደቡብ አፍሪካ አብረውን ለመሥራት የመጡ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ዋናው የፕሮጀክቱ መሠረታዊ ችግር ፋይናንስ ነበር፡፡ ለመዘግየቱ ምክንያት ይኸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአክሲዮን ኩባንያችሁ ስያሜ ስንነሳ ‹‹ሐበሻ›› ይባላል፡፡ ይህንን ስያሜ የያዘ አክሲዮን ኩባንያ ባለቤቶች ሐበሾች ናቸው፡፡ አሁን የአክሲዮን ኩባንያውን ባለድርሻዎች ስናይ ብልጫ ያለውን ወይም 53 በመቶ የሚሆነውን የያዙ ሁለቱ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ይህ የሆነው ለምንድነው? ከአገር ውስጥ መሰብሰብ የነበረበት ገንዘብ ባለመገኘቱ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት ነበር?

ኢንጂነር መስፍን፡- በመጀመርያ የደቡብ አፍሪካዎቹ ኩባንያዎች ድርሻ 47 በመቶ ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማግኘት የነበረብን ብድር አንድ ዓመት በመዘግየቱ ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ አስፈለገ፡፡ ከብድሩ ጋር ተያይዞ የመጣው መዘግየት 30 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ወጪ እንዲጨምርብን አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ያህል ጭማሪ ወጪ በዚህ ምክንያት ብቻ? እንዴት?

ኢንጂነር መስፍን፡- ምክንያቱም ለራሱ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተጨማሪ ወለድ ከፍለናል፡፡ ለፒቲኤ ባንክም እንዲሁ ወለድ እንከፍላለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ፕሮጀክቱ በዘገየ ቁጥር የብር የምንዛሪ ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ ስለዚህ የሚቀንሰውን ያህል እንደገና እያዋጣህ መልሰህ መተካት አለበት፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ተጨማምረው የፕሮጀክቱን ወጪ አሳድገውታል፡፡ የሠራተኛ ደመወዝና የቢሮ ኪራይ ሁሉ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ 30 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ እንድናወጣ አድርጓል፡፡ ይህንን መሸፈን የነበረብን ከባለአክሲዮኖች አውጥተን መሆን ነበረበት፡፡ በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ባለአክሲዮኖች መጀመሪያ የአዋጭነት ጥናቱን ባስረዳነው መጠን ሊከተሉን አልቻሉም ነበር፡፡ ደግሞም ያኔ በመገናኛ ብዙኃን ብዙ እናስተዋውቅ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር ላይ እንዲህ ባለው ማስታወቂያ አክሲዮን መሸጥ ብዙ የሚያዋጣ አልመሰለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ኢንጂነር መስፍን፡- ምክንያቱም ሰው የበለጠ እምነት ማጣት ነበር የሚታይበት፡፡ ስለዚህ ከማስተዋወቅ ይልቅ ባለአክሲዮኖችን በቀጥታ እየደወልንና በስብሰባ ወቅትም ተጨማሪ አክሲዮን ገዝተው ካፒታል እንዲያሳድጉ ነበር ስንጠይቅ የነበረው፡፡ ብዙዎች ቅድም እንዳልኩህ ተጀምረው የነበሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሳይሳኩ ሲቀሩ በአብዛኛው ይኼኛውም የዚህ ዓይነት ችግር ይገጥመዋል በሚል ሐሳብ ነገሩ ተጓዘ፡፡ ነባር ባለአክሲዮኖች ድርሻቸውን መግዛት ካልቻሉ ፍላጎት ያላቸው የንግድ ሕጉ ስለሚፈቅድ ሌሎች ባለአክሲዮኖች ይገዛሉ፡፡ ያው የንግድ ሕጉ ፈቅዷል፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያውያን እንኳን መሸጥ አንችልም፡፡ አሁን ግን መልስ ማግኘት ያስቸግረናል፡፡ ምክንያቱም የአንድ ሰው ይዞታን መንጠቅ አትችልም፡፡ ምናልባት ወደፊት ሊሆን የሚችለው ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን የሚባለው የደቡብ አፍሪካው የኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋናው ሥራ አምስት ዓመት ገደማ ቆይቶ ይዞታውን ለባለአክሲዮኖች ሸጦ መውጣት ነው፡፡ ያኔ ከሲሚንቶ አምራቹ ሽርካችን ጋር በይዞታችን ልክ እንከፋፈል ከተባለ የባለቤትነት ይዞታችን 50፣50 የመምጣት ዕድል ይኖረን ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ በእርግጠኝነት ባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ድርሻ እያገኙ ስለሚሄዱ የሚመደብላቸውን አክሲዮን መግዛት አይከብዳቸውም፡፡ አሁን ግን ለአራት ለአምስት ዓመት የያዝነውን ድርሻ ይዘን እንቀጥላልን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መንገድ ተቋቁሞ እዚህ የደረሰው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ መቼ ትርፍ አምጥቶ የትርፍ ድርሻ ያከፋፍለናል የሚለው የብዙ የባለአክሲዮኖች ጥያቄ ነው፡፡ ቀድሞ ባሰባችሁት ልክስ የትርፍ ድርሻ ትሰጣላችሁ?

ኢንጂነር መስፍን፡- እኛ መጀመርያ ፕሮጀክቱን በምናስብበት ጊዜ በአንድ አክሲዮን ከ100 በላይ ዲቪደንድ እንደሚገኝ ነበር፡፡ አሁንም ከ50 እስከ 60 በመቶ ዲቪደንድ እናገኛለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምክንያቱም የማምረቻ ወጪያችንን እናውቃለን፡፡ ቢዘገይም 155 ሚሊዮን ዶላር በሆነ ወጪ ግንባታውን ብናካሂድም፣ ከሌሎች ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ሲታይ የእኛ የኢንቨስትመንት ወጪያችን አነስተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም  አንደኛ ከኮንትራክተሩ ጋር ጥሩ ዋጋ ለማግኘት ተደራድረን ነበር፡፡ ሁለተኛ ፕሮጀክቱን እንዲያስተዳድር ለሦስተኛ ወገን አልሰጠንም፡፡ ፕሮጀክቱ የተዳደረውና የተመራው በአማካሪ ድርጅት አይደለም፡፡ የራሳችንን ባለሙያዎች አደራጅተን ከዲዛይን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ነው የተመራው፡፡ ይህንን ማድረጋችን በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ ወጪ እንድንቆጣጠር ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ብዙ ጊዜ በአማካሪ መሐንዲሶች የሚሠሩ ሥራዎች የዋጋ ለውጥ የተለመደ ነው፡፡ እኛ በኮንትራክተሩ ምንም ዓይነት የዋጋ ለውጥ እንዲገጥመን አላደረግንም፡፡ ከዚህ በላይ በእኛ በኩል መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች በትክክል ወጪዎቻቸውን ተቆጣጥረን ነው የሠራነው፡፡ የፕሮጀክት ወጪያችን ከዶላር አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋቋሙት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አነስተኛ ነው፡፡

የእኛ ሸሪክ የሆነው የደቡብ አፍሪካው ሲሚንቶ ኩባንያ እኛ ከገነባነው የሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር ተመሳሳይ አቅም ያለውን ፋብሪካ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ገንብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስወጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ እኛ ከሌሎቹ ጋር ስናነፃፅረው የፕሮጀክት ወጪውን በትክክል አስተዳድረናል ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሲጀምር ይዞት የሚሄደው ወጪ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ማለት የማምረቻ ወጪ ላይ ብዙ ጭነት እንዳይኖርብህ በማድረግ ተወዳዳሪ ያደርግሃል፡፡ ለዚህም ነው የምንዛሪ ለውጥ ቢኖርም እንኳን በፊትም የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋችን 150 ብር ይሆናል ያልነው፡፡ አሁንም ዕቅዳችን እዚያ አካባቢ ነው፡፡ ስለህ ያሰብነውን መቶ በመቶ ዲቪደንድ ማግኘት እንኳን ባይቻል አሁን ባለን ደረጃ ከ50 እስከ 60 በመቶ ዲቪደንድ እንከፍላለን፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ይህንን ፋብሪካ ለማቋቋም በተነሳችሁበት ጊዜ በነበረው ገበያና አሁን ባለው መካከል ልዩነት አልተፈጠረም? አሁንም ገበያው እንዳለ ታምናለችሁ?

ኢንጂነር መስፍን፡- ወደዚህ ሥራ ስንገባ ያኔ የነበረውን የእጥረቱን ወቅት ገበያ ታሳቢ ብቻ አድርገን አልነበረም፡፡ መንግሥትም የራሱ ዕቅድ ነበረው፡፡ እንዲያውም የመንግሥት ዕቅድ በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ በዓመት 300 ኪሎ ግራም እንዲሆን ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ያኔ ወደ 150 ኪሎ ግራም ቢደርስ ብለን ነበር ስንሠራ የነበረው፡፡ አሁን ግን የእኛም ምርት ገበያ ውስጥ ገብቶም የሲሚንቶ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ወደ 130 ኪሎ ግራም ገደማ ቢደርስ ነው፡፡ ስለዚህ የሲሚንቶ ገበያ አለ፡፡ ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ ዕድል አለ፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ራሱ አቅርቦትና ፍላጎት እኩል ናቸው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምርት የሚያጥርበት ጊዜ አለ፡፡ አሁንም ሲሚንቶ ለማግኘት አንድ ወር መጠበቅ የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ የሚያሳየው አቅርቦት ላይ ክፍተት መኖሩን ነውና ገበያው አለ፡፡ በፊትም የጠበቅነው ገበያ አለ፡፡ ከአሁን በኋላም በተሻለ ፍጥነት ኢኮኖሚው ያድጋል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ ሌላው ቀርቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከኤልኒኖ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ድርቅ ኢኮኖሚው ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የኮንስትራክሽን ክፍለ በኢኮኖሚው አሁንም በደንብ እያደገ ነው፡፡ የኤልኒኖ ተፅዕኖ በማይኖርባቸው በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጎት ይኖራል ብለን እናስባለን፡፡ በኢትዮጵያ የቻይናን ያህል ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ባይኖረን እንኳን (የቻይና ዓመታዊ የሲሚንቶ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ 1,400 ኪሎ ግራም ገደማ ነው)  የቻይናን ግማሽ ወይም ሩብ ያህል የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖረን በአራትና አምስት ዓመት  ውስጥ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ 300 ኪሎ ግራም ሊገባ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ለመድረስ አሁን ያለውን የሲሚንቶ የምርት መጠን በእጥፍ ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ያሉት ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት የሲሚንቶ እጥረት እንዳያጋጥመን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ ተጨማሪ ፋብሪካዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት አሁን ላሉት የሲሚንቶ ማምረቻዎች ጥሩ ዕድል አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የገበያ ችግር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ባለሙያ እስከ መነጣጠቅ ደርሰዋል እየተባለ ነው፡፡

ኢንጂነር መስፍን፡- አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከመፈጠራቸው በፊት ሙገርና መሰቦ ፋብሪካዎች የሚመሩት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ ነበር፡፡ የሲሚንቶ ፍላጎቱ የፈጠረውን ድንገተኛ የመስፋፋት ያህል የሠለጠነ የሰው ኃይል አልነበረም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እውነት ለመናገር አዳዲስ የሚገቡት ድርጅቶች የሰው ኃይል ልማትን በሚመለከት ከፕሮጀክቱ መነሻ ጀምሮ አላሰቡበትም ማለት እችላለሁ፡፡ የተወሰኑ ሙከራዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የእኛን ሁኔታ ከጠየቅከኝ ደግሞ ፕሮጀክቱን ለሁለት ከፍለን ነው ያየነው፡፡ አንዱ የፋብሪካው ተከላ አለ፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ለኦፕሬሽን ጊዜ ዝግጅት ማድረግ የሚል ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ክፍል የግንባታ ፕሮጀክቱን የሚመራ ሌላው ደግሞ በኦፕሬሽን ጊዜ ፋብሪካውን ሊመራ የሚችል የሰው ኃይል የምናፈራበት ዲፓርትመንት ይዘን ነው ስንሠራ የቆየነው፡፡ በኦፕሬሽን ጊዜ ዋናው ኃይል ሰው ነው፡፡ በዚህ ደረጃ በአገር ውስጥ በቂ ባለሙያ አለ፡፡ ከሥር ደግሞ ማሠልጠን አለብህ፡፡

ከዚህ ውጪ አንድን ፕሮጀክት ስትዘረጋ ሁሉንም ነገር ለአማካሪ ከሰጠኸው አስቸጋሪ ነው፡፡ ፋብሪካው እንዴት ይሠራል? ምን ዓይነት ባለሙያ ያስፈልገዋል? የሚለውን ሙሉ ለሙሉ እንደ ባለቤት አይሠራልህም፡፡ በዚህ ምክንያት የፋብሪካው ግንባታ ካለቀ በኋላ የሚመራው ሰው ይጠፋል፡፡ ኮንትራክተሩ በዚያው ይዞት ይቀጥላል፣ ወይም ህንድ ወይም ፓኪስታን ይመጣል፡፡ የተለመደው እንዲህ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ሰዎች በፍፁም ሌላ ሰው እንዲተካቸው ዕድል አይሰጡም፡፡ ምክንያቱም ዕድሉን ከሰጠ የራሱን የሥራ ዕድል ማጣት ነው የሚሆነው፡፡ የቻለውን ያህል መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ እንዳይገባ እያደረጉ ይሠራሉ፡፡ ኦፕሬሽንና የሜንቴናንስ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩት ሰዎች ሁሉ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ኮንትሮል ሩም ውስጥ ገብቶ እንዳይሠራ ነው የሚያደርጉት፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ በዚህ መንገድ ከሄድክ በአሥርና በ15 ዓመታት ውስጥ ይህ ኩባንያ የሰው ኃይል ማፍራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ከፕሮጀክቱ መነሻ ጀምሮ የሰው ኃይል ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ረገድ ከመጀመርያው ጀምሮ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት በማቋቋም ነው የሠራነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ያፈራናቸው አሁን ፋብሪካውን ተረክበው መምራት ይችላሉ፡፡ እግረ መንገዳችንንም የሲሚንቶ ኢንዱስትሪው በሚፈልገው ሙያ የተመረቁ አዳዲስ ተማሪዎችን በተለማማጅነት እንዲሠሩም እያደረግን ነው፡፡

ከሰው ኃይል ጋር ተያይዞ የደቡብ አፍሪካ ሽርኮቻችን መጀመርያ የነበራቸው እሳቤ ብዙ ሰዎችን ከውጭ አምጥተን ማሠራት ይኖርብናል የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ እኛ አይገባም ብለን መከራከር አልፈለግንም፡፡ ሁኔታውን እያዩ ሲሄዱ በምንም ዓይነት ቀጥታ ቴክኒካዊ ሥራ ላይ ሰው ማምጣት እንደማያስፈልጋቸው ተረዱ፡፡ እንዲያውም ሩዋንዳና ኮንጎ ላሉ ፕሮጀክቶቻችን ከዚህ ሰው መውሰድ እንችላለን እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ መውሰድም ጀምረዋል፡፡ በረዥም ጊዜ ሁሉም ሲሚንቶ አምራቾች የሚያስፈልገውን ነገር በደንብ ተረድተው የሰው ኃይልን ማልማት ማድረግ ከቻልን የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ወደ ሌላ አፍሪካ አገር የምንልክበት ዕድል አለ፡፡ ነገር ግን አሁን በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ሒደት ፋብሪካውን የገነባው ኩባንያ በዚያው የማስተዳደር ሥራ ያከናውናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን አንዳንድ የተጀመሩ ጥረቶች አሉ፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር ሆኖ የማሠልጠኛ ማዕከል ለመገንባት እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቁጥር መጨመር ሲታሰብ የዋጋ ጉዳይ ይነሳል፡፡ እናንተም ስትነሱ አንድ ኩንታል ሲሚንቶን ከመቶ ብር በታች ማውረድ ይቻላል በሚል ነበር፡፡ አሁን ገበያው ሲታይ በተፈለገው መጠን ዋጋ እየቀነሰ አይደለም፡፡ ግን መቀነስ እንደነበረበት ይታመናል? የእናንተ መምጣት የሚለውጠው ነገር አለ?

ኢንጂነር መስፍን፡- ለምሳሌ በብዙ አገሮች አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ስድስት ዶላር አካባቢ ይሸጣል፡፡ ስለዚህ መጀመርያ አንድ ዶላር በአሥር ብር በሚመነዘርበት ጊዜ መቀነስ ነበረበት፡፡ በዚያ ምንዛሪ ሥሌት ከመቶ ብር በታች ይወርድ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ አሁን በዶላር አንፃር ስታየው በጣም ቀንሷል፡፡ በ2001 ዓ.ም. አንድ ኩንታል 350 ብር ወይም 35 ዶላር አካባቢ ነበር፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሚንቶ ይሸጥበት የነበረው ዋጋ በዓለም ትልቁ የሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ ይባል ነበር፡፡ አሁን አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 180 ብር አካባቢ ነው እየተሸጠ ያለው፡፡ ይህ ማለት የአሁን የመሸጫ ዋጋው ዘጠኝ ዶላር አካባቢ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከዶላር አንፃር ዋጋው መቀነሱን ቢሆንም፣ በብር ስታስበው ብዙ ለውጥ አይታይም፡፡ ስለዚህ ምንዛሪው ያመጣው ውጤት ነው እንጂ የሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ በዶላር ቀንሷል፡፡ ከዚህ ውጪ የሲሚንቶ ትልቁ የማምረቻ ወጪ ነዳጅ፣ የድንጋይ ከሰል ነው፡፡ የፋብሪካው ሁለት ሦስተኛ ወጪም ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ በነዳጅ ላይ የሚታየው የዋጋ መዋዥቅ የሲሚንቶ ማምረቻ ወጪን ከፍ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርግጥ የሲሚንቶ ማምረቻዎች ትልቁ ወጪ ኃይል ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር አማራጭ ኃይል መጠቀም አይሞከርም?

ኢንጂነር መስፍን፡- የግድ በነዳጅ ነው መጠቀም ያለብህ፡፡ ወጪውን ለመቀነስ ቢያንስ እስከ 60 በመቶ ድረስ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል መጠቀም ወይም ባዮ ማስ መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁን የሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር አለ፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ኃላፊነቱን ወስዶ እየተሠራ ያለ ፕሮጀክት አለ፡፡ ባዮ ማስ መጠቀምና የከሰል ፍጆታን መቀነስ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማምረቻ ወጪውን መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄውንም እግረ መንገዱን ይመልሳል ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ የአገር ውስጥ ከሰልና ባዮ ማስ ለመጠቀም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ግፊት እያደረገ ነው፡፡ ሲሚንቶ ማምረቻዎችም በጋራ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጥሬ ዕቃ አጠቃቀምስ እንዴት ነው? በቅርቡ የሲሚንቶ አምራቾች የሚጠቀሙባቸውን ማዕድናት ለመጠቀም አዲስ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ እናንተ የራሳችሁ ቦታ ነበራችሁ?

ኢንጂነር መስፍን፡- ሲሚንቶ ለማምረት አምስት ዓይነት ጥሬ ዕቃዎችን ነው የምንጠቀመው፡፡ ከዚህ ውስጥ ለአራቱ የማዕድን ማውጣት ፈቃድ አለን፡፡ ካሳ ከፍለን የማዕድን ማውጫ ቦታ ወስደን ማውጣትም ጀምረናል፡፡ ‹ፑሚስን› በሚመለከት የማዕድን ማውጣት ፈቃድ ነበረን፡፡ ነገር ግን ቦታ አልነበረንም፡፡ ቦታውን ለማግኘት ካሳ ከፍለን ለመያዝ እንቅስቃሴ በምናደርግበት ጊዜ አሁን ያለው ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጥሬ ዕቃውን ለግብዓትነት ስለምንፈልግ ከተደራጁና ጥራቱን ጠብቀው ከሚያመርቱ ወጣቶች ጋር አብሮ ለመሥራት፣ ቢሾፍቱ ድሬ በሚባል አካባቢና አዳማ አካባቢ ከተደራጁ ወጣቶች ጋር በወረዳዎቹ በኩል አብረን ለመሥራት እየተደራደርን ነው፡፡ ከሁለት አንዱ ጋር በቅርቡ ኮንትራት ተፈራርመን ሥራ እንጀምራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከወጣቶቹ በግዥ በመውሰድና በቀድሞ አሠራር ጥሬ ዕቃውን ራሳችሁ አውጥታችሁ በመጠቀም መካከል ያለውን ልዩነት ሊገልጹልን ይችላሉ? እናንተ በቀጥታ አውጥታችሁ ባለመውሰዳችሁ የሲሚንቶ የማምረቻ ዋጋ ይጨምራል እየተባለም ነው፡፡

ኢንጂነር መስፍን፡- እርግጥ ነው ልዩነት አለው፡፡ ከወጣቶቹ ተረክበን ስንሠራ ተጨማሪ ወጪ ማውጣት ይጠበቅብናል፡፡ በራሳችን ብንሠራ ወጪያችን ማዕድኑን ለማውጣት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በአዲሱ አሠራር መጠቀማችን ትንሽ ወጪ ይጨምራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሲሚንቶ አምራቾች በቀጥታ ጥሬ ዕቃውን አውጥተው እንዳይወስዱ ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ ያለው ሁኔታ አንድ ዓይነት መልክ እስኪይዝ ድረስ አሁንም ተደራጅተው ጥሬ ዕቃውን ከሚያወጡ ወጣቶች ላይ ለመግዛት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሐበሻ ሲሚንቶ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ደረጃ የቱ ጋ ነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- ለምሳሌ ደርባ የሚያመርተውን 70 በመቶ ያህል ነው የማምረት አቅማችን፡፡ በምርት መጠን መሪ አይደለንም፡፡ ነገር ግን እንደ መሪ ቃል እየተከተልን ያለነው ኩባንያችን ከሲሚንቶ በላይ ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሲሚንቶ በላይ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

ኢንጂነር መስፍን፡- ግባችን ሲሚንቶ አምርተን መሸጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሲሚንቶ የመጨረሻው ምርት አይደለም፡፡ ኮንክሪት አምርቶ የመሸጥ ዕቅድ አለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሲሚንቶ ውጤቶችን በሚመለከት ከአምራቾቹ ጋር በቅርበት ለመሥራት፣ ጥራታቸው የተጠበቀ የሲሚንቶ ውጤቶችን ለማምረት ከማኅበራት ጋር ለመሥራት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ እንዲሁም ለኮንትራክተሮች ሲሚንቶና ኮንክሪትን በተመለከተ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንሰጣለን ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ከተጠቃሚው በበለጠ እኛ አምራቾቹ ስለሲሚንቶው የተሻለ ዕውቀት አለን ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ኮንትራክተሮቻችን ሥራቸው ላይ ትኩረት አድርገው እኛ እንዲህ ያሉ ቴክኒካዊ ሥራዎችን እንሠራለን ብለን እያሰብን ነው፡፡ ለዚህ ነው ሲሚንቶ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አገልግሎቶችንም አምርተን እንሸጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ምርት ይዘው የሚቀርቡ ኩባንያዎች ዋጋቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ አግባብ ነው? ሲሚንቶ ላይም በዋጋ መወዳደር አይታይም፡፡ ግን ዕድሉ አለ፡፡ ይህ ለምን አይሆንም? እናተስ ወደ ገበያ የምትመጡበት ዋጋ ይለያል?

ኢንጂነር መስፍን፡- ዋጋ ስታወጣ በሁለት መንገዶች ነው የምትሄደው፡፡ አንደኛው መጠን መሪ ከሆንክ ዋጋ ልትወስን ትችላለህ፣ ወይም በምታመርት ቦታ (በሎኬሽን) ላይ መሠረት ያደረገ ዋጋ ልታወጣ ትችላለህ፡፡ እኛ ማምረቻችን ከአዲስ አበባ ቅርብ ነው፡፡ ከፍተኛ አምራች ግን አይደለንም፡፡ ስለዚህ የምንከተለው የዋጋ ስትራቴጂ ተጠቃሚው ሊገዛ በሚችልበት ዋጋ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መግዛት በሚችልበት የዋጋ ነው እየሰጠን ያለነውና ቅርበታችንን ተጠቅመን ብዙ ዋጋ መጠየቅ አልፈለግንም፡፡ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ዋጋ እንዲኖረን አድርገነው የምንሄደው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከሎጂስቲክስና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚመጡት ነገሮች ናቸው እንጂ የሚያውኩን፣  የሲሚንቶ አምራቾቹ ተወዳዳሪ የሆነ ዋጋ እየሰጡ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ የዋጋ መውጣትና መውረድ ላይ ሎጂስቲክስ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ከከሰል ቀጥሎ ትልቁ ወጪው ሎጂስቲክስ ነው፡፡ ይህንን ማስተካከል የሚቻልበት መንገድ ሲኖር ተወዳዳሪ የሆነ ዋጋ እየመጣ ይሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ የራሳቸው የትራንስፖርት ዘርፍ ይዘው ነው፡፡ እናንተስ የራሳችሁ የትራንስፖርት ዘርፍ ይኖራችኋል?

ኢንጂነር መስፍን፡- የለንም፡፡ በባለቤትነት መያዝ አልፈለግንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ኢንጂነር መስፍን፡- የሎጂስቲክስ ማኔጅመንት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ ይሆናል ብለን ያሰብነው ከሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር ዘለቄታ ያለው ሥራ አብረን በመሥራት እነሱም ተከታታይ የሆነ የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸውና ደንበኞቻችንን እንዲያገለግሉ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የትራንስፖርት ማኔጅመንት ሲስተም እያዘጋጀን ነው፡፡ የእኛን ተሽከርካሪዎችን ሳይሆን የሎጂስቲክስ ኩባንያዎችን ተሽከርካሪዎች ለማስተዳደር ነው፡፡ በዚህ መንገድ ከሠራን እነሱም እኛም ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ቢቆይም ግቡን አሳክቷል፡፡ ነገር ግን መዘግየቱ የራሱ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በአጠቃላይ ግን የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዴት ሊገለጹ ይችላሉ? ከእናንተ በኋላ የተቋቋሙ አንዳንዶች በመፈረካከሳቸው ይህ ዕጣ እንዳያጋጥማቸው ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ኢንጂነር መስፍን፡- የአክሲዮን ኩባንያዎች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ተበትኖ ያለውን ካፒታል ሰብስበህ ትልቅ አቅም ያለው ኩባንያ መፍጠር ትችላለህ፡፡ ይህ ለአገርም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ሦስት ተዋንያን አሉ፡፡ ሦስቱም ድርሻቸውን በትክክል መወጣት አለባቸው፡፡ አንዱ አክሲዮን ኩባንያ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ሐሳባቸው ፕሮጀክቱን መፈጸም እንጂ ሌላ ነገር መሆን የለበትም፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አልመው የሚነሱ ከሆነ ሒደታቸው ከመጀመርያው ስህተት ይሆናል፡፡ ራሳቸውንም አገርንም ይጎዳሉ፡፡ ራሳቸውን ይጎዳሉ የምለው ወደ ጥፋት ከሄድክ ተጠያቂነት ይመጣል ማለት ነው፡፡ ከጀመሩ በኋላም የሚያስፈልገውን ነገር ማወቅ አለባቸው፡፡ በቅን ልቦና ብቻ የሚሆን መሆን የለበትም፡፡ ሁለተኛው ተዋናይ ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚፈጠሩ ኩባንያዎችን መንግሥት መቆጣጠር አለበት፡፡ ኩባንያ መፍጠር መብት ነው፡፡ ትክክል ነው፡፡ የምትፈጥረው ኩባንያ የራስህ ብቻ ሆኖ በራስህ ገንዘብ ብትጫወት ምንም አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰው ገንዘብ ሰብስበህ ልትሠራ የማትችል መሆኑን መንግሥት ከገመተ ከመጀመርያው ማስቆም አለበት፡፡ አክሲዮን የሚገዛው ምንድነው? ይኸኛው ከዚያኛው ኩባንያው በምን ይለያል? አደራጆቹ እነማን ናቸው? የሚለውን ነገር መለየት አለበት፡፡ ቢዝነስ ‹ሪስክ› ነው፡፡ ሪስኩን መለየት ከአክሲዮን ገዥው ይጠበቃል፡፡ መንግሥት የመቆጣጠር ሥራውን ቢተጋበት እንኳን በሒደት ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስለዚህ አክሲዮን የሚገዛውም ሰው የራሱን ግምት መውሰድ አለበት፡፡ ለሁሉም አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለበት አክሲዮን ኩባንያዎች እንዴት መቋቋም እንዳለባቸውና ምን እንደሆኑ ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ አለበት፡፡ ለማንኛውም ሦስቱም አካላት የየድርሻቸውን በአግባቡ ከተወጡ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ በተለይ በተለይ ደግሞ እናደራጃለን የሚሉ ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸውና ይህንን መሸከም የሚችሉ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ያህል ጊዜ የሕዝብ ገንዘብ ይዛችሁ በመቆየታችሁና አንዳንዴም ነገሮች በምትፈልጉት መንገድ ሳይሄዱ ሲቀሩ ምነው በቀረብን ያላችሁበት ጊዜ የለም?

