Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች 12 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ምርቶችን አገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን እየተኩ ነው ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ስድስት የፔትሮኬሚካል ማጣሪያዎች ይገነባሉ

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ከ350 ያላነሱ የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ከውጭ የሚገቡትን እየተኩ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች፣ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት፣ በአገሪቱ በኬሚካልና ተዛማጅ ምርቶች ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች 12 ዋና ዋና ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደያሳ ለታ እንዳብራሩት ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ትልቅ ተቀባይነት እያገኙ ከመምጣታቸውም ባሻገር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በመተካት በኩልም ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

የፕላስቲክ፣ የጎማ፣ የፐልፕና ወረቀት፣ የህትመትና የማሸጊያ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳዩ ከመምጣት አልፈው የአገሪቱ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር እንደ ጎማ ያሉት ምርቶችም ወደ ጎረቤት አገሮች መላክ እንደተጀመሩ አቶ ደያሳ ጠቅሰዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የፕላስቲክና ተዛማጅ ዘርፎች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ዮናስ አባተ እንደሚገልጹት፣ ከፕላስቲክና ከጎማ ምርቶች 12 ቢሊዮን ብር ያህል ወጪ ማዳን የተቻለው በአገር ውስጥ በብዛት መመረት በመጀመሩ ነው፡፡ እንደ አቶ ዮናስ ከሆነ፣ በአፍሪካ ጎማና የጎማ ውጤቶችን የሚያመርቱ አገሮች አራት ብቻ ናቸው፡፡ ቀደም ብሎ 12 ያህል ፋብሪካዎች በአፍሪካ በጎማ አምራችነት ቢመዘገቡም በተለያየ ምክንያት ዘርፉን እየለቀቁ በመውጣታቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ብቻ አምራቾች ቀርተዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሆራይዘን አዲስ ጎማ ከ30 እስከ 35 በመቶውን የጎማ ምርት ድርሻ እንደያዘ የጠቀሱት አቶ ዮናስ፣ በመንግሥም ሰፋፊ የጎማ ዛፍ እርሻዎችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት በሚዛን ተፈሪ አካባቢ ቀደም ሲል በ5,000 ሔክታር መሬት ላይ ሲያካሂደው የነበረውን የጎማ ዛፍ እርሻ ሥራ በማስፋፋት ተጨማሪ 5,000 ሔክታር መሬት በመረከብ እርሻ ለመጀመር መዘጋጀቱን አቶ ደያሳ አስታውቀዋል፡፡  

ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ወደፊት የሚተከሉ ስድስት የፔትሮኬሚካል ማጣሪያዎች የአገሪቱን የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃ ፍላጎት በእጅጉ እንደሚቀርፉት ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ አቶ ደያሳ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ኩባንያ ጥናቱን እያካሄደ እንደሚገኝና በቅርቡም አጠናቆ በሚያቀርብበት ወቅት ከተፈጥሮ ጋዝ የሚገኙ ዋና ዋና የፕላስቲክ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በማምረት ለፋብሪካዎች ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ሥራውን የሚከታተለው የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን የተሰኘ መንግሥታዊ ግዙፍ ተቋም መቋቋሙ ሲገለጽ፣ ይህ ተቋም የያዩ ማዳሪያ ፋብሪካን፣ የሙገር ሲሚንቶንና የመሳሰሉትን ትልልቅ ፋብሪካዎች በሥሩ እንደሚመራም አቶ ደያሳ ጠቅሰዋል፡፡

በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በማልማት በቱቦ አማካይነት ወደ ድሬዳዋ የመውሰድ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች እንዳሉ፣ የተፈጥሮ ጋዙን በመጠቀም የኬሚካል ማዳበሪያ ለማምረት የሞሮኮ ግዙፍ ኩባንያ የሆነው ኦሲፒ አፍሪካ ከመንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረሙን አቶ ደያሳ አስታውሰዋል፡፡ ከኬሚካል ማዳበሪያ በበለጠ ግን ፖሊኢትሊን እንዲሁም ፖሊፕሮሊን የተሰኙ ንጥረኬሚካሎችን ከተፈጥሮ ጋዝ በማጠንፈፍ ወይም ከጋዝ ወደ ፍሳሽነት በመቀየር የሚገኘውን ፈሳሽ ፔሮሊየም ጋዝ ለልዩ ልዩ ፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻነት ለማዋል እንደሚያስችል ኃላፊዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 126 ሺሕ ቶን የፖሊፕሮፕሊን ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን የጠቀሱት አቶ ዮናስ፣ ይህ ጥሬ ዕቃ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁት ውስጥ እንደሚመደብ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመሩ 12 ዋና ዋና የፕላስቲክ ውጤቶች ገበያው ላይ ትልቅ ድርሻ በመያዝ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ የበርና መስኮት ፕሮፋይሎች፣ የኮርኒስና የግድግዳ ማካፈያዎች፣ የአልሙኒየም ፍሬሞች፣ የለስላሳ መጠጦች፣ የመድኃኒትና የውኃ ማሸጊያዎች፣ የስፖንጅ ውጤቶች፣ ሲንቴቲክ የቆዳ ምርቶች፣ የፕላስቲክ ብሩሾችና የመሳሰሉት በርካታ ምርቶች አገር ውስጥ መመረታቸው ወደ አገር ውስጥ በገፍ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ለመቀነስ እንዳስቻለ አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በብዛት ከውጭ ይገቡ የነበሩ የውኃና የለስላሳ መጠጦች ማሸጊያዎች በአሁኑ ወቅት አገር ውስጥ እንደልብ እየተመረቱ ነው ብለዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የወረቀት፣ ፐልፕ፣ የሕትመትና የምርት ማሸጊያ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የቆየ ታሪክ ያለው የሕትመት ኢንዱስትሪ ምንም እንኳ ዕድገት እያሳየ ቢመጣም አሁንም በአገሪቱ ያለውን የጥራትና የአቅርቦት ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ከሕትመቱ ባሻገርም የማሸጊያ ምርቶች ፍላጎት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ ጠቅሰው ወደፊት የአገሪቱ ፈታኝ ችግር ሊሆን እንደሚችል ሥጋት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በግብርና ዘርፍ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች መምጣት የማሸጊያ ምርቶችን ፍላጎት በከፍተኛ መጠን ሊጨምሩ ከሚችሉት ውስጥ ዋነኛው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የወረቀት አንዲስትሪውም ቢሆን ገና በጅምር ላይ እንደሚገኝ አቶ ግርማ አስታውሰው፣ በጥራትና በብዛት ምርቱን የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች እንደ አሳታሚዎች ፍላጎት ባለመኖራቸው መጻሕፍት ወደ ውጭ እየተላኩ እንደሚታተሙ አብራርተዋል፡፡ ይሁንና የወረቀትና ተዛማጅ ኢንዱስትሪው ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡

በዚህ መልኩ የተገለጹትን የኢንዱትሪው ንዑሳን ዘርፎችን እንደሚያስተዋውቅ የታመነበት፣ በወረቀት፣ በፐልፕ፣ በማሸጊያ፣ በሕትመት እንዲሁም በፔትሮኬሚካል ዘርፎች ላይ ያተኮረው የንግድና የኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ ለስድስተኛ ጊዜ ሊካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ተብሏል፡፡ ‹‹ኢትዮ5ፒ›› የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ ማዘጋጀቱን ያስታወቀው ሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ማኔጅመንት የተባለው አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊለ በለጠ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ ከሚያዝያ 21 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚካሄደው ዓውደ ርዕይ ለመሳተፍ እስካሁን 67 ያህል የውጭ ኩባንያዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከግብፅ የሚመጡትን 38 ኩባንያዎች ጨምሮ ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከካናዳ፣ ከፈረንሳይ፣ ከህንድ፣ ከቱርክ፣ ከኬንያና ከሌሎችም አገሮች ለመሳተፍ የተመዘገቡ ኩባንያዎች ሲኖሩ በአገር የሚታደሙትን ጨምሮ በጠቅላላው ከ100 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች