Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ሆቴሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የ380 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰባቸው ይፋ አደረጉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የዚህ ዓመት ትርፍ ግብር ይነሳልን አለያም የብድር መክፈያ ጊዜ ያራዝምልን ብለዋል

– ዓመታዊው የአዲስ አበባ ቱሪዝም መጽሔት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል  

በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ ሆቴሎች በአገሪቱ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህንን ተከትሎ አገሮች ባወጡት የጉዞ ክልከላና ማስጠንቀቂያ ሳቢያ በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የ380 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አስታወቁ፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 150 ሆቴሎች ውስጥ 105ቱ የሚወከሉበት የአዲስ አበባ ሆቴሎች ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር ኃላፊዎች፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት በአገሪቱ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አገሮች ያወጧቸው የጉዞ ክልከላዎች ባደረሱት ጫና ምክንያት ሆቴሎች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የ67 በመቶ የክፍል ተከራዮች ቁጥር በአማካይ በ20.5 በመቶ እንዲቀንስባቸው ምክንያት ሆነዋል፡፡

ይህንን በማስመልከት ሆቴሎቹ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አጥንተው አቅርበው እንደነበር የገለጹት፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ብሥራት ናቸው፡፡ የጁፒተር ኢንርናሽናል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቢኒያም እንዳብራሩት ከሆነ፣ በሆቴል ዘርፉ ብቻም ሳይሆን በኢኮኖሚው ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሁሉም እንደሚገነዘበው ጠቅሰው፣ በቱሪዝም መስክ የደረሰውን ጉዳት ያባባሰው ግን አገሮች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የሚከለክሉና የሚያስጠነቅቁ ማሳሰቢያዎችን ማውጣታቸው ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጀምሮ አሁንም ድረስ የሆቴሎች ደንበኞች ቁጥር በቀነሰበት አሐዝ መጠን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የደረሰውን ጉዳት አሳውቁኝ ባለው መሠረት በወቅቱ እንዲያውቀው መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና የደረሰውን ጉዳት በራሱ ለማጣራት በመፈለጉ እስካሁንም ድረስ ለቀረበው ጉዳት ምላሽ እንዳልተሰጠበት አስታውቀዋል፡፡

ሆቴሎች ደርሶብናል ያሉትን ኪሳራ ለማካካስ መንግሥት ማድረግ ይገባዋል ያሏቸውን ጥያቄዎችም ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት መክፈል የሚጠበቅባቸውን የንግድ ትርፍ ግብር እንዲነሳላቸው ማድረግ አንደኛው አማራጭ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ ከዚህ ባሻገር አብዛኞቹ ሆቴሎች ያለባቸውን የባንክ ዕዳ ከነወለዱ የመክፈያ ጊዜ በአንድ ዓመት እንዲራዘምላቸው ማድረግም ሌላኛው አማራጭ ተደርጓል፡፡ ወይም ደግሞ የደረሰውን ኪሳራ የሚያካክስ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ማድረግ ለመንግሥት የቀረቡ የኪሳራ ማካካሻ መፍትሔዎች ቢሆኑም እስካሁን የመንግሥት ምላሽ ይጠናል የሚል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል የሆቴል ባለሙያዎች ማሠልጠኛ አካዴሚ ለመመሥረት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ቢኒያምና ሌሎች የማኅበሩ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ የአካዴሚው አጠቃላይ ሁኔታ በመጪው ነሐሴ ወር ይፋ እንደሚደረግ የጠቀሱት ኃላፊዎቹ፣ ይህም የማኅበሩን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በማስታከክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሆቴሎች በሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ እርስ በርስ ከመነጣጠቅ ባሻገር፣ ልዩ ልዩ የምርት ግብዓቶችን የማግኘት ችግር እያጋጠማቸው እንደሚገኙም የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢና የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ከ20 ዓመት በፊት በ15 ሆቴሎች የተመሠረተው ማኅበር ቀደምት ስያሜው የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች አሠሪዎች ማኅበር እንደነበር ሲጠቀስ ሆኖም በየጊዜው በከተማው ውስጥ እየታየ ካለው ለውጥና ሆቴሎችም ከሚገኙበት ዕድገት አኳያ ለብቻቸው በመውጣት የአሁኑን ማኅበር ለመመሥረት እንዳበቃቸው ጠቅሰዋል፡፡   

እንደ አቶ ቢኒያም ትንታኔ ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በየወሩ አንድ ሆቴል እየተገነባ መቆየቱን፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም በየሦስት ወሩ ሁለት ሆቴሎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአገሪቱ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ ከ100 ያላነሱ ሆቴሎች እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ቢኒያም ከእነዚህ ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚገመቱት ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው የውጭ ሆቴሎች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ባለፈው ዓመት ማሳተም የጀመረውን የአዲስ አበባ ቱሪዝምና ሆቴሎችን የሚያስተዋውቅ መጽሔት ሁለተኛ ዕትም ይፋ አድርጓል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙዎች ተሰናድቶ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚታተመው ‹‹አዲስ አበባ ቱሪዝም ጋይድ 2017›› የተሰኘው መጽሔት፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንፅላዎች፣ ለተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም ማኅበሩ በሚሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒቶችና የንግድ ለንግድ መድረኮች እንደሚያሠራጨው ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች