Monday, July 15, 2024

የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች የወሰን ማካለል መዘግየትና ያስከተለው ጦስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስያሜ ከግብፅ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪካ ክፍል ሙሉ መጠሪያ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ስያሜው ቋሚ የሆነው ደግሞ በአራተኛው ምዕተ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የክርስትና እምነት የተቀበለው የአክሱም ንጉሥ ኢዛና በድንጋይ ላይ ባስቀረፀው አንድ ጽሑፍ ላይ ራሱን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሥ›› ብሎ ከጠራ በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ‹‹የኢትዮጵያዊነት መሠረቱ ጥንታዊ መሆኑና በአካባቢው ተፎካካሪ የሌለው ጠንካራ መንግሥት መሆኑ ነው፤›› በማለት አብራርቷል፡፡

ከጥንት አንስቶ በኢትዮጵያ ዙሪያ ጥናት ሲያደርጉ የነበሩ ምሁራን፣ ‹‹ምን ዓይነት አንድነት ቢሆን ነው የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ኖሯቸው እንደዚህ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩት?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት ስለአገሪቱ አንድነትና ኅብረት ብዙ እንደ ተናገሩና እንደ ጻፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ ተደርገው የሚቆጠሩት አሜሪካዊው ምሁር ዶናልድ ሌቪን፣ ‹‹የኢትዮጵያ የአንድነት ህልውና በሦስት ተዛማጅ አዕማዶች ሥር ይጠቃለላል፤›› ሲሉ ያትታሉ፡፡ የሕዝቦች በጋራ የመኖር ባህል፣ የጋራ የባህል ቅርሶች ባለቤት መሆናቸውና ባዕድ ወረራ ለማድረግ ሲሞክር ያላቸው አንድነት በማለት ያብራራሉ፡፡

ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ብለው በጻፉት ግጥምም ‹‹. . . ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፣ ለኃይል ክንድ የማይዳር

ሕዝባዊነት ነው መሥፈርቱ፣ የሕዝብ ወገን የሕዝብ አጋር

እንጂ፣ ለዘረኞች ቁማር፣ ለአንድ ጎሳ ቡድን፣ ገባር

ሊሆን እንደሚጣል ዕጣ አይደለም ሎተሪ ቢጋር . . ›› በማለት ስለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ኃያልነት ጽፈዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት መገለጫው ብዙ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ የአክሱም ሐውልትን፣ የፋሲል ግንብን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጀጎል ግንብን፣ የተለያዩ መስጊዶችንና አብያተ ክርስቲያናትን ያነፁ ሕዝቦች ባለቤት መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ የሕዝቦች አብሮ መኖር፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳትና በችግር ጊዜ ደግሞ በኅብረት ሆኖ ያንን ችግር ማስወገድ የአገሪቱ ዋነኛ መገለጫ እንደሆነ በየታሪክ ድርሳናቱና በሌሎች የታሪክ መዛግብት ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህ የአገሪቱ እሴቶች እየተሸረሸሩና እየመነመኑ እንደመጡ የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳሉ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ የሚወሳው ደግሞ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ብጥብጦችና ግጭቶችን ነው፡፡  

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድነትን የሚሸረሽር ጉዳይ እዚህም እዚያም እየተፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል፣ ከወልቃይትና ከቅማንት ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል፣ በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል በጠገዴና ፀገዴ መካከል ባለው የወሰን ይገባኛል ጥያቄ፣ በደቡብ ክልል ባሉ አንድ ዞኖችና ወረዳዎች ባሉ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች አማካይነት ለብዙ ወራት የቀጠለ በአገሪቱ ረብሻና ሁከት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ይኼ ረብሻና ሁከት በአገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት እንዲወድም ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ሊተካ የማይችለው የሰው ልጅ ሕይወትም ጠፍቷል፡፡ ብጥብጡና ሁከቱ በቀላሉ ሊቆም ባለመቻሉም መንግሥት በሁለት ጊዜያት የአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቱን ባቀረቡበት ጊዜ እንደገለጸው፣ በዚህ ረብሻና ሁከት የተነሳ የ699 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ በታወጀበት ጊዜም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በወሰን ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ግጭቶች እንደነበሩ መንግሥት ራሱ ሲገልጽ የነበረው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጉዳዩ ወደ ግጭት አምርቶ፣ የሰው ሕይወት እንዲያልፍና ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባሉ በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌና ባሌ ዞኖች የሚኖረው፣ በኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል በፋፈን፣ ሲቲ፣ አፍዴርና ነጎብ (ፊቅ) ዞን ባሉ ወረዳዎች ውስጥ በሚኖረው ኅብረተሰብ መካከል በወሰን ይገባኛል ጥያቄ አማካይነት ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ተገብቶ እንደነበር የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡

በዚህ ግጭት የተነሳም ከሁለቱም ወገኖች ክቡር የሆነው የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋቱን፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይኼንን በአጎራባች ክልሎች መካከል ለግጭት ምክንያት የነበረውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አጎራባች በሆኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ሲከሰቱ የነበሩትን አለመግባባቶችና ግጭቶች ለመፍታት፣ ጥቅምት 14 ቀን 1997 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑ 422 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ እንደነበር የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዚህ ጊዜ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰነው ውሳኔ መሠረት ማኅበረሰቦቹ በመረጡት ክልል እንዲተዳደሩ ሲባል፣ ሕዝበ ውሳኔው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት እንዲካሄድ መደረጉን መረጃው ጠቁሟል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል የሚኖረውን አስተዳደራዊ ወሰን ለመለየትም ሚኒስቴሩ ባለሙያዎችን በመመደብ ከሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ኮሚቴዎችን በማቋቋም፣ ወሰኑን ቀደም ብለው በተጠናቀቁት ላይ ተጨማሪ ሥራ በማከናወን በተሟላ መንገድ ለማጠናቀቅ የሚካሄድ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን አብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳሰ 2006 ዓ.ም. ድረስ በተከናወነው የወሰን ማካለል ሥራ የአካባቢው አስተዳዳርና ኅብረተሰብ በንቃት እንዲሳተፍበት በማድረግ በተደገረው የማግባባት ሥራ፣ ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደባቸው ቀበሌዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ቀበሌዎች የወሰን ማካለል ሥራው ስኬታማና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማጠናቀቅ መቻሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በወሰን ማካለሉ የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሩ አቶ ካሳ፣ ‹‹ውስብስብ ችግር በታየባቸው በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣ በፋፈን፣ በነጎብና ሲቲ ዞኖች ሥር የሚገኙ አካባቢዎችን ለማካለል ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር በማካሄድ ወሰኑን ለማካለል ጥረቶች ቢደረጉም፣ በመዘግየቱ ምክንያት ለበርካታ ወገኖች ጉዳት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፤›› ብለዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች የአካባቢ መንግሥታት፣ የፌዴራል አካላትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት ስምምነት ላይ ደርሰው ወደ ተግባር የገቡትን አካባቢዎች ጨምሮ በሰባት ዞኖችና በሰላሳ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል፣ የአስተዳደራዊ ወሰን ለማካለል የተካሄደ የፊርማ ሥነ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ካሳ በመግቢያ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የአስተዳደራዊ ወሰን ለማካለል በተደረጉ ጥረቶች፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተነሱ ግጭቶች የተጎዱ ወገኖችን በማሰብና በወንጀሉ የተሳተፉትን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል ቃል ኪዳን እየገባን ነው የምንፈራረመው ብለዋል፡፡ አክለውም ይኼ ጉዳይ የዘገየ ቢሆንም ሥርዓታችን ራሱን በራሱ የሚያርምና ለጠንካራ የሕዝቦችና የአገር አንድነት የቆመ በመሆኑ፣ ዛሬም ራስን በራስ የማረም ችሎታችንን ያሳየንበት ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ  ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት መነሻ ምክንያት ተጠይቀው ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳብራሩት፣ ችግሩ እየተፈጠረ ያለው በሕዝቡ መካከል ሳይሆን በአመራሮች እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ካሳ፣ ‹‹ግጭቶችን በመጫር ለሚነግዱ አካላት የአስተዳደር ወሰን የማካለል አጀንዳን በማንሳት ሕዝብ ለማጋጨት እንዳይጠቀሙበት የሚያደርግ ነው፤›› ከማለት በተጨማሪ በትክክልም ጥፋተኛ እከሌ ነው፣ እሱን ወይም እነሱን ለሕግ እናቀርባለን ከማለት ተቆጥበዋል፡፡ ለዚህ ችግር መከሰት ዋነኛ ተዋናዩ ማን እንደሆነ አልገለጹም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ጥፋተኛው በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው አመራር ነው፣ ወይም ሌላ ነው የሚል ፍንጭ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ለዚህ ችግር መንስዔ በሁለቱ ክልሎች ያሉ ጠባብ መስተዳድሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ከራሳችን አመራር ውድቀትም እንበለው ጥፋት ይኼ ችግር ዋጋ አስከፍሎናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ለማ ግጭቱ ከክልልም አልፎ አገራዊ አጀንዳ በመሆን፣ እንዲሁም ለተለያዩ ወጣ ላሉ ሚዲያዎች ግብዓት ሆኖ መክረሙን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ቅራኔ ውስጥ በመግባት ከፍተኛ የሚባል ውድመትና ኪሳራ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

አቶ አብዲ የስምምነቱን ፋይዳ፣ ‹‹ለኦሮሚያም ሆነ ለሶማሌ ሕዝብ አንገብጋቢና ቀዳሚ በሆነው የሰላም አጀንዳ፣ የልማት ፍላጎትና የሕዝቦች አንድነት ላይ ያነጣጠረ ውሳኔ በመሆኑ በሕዝቦችና በክልሎች መቀራረብና አንድነት ላይ በጠላትነት ለተሠለፉ ጠባቦች ከፍተኛ ውድቀትና መርዶ ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታለ፡፡ አቶ ለማ በበኩላቸው፣ ‹‹እዚህ ላይ መድረሳችን ትልቅ ድል ነው፡፡ ድልም የሚያሰኘው ከአሁን በኋላ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ የሰው ደም በከንቱ እንዳይፋስ ጠንክረን ስንሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ በተደጋጋሚ ጊዜ በክልላቸውና በኢትዮጵያ ላይ ይሰነዘር የነበረውን የሽብር ጥቃት ከአገሪቱ የመከላከያና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ማምከን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ትኩረትን ሙሉ በሙሉ ለአገራዊ ግንባታና ለልማት በማዞር ትልቅ ተስፋ መታየት የተጀመረበት ጊዜ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ አብዲ በንግግራቸው፣ ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኢትዮጵያዊነትን ፈቅዶና ወዶ የሚለብሰው ፀጋ መሆኑን ተገንዝቦ በአገር ግንባታ ላይ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት እየጣረ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ለማ የግጭቱን አስከፊነት በተመለከተ ሲገልጹ፣ ‹‹በሁለቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ፣ ብዙ ኪሳራና ውድመት ያመጣ ነበር፡፡ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት በእነኚህ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ለማ፣ ‹‹ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ትልቅ ውድቀት እንዳለብን የምንገነዘብበት ነው ብዬ የማስበው፡፡ ይኼ ችግር እንደተፈጠረ ቁጭ ብሎ መነጋገርና በቁርጠኝነት ተወያይቶ መፍታት ቢቻል ኖሮ፣ ዛሬ የደረስንበት ስምምነት ላይ የዛሬ ስምንትና ሰባት እንዲሁም ከዚያ በፊት እንደርስ ነበር፡፡ ብዙ ሕይወት ማትረፍ፣ ብዙ ውድመት ማዳን ይቻል ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚዋሰን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ርዕሰ መስተዳድሩ ሲገልጹ፣ ‹‹ይኼንን ሁሉ ድንበር የክልላቸን ሕዝብ በኃላፊነት የመጠበቅና የማስከበር ተልዕኮ ከአገር መከላከያ ኃይል ጎን ተሠልፎ ይሠራል፡፡ ወደ ፊትም አገርን ይጠብቃል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አብዲ አክለውም፣ ‹‹ይህ የአስተተዳደራዊ ወሰን ከዚህ በፊት ከአፋር ክልል ጋር መሠረታዊ በሆነ መንገድ በመስማማታችንና መፍታት በመቻላችን፣ ሕዝቦቻችን የሰላም ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በዚህ ለወራት ያህል በሁለቱ ክልሎች ግጭት ተነስቶ በነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ፣ ‹‹የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ የሚጋራ፣ ሃይማኖት የሚጋራ፣ ባህል የሚጋራ፣ ሁሉ ነገሩ አንድና ተመሳሳይ ሕዝብ ነው፡፡ የተዋለዱና በብዙ መልኩ የተሳሰሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን የአርብቶ አደሮች አካባቢ በመሆኑ እንደ ሌላው አካባቢ በበቂ ደረጃ ተጠቃሚ ባለመሆኑና ልማት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ፣ ተፈጥሮም ከጫነችው ችግር በስተቀር ሁለቱም ወገኖች ምንም ዓይነት ልዩነት የላቸውም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ፣ ‹‹ከአሁን በኋላ ሁለቱን ሕዝቦች በልማት ማስተሳሰር አለብን፡፡ በተለይም ሁለቱም ውኃ ማግኘት አለባቸው፡፡ ሕዝቦችን በመንገድ ማስተሳሰር አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ይኼ የግጭት መንስዔ የሆነው አካባቢ መሠረተ ልማቱ ያልተሟላ ከመሆኑም በላይ ማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የሚመሩበት አካባቢ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ ለማ ከዚህ ጋር ከተያያዘ እንደተናገሩት፣ ‹‹እነዚህ የግጭት መነሻ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ አካባዎችን ብንመለከት፣ አካባቢው ምንም የተለያየ ማዕድን ኑሮት አይደለም፡፡ ደረቅ መሬት ነው፡፡ ስንዝር በማይሞላና በደረቅ መሬት እንጋጫለን፡፡ ለሁላችንም የምትበቃ አገር እያለችን፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን፣ በእንዲህ ዓይነት ነገር ሕዝቡ ለአደጋ እንዲዳረግ መደረጉ ሁላችንም የምናፍርበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አብዲ ይኼንን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ‹‹ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች በማይረባ ነገር ነው የተጋጩት፡፡ ኦሮሚያ የመሬት ችግር የለበትም፣ ሶማሊያም የመሬት ችግር የለበትም፡፡ በትንሽ ቀበሌ የሰው ደም ማፍሰስ ከባድ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሆኗል፡፡ ከአሁን በኃላ ግን መደገም የለበትም፡፡ የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ኅብረተሰቦች ወንድምና እህት ናቸው፡፡ ታናሽ ወንድምየው የአንዱ ክልል ወረዳ ሊቀ መንበር፣ ታላቅ ወንድም ደግሞ የሌላው ክልል ሊቀ መንበር ሆነው ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰፊ መሬትና ዝምድና አለ፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከማንነትም ሆነ ከድንበር ጋር ተያይዘው ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ወደ አለመግባባትና ግጭት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ለመፍታት የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ግጭቶች አንዳንድ ጊዜም በባህላዊ መንገድ ሲፈቱ ይስተዋላል፡፡ በዚህ መሠረት ይኼ የስምምነት ሰነድ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖረውን አስተዳደራዊ ወሰን በተመለከተ ለማንኛውም አካል በማጣቀሻነት የሚያገለግል ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሰነድ ሆኖ እንደተዘጋጀ ተጠቁሟል፡፡

