በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ሥራ ጀምሮ ነበረ የተባለው የአህያ ሥጋ ቄራ ሥራን እንዲያቆም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ መስጠቱን የሚያመላክት ዜና በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ተሰምቷል፡፡
እንቅስቃሴው የተገታው ይህ ቄራ ለኢንቨስትመንቱ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ነው የተባለው ይህ የአህያ ሥራ መበለቻ ቄራ አህያ አርዶ ሥጋውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ እንደነበር ተገልጿል፡፡ የከተማው አስተዳደር ቄራው ሥራ እንዲያቆም መወሰኑን አስመልክቶ ሰጠ በተባለው መግለጫ ዕርምጃውን ሊወስድ የቻለው፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ ጥያቄ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ምናልባት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ጥያቄን መሠረት አድርጎ የወሰደው ፈጣን ምላሽ እንደሆነ ይገመታል፡፡
ከውሳኔው ጋር ተያይዞ ተሰጠ በተባለው ማብራሪያ ውስጥ አንዳንድ የማይመቹ ነጥቦች የተካተቱበት ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ቄራው ከመገንባቱ በፊት ሕዝብ ያልመከረበት ነበር፡፡ የሚለው ገለጻ አንዱ ነው፡፡ ሕዝብ ያልመከረበት ኢንቨስትመንት በመሆኑም ለቄራው መዘጋት ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡
እንዲህ ባሉ ቃላቶችን የያዘው የአስተዳደሩ ዕርምጃ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም፡፡ ኢንቨስትመንቶችን ለመትከል የሕዝብ ምክር ያስፈልጋል? አያስፈልግም? የሚለውም ጉዳይ ያጠያይቃል፡፡ ሥራ የጀመረን ኢንቨስትመንት አንድ የከተማ አስተዳደር ማስቆም ይችላል ወይ? የሚለውም ጉዳይ ሌላ አነጋጋሪ ነው፡፡ አዞ ተበልቶ ለውጭ የሚቀርብበት አገር እንደመሆኑ የአህያ ቄራ ቢኖር ችግሩ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት የአስተዳደሩ ዕርምጃው ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችም አጋጥመውናል፡፡
እንዲህ ያሉ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ሲገነቡ ሕዝብ ምክረ ሐሳብ ሊሰጥበት ይገባል የሚል ሕግ የለም፡፡ ካለም ይህ ሕግ ተጥሶ የተገነባ ከሆነ ከመጀመሪያው ሕዝብ ሊመክርበት ይገባ ነበር፡፡ ወይም እንዲህ ዓይነት ከመፈጠሩ በፊት የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዳይሰጥ ማድረግ እየተቻለ ይህንን ያህል ወጪ የወጣበትን ተቋም እንዲህ በቀላሉ መሰረዝ ምን ያህል አግባብ ነው? እርግጥ ነው አህያ ማረድ ባህላችን አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህን ያህል ደረጃ የሚታሰብ ከሆነ መጀመርያውኑ ቄራው እንዲቋቋም ለምን ተፈቀደ?
ከዕርድ ጋር በተያያዘ በአገራችን እንግዳ የሆኑና ከባህልም ከሃይማኖት ጋር ይጋጫል የሚባሉ ሌሎች እንስሳት እንደሚታረዱ ይታወቃል፡፡ አሳማ አርብቶ፣ አርዶና አቀነባብሮ ለገበያ ማቅረብ ዛሬ ላይ የተለመደ ነው፡፡ የተመጋቢዎችም ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ዛሬ በየሱፐር ማርኬቱ ባለመስታወት ፍሪጅ ውስጥ የዓሳማ ሥጋ ያለችግር ይሸጣል፡፡ ለውጭ ገበያም ይቀርባል፡፡ በተለይ ብዙ የአሳማ ሥጋ የሚመገቡ የውጭ ዜጎች ያሉባት አገር እንደመሆኗ የአሳማ ሥጋ ፍላጎት አድጓል፡፡ ዛሬ በእያንዳንዱ ቡፌ ላይ የአሳማ ሥጋ እየተዘወተረ መሆኑን መሳት የለብንም፡፡ እንደ አሳማው ሁሉ የአዞ በልቶ ቆዳውንና ሥጋውን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ ይሠራል፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ የአህያ ቄራ መቋቋሙ ብዙ ባይገርምም የብዙዎቻችንን ቀልብ የሳበ ኢንቨስትመንት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ብዙም ስሜት የማይሰጥ አይደለም፡፡ ባህላችንን የሚጋፋ ነገር መቀበሉ ተገቢ መሆኑ ባይሳትም በሕግ የተቋቋመ ኩባንያ ሥራ እንዲያቆም የሚደረገው እንዴት እንደሆነ እንድመራመር አድርጎናል፡፡ ይልቅ የዓሳማ ሥጋ ግብይት ጉዳይን ከዚሁ ጋር አያይዘን እንይ፡፡
የአህያው ሥጋ እዚህ በአገር ገበያ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ከዘርፉ ይገኝ የነበረ የውጭ ምንዛሪ ካልቆጨን ቢቀር መዘጋቱም መኖሩም አያሳስበንም፡፡ የዓሳማ ሥጋ ግን ብዙዎቻችን ባንጠቀምበትም ደንበኞች ግን አሉ፡፡ በይበልጥ ደግሞ የውጭ ዜጎች ይህንን ምርት በገፍ ይሸምታሉ፡፡ የአገሪቱ ፍጆታ መጠንም ጨምሯል፡፡ ስለዚህ የዓሳማ ሥጋ ዕርድ፣ ቅንብርና የገበያ ሁኔታ በቀጥታ ይመለከተናል፡፡ የአሳማ ሥጋ ባህላችን አይደለም ብለን ትኩረት ልንነፍገው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡
ከፍላጎቱ ዕድገት አንፃር ከጤናና ከአገር ኢኮኖሚ ጋር ያለው ትስስር ግምት ውስጥ ገብቶ የዓሳማ አጠቃላይ የገበያ ሁኔታ መታየት ክትትል የሚያሻው እየሆነ ነው፡፡ ይህንን ያነሳሁት እንደ ሸማች ታሳቢ ብቻ በማድረግ ሳይሆን፣ የዓሳማ ሥጋ አዘገጃጀት ወደ ሕገወጥነት እየተሸጋረ የገበያ ሥርዓቱ ፈር እየለቀቀ ስለመሄዱ በግልጽ እየታየ በመሆኑ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ ከዓሳማ ሥጋ ዝግጅትና ቅንብር ጋር ስማቸው የሚነሳው የውጭ ዜጎች እጃቸውን እያስገቡበት መሆኑን ልብ ይላል፡፡ ጉዳዩ ትኩረት በመነፈጉም በዓሳማ ዕርድና ግብይት ውስጥ በቀጥታ የቻይና ዜግነት ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች እጅ እንዳለበት መግለጽም አግባብ ነው፡፡
በሕጋዊ መንገድ አሳማ አርደውና አቀነባብረው ከሚሸጡ ሕጋዊ ድርጅቶች ውጭ ታርደውና ተዘጋጅተው የሚቀርቡትን የአሳማ ሥጋ የሚቀበሉ ሱፐርማርኬቶች አሉ ከተባለም ባለቤትነታቸው በቻይና ዜጎች የተያዙ መሆናቸው መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ግን ይህንን በግልጽ እየተረዳን ነው የሚባል ተግባር ሥራዬ ብሎ በአግባቡ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡
ለዚህ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢ የተሰበሰቡ በቻይናውያን ባለቤቶች የተያዙ ሱፐር ማርኬቶችና መደብሮችን ብቻ ሄዶ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በተለይ ቦሌ አካባቢ በቻይኖች ብቻ የሚዘወተሩ ሱፐር ማርኬቶች ማየት ይቻላል፡፡ ከቻይናውያን የአመጋገብ ባህል አንፃር ብዙ ገበያ ያለው የአሳማ ሥጋ ግን ምንጩ በሕገወጥ መንገድ ዕርድ ከሚፈጽሙ ግለሰቦች የሚቀርብ ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ከተፈለገ ግብይቱ የተፈጸመበትን ደረሰኝ መጠየቅ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕጋዊ አሳማ አቅራቢዎችስ እዚህ ገበያ ውስጥ ያላቸው ድርሻ በመጠየቅ የሚገኘው ምላሽ ነገሩን በደንብ ሊያሳይ ይችላል፡፡
በሕገወጦች ታርዶ ለነዚህ ሱፐር ማርኬቶች የቀርባል የተባለው የአሳማ ሥጋ ዝውውር ራሱ አደገኛ ነው፡፡ በአይሱዙ ይጭናል፡፡ አስገራሚው ነገር ይህ ሁሉ የሚሆነው ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ ተይዞ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትን መጋፋቱ ነው፡፡
የአሳማ ግብይቱ የሚፈጸመው በሕጋዊ የግብይት ሰንሰለት ተከትሎ አለመሆኑ ነው፡፡ ግብይቱ ያለደረሰኝ የሚካሄድ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ደግሞ ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ ይዘው የሚሠሩትን ዜጎች ከመጎዳቱም በላይ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የታየ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ሕገወጥ ግብይቱ እየታወቀ ዕርምጃ ያልተወሰደው ደግሞ ድርጊቱን የሚፈጽሙት አካላት ተቆጣጣሪዎችን በማሳሳታቸው ነው እየተባለ ነው፡፡
ይህንን ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው የሚባሉትን ወገኖች በጉቦ መደለልም ሕገወጥነቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል የሚለው ሹክሹክታ በዝምታ የሚታለፍ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ፋብሪካ መዝጋት ጭምር አቅም ካለ የበለጠ ለአገር ጉዳት ሊሆን የሚችለውንም እንዲህ ዓይነቱ ሕገወጥ ሥራዎችን ለማስቆም ለምን ይከብደናል?
በሕገወጥ መንገድ ዕርድ የሚከናወኑትም ቢሆኑ ሥራውን ሕጋዊ ማድረግ ምን የሚከለክላቸው ነገር አለ፡፡ መቼም ለአህያ ቄራ የተፈቀደ ሥራ አሳማን በሕጋዊ መንገድ በልቶ በሕጋዊ መንገድ ለመሸጥ የሚፈልግ ክልከላ አይኖርበትም፡፡ ችግሩ ሕጋዊ መሆን አለመፈለጉ ነው፡፡ የአሳማ ሥጋ ገበያ ከዕርድ እስከ ግብይት የመጨረሻ ሰንሰለት ድረስ በሕጋዊ መንገድ እንዲጓዝ መንግሥት ኃላፊነት አለበት ሕገወጦችንም ተከትሎ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ የማይወሰድ ከሆነ ይህ ካልሆነ ድርጊቱ ተባብሶ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