ኢንጂነር መስፍን፡- ነገሩ ተስፋ መቁረጥ ያመጣል፡፡ ይህንን የመቋቋም ችሎታ ያስፈልጋል፡፡ የራስህ ንብረት ቢሆን ዘግተህ ትሄዳለህ፣ ይህንን ግን ዘግተህ አትሄድም፡፡ የተረከብከውን ዳር ማድረስ ይኖርብሃል፡፡ ለዚህም ነው ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል የምለው፡፡ አቅቶኛል ትቼው እሄዳለሁ ብትል የሕግ ተጠያቂነት እንኳን ባይኖርብህ፣ የሞራል ተጠያቂ የምትሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እንደ ሁኔታው የሕግ ተጠያቂነትም ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ዳር ማድረስ ግዴታ ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት ከየትኛው ማዕዘን የማትጠብቀው እንቅፋት ሊገጥምህ ይችላል፡፡ እንደ መንግሥት ኩባንያ አትፈራም፡፡ እንደ ግል ኩባንያ በመተዋወቅ ወይም በሌላ ልትሠራ አትችልም፡፡ ያለው መንገድ ቀጥተኛውን መንገድ መከተል ነው፡፡ በዚህ ሒደት ያየነው ታች ቢሮዎች ላይ የሚያጋጥምህን እንቅፋት ተሰላችተህ ከተውክ ውድቀት ነው የሚጠብቅህ ወደ ላይ በወጣህ ቁጥር የመንግሥት ቢሮዎች ክፍት ናቸው፡፡ ውሳኔም በቶሎ ታገኛለህና የትኛውም ቦታ ችግር ሲያጋጥምህ ወደሚቀጥለው እርከን ሄደህ መታገል ነው እንጂ፣ ጉዳዩን በዚያው ደረጃ ቀርቷል ብለህ አይሆንልኝም ካልክ አደጋ አለው፡፡  መታገል ነው እንጂ ጉዳዩ በዚያው ደረጃ ቀርቷል አይሆንልኝም የምትለው ነገር የለም፡፡ ጊዜ ቢወስድብህም ወደ ከፍተኛው መንግሥት አካል በሄድክ ቁጥር ጉዳይህን በቀላሉ ትጨርሳለህ፡፡ እና የግዴታ ወደዚያ መግፋት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ግን አሁን ባለው አሠራር ለየዘርፎቹ መንግሥት ድጋፍ የሚያደርጉ ኢንስቲትዩቶች አቁሟልና እነሱ ያልተቋረጠ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ ዘርፍ ምን አገኛችሁ?

ኢንጂነር መስፍን፡- ለምሳሌ በእኛ ዘርፍ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት ከእኛ በበለጠ የእኛን ጉዳይ ይዘው ነበር፡፡ ልማት ባንክ ጋ ችግር ሲገጥመን፣ ኤሌክትሪክ ለማግኘት ስንቸገርና በማንኛውም ጉዳይ በጠየቅናቸው ቁጥር ከእኛ እኩል ጉዳያችንን ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን በመግፋት በእነዚህም በኩል ጉዳይህን ማሳካት ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለአክሲዮኖቻችሁ ተሰላችተው የወጡ አሉ ይባላል፡፡

ኢንጂነር መስፍን፡- የተወሰኑ ባለአክሲዮኖች ተስፋ ይቁረጡ ወይም ለሌላም ያስተላልፉ አሉ፡፡ በዚያው መጠን ግን አገር ውስጥ ያለውንና ሁሉንም ነገር የሚረዱት ደግሞ ከእኛ ጋር ነበሩ፡፡ በአጋጣሚው ጥሩ ነገር ያየነው በብዙ ቦታዎች ላይ ባለአክሲዮኖች አሉ፡፡ እነዚህ የሚችሉትን አድርገውልናል፡፡ በትክክል ችለው እስካሁን ድረስ የጠበቁን፣ የምንሠራውን ሥራ በትክክል ተረድተውን አብረውን የቆዩት ይበዛሉ፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ምንም ዓይነት ረብሻ ገጥሞን የማያውቀው፡፡ እኛም ያለውን ሁኔታ በደንብ እናስረዳለን፡፡ ሰውም በደንብ ይረዳል፡፡ የመንግሥትንም ትጋት እያዩ ስለሚሄዱና የጊዜ ጉዳይ አንዳንዴ የሚያናድድና የሚያሰለችም ቢሆን፣ ባለአክሲዮኖቻችን ሁኔታውን ተረድተው በትዕግሥት ጠብቀውናል፡፡  

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...