‹‹በስምምነቱ ላይም በሁለቱ ክልሎች መካከል በአስተዳደራዊ ወሰን ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ይነሱ የነበሩ አለመግባባቶችን በማስወገድ የሁለቱን አጎራባች ማኅበረሰብ ለጋራ ልማት፣ ለመልካም አስተዳደር ትስስር፣ ለሰላም ባህል ግንባታ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ነው፡፡ ለፌዴራል ሥርዓት መጠናከርና ለሕዝቦች አንድነት መጎልበት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልዊ መንግሥት መካከል በአዲስ አበባ ከተማ በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አዳራሽ ዛሬ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ይኼ ታሪካዊ ስምምነት ተፈርሟል ይላል፡፡››

የስምምነቱ ሰነዱ ዋና ዓላማ በሁለቱ ክልል ሥር በሚገኙ በሰባቱ አዋሳኝ ዞኖች መካከል ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር ተያይዞ ይከሰቱ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት፣ አጎራባች ማኅበረሰቦችን በልማትና በመልካም አስተዳደር በማስተሳሰር ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአካባቢውንና የአገሪቱን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በስምምነቱ አሥራ ሦስት ነጥቦች የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የ1997 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ የተደረሰውን የአስተዳደራዊ ወሰን ስምምነት ሁሉም ክልሎች ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትንና እሱን መነሻ አድርገው የወጡ ሕጎችን መሠረት ያደረገ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝት ለመሥራት፣ ሁለቱም ክልሎች የስምነቱን ሰነድ በተፈራረሙ ከሦስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኑን ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ፣ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ቅሬታዎችንና ጠባሳዎችን ከመሠረቱ ሊያስወግድ በሚችል መልኩ ተከታታይነት ያለው የእርቅና የመስማማት ሥራዎችን ክልሎች በመተባበር ለመሥራት፣ አጎራባች ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎችን በልማትና በመልካም አስተዳደር ለማስተሳሰር፣ በሁለቱ ክልል መንግሥታት በኩል የዚህን ውሳኔ አፈጻጸም የሚያስተጓጉሉ አካላት፣ አመራሩንና ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግና በጋራ ለመሥራት፣ ሁለቱም ክልሎች በአካባቢው አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲጠናከር በአንዱ ክልል የሚከሰተውን ችግር ሌላኛው ክልል እንደ ራሱ ተመልክቶ በባለቤትነት መንፈስ በመፍታት ረገድ ለመተጋገዝ፣ ከአስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሰዎች ካሉ ለመልቀቅ፣ አስተዳዳዊ ወሰን ከማካለል ስምምነት በኋላ በማናቸውም ሁኔታ ማኅበረሰቦችን ያለማፈናቀል፣ ከዚህ ስምምነት በኋላ በአጎራባች አካባቢዎች ለግጭት መንስዔ የሆኑ ኬላዎችን ለማስወገድ፣ ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች በስምምነቱ ተካተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያይዘ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረሱ ዘጠኝ ያህል ዝርዝር ስምምነቶች የተቀመጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፣ በየጊዜው በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ተስማምተዋል፡፡ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ሰባት ዞኖችና ሰላሳ ሶስት ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰኑን ለማካለል በአንቀጽ 5/1 2 እና 3 በተዘረዘሩት ነጥቦች እንደተስማሙ ያብራራል፡፡ የአስተዳደራዊ ወሰን ስምምነቱን ለማስፈጸምም ተከታታይነት ያለው እርቅና የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከዚህ በፊት ተቋቁሞ የነበረውን የጋራ የልማት ኮሚሽንን እንደገና በማጠንከር ወደ ሥራ ለመግባት፣ እንደዚሁም ከፌዴራል መንግሥት አካላት ጋር በመተባበር በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታና የአስተዳደር አካላትን ለማጠናከርና አቅምን ለመገንባት ተስማምተዋል፡፡ አስተዳደራዊ ወሰን በተከለለባቸው ዞኖች ሥር በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ሥርዓትን በመዘርጋት አለመግባባቶች ባሉበት እንዲመክኑ ለማስቻል፣ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡  

በኢትዮጵያ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሠረቱ እየሰፋ መምጣቱን አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በፊት በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች፣ በደቡብ ክልል በአንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሱ ይደመጣል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ለረዥም ጊዜ ያልተፈታ የወሰን ጥያቄ እንዳለ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለሪፖርተር ጋዜጣ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ንጉሡ በሁለቱ ክልሎች የአመራር አካላት መካከል በነበረ አለመግባበት ይኼ ችግር ሊፈታ እንዳልቻለና ከተሃድሶው በኋላ ግን የሁለቱም ክልል አመራሮች ራሳቸውን በተሃድሶ ውስጥ እያሳለፉ ስለሆነ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሊፈታ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላም ቢሆን ይህ የድንበር ይገባኛ ጥያቄ ሊፈታ እንዳልቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ ባለው የጠገዴና በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው የፀገዴ አካባቢዎች ችግሩ እስካሁን ድረስ እልባት እንደላገኘ የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የነበረው ከአሥር ዓመታት የበለጠ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ እዚህ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰው አፋጠኝ ምላሽ ባለመሰጠቱ መሆኑን፣ በስምምነቱ ላይ የተገኙት የሁለቱም ክልሎች ርዕስ መስተዳድሮች ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ይህ ስምምነት የተደረሰው ጉዳዩ ጫፍ በመድረሱ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አሥር ዓመት ሲንከባለል እንደቆየው ሁሉ ገና አሥር ዓመት ወደ ፊትም ይቀጥል ነበር ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም በሌሎች አካባቢዎች ዛሬ ትንሽ መስለው የሚታዩ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች ነገ ገዝፈውና ውስብስብ ሆነው የሚመጡበት ዕድል አለ፡፡ ስለሆነም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ነገ ሳይይል እልባት እየሰጠ መሄድና ችግሮችን ከሥር ከሥር መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -