Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቁልቁለት ላይ ሆነን እንኳንም ቤንዚን አልኖረን!

ሰላም! ሰላም! የቱንም ያህል ያሰብነው ቢሳካ፣ የወጠንነው ቢሰምር ያለጤና ምንም ዋጋ እንደማይኖረው በጣም እንዳልገባኝ ስሆን አንዳንዴ አፈራለሁ። ለነገሩ ዛሬ ማፈር የሚባለው ነገር ተረስቷል አይደል? ‘እያዩት ከማይበሉት ሰዎች ተርታ አያስቆጥራችሁ!’ ሲባል አሉ አላሳፍር ብሏል። ዘመኑ በልተን እንሙት ባዩን ነዋ የሚወደው። መብላቱንስ ይብሉ። ካልተባላን ብለው የሚስጨንቁን ነገር አይደብርም?! ባሻዬ ባለፈው ከዕድር ስብሰባቸው ሲመለሱ፣ ‹‹አቤት! እግዚኦ አንተ ፈጣሪ!›› እያሉ ሲጓዙ አገኘኋቸው። እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ረቂቅ ትዝብታቸውን ለአምላካቸው ይኸው ብለው እንደ ንድፍ የሚያሳዩት ይመስላሉ። ‹‹ምነው ባሻዬ?›› ስል እንደ ልማዴ ‹‹እንዲያው ማን ይሆን ጤነኛ ዘንድሮ አንበርብር? ሰው ሁሉ ጉዱን ከኋላው ቀብሮ ነው ለካ የሚኖር?!›› ሲሉኝ ምን ሰምተው እንደሆነ አልጠየቅኳቸውም። ምድረ ሙሰኛ እንደ ቀበሮ ካለበት ጉድጓድ እየታደነ ለሕግ መቅረብ በሚኖርበት ጊዜ የምን ጥያቄ ማብዛት ነው እሱ? ያውስ በጥልቅ እየታደስን? ይልቅ የገረመኝ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ነው።

በስርቆትና በሕገወጥ መንገድ ዘመናችንን በሙሉ ለምን የተደላደለ ነገር ይዘን ለመኖር እንደምንደክም ሳስበው ብቻዬን ገርሞኝ እስቅ ጀመር። ወደው አይስቁ እኮ ነው! ስለዚህ አመራማሪ ስለሆነ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ከባሻዬ ጋር ስንጨዋወት፣ ‹‹ይኼ አሁን የምትለኝ ነገር ከጥንትም ከእነ አዳም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ አመል ነው። ቀናው እያለ ጠማማውን፣ ፊት ለፊቱ እያለ ጓሮውን፣ ብርሃን እያለ ጨለማ ጨለማውን መሄድ ነው የምንወደው። እንዲያው እንዴት ያለ ባህሪ ነው ግን?›› ብለውኝ ባሻዬ ራሳቸው እጅግ ገርሟቸው ሳቁ። በዚህ መሀል ስለሰው ልጅ በሥልጣኔ መገስገስና መራቀቅ ለማሰብ ሞከርኩ። ጨርሶ የሚዋጥልኝ ነገር አልሆነም። ሰው ሰውን የሚጥልበትን ገደል እየማሰ፣ ለሰውነቱም ለአዕምሮውም ጤና የማይሰጠውን የሕዝብ ገንዘብ እየቀማ፣ የአገርን ኢኮኖሚ ለማድማት የማይገባበት ሲገባ ስታዩ እውነት 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን ወይስ የጋርዮሽ ዘመን ላይ ትላላችሁ እኮ! እያወቁ አለቁ ነው በደፈናው የእኛ ነገር!

እንደምታውቀት በማንጠግቦሽ በኩል የሚመጣብኝ የማኅበራዊ ሕይወት ግዳጅ አለ። ግዳጄን ከተወጣሁ በኋላ በእንጥልጥል ወደ ተውኳቸው ሥራዎቼ እመለሳለሁ። ‘ማኅበራዊ ሕይወትና ማኅበረሰባዊነት በእነ ሌኒን ጊዜ ቀረ’ ያለውን ማስታወስ ቢያቅተኝ ‘ጊዜው የግለኝነት ነው’ ያለው ግን አልጠፋኝም። ከግለኝነትም አልፎ አሁን ጭራሽ የጡንቻ ውድድር ተጀምሯል። የባሻዬ ልጅ እንደሚያብራራው ከሆነ ያለ ጥርጥር የሦስተኛው ዓለም ቀዝቃዛ ጦርነት የተጀመረው አሁን ነው። ቢሆን ባይሆን ለነገሩ እኛ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ሚና ያለን አይመስለኝም። ለማዘንም እኮ መፈጠር አንዳንዴ መታደል ነው ብዬ ብላችሁ ሳቅ ሳቅ ይላችሁ ይሆን? ቂቂቂ! እንግዲህ በስንቱ አዝነን እንችለዋለን? በዘመኑም በዘመነኞችም ታዝኖ አይገፋም። የኑሮ ፋታ አለመስጠት ከታሰበን ግን የማኅበራዊ ሕይወት ግዳጅ ጦርነት መስሎ ቢታየን አይገርምም። ለማንኛውም ይህን ጨዋታ ለጊዜው እዚህ ላይ ቆም አድርገነው ሰሞኑን በማሽነሪዎች ዙሪያ ስለታዘብኩት አንዳንድ ነገር ላውጋችሁ። ጂቡቲ ወደብ የደረሰ ‘ኤክስካቫተር’ ለአንድ ደንበኛዬ ስደልል አገኘሁና ስሯሯጥ ነው የሰነበትኩት። በዚህ የዓመታት ደንበኛዬ ገድ ያገኘሁት ሥራ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ማሽን ማሻሻጥ። ይኼ ሁሉ ሰው ይኼን ሁሉ ማሽን እየገዛ ምን ሊያደርገው ነው? ብዬ መገረሜ አልቀረም።

ምንም እንኳ የአገሪቷን የኮንስትራክሽን ዕድገት ቀጣይነት አይጠረጠሬ ቢሆንም፣ እዚህ አገር ዓይን የበዛበት ቢዝነስ መጨረሻው ሲያምር ስላላየሁ ቅር አለኝ። በተለይ ደግሞ የተሻለ መካከለኛ ገቢ ካለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚመደበው ማሽን ገዝቶ በማከራየት ለመክበር የሚያደርገውን መጋደል ላየ፣ ሰውና ገንዘብ መጨረሻው የት እንደሚሆን ለመገመት ይቸገራል። ሩቅ ሳንሄድ ይኼው የእኔ ደንበኛ ምን እያለ ያወራኝ ነበር፣ ‹‹ይኼን ማሽን ገዝቼ ተገላግዬ!›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ምን እንዴት አለው?  በዚህን ያህል ጊዜ ይኼን ያህል ሰዓት ቢሠራ የምቆጥረውን አስበኸዋል? ቁጭ እንዳልክ እግርህን ሰቅለህ ኪራይ መሰብሰብ ነው ወንድሜ!›› ብሎኝ የከበርቴ ሳቅ ለቀቀብኝ። ሰው በዚህም በዚያ ይዞ ለመገኘት የሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ፈተናና ትግል ጦዟል። አንዳንዴማ የጤና አልመስልህ እያለኝ ሥራዬም ያስጠላኛል። የፈረደበት ወዳጄን የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹እኔ ብቻ ነኝ ገንዘብ መጠገብ አለበት የምለው?›› ብዬ ብጠይቀው። ‹‹አዎ አንተን ብቻ ነህ። ገንዘብና ገንፎ ጠገብኩ ሲባል ያየኸው የት አገር ነው?›› አለኝ። እውነቱን ነበር። ግን እኔምለው በላይም በታችም ሰው ለብር ብን እንዳለ ሲውል የፍቅር መዋያው የት ሆኖ ይሆን? እስኪ ያየው ያውራ! 

ሐሳብ እያበዛሁ ነገር ማውጠንጠን በሽታ ቢሆንብኝ ትንሽ ልሸቃቅል አልኩና ከረፈደ ከቤቴ ወጣሁ። ፍጥረት ላይሞላለት ሊደክም ወደሚባክንበት ጎዳና ተቀላቀልኩ። አልሠራ እያለ ያስቸገረኝ ‘ኔትወርክ’ ስልኬን ቢዳስሳት በድንገት ተንጫጫች። ‘መቼም ለደህና ነገር በዚህ ሰዓት እንዲህ ደመቅ ብላ አትጮህብኝም’ እያልኩ፣ ‹‹ሄሎ?›› በወዲያ በኩል በቀጭኑ ሽቦ የሚያነጋግረኝ ወዳጄ የአንድ ጓደኛችን እህት በድንገት ስላረፈች ለድንገተኛ ቀብር አስፈጻሚዎች ስለሚከፈል ክፍያ መዋጮ ይጠይቀኛል። ነገርኳችሁ የወጪ እንጂ የገቢ ኔትወርክ ድራሹ ከጠፋ ዘመን ተቆጥሯል። ከአገር እስከ ግለሰብ በመዋጮ እየኖርን እስከ ዛሬ መዝለቃችን ግን ይገርመኛል። መቼም ሐበሻ ኖሮት አይነፍግም። ባይኖረንም፣ ገንዘብ ባናጣም ኩራት አናጣምና ተበድረንም ቢሆን እናበድራለን (ይህ ባህሪያችን በጊኒስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ሳይመዘገብ ቀርቷል ብላችሁ ነው?) ወዲያውኑ ወዳጄን የጠየቀኝን መዋጮ ካለሁበት ሥፍራ ድረስ መጥቶ እንዲወስድ ነገርኩት። እሱም ወዲያውኑ ከተፍ ብሎ ተቀበለኝ። ለሞትና ለሕይወት እያዋጣን ሲመጡ ስንቀበል ሲሄዱ ስንሸኝ፣ የራሳችንን ግን መጀመሪያውንም መጨረሻውንም ሳናውቀው እንዲሁ መቅረታችን አያበሽቅም?

ደግሞ በስንተኛው ቀን አንድ የሚሸጥ አይሱዙ ነበርና ገዢ ፍለጋ እባክን ጀመር። የአብዛኞቻችን ትከሻ የአይሱዙን የሥራ ድርሻ ከተረከበ ቆየት ቢልም፣ የሚታይ የሚታየውን ጭኖ ለማራገፍ ገዥ እንደማላጣ እግርጠኛ ሆኛለሁ። እንደ ቀድሞው ሙቀቱ የጠፋው የአይሱዙዎችን መንድር ሳይ ‘ምን ያለው ደፋርና ቆራጥ ይገዛው?’ ብዬ አልኩ (ምን ያልቀዘቀዘ ነገር አለ ከሌብነቱ ሰፈር በቀር?)። ይኼኔ ነው አንድ ደርባባ ጎልማሳ ገዢ ነኝ ባይ ያገኘሁ። መኪናውን ከሞዴል እስከ አቋም አስፈትሸን አስተማማኝነቱን ቢያረጋግጥም ጎልማሳው ፊቱ ደስተኛ አልነበረም። ‹‹ምነው ቅር ያለህ ነገር አለ?›› ብለው ‹‹አይ እንዲያው ነው። ነገ መልሼ ጆሮውን ማለት ብፈልግ ያዋጣኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ ተስኖኝ ነው፤›› አለኝ። ‹‹ሳትገዛው ለመሸጥ እንዴት ታስባለህ? ለማትረፍ ነው የምትገዛው ማለት ነው?›› ስለው፣ ‹‹የለም! እንዲያው አዝማሚያው ባይጥምህ ዝም ብለህ አትቀጥልም እኮ። ‘አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’ አይደል የሚባል?›› ብሎኝ ሲያበቃ ድምፁን ዝቅ ዓይኑን ቅልስልስ አድርጎ፣ ‹‹አታይም ስንቱን ቱጃር እዚያም እዚህም ብሎ ሲተኮስ? ማን ነው በጀመረው ጨርሶ የተጨበጨበለት?›› ሲለኝ ነገሩ ገባኝ። ይበልጥ እየገባኝ ተመጣጣኝ በሆነ የዕድገት ሒደት በጀመረው የጨረሰ እንደሌለ ተገለጸልኝ። ይኼኔ ዕድሜ ጠገብ ፋብሪካዎች፣ ዕድሜ ጠገብ ድርጅቶች፣ ዕድሜ ጠገብ የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የተቀላጠፈና አስተማማኝ የዕድገት ሒደት፣ ዕድሜ ጠገብ ሕግ ማየት ናፈቀኝ። እውነት አይናፍቅም?  

በሉ እንሰነባበት። በቀደም ባሻዬ፣ ‹‹እኔን የገረመኝ?›› አሉኝ ወደ ሥራ ለመሄድ ስጣደፍ መንገድ አግኝተውኝ። ሳልነግራችሁ ረስቼው ነው እንጂ ባለፈው የፋሲካ በዓል እንደ ባሻዬ እጅግ ተበሳጭቶ ያሳለፈ ሰው አልነበረም። ለምን? ያው ደጋግመን የተጨዋወትነው የገበያው ጉዳይ ነዋ። እዚህ አገር የብዙ ሰው ዕድሜና ጤና እየበላ ያለው እኮ በወደቀ ብር ሸመታ ብቻ መሆኑ መሰለኝ። እና ልክ ሳገኛቸው፣ ‹‹ምን አገኙ ባሻዬ?›› አልኳቸው። ‹‹ባለፈው የእርዱ ገበያ ደንቆኝ ሳዳንቅ ከርሜ ደግሞ ሰሞኑን የባሰው መጣ፤›› ብለው ቆዘሙ። እኔ ደግሞ ፋሲካ ተመልሶ መጣ ያሉኝ መስሎኝ የማንጠግቦሽ የማያልቅ የማኅበራዊ ሕይወት ትስስር፣ የማወጣው ወጪ፣ ወዘተ ታስቦኝ ቀለጥኩ።

አስቡት የሰሞኑ ሙቀት ሳይጨመር ብቻዬን ስቀልጥ። ለካ ባሻዬ ዕርዱ በዕርድ ተተካ የሚሉኝ የኃያላን መንግሥታትን የጦር መሣሪያ ሽለላ እያዩ ነው። ‹‹አይ ጉድ?›› አሉ። ‹‹የምን ጉድ?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዲያው የፈጣሪ ሥራ ገርሞኝ። ገና ጎረምሳ ስለሆነ ነው (የሰሜን ኮሪያውን መሪ መሆኑ ነው) እንዳትል እነ ትራምፕ አሉ። በመቁረቢያቸው ሥልጣን ይዘው በዚህ የትብብር ጊዜ ብቻ ለብቻ ካልቆምን ሲሉ ታያለህ። ለነገሩ ‘ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰማላችሁ’ አይደል የሚለው ቃሉ…›› ብለው ተለዩኝ። ‹‹ዓለም እንደ አራስ ልጅ ዕድሜዋን ስትገፋ፣ አወዛውዙኝ ባይ ናት እስክታንቀላፋ›› ነበር ያሉት ከበደ ሚካኤል? መቼ ይሆን ግን ዓለም ሁሉ ነገር ታክቷት የምታረጀው? ዛሬም ተመልሶ የጥፋት፣ የጦርነት፣ የጡንቻ ውድድር ስናይ አያሳፍርም? እኛማ ቁልቁለት ላይ ሆነን እንኳንም ቤንዚን አልኖረን እንጂ፣ የማታረጀው ዓለም ገና ጉድ አለባት፡፡ መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት